በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አይሁዳውያን የፋሲካን በዓል ሲያከብሩ “እርሾ ያለበትን ምንም ነገር” እንዳይበሉ ታዘው ከነበረ፣ ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ ባቋቋመበት ዕለት የወይን ጠጅ የተጠቀመው ለምንድን ነው?—ዘፀአት 12:20፤ ሉቃስ 22:7, 8, 14-20

እስራኤላውያን ከግብጽ ነፃ የወጡበትን ጊዜ ለማስታወስ የሚያከብሩት የፋሲካ በዓል የተቋቋመው በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። ይሖዋ የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ለእስራኤላውያን መመሪያ ሲሰጣቸው “እርሾ ያለበትን ምንም ነገር አትብሉ፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ያልቦካ ቂጣ ነው መብላት ያለባችሁ” ብሏቸዋል። (ዘፀአት 12:11, 20) ይህ መለኮታዊ መመሪያ የሚሠራው በፋሲካ በዓል ወቅት በሚበላው ቂጣ ላይ ብቻ ነበር። ስለ ወይን ግን የተጠቀሰ ነገር የለም።

በዚያን ወቅት እስራኤላውያን እርሾ ያለበትን ምግብ እንዳይበሉ የተከለከሉበት ዋነኛው ምክንያት ግብጽን በፍጥነት ለቅቀው ከመውጣታቸው ጋር የተያያዘ ነው። ዘፀአት 12:34 በጊዜው ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽ “ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሆ ዕቃው አድርገው በጨርቅ ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙ” ይላል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በነበሩት የፋሲካ በዓላት ላይ ያልቦካ ቂጣ መመገባቸው መጪው ትውልድ ይህን ትልቅ ክንውን እንዲያስታውስ ይረዳዋል።

ከጊዜ በኋላ ሰዎች እርሾን ኃጢአትን ወይም ብክለትን የሚያመለክት ነገር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ጀመር። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ይገኝ ስለነበረ ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው በተናገረ ጊዜ “ጥቂት እርሾ ብዙውን ሊጥ እንደሚያቦካው አታውቁምን?” በማለት ጠይቆ ነበር። አክሎም እንዲህ ብሏል:- “አሁን ያለ እርሾ እንደ ሆናችሁ ሁሉ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ የፋሲካ በጋችን የሆነው ክርስቶስ ተሠውቶአልና። ስለዚህ በዓሉን ግፍና ክፋት በሞላበት እርሾ፣ በአሮጌ እርሾ ሳይሆን፣ እርሾ በሌለበት ቂጣ በቅንነትና በእውነት እናክብር።” (1 ቆሮንቶስ 5:6-8) ኃጢአት የሌለበትን የኢየሱስን ሥጋ ለማመልከት ሊያገለግል የሚችለው እርሾ ያልገባበት ቂጣ ብቻ ነው።—ዕብራውያን 7:26

አይሁዳውያን በፋሲካ በዓል ላይ የወይን ጠጅ መጠቀም የጀመሩት ከጊዜ በኋላ ሲሆን እንዲያውም ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ማድረጋቸውን አያወግዝም፤ ኢየሱስም በፋሲካ በዓል ላይ የወይን ጠጅን የተጠቀመው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። እርግጥ ነው፣ በጥንት ዘመን ሰዎች የወይን ጠጅ ለማፍላትና ሊጥ እንዲቦካ ለማድረግ ይጠቀሙበት የነበረው ዘዴ የተለያየ ነበር። ሊጥ እንዲቦካ እርሾ ይጨመርበታል። ከወይን ፍሬ የሚጠመቀው የወይን ጠጅ ግን እንዲህ ያለ ነገር አይገባበትም። ወይኑ እንዲፈላ የሚያደርገው ንጥረ ነገር ቀድሞውንም ቢሆን በፍሬው ውስጥ አለ። የፋሲካ በዓል የሚከበርበት የጸደይ ወቅት ከመከር ጊዜ የራቀ ስለነበር፣ በዚህ ወቅት ያልፈላ የወይን ጭማቂ ማግኘት አይቻልም ነበር።

በመሆኑም ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ባቋቋመበት ጊዜ የወይን ጠጅን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ መጠቀሙ አይሁዳውያን በፋሲካ በዓል ላይ እርሾ እንዳይበሉ ከተሰጣቸው ትእዛዝ ጋር ፈጽሞ አይጋጭም። ማጣፈጫ ወይም ሌላ ዓይነት አልኮል ያልተቀላቀለበት ማንኛውም ቀይ የወይን ጠጅ የክርስቶስን “ክቡር ደም” ለማመልከት ሊውል ይችላል።—1 ጴጥሮስ 1:19