ዮናታን ‘ይህን ያደረገው በአምላክ እርዳታ ነው’
ዮናታን ‘ይህን ያደረገው በአምላክ እርዳታ ነው’
የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ልጅ በሽሽት ላይ ያለ አንድ ስደተኛን ለመጠየቅ ሄደ። ከዚያም ይህን ሰው እንዲህ በማለት አበረታታው:- “አትፍራ፤ አባቴ ሳኦል እጁን በአንተ ላይ አያሳርፍም፤ በእስራኤል ላይ ትነግሣለህ፤ እኔም ካንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ።”—1 ሳሙኤል 23:17
ስደተኛውን ለመጠየቅ የሄደው ሰው ዮናታን ሲሆን በሽሽት ላይ የነበረው ደግሞ ዳዊት ነበር። ዮናታን ቶሎ ባይሞት ኖሮ የዳዊት ቀኝ እጅ መሆኑ አይቀርም ነበር።
የዮናታንና የዳዊት ጓደኝነት ያልተለመደ ዓይነት ነበር። ለነገሩ ዮናታንም ቢሆን የሚደነቅ ሰው ነበር። በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ዮናታንን አስመልክተው ‘ይህን ያደረገው በአምላክ እርዳታ ነው’ ሲሉ መናገራቸው እነሱም ተመሳሳይ አመለካከት እንደነበራቸው ያሳያል። (1 ሳሙኤል 14:45) ሰዎቹ እንዲህ ያሉት ለምንድን ነው? ዮናታን ምን ዓይነት ባሕርይ ነበረው? የዮናታንን የሕይወት ታሪክ መመርመርህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
‘በአስጊ ሁኔታ’ ውስጥ የወደቁት እስራኤላውያን
ዮናታን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኘው እስራኤላውያን ‘በአስጊ ሁኔታ’ ውስጥ እንደነበሩ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ነው። በወቅቱ ፍልስጥኤማውያን የእስራኤልን ምድር በመውረር ነዋሪዎቹ ራሳቸውን መከላከል እንዳይችሉ አድርገዋቸው ነበር።—1 ሳሙኤል 13:5, 6, 17-19
ይሁን እንጂ ይሖዋ ቀደም ሲል ሕዝቡን እንደማይተው ተናግሮ ነበር፤ ዮናታንም ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኛ ነበር። አምላክ፣ የዮናታንን አባት ማለትም ሳኦልን በተመለከተ “ሕዝቤን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ይታደጋል” ብሎ ነበር። ዮናታን ይህ ቃል እንደሚፈጸም እምነት ነበረው። ከዚህ በፊት ዮናታን ራሱ በደንብ ያልታጠቁ 1,000 እስራኤላውያንን ይዞ በመዝመት ፍልስጥኤማውያንን ድል አድርጓቸዋል። አሁን ግን፣ ፍልስጥኤማውያንን ሙሉ በሙሉ ድል በማድረግ ሕዝቡን ከስጋት ለማላቀቅ ፈለገ።—1 ሳሙኤል 9:16፤ 12:22፤ 13:2, 3, 22
ድፍረት የተሞላበት ወረራ
ዮናታን በማክማስ ሸለቆ መተላለፊያ አቅራቢያ በሚገኝ የፍልስጥኤማውያን የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አሰበ። (1 ሳሙኤል 13:23) ወደ ጦር ሰፈሩ ለመድረስ ‘በእጁና በእግሩ’ ተፍጨርጭሮ አቀበት መውጣት ነበረበት። ይህ ግን ያሰበውን ከመፈጸም አላገደውም። ዮናታን ከጋሻ ጃግሬው ጋር ብቻ ሆኖ ፍልስጥኤማውያኑን ለመውጋት ወሰነ። ለጋሻ ጃግሬውም እንዲህ አለው:- “ምናልባትም እግዚአብሔር ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን እግዚአብሔርን የሚያግደው የለምና።”—1 ሳሙኤል 14:6, 13
እነዚህ ሁለት እስራኤላውያን ይሖዋ ምልክት እንዲያሳያቸው ፈለጉ። በመሆኑም በጦር ሰፈሩ ውስጥ በነበሩት ሰዎች ፊት ለመታየት ወሰኑ። ፍልስጥኤማውያኑ “ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ጠብቁን” ካሏቸው ባሉበት ሆነው ለመጠበቅ ተስማሙ። ይሁን እንጂ ጠላቶቻቸው “ወደ እኛ ውጡ” ካሏቸው ይሖዋ ለዮናታንና ለጋሻ ጃግሬው ድል ይሰጣቸዋል ማለት ነው። ዮናታን አምላክ እንደሚረዳው ካረጋገጠለት ወደ ጦር ሰፈሩ ሄዶ ለመዋጋት ወስኗል።—1 ሳሙኤል 14:8-10
ሁለቱ ሰዎች ብቻቸውን በአንድ የጦር ሰፈር ውስጥ በሚገኝ ሠራዊት ላይ ምን መፍጠር ይችላሉ? እስራኤላውያን ከሞዓባውያን ጋር በተዋጉበት ጊዜ ይሖዋ መስፍኑን ናዖድን ረድቶት አልነበረም? ሰሜጋር፣ አምላክ ባይረዳው ኖሮ በበሬ መንጃ 600 ፍልስጥኤማውያንን መግደል ይችል ነበር? ሳምሶን፣ ከይሖዋ ባገኘው ኃይል ብቻውን ፍልስጥኤማውያንን አሸንፏቸው አልነበረም? ዮናታን፣ እሱንም አምላክ እንደሚረዳው ሙሉ እምነት ነበረው።—መሳፍንት 3:12-31፤ 15:6-8, 15፤ 16:29, 30
ፍልስጥኤማውያኑ ሁለቱን እስራኤላውያን ባዩአቸው ጊዜ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ አንድ ነገር እናሳያችሁ” በማለት ጮኹ። ዮናታንና ጋሻ ጃግሬውም ወጡ። ከዚያም በድፍረት በመዋጋት 20 የሚሆኑ የጠላት ወታደሮች ገደሉ፤ የጦር ሰፈሩ በሽብር ተሞላ። ይህም የሆነው ምናልባት ፍልስጥኤማውያኑ ሁለቱን ሰዎች ተከትለው በርካታ 1 ሳሙኤል 14:11-23, 31
እስራኤላውያን ተዋጊዎች ይመጣሉ ብለው ስላሰቡ ሊሆን ይችላል። ዘገባው ከዚያ በኋላ የሆነውን ሲገልጽ “በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ . . . ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር” ይላል። አምላክ ምድሪቱ እንድትናወጥ በማድረጉ በፍልስጥኤማውያኑ መካከል የተቀሰቀሰው ሽብር እየተባባሰ ሄደ። በመሆኑም እርስ በርሳቸው ‘በሰይፍ መጨፋጨፍ’ ጀመሩ። እስራኤላውያን ተዋጊዎች ይህን ሁኔታ ሲመለከቱ የልብ ልብ ተሰማቸው። ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው ከፍልስጥኤማውያን ጎን ተሰልፈው በነበሩትና ከየተሸሸጉበት በወጡት እስራኤላውያን ተዋጊዎች በመታገዝ ‘ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ መቷቸው።’—ሕዝቡ የዮናታንን ሕይወት ታደገው
ንጉሥ ሳኦል በስሜት ተገፋፍቶ ማንኛውም ተዋጊ ጦርነቱ ከመጠናቀቁ በፊት እህል እንዳይቀምስ አዘዘ። ዮናታን ስለወጣው ትእዛዝ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። በመሆኑም በእጁ በያዘው ዘንግ የማር ወለላ አጥቅሶ በላ። ይህን ማድረጉ በውጊያው ለመግፋት የሚያስችል ኃይል ሳይሰጠው አልቀረም።—1 ሳሙኤል 14:24-27
ሳኦል፣ ዮናታን ምግብ መብላቱን ሲሰማ መሞት እንዳለበት ተናገረ። በዚህ ጊዜ ዮናታን ሞት ከመፍራት ይልቅ “እነሆ፤ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ። “ሕዝቡ ግን ሳኦልን፣ ‘ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘ ዮናታን መሞት ይገባዋልን? አይደረግም! ዛሬ ይህን ያደረገው በእግዚአብሔር ርዳታ ስለ ሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ከራስ ጠጕሩ አንዲቱ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም’ አሉት። ስለዚህ ሰዎቹ ዮናታንን ታደጉት፤ እርሱም ከመሞት ዳነ።”—1 ሳሙኤል 14:38-45
በዛሬው ጊዜ፣ አንድ የአምላክ አገልጋይ ቃል በቃል በጦርነት አይካፈልም። ይሁንና በሕይወትህ ውስጥ እምነትና ድፍረት ማሳየትህ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ይገጥምህ ይሆናል። መጥፎ ነገር በሚሠሩ ሰዎች መካከል ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ብርታት ይሰጥሃል እንዲሁም የጽድቅ መሥፈርቶቹን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት ይባርክልሃል። አገልግሎትህን እንደማስፋት፣ አዳዲስ መብቶችን እንደመቀበል አሊያም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ እንደማገልገል ያሉ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል ድፍረት ያስፈልግህ ይሆናል። እነዚህን ኃላፊነቶች ለመቀበል ብቁ እንዳልሆንክ ይሰማህ ይሆናል። ይሖዋ በፈለገው መንገድ እንዲጠቀምብህ ራስህን በፈቃደኝነት እስካቀረብክ ድረስ መልካም የሆነውን ነገር እንዳደረግህ ሊሰማህ ይገባል። ዮናታንን አስታውስ! ሁሉንም ነገሮች ማድረግ የቻለው ‘በአምላክ እርዳታ ነው።’
ዮናታንና ዳዊት
ከ20 ዓመት ገደማ በኋላ ጎልያድ የተባለ ፍልስጥኤማዊ ጀግና የእስራኤልን ሠራዊት ተገዳድሮ ነበር፤ ይሁን እንጂ ዳዊት ገደለው። ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ያህል ቢበልጠውም እንኳ የሚመሳሰሉባቸው በርካታ ነገሮች ነበሩ። a ዳዊት፣ ዮናታን በማክማስ ያሳየው ዓይነት ድፍረት ነበረው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ዳዊት ልክ እንደ ዮናታን በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ ይታመን ነበር። ይህም እስራኤላውያን ጎልያድን ለመግጠም በፈሩበት ወቅት በድፍረት እንዲጋፈጠው አስችሎታል። በዚህ ጊዜ “የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቈራኘች፤ እንደራሱም አድርጎ ወደደው።”—1 ሳሙኤል 17:1 እስከ 18:4
ዳዊት በፈጸመው የጀግንነት ተግባር የተነሳ ንጉሥ ሳኦል ተቀናቃኙ እንደሆነ አድርጎ የተመለከተው ቢሆንም ዮናታን ግን በዳዊት ላይ ምንም ዓይነት የቅናት ስሜት
አላደረበትም። ዮናታንና ዳዊት የልብ ጓደኛሞች ነበሩ። ስለሆነም ዳዊት ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ ለመሆን መቀባቱን ለዮናታን ሳይነግረው አይቀርም። ዮናታን የአምላክን ውሳኔ አክብሯል።ንጉሥ ሳኦል ለልጁ ለዮናታንና ለአገልጋዮቹ ዳዊትን እንዲገድሉት በነገራቸው ጊዜ፣ ዮናታን ዳዊትን አስጠነቀቀው። ዮናታን፣ ዳዊትን የሚፈራበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ለሳኦል ነገረው። ደግሞም ዳዊት ንጉሡን ምንም አልበደለውም! ዳዊት ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ጎልያድን አልገጠመውም? ዮናታን የተበደለውን ጓደኛውን አስመልክቶ ያቀረበው ከልብ የመነጨ ልመና ሳኦልን አረጋጋው። ይሁን እንጂ፣ ንጉሡ ቀድሞ ወደ ነበረው ነፍስ የማጥፋት እቅድ በመመለስ ዳዊትን ለመግደል ተደጋጋሚ ሙከራዎች አደረገ። በመሆኑም ዳዊት ለመሸሽ ተገደደ።—1 ሳሙኤል 19:1-18
በዚህ ጊዜ ዮናታን በታማኝነት ከዳዊት ጎን ቆሟል። ሁለቱ ጓደኛሞች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመነጋገር ተገናኙ። ለጓደኛውም ሆነ ለአባቱ ታማኝ ለመሆን ይጥር የነበረው ዮናታን ዳዊትን “ይህስ ከቶ አይሁንብህ፣ አትሞትም!” አለው። ይሁን እንጂ ዳዊት “በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ብቻ ቀርቶአል” በማለት መለሰለት።—1 ሳሙኤል 20:1-3
ዮናታንና ዳዊት፣ የሳኦልን ሐሳብ ለማወቅ እቅድ አወጡ። ዳዊት በንጉሡ ማዕድ አለመገኘቱ ሲታወቅ ዮናታን፣ ዳዊት የቀረው ቤተ ዘመዶቹ በሚያቀርቡት መሥዋዕት ላይ ለመገኘት በመሄዱ እንደሆነ ለአባቱ እንዲነግረው ተስማሙ። ሳኦል ይህን ሲሰማ ከተቆጣ ለዳዊት ከፍተኛ ጥላቻ አድሮበታል ማለት ነው። ዮናታን ጓደኛውን ከመረቀው በኋላ “እግዚአብሔር ከአባቴ ጋር እንደ ነበር እንደዚሁ ከአንተም ጋር ይሁን” በማለት ወደፊት ንጉሥ እንደሚሆን አምኖ መቀበሉን በተዘዋዋሪ መንገድ ገለጸለት። አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ለመሆን ከተማማሉ በኋላ ዮናታን ለዳዊት ያገኘውን ውጤት እንዴት እንደሚያሳውቀው ተነጋገሩ።—1 ሳሙኤል 20:5-24
ሳኦል፣ ዳዊት በግብዣው ላይ ያልተገኘው ለምን እንደሆነ ሲጠይቅ ዮናታን፣ ዳዊት “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ወንድሞቼን ለማየት እንድሄድ አሰናብተኝ” በማለት እንደለመነው ነገረው። ዮናታን፣ ዳዊት በፊቱ ሞገስ ማግኘቱን ከመናገር ወደኋላ አላለም። ንጉሡ ተቆጣ! ዮናታንንም ሰደበው፤ እንዲሁም የዳዊት በሕይወት መኖር ወራሽ ለሆነው ልጁ ስጋት መሆኑን በቁጣ ተናገረ። ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ዮናታን ይዞት እንዲመጣ አዘዘው። ዮናታንም “ለምን ይገደላል? ጥፋቱስ ምንድን ነው?” በማለት በንዴት መለሰ። ሳኦልም በቁጣ ጦሩን በልጁ ላይ ወረወረበት። ዮናታን ጉዳት ሳይደርስበት ያመለጠ ቢሆንም የዳዊት ሁኔታ ከልቡ አሳዝኖታል።—1 ሳሙኤል 20:25-34
ዮናታን እንዴት ያለ ታማኝነት አሳይቷል! ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ዮናታን ከዳዊት ጋር የመሠረተው ወዳጅነት ከሚያስገኝለት ጥቅም ይልቅ የሚያሳጣው ነገር ይበልጣል። ያም ሆኖ ዳዊት፣ ሳኦልን ተክቶ እንዲነግሥ ይሖዋ ወስኗል። አምላክ ደግሞ ይህን ያደረገው ለዮናታንም ሆነ ለሌሎች ጥቅም ሲል ነው።
በእንባ መለያየት
ዮናታን ሁኔታውን ለዳዊት ሊነግረው በድብቅ ተገናኙ። ዳዊት መቼም ቢሆን ወደ ሳኦል ቤተ መንግሥት እንደማይመለስ ግልጽ ነው። ዳዊትና ዮናታን ተቃቅፈው ተላቀሱ። ከዚያም ዳዊት ወደ መሸሸጊያው ሄደ።—1 ሳሙኤል 20:35-42
ከዚያ በኋላ ዮናታን ከዳዊት ጋር የተገናኘው አንዴ ብቻ ሲሆን ይኸውም ዳዊት “በዚፍ ምድረ በዳ ሖሬሽ በተባለ ቦታ ሳለ” ነበር። ዮናታን ዳዊትን እንደሚከተለው ሲል ያጽናናው በዚህ ጊዜ ነበር:- “አትፍራ፤ አባቴ ሳኦል እጁን በአንተ ላይ አያሳርፍም፤ በእስራኤል ላይ ትነግሣለህ፤ እኔም ካንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ፤ ይህንም አባቴ ሳኦል እንኳ ያውቀዋል።” (1 ሳሙኤል 23:15-18) ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ዮናታንና ሳኦል ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተካሄደ ውጊያ ሞቱ።—1 ሳሙኤል 31:1-4
አምላክን የሚወዱ ሁሉ ዮናታን በተወው ምሳሌ ላይ በቁም ነገር ሊያሰላስሉ ይገባል። ታማኝነትህን የሚፈታተን ጉዳይ አጋጥሞሃል? ከሆነ ሳኦል ዮናታን የግል ጥቅሙን እንዲያስቀድም ለመገፋፋት ሞክሮ እንደነበር አስታውስ። ይሁንና ዮናታን ይሖዋን ከልብ በመታዘዝ፣ አክብሮታዊ ፍርሃት በማሳየትና አምላክ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን በመረጠው ሰው ደስ በመሰኘት አክብሮታል። አዎን፣ ዮናታን ዳዊትን ደግፏል እንዲሁም ለይሖዋ ታማኝ ሆኗል።
ዮናታን ግሩም ባሕርያት ነበሩት። አንተም እነዚህን ባሕርያት ኮርጅ! እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ሕዝቡ ዮናታን ‘ይህን ያደረገው በአምላክ እርዳታ ነው’ እንዳሉ ሁሉ ለአንተም እንዲህ ሊባልልህ ይችላል።—1 ሳሙኤል 14:45
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዮናታን የጦር አዛዥ መሆኑ የተጠቀሰው ሳኦል በንግሥና በቆየባቸው 40 ዓመታት መጀመሪያ ላይ ሲሆን በዚያን ጊዜ ቢያንስ 20 ዓመቱ ነበር። (ዘኍልቍ 1:3፤ 1 ሳሙኤል 13:2) በመሆኑም ዮናታን በ1078 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሞት ዕድሜው ወደ 60 ተጠግቶ መሆን አለበት። በዚህ ወቅት ዳዊት 30 ዓመቱ ስለነበር ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ያህል እንደሚበልጠው በግልጽ መረዳት ይቻላል።—1 ሳሙኤል 31:2፤ 2 ሳሙኤል 5:4
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮናታን በዳዊት አልቀናም ነበር