በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠፍቶ የነበረው የጆን ሚልተን ድርሰት

ጠፍቶ የነበረው የጆን ሚልተን ድርሰት

ጠፍቶ የነበረው የጆን ሚልተን ድርሰት

በዓለማችን ላይ ታላቅ ተጽዕኖ ካሳደሩ በጣም ጥቂት ደራሲያን መካከል ፓራዳይዝ ሎስት (የጠፋችው ገነት) የተሰኘውን የእንግሊዝኛ የግጥም መድብል የደረሰው ጆን ሚልተን ይገኝበታል። አንድ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ እንዳሉት ሚልተን “በብዙዎች የሚወደድ፣ በአንዳንዶች የሚጠላ፣ በጥቂቶች ደግሞ ጭራሽ የማይታወቅ ሰው ነው።” የሚልተን ሥራዎች አሁንም ድረስ ለእንግሊዝ የሥነ ጽሑፍና የባሕል እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።

ጆን ሚልተን ይህን ያህል ተጽዕኖ ማሳደር የቻለው እንዴት ነው? ስለ ክርስትና መሠረተ ትምህርት የሚናገረው ኦን ክርስቺያን ዶክትሪን የተባለው የመጨረሻ የጽሑፍ ሥራው ለ150 ዓመታት ሳይታተም እስኪቆይ ድረስ አወዛጋቢ የነበረው ለምንድን ነው?

የጆን ሚልተን የልጅነት ሕይወት

ጆን ሚልተን በ1608 በእንግሊዝ ከሚኖር አንድ ሀብታም ቤተሰብ ተወለደ። ሚልተን ያሳለፈውን የልጅነት ሕይወት በማስታወስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “አባቴ ገና በልጅነቴ ሥነ ጽሑፍ እንዳጠና ያበረታታኝ ነበር። እኔም ለሥነ ጽሑፍ ካደረብኝ ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ ከአሥራ ሁለት ዓመቴ ጀምሮ ከእኩለ ሌሊት በፊት ወደ መኝታዬ የሄድኩባቸው ቀናት በጣም ጥቂት ነበሩ።” ጆን ሚልተን ጎበዝ ተማሪ የነበረ ሲሆን በ1632 ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪውን አግኝቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የጥንት ግሪካውያንን እና የሮማውያንን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ጨምሮ የታሪክ መጻሕፍትን ያነብ ነበር።

ሚልተን ገጣሚ የመሆን ፍላጎት የነበረው ቢሆንም በወቅቱ እንግሊዝ በአብዮተኞች ትታመስ ነበር። ንጉሥ ቀዳማዊ ቻርልስ፣ በኦሊቨር ክሮምዌል የሚመራው ፓርላማ በሰየመው ችሎት ብይን መሠረት በ1649 ተገደሉ። በዚህ ጊዜ ሚልተን የተወሰደውን እርምጃ በመደገፍ ሌሎችን የሚያሳምን ጽሑፍ የጻፈ ሲሆን የክሮምዌል ቃል አቀባይ ለመሆንም በቃ። ጆን ሚልተን በግጥም ሥራዎቹ ከመታወቁ በፊት ፖለቲካንና ግብረ ገብነትን አስመልክቶ በሚጽፋቸው በራሪ ወረቀቶች ዝናን አትርፎ ነበር።

ይሁንና በ1660 ዳግማዊ ቻርልስ ዘውድ ሲጭኑና ንጉሣዊው አገዛዝ ተመልሶ ሲቋቋም ሚልተን ለክሮምዌል ሲሰጥ በነበረው ድጋፍ ምክንያት ሕይወቱ አደጋ ላይ ወደቀ። በመሆኑም ሚልተን መደበቅ ግድ ሆነበት፤ በወቅቱ ከሞት ማምለጥ የቻለውም ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ወዳጆቹ እርዳታ ነበር። ያም ሆኖ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ሚልተን ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበረው ፍላጎት አልጠፋም።

‘መጽሐፍ ቅዱስን ብቸኛ መመዘኛ አድርጎ መጠቀም’

ሚልተን በልጅነቱ ስለነበረው መንፈሳዊ ፍላጎት ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ብሉይና አዲስ ኪዳንን መጀመሪያ በተጻፉበት ቋንቋ በቁም ነገር ማጥናት የጀመርኩት ልጅ ሳለሁ ነበር።” በመሆኑም ሚልተን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት የሚቻለው ከቅዱሳን መጻሕፍት ብቻ እንደሆነ ያምን ነበር። በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ለመመርመር ያደረገው ሙከራም ለተስፋ መቁረጥ ዳረገው። ከጊዜ በኋላ ሚልተን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእነዚህ ጽሑፎች ላይ እምነት ልጥልም ሆነ የመዳን ተስፋ ያስገኙልኛል ብዬ ሙሉ በሙሉ ልታመንባቸው እንደማልችል ተሰማኝ።” ሚልተን “መጽሐፍ ቅዱስን ብቸኛ መመዘኛ” አድርጎ በመጠቀም የሚያምንባቸውን ነገሮች ሥራዬ ብሎ ለመገምገም ወሰነ። በመሆኑም ቁልፍ ናቸው ብሎ ያሰባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ሥር ማስፈርና እነዚህን ጥቅሶች በሥራዎቹ ላይ መጥቀስ ጀመረ።

በዛሬው ጊዜ ጆን ሚልተን ይበልጥ የሚታወሰው የሰው ልጅ ፍጽምናውን ያጣው እንዴት እንደሆነ በሚተርከው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ተመሥርቶ በጻፈው ፓራዳይዝ ሎስት በተሰኘው የግጥም መድብሉ ነው። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 3) በተለይም እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆነው ዓለም ዝነኛ ደራሲ እንዲሆን ያስቻለው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1667 የታተመው ይህ የጽሑፍ ሥራው ነው። ሚልተን ቆየት ብሎ ፓራዳይዝ ሪጌይንድ (ዳግም የተቋቋመችው ገነት) የተባለውን ከመጀመሪያ ሥራው የቀጠለ የግጥም መድብል ለሕትመት አበቃ። እነዚህ ግጥሞች አምላክ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹም ሕይወት እንዲመሩ ስለነበረው የመጀመሪያ ዓላማና በክርስቶስ አማካኝነት ዳግመኛ በምድር ላይ ገነትን እንደሚያቋቁም የሚተርኩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ፓራዳይዝ ሎስት የተባለው ግጥም፣ ክርስቶስ “ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ወሮታ የሚከፍልበትና እነዚህ ሰዎች በምድር አሊያም በሰማይ ለዘላለም የሚደሰቱበት እንዲሁም መላዋ ምድር ገነት እንዲያውም ከኤደን ገነት የላቀ አስደሳች ቦታ የምትሆንበትና ሕይወት ይበልጥ አስደሳች የሚሆንበት” ጊዜ እንደሚያመጣ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ትንቢት መናገሩን ይገልጻል።

ኦን ክርስቺያን ዶክትሪን

ሚልተን ስለ ክርስቲያኖች ሕይወትና ስለሚያምኑባቸው መሠረተ ትምህርቶች በጥልቀት የሚዳስስ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ለብዙ ዓመታት ሲመኝ ኖሯል። በ1652 የዓይን ብርሃኑን ያጣ ቢሆንም በጸሐፊዎቹ በመታገዝ ሕይወቱ እስካለፈበት እስከ 1674 ድረስ ይህን ፕሮጀክቱን ከግብ ለማድረስ ብዙ ደክሟል። ሚልተን ስለ ክርስትና መሠረተ ትምህርት የሚናገረውን ይህን የመጨረሻ ሥራውን ኤ ትሪቲስ ኦን ክርስቺያን ዶክትሪን ኮምፓይልድ ፍሮም ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ አሎን የሚል ርዕስ ሰጥቶታል። በመቅድሙ ላይም እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ይህን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክተው የጻፉ አብዛኞቹ ደራሲያን . . . ትምህርቶቻቸው ሙሉ በሙሉ የተመሠረቱባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ምዕራፍና ቁጥራቸውን ከጥቂት ማብራሪያ ጋር በግርጌ ማስታወሻ ላይ ማስፈር ይቀናቸዋል። እኔ ግን የመጽሐፌ ገጾች ከሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተወሰዱ ብዙ ጥቅሶች የታጨቁ እንዲሆኑ የተቻለኝን ሁሉ ጥሬያለሁ።” በእርግጥም ሚልተን እንዳለው ኦን ክርስቺያን ዶክትሪን በተባለው መጽሐፍ ላይ ከ9,000 የሚበልጡ ጥቅሶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቅሰው ይገኛሉ።

በቀደሙት ዓመታት፣ ሚልተን የተሰማውን ከመግለጽ ወደኋላ የሚል ሰው አልነበረም፤ ያም ሆኖ ይህን መጽሐፍ ከማሳተም ተቆጥቧል። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ በመጽሐፉ ላይ ያሰፈራቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያዎች በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት ካገኙ ትምህርቶች እጅግ የተለዩ መሆናቸውን ተገንዝቦ ነበር። ከዚህም በላይ ንጉሣዊው አገዛዝ ተመልሶ በመቋቋሙ ምክንያት በመንግሥት ዘንድ የነበረውን ተደማጭነት አጥቶ ነበር። በመሆኑም ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ሲጠብቅ ቆይቶ ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ እሱ ከሞተ በኋላ የሚልተን ጸሐፊ በላቲን የተጻፈውን ቅጂ ለማሳተም ወደ አንድ አሳታሚ ድርጅት ወሰደው፤ ሆኖም አሳታሚው ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ከዚያም አንድ የእንግሊዝ መንግሥት የካቢኔ አባል በእጅ የተጻፈውን ቅጂ በመውረስ አሽገው አስቀመጡት። የሚልተን የጽሑፍ ሥራ ከተቀመጠበት የተገኘው ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በኋላ ነበር።

በ1823 አንድ የመዝገብ ቤት ጸሐፊ ታሽጎ የተቀመጠውን የዚህን ዝነኛ ገጣሚ የጽሑፍ ሥራ አገኘ። በወቅቱ እንግሊዝን ያስተዳድሩ የነበሩት ንጉሥ ጆርጅ አራተኛ ይህ ሥራ ከላቲን ወደ እንግሊዝኛ እንዲተረጎምና ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን አዘዙ። መጽሐፉ ከሁለት ዓመት በኋላ በእንግሊዝኛ ሲታተም በሃይማኖታዊ ትምህርቶችና በሥነ ጽሑፍ መስክ ከፍተኛ ውዝግብ ተነሳ። በብዙሃኑ ዘንድ ታላቅ እንግሊዛዊ የሃይማኖት ገጣሚ ተደርጎ የሚታየው ሚልተን፣ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ አድርጋ የምትመለከታቸውን ትምህርቶች አጥብቆ የሚቃወመውን ይህን መጽሐፍ ጽፏል ብለው ማመን የከበዳቸው አንድ ጳጳስ ወዲያውኑ የጽሑፉ ደራሲ ሚልተን እንዳልሆነ ገለጹ። ይሁንና ተርጓሚው ይህን መሰል ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስቦ ስለነበር መጽሐፉን የደረሰው ሚልተን ራሱ ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንዲሆን በማለት ይህ መጽሐፍና ፓራዳይዝ ሎስት የተሰኘው የግጥም መድብል የሚመሳሰሉባቸውን 500 ነጥቦች በዝርዝር የያዘ የግርጌ ማስታወሻ አስፍሮ ነበር። a

የሚልተን አመለካከት

ሚልተን በኖረበት ዘመን እንግሊዝ የፕሮቴስታንቶችን የተሃድሶ እንቅስቃሴ በመቀበል ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራትን ትስስር አቋርጣ ነበር። በጥቅሉ ሲታይ ፕሮቴስታንቶች ከእምነትና ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች፣ የመወሰን ሥልጣን ያላቸው ጳጳሱ ሳይሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። ይሁን እንጂ ሚልተን ኦን ክርስቺያን ዶክትሪን በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ብዙዎቹ የፕሮቴስታንት ትምህርቶችና ልማዶች ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የማይስማሙ መሆናቸውን ገልጿል። ሚልተን መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም የካልቪን ተከታዮች የሚያራምዱት የሰው ልጅ ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው እምነት የተሳሳተ መሆኑን አሳይቷል። ከዚህ ይልቅ ሰዎች የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል የሚለውን ሐሳብ እንደሚደግፍ ገልጿል። ይሖዋ የተባለውን የአምላክን ስም በጽሑፉ ላይ ደጋግሞ በመጠቀስ ሰዎች ለዚህ ስም አክብሮት እንዲኖራቸው አበረታቷል።

ሚልተን መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም የሰው ነፍስ ሊሞት እንደሚችል አብራርቷል። ዘፍጥረት 2:7ን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[መጽሐፍ ቅዱስ] ሰው ከተፈጠረ በኋላ ስለሆነው ሁኔታ ሲናገር ‘ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ’ ይላል። . . . የሰው ልጅ የሁለት ነገሮች ጥምረት ወይም ሊከፈል የሚችል ነገር አይደለም። ብዙዎች እንደሚያስቡት የሰው ልጅ ከሁለት የተለያዩ ነገሮች ማለትም ከሥጋና ከነፍስ የተሠራ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰው ራሱ ነፍስ ሲሆን ነፍስ ደግሞ ራሱ ሰው ነው።” አክሎም ሚልተን የሚከተለውን ጥያቄ አቅርቧል:- “አንድ ሰው ሲሞት፣ የሚሞተው ሥጋው ብቻ ነው ወይስ ሁለመናው?” ሚልተን አንድ ሰው ሞቷል የሚባለው ሁለመናው ሲሞት እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ይሁንና ከሁሉም በላይ ነፍስ እንደምትሞት የሚያሳይ ይበልጥ አሳማኝ ማስረጃ ሆኖ ያገኘሁት በሕዝቅኤል 18:20 ላይ የሚገኘው አምላክ ራሱ የተናገረው ቃል ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- መሞት የሚገባት ኀጢአት የሠራችው ነፍስ ናት።” በተጨማሪም ሚልተን ሉቃስ 20:37ን እና ዮሐንስ 11:25ን በመጥቀስ የሞቱ ሰዎች ያላቸው የወደፊት ተስፋ ትንሣኤ መሆኑን ገልጿል።

ኦን ዘ ክርስቺያን ዶክትሪን የተባለው መጽሐፍ ከባድ ተቃውሞ እንዲነሳበት ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? ሚልተን የአምላክ ልጅ የሆነው ክርስቶስ ከአባቱ እንደሚያንስ የሚያሳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ቀላል ሆኖም ጠንካራ ማስረጃ ማቅረቡ ነው። ሚልተን ዮሐንስ 17:3ን እና ዮሐንስ 20:17ን ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቧል:- “አብ የክርስቶስም ሆነ የእኛ አምላክ ከሆነና አንድ አምላክ ብቻ ካለ፣ ከአብ በቀር አምላክ ሊሆን የሚችል ማን ይኖራል?”

በተጨማሪም ሚልተን እንዲህ ብሏል:- “ራሱ የአምላክ ልጅም ይሁን ሐዋርያቱ በተናገሩትም ሆነ በጻፉት ሁሉ ላይ አብ በሁሉም ረገድ ከወልድ እንደሚበልጥ ያምኑ እንደነበር አሳይተዋል።” (ዮሐንስ 14:28) አክሎም የሚከተለውን ጽፏል:- “በማቴዎስ 26:39 ላይ ‘አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን’ ሲል የተናገረው ራሱ ክርስቶስ ነው። . . . በእርግጥ እሱ ራሱ አምላክ ከሆነ ወደ ራሱ ከመጸለይ ይልቅ ወደ አባቱ ብቻ የጸለየው ለምንድን ነው? ክርስቶስ ሰውም ኃያል አምላክም ከነበረ ሁሉንም ነገር ራሱ ማድረግ ሲችል ለምን ይጸልያል? . . . ወልድ በሁሉም ቦታ ላይ ለአብ ብቻ ክብር እንደሰጠ ሁሉ እኛም እንዲሁ እንድናደርግ አስተምሮናል።”

ሚልተን የነበሩት ድክመቶች

ጆን ሚልተን እውነትን ለማግኘት ጥሯል። ይሁን እንጂ እንደማንኛውም ሰው ድክመቶች ነበሩት። እንዲሁም አንዳንድ አመለካከቶቹ ባሳለፋቸው መጥፎ የሕይወት ገጠመኞች ላይ የተመረኮዙ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የአንድ ባለ ርስት ልጅ የነበረችው ወጣት ሚስቱ ከተጋቡ ብዙም ሳይቆዩ ትታው ወደ ቤተሰቦቿ የሄደች ሲሆን በዚያም ለሦስት ዓመታት ያህል ቆይታለች። በዚህን ወቅት ሚልተን ኢየሱስ ብቸኛ ምክንያት አድርጎ በጠቀሰው በምንዝር ምክንያት ብቻ ሳይሆን የትዳር ጓደኛሞች በማይጣጣሙበት ጊዜም መፋታት እንደሚችሉ የሚገልጹ፣ ፍቺን የሚደግፉ ሐሳቦችን የያዙ በራሪ ወረቀቶችን ጽፏል። (ማቴዎስ 19:9) ሚልተን ኦን ክርስቺያን ዶክትሪን በተባለው መጽሐፉም ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ አስፍሯል።

ሚልተን የራሱ ድክመቶች የነበሩት ቢሆንም ኦን ክርስቺያን ዶክትሪን በተባለው የጽሑፍ ሥራው ላይ ወሳኝ የሆኑ በርካታ ትምህርቶችን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ጎላ አድርጎ ገልጿል። ሚልተን ያዘጋጀው ይህ መጽሐፍ፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንባቢያን ፍጹም የሆነውን መመዘኛ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው የሚያምኑባቸውን ነገሮች እውነተኝነት እንዲገመግሙ ያሳስባቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በ1973 ዬል ዩኒቨርሲቲ ያሳተመው ኦን ክርስቺያን ዶክትሪን የተሰኘው መጽሐፍ አዲስ ትርጉም፣ ሚልተን በላቲን ካዘጋጀው የመጀመሪያ ጽሑፍ ጋር ይበልጥ ይቀራረባል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚልተን ንቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ነበር

[ምንጭ]

Courtesy of The Early Modern Web at Oxford

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ፓራዳይዝ ሎስት” የተባለው የግጥም መድብል ሚልተንን ዝነኛ አድርጎታል

[ምንጭ]

Courtesy of The Early Modern Web at Oxford

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚልተን የመጨረሻ ሥራ ለ150 ዓመት ጠፍቶ ነበር

[ምንጭ]

Image courtesy of Rare Books and Special Collections, Thomas Cooper Library, University of South Carolina

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Image courtesy of Rare Books and Special Collections, Thomas Cooper Library, University of South Carolina