በዛሬው ጊዜ ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር
በዛሬው ጊዜ ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር
“በሕይወት ያሉትም . . . ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ [ክርስቶስ] ስለ ሁሉ ሞተ።” —2 ቆሮንቶስ 5:15
1. አንድ ሚስዮናዊ በተመደበበት ክልል ያጋጠመውን ተሞክሮ ተናገር።
“የእርስ በርስ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ርቆ ወደሚገኘው የአፍሪካ መንደር የገባው የመጀመሪያው የሲቪል መኪና የእኛ ነበር” በማለት አሮን የተባለ ሚስዮናዊ ያስታውሳል። a አክሎም እንዲህ ብሏል:- “በዚያ መንደር ከነበረው ጥቂት አባላት ያሉት ጉባኤ ጋር የምናደርገው ግንኙነት ስለተቋረጠ ወንድሞች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት ነበረብን። ከምግብ፣ ከልብስና ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት የተባለውን የቪዲዮ ፊልም ይዘንላቸው ሄድን። b ይህን ፊልም ለማየት በመንደሩ ውስጥ ወደሚገኘው ‘ቲያትር ቤት’ ፍላጎት ያላቸው በጣም ብዙ ሰዎች በመጉረፋቸው ፊልሙን ሁለት ጊዜ ማሳየት ነበረብን። እንደ ‘ቲያትር ቤት’ ሆኖ በሚያገለግለው ትልቅ ጎጆ ቤት ውስጥ የቪዲዮ ካሴት ማጫወቻና ቴሌቪዥን ነበር። ፊልሙን ከተመለከቱት ሰዎች መካከል በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማግኘት ችለናል። ከተገኘው ውጤት አንጻር ያደረግነው ጥረት ሁሉ የሚያስቆጭ አልነበረም።”
2. (ሀ) ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ለአምላክ አገልግሎት ለማዋል የሚወስኑት ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 አሮንና ጓደኞቹ ይህን የመሰለ አስቸጋሪ ተልእኮ ለመወጣት የተነሱት ለምን ነበር? ለኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያላቸውን አድናቆት ለማሳየት ራሳቸውን ለአምላክ ከመወሰናቸውም በላይ ሕይወታቸውን ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ ነው። እንደነዚህ ሚስዮናውያን ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ ‘ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር’ ይልቅ ‘ለወንጌሉ’ ብለው የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:15፤ 1 ቆሮንቶስ 9:23) ይህ ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ በዓለም ላይ ያለው ሀብትና ክብር ሁሉ ምንም ጥቅም እንደማይኖረው ያውቃሉ። በመሆኑም በሕይወት እስካሉና በተወሰነ መጠን ጤንነት እስካላቸው ድረስ ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ይፈልጋሉ። (መክብብ 12:1) እኛስ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ድፍረትና ጥንካሬስ እንዴት ማግኘት እንችላለን? በየትኞቹ መስኮች አምላክን ማገልገል እንችላለን?
ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እርምጃዎችን ደረጃ በደረጃ መውሰድ
3. የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም የሚረዱን መሠረታዊ እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?
3 እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ በሕይወታቸው ሙሉ የሚያከናውኑት ተግባር ነው። የአምላክን ፈቃድ መፈጸም የሚጀምሩት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመዝገብን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብን፣ በስብከቱ ሥራ መካፈልን እንዲሁም ራስን ወስኖ መጠመቅን የመሳሰሉ መሠረታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ነው። እድገት እያደረግን ስንሄድ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሰው ሁሉ ማደግህን ያይ ዘንድ በእነዚህ ነገሮች ላይ አትኵር፤ በትጋትም ፈጽማቸው” በማለት የሰጠውን ምክር እናስታውሳለን። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) እንዲህ ያለ እድገት የምናሳየው ለራሳችን ክብር በመፈለግ ሳይሆን ከራስ ወዳድነት በራቀ መንፈስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ ስላደረግን ነው። ይህን ዓይነት ጎዳና መምረጣችን አምላክ በሕይወታችን ውስጥ በማንኛውም መስክ እርምጃችንን እንዲመራልን እንደፈቀድን የሚያሳይ ነው፤ እሱም አካሄዳችንን ከእኛ በጣም በተሻለ መንገድ ይመራልናል።—መዝሙር 32:8
4. አላስፈላጊ ፍርሃትን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ውሳኔ ለማድረግ ማመንታት ወይም ስለ ራስ ከልክ በላይ መጨነቅ ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት እድገት እንዳናደርግ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። (መክብብ ) ስለዚህ አምላክንም ሆነ ሰዎችን በማገልገል እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንድንችል በመጀመሪያ ፍርሃታችንን ማሸነፍ ያስፈልገን ይሆናል። ኤሪክን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ወንድም በሌላ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ቢያስብም ‘ከጉባኤው አባላት ጋር በቀላሉ እቀላቀል እሆን? ወንድሞችን እወዳቸው ይሆን? እነሱስ ይወዱኝ ይሆን?’ እያለ ይጨነቅ ነበር። ኤሪክ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “ስለ ራሴ ከሚገባው በላይ ከመጨነቅ ይልቅ ስለ ወንድሞች ማሰብ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። በመሆኑም በአእምሮዬ ውስጥ ስለሚጉላሉት ነገሮች መጨነቄን አቁሜ ለሌሎች ማድረግ በምችለው ነገር ላይ ለማተኮር ወሰንኩ። ይሖዋ እንዲረዳኝ ከጸለይኩ በኋላ ያሰብኩትን ማከናወን ጀመርኩ። አሁን በዚያ ጉባኤ ውስጥ በማከናውነው አገልግሎት ደስተኛ ነኝ።” ( 11:4ሮሜ 4:20) በእርግጥም፣ አምላክንም ሆነ ሰዎችን ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ መልኩ ይበልጥ ባገለገልን መጠን የምናገኘው ደስታና እርካታም በዚያው ልክ ይጨምራል።
5. ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር በጥንቃቄ እቅድ ማውጣት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
5 ከአምላክ ዓላማ ጋር ተስማምቶ በመኖር ረገድ ስኬታማ ለመሆን እንድንችል እቅዶቻችንንም በጥንቃቄ ልናስብባቸው ይገባል። ለምሳሌ፣ የዚህ ሥርዓት ባሪያ እንድንሆን በሚያደርገን ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ላለመዘፈቅ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ አካሄድ በአምላክ አገልግሎት የመካፈል ነጻነታችንን ይገድብብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው” በማለት ያሳስበናል። (ምሳሌ 22:7) በይሖዋ መታመንና ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት በተገቢው ነገር ላይ ትኩረት ለማድረግ ይረዳናል። ለአብነት ያህል፣ ግዎሚንግ እና ሁለት እህቶቹ በሚኖሩበት አካባቢ ቤት በጣም ውድ ከመሆኑም በላይ አስተማማኝ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት ሥራ ባይኖራቸውም ገንዘባቸውን በቁጠባ በመጠቀምና ወጪዎቻቸውን በጋራ በመሸፈን መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት ችለዋል። ግዎሚንግ እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ ሥራ የሚኖረን ሁላችንም ላንሆን እንችላለን። እንደዛም ሆኖ በአቅኚነት እያገለገልን እናታችንን ጥሩ አድርገን መንከባከብ ችለናል። እማማም የቅንጦት ኑሮ ለመኖር ስትል አቅኚነታችንንና ሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን መሥዋዕት እንድናደርግ ስለማትፈልግ አመስጋኞች ነን።”—2 ቆሮንቶስ 12:14፤ ዕብራውያን 13:5
6. ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ሕይወታችንን ማስተካከል እንደምንችል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
6 ሕይወትህ፣ ከገንዘብ ጋር በተያያዙ ነገሮችም ይሁን በሌሎች ሰብዓዊ ጉዳዮች ከመጠን በላይ የተጠላለፈ ከሆነ የአምላክን ዓላማ ለማስቀደም ትልቅ ለውጥ ማድረግ ይኖርብህ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ በአንድ ጀምበር ውስጥ እነዚህን ለውጦች ማድረግ አይቻልም፤ መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ስህተቶችን ብትሠራም እንኳ አይሳካልህም ማለት አይደለም። አብዛኛውን ጊዜውን በመዝናናት ያሳልፍ የነበረውን ኮይቺን እንመልከት። ኮይቺ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት የቪዲዮ ጨዋታ ሕይወቱን ተቆጣጥሮት ነበር። አንድ ቀን ኮይቺ ‘ምን እያደረግኩ ነው? በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምገኝ ብሆንም በሕይወቴ ውስጥ ዓላማ ያለው አንድም ነገር እያከናወንኩ አይደለሁም!’ ብሎ አሰበ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኮይቺ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን የቀጠለ ሲሆን ከጉባኤ የተሰጠውን እርዳታም ተቀበለ። ለውጥ ለማድረግ ጊዜ የወሰደበት ቢሆንም ተስፋ አልቆረጠም። አጥብቆ መጸለዩና ከሌሎች ሰዎች ያገኘው ፍቅራዊ እርዳታ ከነበረበት ሱስ ለመላቀቅ አስችሎታል። (ሉቃስ 11:9) ኮይቺ በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ በደስታ ያገለግላል።
ሚዛናዊ መሆንን ተማሩ
7. የአምላክን ሥራ ስናከናውን ሚዛናዊ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
7 ከአምላክ ዓላማ ጋር ተስማምተን ለመኖር በሙሉ ነፍስ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም የምንለግም ወይም ሰነፎች መሆን የለብንም። (ዕብራውያን 6:11, 12) ያም ቢሆን ግን ይሖዋ በአካላዊና በአእምሯዊ ወይም በስሜታዊ ሁኔታ እንድንዝል አይፈልግም። የአምላክን ሥራ በራሳችን ኃይል ማከናወን እንደማንችል በትሕትና አምነን መቀበላችን ይሖዋን የሚያስከብረው ከመሆኑም በተጨማሪ ሚዛናዊ መሆናችንን ያሳያል። (1 ጴጥሮስ 4:11) ይሖዋ ፈቃዱን እንድናደርግ የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠን ቃል የገባልን ቢሆንም እሱ ከሚጠብቅብን አልፈን ለመሥራት በመሞከር ከአቅማችን በላይ ራሳችንን ማስገደድ የለብንም። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ኃይላችን ሳናሟጥጥ አምላክን ማገልገላችንን ለመቀጠል እንድንችል ኃይላችንን በጥበብ መጠቀም ይኖርብናል።
8. አንዲት ክርስቲያን ወጣት ለዓለምም ሆነ ለይሖዋ ምርጧን ለመስጠት በመሞከሯ ምን አጋጠማት? ምን ማስተካከያስ አደረገች?
8 ለምሳሌ ያህል፣ በምሥራቅ እስያ የምትኖረው ጂ ሄይ ለሁለት ዓመታት ያህል ጉልበቷንና ጊዜዋን የሚያሟጥጥ አድካሚ ሥራ እየሠራች አቅኚ ሆና ታገለግል ነበር። እንዲህ ትላለች:- “ለይሖዋም ሆነ ለዓለም ምርጤን ለመስጠት እጥር ነበር፤ ሆኖም በቀን ውስጥ የምተኛው ለአምስት ሰዓታት ብቻ ነበር። ውሎ አድሮ ኃይሌ በሙሉ በመሟጠጡ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግም ሆነ ለይሖዋ በማቀርበው አገልግሎት ደስታ ማግኘት አልቻልኩም።” ጂ ሄይ ይሖዋን ‘በፍጹም ልቧ፣ በፍጹም ነፍሷ፣ በፍጹም ሐሳቧና በፍጹም ኃይሏ’ ለማገልገል ስትል ብዙም አድካሚ ያልሆነ ሥራ መፈለግ ጀመረች። (ማርቆስ 12:30) እንዲህ ብላለች:- “ቤተሰቤ ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ እንድሠራ ተጽዕኖ ቢያደርግብኝም የአምላክን ዓላማ ለማስቀደም ጥረት አደረግሁ። አሁንም ቢሆን መሠረታዊ ለሆኑ ነገሮች የሚበቃኝ ገቢ አገኛለሁ፤ ለምሳሌ ጥሩ ልብስ መግዛት እችላለሁ። በቂ እንቅልፍ ስለማገኝም ደስተኛ ነኝ! አሁን በአገልግሎቴ የምደሰት ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ጠንካራ ነኝ። ይህም የሆነው ዓለም ለሚያቀርባቸው መስህቦችና ትኩረት ለሚሰርቁ ነገሮች ጊዜ ስለሌለኝ ነው።—መክብብ 4:6፤ ማቴዎስ 6:24, 28-30
9. በአገልግሎት የምናደርገው ጥረት በመስክ በምናገኛቸው ሰዎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
9 አምላክን በሙሉ ጊዜ ማገልገል የሚችለው ሁሉም ሰው እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ከእርጅና፣ ከጤና ማጣት ወይም ከሌሎች የአቅም ገደቦች ጋር የምትታገል ከሆነ ይሖዋ ታማኝነትህንና በሙሉ ልብ የምታቀርበውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አስታውስ። (ሉቃስ 21:2, 3) በመሆኑም ማናችንም ብንሆን ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት የቱንም ያህል ውስን ቢሆን በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልለን መመልከት የለብንም። ለምሳሌ ያህል፣ ጥቂት ቤቶችን አንኳክተን ለመልእክታችን ፍላጎት ያለው ሰው አላገኘንም ይሆናል። ከሄድን በኋላ ግን በራቸውን ያልከፈቱልን ሰዎችም እንኳ ስለ እኛ ለሰዓታት ምናልባትም ለቀናት ያወሩ ይሆናል። ምሥራቹን የሚሰማ ሁሉ ጥሩ ምላሽ ይሰጠናል ብለን ባንጠብቅም አንዳንዶች ግን መልእክቱን ይቀበላሉ። (ማቴዎስ 13:19-23) ሌሎች ደግሞ በዓለም ላይ ወይም በሕይወታቸው ውስጥ ሁኔታዎች ሲለዋወጡ ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን በአገልግሎት የተቻለንን ያህል ስናከናውን የአምላክን ሥራ እየፈጸምን ነው። ደግሞም “ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነን።”—1 ቆሮንቶስ 3:9
10. በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ ምን አጋጣሚዎች አሏቸው?
10 ከዚህም በተጨማሪ ሁላችንም የቤተሰባችንን አባላት እንዲሁም መንፈሳዊ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መርዳት እንችላለን። (ገላትያ 6:10) በሌሎች ላይ ዘላቂ የሆነ ከፍተኛ ተጽዕኖ ልናሳድር እንችላለን። (መክብብ 11:1, 6) ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ኃላፊነታቸውን በትጋት ሲወጡ የጉባኤው አባላት በመንፈሳዊ ጤናሞች እንዲሆኑና ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ጠብቀው ለመቀጠል እንዲችሉ የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ የጉባኤው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ይጨምራል። ‘ለጌታ ሥራ የምንተጋ’ ከሆነ ድካማችን ‘ከንቱ እንደማይሆን’ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።—1 ቆሮንቶስ 15:58
የአምላክን ዓላማ የሕይወታችን ግብ ማድረግ
11. በጉባኤያችን ከማገልገል በተጨማሪ በየትኞቹ የአገልግሎት መስኮች መካፈል እንችላለን?
11 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሕይወት መኖራችን የሚያስደስተን ከመሆኑም በላይ የምናደርገው ነገር ሁሉ ለአምላክ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን እንፈልጋለን። (1 ቆሮንቶስ 10:31) የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ሰዎች ኢየሱስ ያዘዘውን እንዲፈጽሙ በማስተማሩ ሥራ በታማኝነት ስንካፈል ደስታ የሚያስገኙ በርካታ የአገልግሎት መስኮች ይከፈቱልናል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በጉባኤያችን ውስጥ ከማገልገል በተጨማሪ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ክልል፣ ቋንቋ ወይም አገር የማገልገል አጋጣሚዎች ይኖሩን ይሆናል። በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል ብቁ የሆኑ ያላገቡ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በዚህ ትምህርት ቤት እንዲሠለጥኑ ይጋበዙ ይሆናል፤ ከተመረቁ በኋላ በአገራቸው ወይም በውጭ አገር በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖች እርዳታ በሚያስፈልግባቸው ጉባኤዎች ይመደባሉ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የሚገኙ ባልና ሚስትም የሚስዮናውያን ማሠልጠኛ በሆነው በጊልያድ ትምህርት ቤት ሠልጥነው በሌሎች አገሮች ማገልገል ይችላሉ። ከዚህም ሌላ በቤቴል ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውኑ፣ የመሰብሰቢያ ቦታዎችን እንዲሁም ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመገንባትና በማደስ ሥራ የሚካፈሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች ምንጊዜም ይፈለጋሉ።
12, 13. (ሀ) በየትኞቹ የአገልግሎት መስኮች እንደምትሠማራ መወሰን የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) በአንድ የአገልግሎት ዘርፍ ያገኘነው ልምድ በሌሎች መስኮችም የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
12 አንተስ በየትኞቹ የአገልግሎት መስኮች መካፈል ትፈልጋለህ? ራስህን ለይሖዋ የወሰንክ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን ምንጊዜም ከይሖዋና ከድርጅቱ መመሪያ ለማግኘት መጣር ይኖርብሃል። ይሖዋም ‘መልካም መንፈሱን’ በመስጠት ትክክለኛ ውሳኔ እንድታደርግ ይረዳሃል። (ነህምያ 9:20 የ1954 ትርጉም) አብዛኛውን ጊዜ አንድ የአገልግሎት ዘርፍ ለሌላ የአገልግሎት መስክ መንገድ ይከፍትልናል፤ እንዲሁም በአንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ያገኘነው ልምድና ችሎታ በሌላ የአገልግሎት መስክ ሊጠቅመን ይችላል።
13 ለምሳሌ ያህል፣ ዴኒስና ባለቤቱ ጄኒ በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ አዘውትረው ይካፈላሉ። ደቡባዊው የዩናይትድ ስቴትስ ክፍል ካትሪና በተባለችው አውሎ ነፋስ ከተመታ በኋላ በአደጋ የተጎዱትን ለመርዳት ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ። ዴኒስ እንዲህ ይላል:- “በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ላይ ባገኘነው ችሎታ ተጠቅመን ወንድሞቻችንን ለመርዳት መቻላችን ትልቅ ደስታ አስገኝቶልናል። የረዳናቸው ሰዎች ያሳዩት የአመስጋኝነት መንፈስ ልብ የሚነካ ነው። ሌሎች እርዳታ ሰጪ ቡድኖች በአደጋው የተጎዱ ቤቶችን መልሶ በመገንባቱ ሥራ እምብዛም አልተሳካላቸውም። የይሖዋ ምሥክሮች ግን ከ5,300 በላይ ቤቶችንና በርካታ የመንግሥት አዳራሾችን አድሰዋል ወይም እንደገና ሠርተዋል። ሌሎች ሰዎችም ይህንን የታዘቡ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ይበልጥ ፍላጎት አላቸው።”
14. በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሠማራት የምትፈልግ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?
14 አንተስ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግብህ በማድረግ ከይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ትችላለህ? እንዲህ ካደረግህ ብዙ በረከት እንደምታገኝ ጥርጥር የለውም። ሁኔታህ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሠማራት የማይፈቅድልህ ከሆነ ማስተካከያ ልታደርግ ትችል ይሆናል። ነህምያ፣ አስፈላጊ ሥራ ለማከናወን በፈለገበት ወቅት እንዳደረገው ሁሉ አንተም “እግዚአብሔር ሆይ፤ . . . ለባሪያህ መከናወንን ስጠው” በማለት ጸልይ። (ነህምያ 1:11) ከዚያም ‘ጸሎትን በሚሰማው’ አምላክ በመታመን ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰድ። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ እሱን ይበልጥ ለማገልገል የምታደርገውን ጥረት እንዲባርክልህ በመጀመሪያ አንተ ጥረት ማድረግ አለብህ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ከወሰንክ ከውሳኔህ ጋር ተስማምተህ ኑር። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የበለጠ ተሞክሮ የምታገኝ ከመሆኑም በላይ ደስታህ ይጨምራል።
የሚክስ ሕይወት
15. (ሀ) ለረጅም ጊዜ አምላክን ያገለገሉ ክርስቲያኖችን ማነጋገርና ተሞክሯቸውን ማንበብ የሚጠቅመን እንዴት ነው? (ለ) በጣም አበረታች ሆኖ ያገኘኸውን የሕይወት ታሪክ ጥቀስ።
15 ከአምላክ ዓላማ ጋር ተስማምተህ መኖርህ ምን ውጤት ያመጣል? ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉትን በተለይም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በርካታ ዓመታት ያሳለፉ የአምላክ አገልጋዮችን ጠይቃቸው። እንዴት ያለ የሚያረካና ዓላማ ያለው ሕይወት አሳልፈዋል! (ምሳሌ 10:22) ይሖዋ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያትም እንኳ የሚያስፈልጋቸውንና ከዚያም በላይ ሳይሰጣቸው የቀረበት ጊዜ እንደሌለ ይነግሩሃል። (ፊልጵስዩስ 4:11-13) ላለፉት አሥርተ ዓመታት በመቶ የሚቆጠሩ የሕይወት ታሪኮች በመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ ወጥተዋል። እነዚህ የሕይወት ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተገለጹት የጥንት ክርስቲያኖች የነበራቸውን ቅንዓትና በአገልግሎት ያገኙትን ደስታ ያስታውሰናል። እንደነዚህ የመሳሰሉ አስደሳች ታሪኮችን ማንበብህ ‘እኔ የምፈልገው እንዲህ ያለ ሕይወት ነው!’ እንድትል ይገፋፋሃል።
16. የአንድ ክርስቲያን ሕይወት ዓላማ ያለውና ደስታ የሞላበት እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?
16 በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው አሮን እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “አፍሪካ ውስጥ፣ ለሕይወታቸው ዓላማ ለማግኘት የሚባዝኑ ወጣቶች ብዙ ጊዜ አጋጥመውኛል። አብዛኞቹ የሚፈልጉትን አያገኙም። እኛ ግን የመንግሥቱን ምሥራች በማስፋፋት ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖርን ሲሆን ይህ ደግሞ በሥራ እንድንጠመድና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ አስችሎናል። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የበለጠ ደስታ እንደሚያገኝ ከራሳችን ተሞክሮ ለመመልከት ችለናል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35
17. በአሁኑ ጊዜ ሕይወታችንን ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መምራት ያለብን ለምንድን ነው?
17 አንተስ? ምን ዓይነት ግብ ላይ ለመድረስ እየጣርክ ነው? ግልጽ የሆነ መንፈሳዊ ግብ ከሌለህ ሌሎች ነገሮች ጊዜህንና ጉልበትህን ያሟጥጡብሃል። የሰይጣን ሥርዓት አስፈላጊ እንደሆኑ አድርጎ በሚያቀርባቸው ነገሮች ውድ ሕይወትህን ለምን ታባክናለህ? በቅርቡ “ታላቁ መከራ” ሲመጣ ቁሳዊ ሀብትም ሆነ በዓለም ላይ የሚገኘው ክብር ዋጋ ቢስ ይሆናሉ። በዚያን ጊዜ ዋጋ የሚኖረው ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ነው። አምላክንና ሰዎችን ማገልገላችንን እንዲሁም ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መምራታችንን በዚያን ወቅት እናደንቀዋለን!—ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 7:14, 15
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
ልታብራራ ትችላለህ?
• ይሖዋ ለእሱ የምናቀርበውን አገልግሎት እንዴት ይመለከተዋል?
• ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እርምጃዎችን መውሰዳችን እንዲሁም ሚዛናዊ መሆናችን አምላክንና ሰዎችን ለማገልገል የሚረዳን እንዴት ነው?
• በየትኞቹ መስኮች አምላክን ማገልገል እንችላለን?
• በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት የምንችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን ማገልገላችንን ለመቀጠል ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገናል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክን ማገልገል የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ