በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እውነት ምንድን ነው?”

“እውነት ምንድን ነው?”

“እውነት ምንድን ነው?”

ይህን ምጸት የተንጸባረቀበት ጥያቄ ለኢየሱስ ያቀረበው የሮም አገረ ገዥ የነበረው ጳንጥዮስ ጲላጦስ ነበር። ጲላጦስ ይህን ጥያቄ ያነሳው መልሱን ለማወቅ ፈልጎ አልነበረም፤ ኢየሱስም ቢሆን መልስ አልሰጠውም። ጲላጦስ፣ እውነትን ለመረዳት አዳጋች እንደሆነ ጽንሰ ሐሳብ አድርጎ ሳይመለከተው አልቀረም።—ዮሐንስ 18:38

በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የሃይማኖት መሪዎችን፣ ምሑራንንና የፖለቲካ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ለእውነት እንዲህ ያለ የንቀት አመለካከት አላቸው። እነዚህ ሰዎች፣ በተለይ ከሥነ ምግባራዊና ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ፍጹም እውነት የሆነ ነገር እንደሌለና እውነት አንጻራዊ ብሎም ተለዋዋጭ እንደሆነ ያምናሉ። ይህ ደግሞ፣ ሰዎች ትክክል ወይም ስሕተት የሆነውን ነገር በራሳቸው ለይተው ማወቅ ይችላሉ የሚል አንድምታ አለው። (ኢሳይያስ 5:20, 21) ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ያለው አመለካከት፣ ቀደም ባሉት ዘመናት ከፍ ተደርገው ይታዩ የነበሩ የሥነ ምግባር እሴቶችና መሥፈርቶች ጊዜ እንዳለፈባቸው ተቆጥረው እንዲተዉ መንገድ ይከፍታል።

ጲላጦስ እንዲህ ያለውን ጥያቄ እንዲጠይቅ ያነሳሳው ነገር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ከዚያ ቀደም ብሎ ኢየሱስ “የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው” ብሎት ነበር። (ዮሐንስ 18:37) በኢየሱስ አመለካከት እውነት የተድበሰበሰና ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ አልነበረም። ለደቀ መዛሙርቱ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል” በማለት ቃል ገብቶላቸው ነበር።—ዮሐንስ 8:32

ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ እውነት ሊገኝ የሚችለው የት ነው? በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለአምላክ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 17:17) በመሆኑም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ አስተማማኝ መመሪያ እንዲሁም እርግጠኛ የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ የያዘ እውነት ይገኛል።—2 ጢሞቴዎስ 3:15-17

ጲላጦስ እንዲህ ዓይነቱን እውነት ለማወቅ የነበረውን አጋጣሚ በቸልታ አሳልፎታል። አንተስ ይህን አጋጣሚ እንዴት ትመለከተዋለህ? ኢየሱስ ያስተማረው “እውነት” ምን እንደሆነ እንዲያብራሩልህ ለምን የይሖዋ ምሥክሮችን አትጠይቃቸውም? እነሱም ይህንን እውነት ሊያብራሩልህ ፈቃደኞች ናቸው።