በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስተኛ ለመሆን የሚረዳ ምርጫ

ደስተኛ ለመሆን የሚረዳ ምርጫ

ደስተኛ ለመሆን የሚረዳ ምርጫ

“ምነው እንዲህ ባላደረግኩ ኖሮ!” በማለት የተናገርክባቸውን ጊዜያት ታስታውሳለህ? ሁላችንም፣ በተለይ ሕይወታችንን የሚነኩ ምርጫዎች በምናደርግበት ጊዜ ምርጫዎቻችን በኋላ የማያስቆጩን እንዲሆኑ እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ ደስተኛ ለመሆን የሚረዱ ምርጫዎች ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ አስተማማኝ የሆኑ መሥፈርቶች ያስፈልጉናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት መሥፈርቶች ይኖራሉ? ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት መሥፈርቶች ያሉ አይመስላቸውም። በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ ጥናት መሠረት 75 በመቶ የሚሆኑ የኮሌጅ የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆኑትን ነገሮች ለመለየት የሚያስችል መሥፈርት እንደሌለ እንዲሁም መልካም ወይም ክፉ የሚባሉ ነገሮች “እንደ ግለሰቦች አመለካከትና እንደየባሕሉ” የተለያዩ እንደሆኑ ያምናሉ።

ይሁን እንጂ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚወሰኑት በግለሰቦች ወይም በብዙኃኑ አመለካከት መሠረት ነው የሚለው አስተሳሰብ ምክንያታዊ ነው? በፍጹም አይደለም። ሰዎች የተመኙትን ሁሉ ማድረግ የሚችሉ ቢሆን ኖሮ ትርምስ ይፈጠር ነበር። ሕግም ሆነ ፍርድ ቤት እንዲሁም ፖሊሶች በሌሉበት ቦታ ለመኖር ማን ይፈልጋል? ከዚህም በተጨማሪ የግል አመለካከት አስተማማኝ መመሪያ የሚሆነው ሁልጊዜ አይደለም። ትክክል እንደሆነ ያመንበትን ነገር ለማድረግ እንመርጥ ይሆናል፤ ውሎ አድሮ ግን ተሳስተን እንደነበረ እንገነዘባለን። በእርግጥም የሰው ልጅ ታሪክ በአጠቃላይ “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል” የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነት እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው። (ኤርምያስ 10:23) ይህ ከሆነ ታዲያ በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን ስናደርግ መመሪያ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ወጣት አለቃ ምክር ለማግኘት ወደ ኢየሱስ መሄዱ የጥበብ እርምጃ ነበር። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ኢየሱስም የዚህን ወጣት ጥያቄ ለመመለስ የአምላክን ሕግ ተጠቅሟል። ኢየሱስ፣ የእውቀትና የጥበብ ሁሉ ዋና ምንጭ ይሖዋ አምላክ እንደሆነ እንዲሁም ለፍጥረታቱ ከሁሉ የተሻለውን እንደሚያውቅ ተገንዝቧል። በዚህም የተነሳ “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) በእርግጥም የአምላክ ቃል በሕይወታችን ውስጥ ጥበብ የተሞላባቸው ምርጫዎች ለማድረግ የሚረዳን አስተማማኝ መመሪያ ይዟል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙና ተግባራዊ ካደረግናቸው ደስተኞች እንድንሆን የሚረዱ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እስቲ እንመልከት።

ወርቃማው ሕግ

ኢየሱስ ታዋቂ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ፣ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎች ለማድረግ ሊረዳን የሚችል መሠረታዊ ሥርዓት አስተምሯል። ኢየሱስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:12) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ብዙውን ጊዜ ወርቃማው ሕግ ተብሎ ይጠራል።

አንዳንዶች ይህንን አባባል በተቃራኒ መንገድ በመግለጽ “ሌሎች ሊያደርጉባችሁ የማትፈልጉትን ነገር እናንተም አታድርጉባቸው” ይላሉ። በዚህኛው ሕግና በወርቃማው ሕግ መካከል ያለውን ልዩነት ለማየት ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የሰጠውን ምሳሌ እንመልከት። ወንበዴዎች አንድን አይሁዳዊ ክፉኛ ደብድበው በሕይወትና በሞት መካከል ትተውት ሄዱ። አንድ ካህንና አንድ ሌዋዊ ይህን ሰው ቢመለከቱትም አልፈውት ሄዱ። እነዚህ ሰዎች ሰውየውን የሚጎዳ ነገር ስላላደረጉ የወርቃማው ሕግ ተቃራኒ የሆነውን ሕግ ተግባራዊ አድርገዋል ሊባል ይችል ይሆናል። ከዚህ በተቃራኒ ግን በዚያ መንገድ ሲያልፍ የተደበደበውን ሰው የተመለከተው አንድ ሳምራዊ የሰውየውን ቁስል ጠራርጎ ካሰረለት በኋላ ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው። ይህ ሳምራዊ ለራሱ እንዲደረግለት የሚፈልገውን ነገር ለቆሰለው ሰው አድርጎለታል። በመሆኑም ወርቃማውን ሕግ በተግባር ያዋለ ሲሆን ያደረገው ምርጫም ትክክል ነበር።—ሉቃስ 10:30-37

ኢየሱስ የሰጠውን ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፤ እንዲህ በማድረጋችንም አስደሳች ውጤት እናገኛለን። ለምሳሌ፣ አንድ ቤተሰብ ወደምትኖርበት ሠፈር መጣ እንበል። ቅድሚያውን ወስደህ እነዚህን ሰዎች በመተዋወቅ ለምን ጥሩ አቀባበል አታደርግላቸውም? ሰዎቹ አካባቢውን እንዲያውቁት ልትረዳቸው እንዲሁም ጥያቄዎቻቸውን ልትመልስላቸውና በሚያስፈልጓቸው ነገሮች ረገድ ልታግዛቸው ትችል ይሆናል። ቅድሚያውን ወስደህ አሳቢነት በማሳየት ከአዲሶቹ ጎረቤቶችህ ጋር ጥሩ ግንኙነት ልትመሠርት ትችላለህ። ከዚህም በላይ አምላክን የሚያስደስት ነገር እንዳደረግህ ማወቅህ እርካታ ያመጣልሃል። ታዲያ ይህ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ አይደለም?

ለሰዎች ባለን ፍቅር ተነሳስተን የምናደርጋቸው ምርጫዎች

ኢየሱስ ከወርቃማው ሕግ በተጨማሪ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ምርጫዎች ለማድረግ የሚረዳህ ሌላ መመሪያም ሰጥቷል። ኢየሱስ፣ በሙሴ ሕግ ውስጥ ከሚገኙት ትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ እንዲህ በማለት መልሷል:- “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።”—ማቴዎስ 22:36-40

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ የሚያዝ “አዲስ ትእዛዝ” ሰጣቸው። (ዮሐንስ 13:34) ኢየሱስ ይህንን ትእዛዝ አዲስ በማለት የገለጸው ለምን ነበር? ደግሞስ ሕጉ በሙሉ ከተመሠረተባቸው ሁለት ትእዛዛት አንዱ ጎረቤታቸውን መውደድ እንደሆነ አስቀድሞ ተናግሮ አልነበረም? በሙሴ ሕግ ውስጥ እስራኤላውያን “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 19:18) በዚህ ወቅት ግን ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ የበለጠ ነገር እንዲያደርጉ ማዘዙ ነበር። በዚያው ምሽት ኢየሱስ ሕይወቱን ለእነሱ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ነገራቸው። ከዚያም እንዲህ አላቸው:- “ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር ማንም የለውም።” (ዮሐንስ 15:12, 13) ይህ ትእዛዝ ከራስ ጥቅም ይልቅ የሌሎችን ጥቅም ማስቀደምን የሚጠይቅ በመሆኑ በእርግጥም አዲስ ትእዛዝ ነበር።

ስለ ራሳችን ጥቅም ብቻ ባለማሰብ ከራስ ወዳድነት የራቀ ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ለአብነት ያህል፣ የምትኖረው በአፓርታማ ውስጥ እንበል፤ ድምፁን ከፍ አድርገህ ሙዚቃ ማዳመጥ ብትወድም እንዲህ ማድረግህ ጎረቤትህን ይረብሸዋል። ጎረቤትህ እንዳይረበሽ ስትል ደስታህን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ትሆናለህ? በሌላ አባባል ከራስህ ይልቅ የጎረቤትህን ጥቅም ታስቀድማለህ?

ሌላ ሁኔታ ደግሞ እንመልከት። በካናዳ፣ በአንድ ቀዝቃዛ የክረምት ቀን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አንድ አረጋዊ ሰው ቤት ሄዱ፤ በዕለቱ በረዶ ይጥል ነበር። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ከአረጋዊው ጋር እየተወያዩ ሳለ ሰውየው የልብ ሕመም ስላለባቸው ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን በረዶ መጥረግ እንዳልቻሉ ገለጹላቸው። ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ አረጋዊው ሰው በረዶው በአካፋ ሲዛቅ ሰሙ። ሁለቱ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አረጋዊው ቤት በሚወስደው መንገድ እንዲሁም ደረጃቸው ላይ ያለውን በረዶ ለመጥረግ ተመልሰው ነበር። እኚህ አረጋዊ፣ በካናዳ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፈዋል:- “ዛሬ፣ እውነተኛ የክርስቲያኖች ፍቅር በተግባር ሲገለጽ ተመልክቻለሁ። በዛሬው ጊዜ ስላለው ዓለም የነበረኝን አሉታዊ አመለካከት ለማስተካከል የረዳኝ ከመሆኑም በላይ በዓለም ዙሪያ ለምታከናውኑት ሥራ የነበረኝ አክብሮት የበለጠ እንዲጨምር አድርጓል።” አዎን፣ ትንሽ በሚመስሉ መንገዶችም እንኳ ሰዎችን መርዳት በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በእርግጥም የራስን ጥቅም በመሠዋት እንዲህ ያለ ምርጫ ማድረግ ታላቅ ደስታ ያስገኛል!

ለአምላክ ባለን ፍቅር ተነሳስተን የምናደርጋቸው ምርጫዎች

ምርጫ በምናደርግበት ጊዜ ግምት ውስጥ ልናስገባው የሚገባን ሌላው ነገር ደግሞ ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ ብሎ የጠቀሰውን ትእዛዝ ማለትም ለአምላክ ያለንን ፍቅር ነው። ኢየሱስ ይህን የተናገረው በብሔር ደረጃ ለይሖዋ የተወሰኑ ሕዝቦች ለነበሩት ለአይሁዳውያን ነበር። እንደዚያም ሆኖ እያንዳንዱ እስራኤላዊ፣ በፍጹም ነፍሱና በፍጹም ልቡ አምላክን በመውደድ እሱን ለማገልገል መምረጥ ነበረበት።—ዘዳግም 30:15, 16

በተመሳሳይ አንተም የምታደርጋቸው ምርጫዎች ስለ አምላክ ያለህን አመለካከት ያሳያሉ። ለአብነት ያህል፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለህ እውቀት እየጨመረና ጠቃሚነቱን እየተገነዘብክ ስትሄድ አንተም ምርጫ ይደቀንብሃል። ታዲያ የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ብለህ መጽሐፍ ቅዱስን ሥርዓታማና ወጥ በሆነ መልኩ ለማጥናት ፈቃደኛ ነህ? ይህን ለማድረግ ከመረጥህ ደስተኛ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” ብሏል።—ማቴዎስ 5:3 NW

ወጣቱ አለቃ ባደረገው ውሳኔ ተጸጽቶ ይሁን አይሁን የምናውቀው ነገር የለም። በሌላ በኩል ግን፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ለበርካታ ዓመታት ኢየሱስ ክርስቶስን ከተከተለ በኋላ ምን እንደተሰማው ተገልጿል። ጴጥሮስ በ64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ወደ ሕይወቱ ማብቂያ ሲቃረብ የእምነት ባልንጀሮቹን “ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም [በአምላክ ዘንድ] እንድትገኙ ትጉ” በማለት አበረታቷቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:14፤ 3:14 የ1954 ትርጉም) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ጴጥሮስ ከ30 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ባደረገው ምርጫ አልተጸጸተም፤ እንዲያውም ሌሎች ባደረጉት ምርጫ ጸንተው እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል።

የጴጥሮስን ምክር መከተል ሲባል የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ለመቀበልና የአምላክን ትእዛዛት ለመጠበቅ መምረጥ ማለት ነው። (ሉቃስ 9:23፤ 1 ዮሐንስ 5:3) እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊመስል ቢችልም ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቶልናል:- “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።”—ማቴዎስ 11:28-30

የአርተርን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አርተር፣ የቫዮሊን ተጫዋች የመሆን ግብ በመያዝ በአሥር ዓመቱ ሥልጠና ጀመረ። አሥራ አራት ዓመት ሲሆነው በሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ ይጫወት ነበር። ያም ሆኖ ግን ደስተኛ አልነበረም። አባቱ የሕይወትን ትርጉም በተመለከተ ጥያቄዎች ስለነበሩት የተለያዩ የሃይማኖት አስተማሪዎችን ወደ ቤታቸው ይጋብዝ ነበር፤ እንደዚያም ሆኖ አጥጋቢ መልስ አላገኘም። የቤተሰቡ አባላት፣ አምላክ ስለ መኖሩ እንዲሁም ክፋትን ለምን እንደፈቀደ ይወያዩ ነበር። ከጊዜ በኋላ የአርተር አባት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መወያየት ጀመረ። የሚያደርጉት ውይይት የአርተርን አባት ስላስደሰተው ቤተሰቡ በአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ።

ከጊዜ በኋላ አርተር፣ አምላክ የሰው ልጆች ሥቃይ እንዲደርስባቸው ለምን እንደፈቀደ እንዲሁም የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ከቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ለመረዳት ቻለ። አርተርና ሦስት የቤተሰቡ አባላት ፈጽሞ ተቆጭተውበት የማያውቁትን ምርጫ አደረጉ። አርተር ሕይወቱን ለይሖዋ የወሰነ ሲሆን እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ይሖዋ እውነትን እንዳውቅ ስላደረገኝና በሙዚቃ ባለሙያዎች ዘንድ ከሚታየው የፉክክር መንፈስ እንድገላገል ስለረዳኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሰዎች ስኬታማ ለመሆን ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም።”

አርተር አሁንም ጓደኞቹን ለማዝናናት ቫዮሊን መጫወት የሚወድ ቢሆንም ሕይወቱ በዚህ ሙያ የተጠላለፈ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሕይወቱ አምላክን በማገልገል ላይ ያተኮረ ነው። አርተር በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአንዱ ውስጥ እያገለገለ ነው። ባለጠጋው ወጣት ካደረገው ምርጫ በተቃራኒ አንተም እንደ አርተርና ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኢየሱስ የእሱ ተከታይ እንድትሆን ያቀረበልህን ግብዣ በመቀበል ታላቅ ደስታ የሚያመጣልህ ምርጫ ማድረግ ትችላለህ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምታደርገው ምርጫ በሌሎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተህ የኢየሱስ ተከታይ ለመሆን ፈቃደኛ ነህ?