በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥበብ የጎደለው ምርጫ ያደረገ ባለጠጋ አለቃ

ጥበብ የጎደለው ምርጫ ያደረገ ባለጠጋ አለቃ

ጥበብ የጎደለው ምርጫ ያደረገ ባለጠጋ አለቃ

ባለጠጋው ወጣት ትክክል የሆነውን የሚያደርግ፣ ሕግ አክባሪና ሃይማኖተኛ ሰው ነበር። የአይሁድ አለቃ የሆነው ይህ ወጣት ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በጉልበቱ በመንበርከክ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” በማለት ጠየቀው።

ኢየሱስም ሕይወት ለማግኘት የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ እንዳለበት ነገረው። ሰውየውም፣ የትኞቹን ትእዛዛት ማለቱ እንደሆነ ግልጽ እንዲያደርግለት ኢየሱስን ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አትግደል፣ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤ ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” በማለት መለሰለት። እነዚህ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ ውስጥ የሚገኙ መሠረታዊ ትእዛዛት ነበሩ። በዚህ ጊዜ ሰውየው “እነዚህንማ ጠብቄአለሁ፤ ከዚህ ሌላ የሚጐድለኝ ምን አለ?” የሚል ጥያቄ አነሳ።—ማቴዎስ 19:16-20

ኢየሱስ ሰውየውን ‘ስለወደደው’ እንዲህ አለው፦ “አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላ ና፤ ተከተለኝም።”—ማርቆስ 10:17-21

በዚህ ጊዜ ወጣቱ አለቃ በድንገት ከባድ ውሳኔ ተደቀነበት። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? ሀብት ንብረቱን ትቶ የኢየሱስ ተከታይ ይሆናል ወይስ ሀብቱን የሙጥኝ ብሎ ይቀጥላል? በሰማይ ሀብት ያከማች ይሆን ወይስ በምድር? ይህ ወጣት ምርጫ ማድረግ ከብዶት መሆን አለበት። ሕጉን ይጠብቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከዚህ በተጨማሪ ምን ማድረግ እንዳለበት መጠየቁ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ያሳያል። ታዲያ ወጣቱ ምን ውሳኔ አደረገ? “ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ።”—ማርቆስ 10:22

ወጣቱ አለቃ ያደረገው ውሳኔ ጥበብ የጎደለው ነበር። ይህ ሰው የኢየሱስ ታማኝ ተከታይ ቢሆን ኖሮ ይፈልገው የነበረውን የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይችል ነበር። ይህ ወጣት መጨረሻው ምን እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ከአርባ ዓመታት ገደማ በኋላ የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና አብዛኛውን የይሁዳን ግዛት እንደደመሰሰ እናውቃለን። በዚህ ጊዜ በርካታ አይሁዳውያን ሀብታቸውንም ሆነ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ከዚህ ወጣት አለቃ በተቃራኒ ሐዋርያው ጴጥሮስም ሆነ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ጥበብ የተሞላበት ምርጫ አድርገዋል። እነሱ ‘ሁሉን ትተው’ ኢየሱስን የተከተሉ ሲሆን ያደረጉት ውሳኔም በጣም ጠቅሟቸዋል! ኢየሱስ፣ ትተዋቸው ከመጡት ነገሮች ብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነገር እንደሚያገኙ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት እንደሚወርሱ ነግሯቸዋል። እነዚህ ሰዎች ያደረጉት ውሳኔ በኋላ የሚያስቆጫቸው አልነበረም።—ማቴዎስ 19:27-29

ሁላችንም ቢሆን በሕይወታችን ውስጥ ቀላል ወይም ከባድ ውሳኔዎች ይደቀኑብናል። ኢየሱስ እንደነዚህ ያሉ ውሳኔዎችን በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል? እሱ የሰጠውን ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ ነህ? እንዲህ ለማድረግ ከመረጥህ የተትረፈረፈ በረከት ታገኛለህ። ኢየሱስን መከተልና ከሰጠው ምክር ተጠቃሚ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።