በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለማመን የሚያዳግተው ቆራጥነቱ አስደንቆኛል’

‘ለማመን የሚያዳግተው ቆራጥነቱ አስደንቆኛል’

‘ለማመን የሚያዳግተው ቆራጥነቱ አስደንቆኛል’

በ1999 በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ የሆነ ጉንተር ግራስ የተባለ ጀርመናዊ ደራሲ በ2006 የሕይወት ታሪኩን የሚያወሳ መጽሐፍ ለሕትመት አብቅቷል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ግራስ የጀርመን የደህንነት ኃይል አባል እንዲሆን ተመልምሎ ስለነበረበት ጊዜ ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ከ60 ዓመትም በኋላ እንኳ ስለሚያስታውሰውና ከፍተኛ አድናቆት ስላሳደረበት አንድ ሰው ገልጿል። ጉንተር፣ በእምነቱ ምክንያት የደረሰበትን ስደት በመቋቋም ረገድ የሚያውቀው ሰው ቢኖር ይህን ሰው ብቻ እንደሆነ ተናግሯል።

በጀርመን የሚታተመው ፍራንክፈርተር አልጀሚን ቲስቱንግ የተባለ ዕለታዊ ጋዜጣ ባሰፈረው ቃለ ምልልስ ላይ ግራስ የጦር መሣሪያ ለማንገብ ፈቃደኛ ስላልነበረው ስለዚህ አስደናቂ ሰው ተናግሯል። ግራስ እንዲህ ብሏል:- “[ሰውየው] በወቅቱ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ከነበሩት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች መካከል የየትኛውም ማለትም የናዚ፣ የኮሚኒስት አሊያም የሶሻሊስት ደጋፊ አልነበረም። ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር ነበር።” ግራስ ‘እኛ እንዲህ አናደርግም’ የሚል ቅጽል ስም ያወጣለትን የዚህን ሰው ትክክለኛ ስም አያስታውስም። የይሖዋ ምሥክሮችን ታሪክ የሚያጠኑ ምሑራን ግን ሰውየው ዮአኪም አልፈማን ይባል እንደነበር ገልጸዋል። ይህ ሰው በተደጋጋሚ ጊዜያት ከተደበደበና ክብሩን የሚነካ ድርጊት ከተፈጸመበት በኋላ በአንድ ክፍል ውስጥ ለብቻው እንዲታሰር ተደረገ። ያም ሆኖ በአቋሙ የጸና ሲሆን የጦር መሣሪያ ለማንገብም ፈቃደኛ አልሆነም።

ግራስ እንዲህ ብሏል:- “ይህ ሰው ያሳየው ለማመን የሚያዳግት ቆራጥነት አስደንቆኛል። ‘ይህን ሁሉ እንዴት በጽናት ሊቋቋም ቻለ? ይህን ማድረግ የቻለው እንዴት ነው?’ እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር።” አልፈማን ለአምላክ ያለውን ጽኑ አቋም እንዲያላላ ለማድረግ ይደርስበት የነበረውን ፈተና ከተቋቋመ በኋላ በየካቲት 1944 ወደ ሹትኽፍ ማጎሪያ ካምፕ ተላከ። በሚያዝያ 1945 ከእስር ነጻ የወጣ ሲሆን የጦርነቶቹን ጊዜያት በሕይወት አልፎ እስከሞተበት እስከ 1998 ድረስ ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ሆኖ መጽናት ችሏል።

አልፈማን በጀርመንና በናዚ አገዛዝ ሥር በነበሩ አገሮች ውስጥ በእምነታቸው ምክንያት ከባድ ቅጣት ይደርስባቸው ከነበሩ 13,400 የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ ነበር። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆንና የጦር መሣሪያዎችን ባለማንገብ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ታዘዋል። (ማቴዎስ 26:52፤ ዮሐንስ 18:36) በወቅቱ ወደ 4,200 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ማጎሪያ ካምፖች የገቡ ሲሆን 1,490 የሚሆኑት ሕይወታቸውን አጥተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በዚያን ወቅት ያሳዩት ጽኑ አቋም ዛሬም ቢሆን እምነታቸውን በማይጋሩ ሰዎች ዘንድ አድናቆት አትርፎላቸዋል።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮአኪም አልፈማን