ሰራኩስ ጳውሎስ ለጥቂት ጊዜ ያረፈባት ከተማ
ሰራኩስ ጳውሎስ ለጥቂት ጊዜ ያረፈባት ከተማ
በ59 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ አንዲት መርከብ በሜድትራኒያን ባሕር ላይ ከምትገኘው የመላጥያ ደሴት ተነስታ ወደ ጣሊያን አቀናች። የባሕረተኞች ጠባቂ እንደሆኑ የሚታመንባቸው “ዲዮስቆሮስ” ተብለው የሚጠሩት መንትያ አማልክት ምስል በመርከቧ የፊተኛው ጫፍ ላይ ተቀርጿል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ሉቃስ መርከቧ በሲሲሊ ደሴት ደቡባዊ ምሥራቅ የባሕር ዳርቻ ላይ በምትገኘው ‘በሰራኩስ ለሦስት ቀናት’ እንደቆመች ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 28:11, 12) ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሉቃስ፣ አርስጥሮኮስና ለፍርድ እንዲቀርብ ወደ ሮም እየተወሰደ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ ይገኙበት ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 27:2
ጳውሎስ በሰራኩስ ከመርከቧ እንዲወርድ ተፈቅዶለት እንደሆነና እንዳልሆነ የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና እሱ ወይም የጉዞ ጓደኞቹ ከመርከቧ እንዲወርዱ ተፈቅዶላቸው ከነበረ በአካባቢው ምን አይተው ሊሆን ይችላል?
በግሪካውያንና በሮማውያን ዘመን ሰራኩስ ልክ እንደ አቴንስና ሮም ታላቅ ከተማ ነበረች። በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ከተማዋን በ734 ከክርስቶስ ልደት በፊት የቆረቆሯት የቆሮንቶስ ሰዎች ነበሩ። ሰራኩስ እጅግ ዝነኛ የሆነችባቸው ጊዜያት ነበሩ። እንዲሁም የተውኔት ጸሐፊውን ኤፒካሜስንና የሒሳብ ሊቁን አርኪሜድሲን የመሳሰሉ በጥንት ጊዜ የነበሩ ስመ ጥር ሰዎች የትውልድ ከተማ ነች። በ212 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሮማውያን ሰራኩስን ወረሯት።
ዘመናዊቷን የሰራኩስ ከተማ መጎብኘትህ በጳውሎስ ዘመን ከተማዋ ምን ትመስል እንደነበር ለመገንዘብ ይረዳሃል። ከተማዋ ለሁለት የተከፈለች ሲሆን የከተማዋ አንደኛው ክፍል የሚገኘው ኦርቲጂያ በተሰኘው አነስተኛ ደሴት ላይ ነው። ጳውሎስ ተሳፍሮባት የነበረችው መርከብ ለጥቂት ጊዜ የቆመችው በዚህ ቦታ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ሌላው የከተማዋ ክፍል ደግሞ በዋነኛው የሲሲሊ ደሴት ላይ ይገኛል።
በዛሬው ጊዜ፣ የሲሲሊ ክፍል በሆነችው ደሴት ላይ የጥንት ግሪካውያን የሕንጻ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ ይገኛል። ይህ የሕንጻ ፍርስራሽ የአፖሎ ቤተ መቅደስ የነበረ ሲሆን የተገነባውም በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተሠራው የአቴና ቤተ መቅደስ ምሰሶዎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ምሰሶዎች ካቴድራል ተገንብቶባቸዋል።
የዘመናዊቷ ሰራኩስ መሃል ከተማ የሚገኘው በዋነኛው የሲሲሊ ደሴት ላይ ሲሆን በዚህ ቦታ ላይ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች የሚጎበኙበት የኒያፖሊስ ፓርክ ይገኛል። በዚህ ፓርክ መግቢያ አቅራቢያ የግሪካውያን የቲያትር ማሳያ ስፍራ ይታያል። ይህ ቅርስ የግሪካውያንን የቲያትር ቤቶች የሕንጻ ጥበብ ከሚያሳዩት አስደናቂ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው። የቲያትር ማሳያ ስፍራው ባሕሩን ለማየት በሚያስችል ሁኔታ የተሠራ በመሆኑ ለሚቀርቡት ትርዒቶች ግሩም ድምቀት ሰጥቷቸዋል። በፓርኩ ደቡባዊ ጫፍ ላይ በሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተገነባ የሮማውያን አምፊቲያትር ይገኛል። አምፊቲያትሩ ሞላላ ቅርጽ ያለው ሲሆን 140 ሜትር ርዝመትና 119 ሜትር ስፋት አለው። ይህ የቲያትር ማሳያ ስፍራ በጣሊያን ካሉት አምፊቲያትሮች ውስጥ በትልቅነቱ ሦስተኛ ደረጃ ይይዛል።
ሰራኩስን የመጎብኘት አጋጣሚ ካገኘህ በኦርቲጂያ ደሴት ላይ ባሕሩን ለማየት በሚያስችልህ ወንበር ላይ ተቀምጠህ የሐዋርያት ሥራ 28:12ን አንብብ። ከዚያም ሐዋርያው ጳውሎስ የተሳፈረባት መርከብ ወደ ወደቡ ስትመጣ የነበረው ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጣሊያን
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮም
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፑቲዮሉስ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሬጊዩም
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሲሲሊ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰራኩስ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መላጥያ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰራኩስ የሚገኘው የግሪካውያን ቲያትር ማሳያ ስፍራ ፍርስራሽ