በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስብ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስብ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስብ

ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አቅራቢያ በሚገኝ ተራራ ላይ ሆኖ ባቀረበው ዝነኛ ስብከቱ ላይ “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ” ብሏል።—ማቴዎስ 6:34 የ1954 ትርጉም

“ነገ ለራሱ ይጨነቃል” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም ያላቸው ይመስልሃል? ስለ ወደፊቱ ማሰብህን ችላ ብለህ ዛሬን ብቻ መኖር እንዳለብህ የሚያበረታታ ነው? ይህ አስተሳሰብ ኢየሱስም ሆነ ተከታዮቹ ከነበራቸው እምነት ጋር በእርግጥ ይስማማል?

“መጨነቃችሁን ተዉ”

እባክህ መጽሐፍ ቅዱስህን ክፈትና በማቴዎስ 6:25-32 ላይ ያሉትን የኢየሱስን ቃላት አንብብ። ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይላል:- “ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ [“መጨነቃችሁን ተዉ፣” NW]። . . . እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። . . . ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት [“በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ፣” NW] መጨመር የሚችል አለን? ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። . . . ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።”

ኢየሱስ ሁለት ምክሮችን በመስጠት ንግግሩን ደመደመ። የመጀመሪያው “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል” የሚል ነው።—ማቴዎስ 6:33, 34 የ1954 ትርጉም

አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል

እዚህ ላይ ኢየሱስ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩትን ጨምሮ ደቀ መዛሙርቱ እህል ‘እንዳይዘሩ፣ እንዳያጭዱና፣ በጎተራ እንዳያከማቹ’ አሊያም ‘ለፍተውና ፈትለው’ ልብሳቸውን እንዳይሠሩ መናገሩ ነበር? (ምሳሌ 21:5፤ 24:30-34፤ መክብብ 11:4) እንዲህ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ደቀ መዛሙርቱ መሥራታቸውን ካቆሙ የሚቀምሱትም ሆነ የሚለብሱት ስለሚያጡ ‘በመከር ወራት መለመናቸው’ አይቀርም።—ምሳሌ 20:4 የ1954 ትርጉም

ስለ ጭንቀትስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ አድማጮቹ ሙሉ ለሙሉ ከጭንቀት መላቀቅ እንደሚችሉ መናገሩ ነበር? ይህ የማይመስል ነገር ነው። ኢየሱስ ራሱ በታሰረበት ምሽት ላይ እጅግ ተጨንቆና ተረብሾ ነበር።—ሉቃስ 22:44

እዚህ ላይ ኢየሱስ ስለ አንድ መሠረታዊ ሐቅ መናገሩ ነበር። ከልክ በላይ መጨነቅ ያጋጠሙህን ችግሮች ለመፍታት አይረዳህም። ለምሳሌ ያህል ረጅም ዕድሜ እንድትኖር አያደርግህም። ጭንቀት ‘በዕድሜህ ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ’ እንደማይጨምር ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:27 NW) እንዲያውም ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ከባድ ጭንቀት ዕድሜህን ማሳጠሩ አይቀርም።

ኢየሱስ የሰጠው ምክር በእርግጥም ተግባራዊ ነው። የሚያስጨንቁን አብዛኞቹ ነገሮች እንዳሰብነው ሆነው አናገኛቸውም። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል፣ አስከፊ በሆነው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ይህን ሐቅ ተገንዝበዋል። በጊዜው ይሰማቸው የነበረውን ጭንቀት አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሲያስጨንቁኝ የነበሩትን ነገሮች አሁን መለስ ብዬ ሳስብ፣ በሞት አፋፍ ላይ ሳሉ፣ ‘በሕይወታቸው ውስጥ በርካታ ጭንቀቶች የነበሩባቸው ቢሆንም እንኳ ብዙዎቹ ፈጽሞ እንዳልደረሱባቸው’ የተናገሩ አንድ አረጋዊ ትዝ ይሉኛል።” በተለይ ደግሞ የሚያጋጥሙን ውጥረቶችና ችግሮች በቀላሉ ከባድ ጭንቀት ላይ የሚጥሉን ከሆነ እያንዳንዱን ቀን እንደየአመጣጡ ማስተናገድ ጥበብ ነው።

‘አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት ፈልጉ’

ኢየሱስ ይህን ምክር የሰጠው ስለ አድማጮቹ አካላዊና ስሜታዊ ጤንነት በማሰብ ብቻ አልነበረም። ኢየሱስ፣ አንድ ሰው ለሕይወት ስለሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች መጨነቁም ሆነ ሀብትና ደስታ ለማግኘት ከልክ በላይ መመኘቱ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳያተኩር እንቅፋት እንደሚሆንበት ያውቃል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ‘ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከማግኘት የሚበልጡ ነገሮች አሉ?’ በማለት ትጠይቅ ይሆናል። አዎን አሉ! እነዚህም ለአምላክ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር የተያያዙ መንፈሳዊ ነገሮች ናቸው። ኢየሱስ ‘አስቀድመን የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን’ መፈለጋችን በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግሯል።—ማቴዎስ 6:33

በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ብዙ ሰዎች ቁሳዊ ሀብት ያሳድዱ ነበር። በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የያዘው ሀብት ማካበት ነበር። ይሁንና ኢየሱስ አድማጮቹ ከዚህ የተለየ አመለካከት እንዲይዙ አሳስቧቸዋል። ለአምላክ ራሳቸውን የወሰኑ ሕዝቦች እንደመሆናቸው መጠን ‘ሁለንተናዊ ተግባራቸው’ እውነተኛውን ‘አምላክ መፍራትና ትእዛዛቱን መጠበቅ’ ሊሆን ይገባ ነበር።—መክብብ 12:13

የኢየሱስ አድማጮች ስለ ቁሳዊ ነገር በማሰብ መጠመዳቸው ማለትም ‘ለዚህ ዓለም መጨነቃቸውና በብልጽግና ሐሳብ መታለላቸው’ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዳያተኩሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። (ማቴዎስ 13:22) ሐዋሪያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ . . . ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:9) ኢየሱስ ተከታዮቹን ከዚህ “ወጥመድ” እንዲርቁ ለመርዳት ሲል በሰማይ ያለው አባታቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያውቅ መሆኑን እንዲያስታውሱ ነግሯቸዋል። አምላክ ‘ለሰማይ ወፎች’ እንደሚያደርገው ሁሉ እነሱንም ይንከባከባቸዋል። (ማቴዎስ 6:26, 32) በጭንቀት ከመዋጥ ይልቅ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት የቻሉትን ያህል መጣርና ቀሪውን ለይሖዋ መተው ነበረባቸው።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ኢየሱስ “ነገ ለራሱ ይጨነቃል” ማለቱ ዛሬ ባለብን ችግር ላይ ገና ለገና ይከሰት ይሆናል የሚል አላስፈላጊ ጭንቀት መደረብ እንደሌለብን መናገሩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና” ይላል።—ማቴዎስ 6:34

“መንግሥትህ ትምጣ”

ይሁን እንጂ ስለ ነገ ከልክ በላይ ባለመጨነቅና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ፈጽሞ ባለማሰብ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንዳያስቡ ፈጽሞ አላበረታታቸውም። ከዚህ ይልቅ ለወደፊቱ ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስቧቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ የዕለት እንጀራቸውን ማለትም በወቅቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት መጸለያቸው ተገቢ ነበር። ይሁን እንጂ፣ በቅድሚያ ወደፊት ስለሚሆኑት ነገሮች ማለትም የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም መጸለይ ነበረባቸው።—ማቴዎስ 6:9-11

በኖኅ ዘመን እንደነበሩት ሰዎች መሆን አይገባንም። እነዚህ ሰዎች ‘በመብላት፣ በመጠጣትና በመጋባት’ የተጠመዱ ስለነበሩ ሊመጣባቸው ያለውን ነገር ‘ሳያውቁ’ ወይም ሳያስተውሉ ቀርተዋል። ውጤቱስ ምን ሆነ? ‘በድንገት የጥፋት ውሃ አጥለቀለቃቸው።’ (ማቴዎስ 24:36-42) ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን ታሪካዊ ክንውን በመጥቀስ የወደፊቱን ጊዜ ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል። እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ [“በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ፣” NW] ይገባል።”—2 ጴጥሮስ 3:5-7, 11, 12

በሰማይ ሀብት አከማቹ

አዎን፣ የይሖዋን ቀን ‘በአእምሯችን አቅርበን እንመልከት።’ እንዲህ ማድረጋችን ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን፣ ክህሎታችንን፣ ሀብታችንን እና ችሎታችንን በምንጠቀምበት መንገድ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ‘እውነተኛ መንፈሳዊነትን’ እንዳናዳብር እንቅፋት እስኪሆንብን ድረስ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላትም ሆነ ደስታ ለማግኘት ስንል ቁሳዊ ሀብት በማሳደድ መጠመድ የለብንም። በዛሬ ላይ ብቻ ማተኮር አንዳንድ ለውጦችን ሊያመጣ ቢችልም የሚያስገኛቸው መልካም ውጤቶች እንኳ ጊዜያዊ ናቸው። ኢየሱስ፣ በምድር ላይ ሀብት ከማካበት ይልቅ ‘ለራሳችን በሰማይ ሀብት ማከማቸታችን’ ብልህነት መሆኑን ተናግሯል።—ማቴዎስ 6:19, 20

ኢየሱስ፣ ትልቅ እቅድ አውጥቶ ስለነበረ አንድ ሰው በተናገረው ምሳሌ ላይ ይህን ነጥብ ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህ ሰው ያወጣቸው እቅዶች ከአምላክ ጋር ያለውን ግንኙነት ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ነበሩ። ሰውየው እርሻው እጅግ ፍሬያማ ሆነለት። በመሆኑም ያሉትን ጎተራዎች አፍርሶ በቀሪው ሕይወቱ ለማረፍ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣትና ለመደሰት የሚያስችል ሀብት ለማከማቸት ሲል ሌሎች ሰፋ ያሉ ጎተራዎችን ለመሥራት አሰበ። ታዲያ ይህ ምን ስህተት አለው? ይህ ሰው በድካሙ ፍሬ ሳይደሰት ሕይወቱን አጥቷል። ከአምላክ ጋር ዝምድና ሳይመሠርት መሞቱ ደግሞ ከምንም በላይ የከፋ ነው። ኢየሱስ ምሳሌውን እንደሚከተለው ሲል ደምድሟል:- “ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”—ሉቃስ 12:15-21፤ ምሳሌ 19:21

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የገለጸው ሰው የሠራውን ዓይነት ስህተት መፈጸም የለብህም። አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለውን ዓላማ ለማወቅና ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ ሕይወትህን ለመምራት ጥረት አድርግ። አምላክ የወደፊት ዓላማውን ከሰው ልጆች አልሰወረም። በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ነቢዩ አሞጽ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ምስጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣ ምንም ነገር አያደርግም።” (አሞጽ 3:7) ይሖዋ ለነቢያቱ የገለጠላቸውን ነገሮች በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ትችላለህ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከገለጠላቸው ነገሮች መካከል በመላው ምድር ላይ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ታላቅ ለውጥ የሚያመጣ አንድ ክንውን በቅርቡ እንደሚፈጸም የሚገልጸው ዘገባ ይገኝበታል። ኢየሱስ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ . . . ታላቅ መከራ ይሆናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:21) ማንኛውም ሰው ይህ ሁኔታ እንዳይፈጸም ማገድ አይችልም። እርግጥ ነው፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን ሁኔታ የሚፈሩበት ምንም ምክንያት የለም። ለምን? ምክንያቱም ይህ ክንውን ክፋትን ሁሉ ከምድር ላይ ያስወግዳል እንዲሁም “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ማለትም አዲስ የሰማይ መስተዳድርና በምድር ላይ የሚኖር አዲስ ኅብረተሰብ እንዲቋቋም ያደርጋል። በዚህ አዲስ ሥርዓት ውስጥ አምላክ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው [ከሰዎች ዐይን] ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም።”—ራእይ 21:1-4

ታዲያ በአሁኑ ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንደሚል ጊዜ ሰጥቶ መመርመር አስፈላጊ ነው ቢባል አትስማማም? ይህን ለማድረግ የሚያስችልህ እርዳታ ማግኘት ትሻለህ? ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲረዱህ መጠየቅ አሊያም ደግሞ ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ትችላለህ። ያም ሆነ ይህ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ የሚመጣውን ግሩም ሕይወት በማሰብ ኑር።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር ስላለው መጨነቃችሁን ተዉ’