በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በባሕር ላይ የሚመላለሱት “የኪቲም መርከቦች”

በባሕር ላይ የሚመላለሱት “የኪቲም መርከቦች”

በባሕር ላይ የሚመላለሱት “የኪቲም መርከቦች”

በምሥራቃዊ ሜድትራኒያን በርካታ የባሕር ላይ ውጊያዎች ተካሂደዋል። ከክርስቶስ ልደት በፊት አምስት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ የተካሄደን አንድ የባሕር ላይ ውጊያ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ወደተፈለገው አቅጣጫ እንደልብ መንቀሳቀስ የምትችል፣ በሁለቱም ጎኖቿ ሦስት ሦስት ደርብ መቅዘፊያዎች ያሏት ትራይሪም የተባለች አንዲት መርከብ ባለ በሌለ ኃይሏ ወደፊት ትከንፋለች። በሦስቱ ደርብ ውስጥ የሚገኙት 170 የሚያህሉ ቀዛፊዎች ከመቀመጫቸው ጋር በታሰረ የቆዳ ትራስ ላይ ተቀምጠው ወደፊትና ወደኋላ እያሉ በፈርጣማ እጆቻቸው ይቀዝፋሉ።

መርከቧ በሰዓት ከ13-17 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት ባሕሩን እየሰነጠቀች ወደ ጠላት መርከብ መገስገሷን ቀጠለች። የጠላት መርከብም ከታለመባት ጥቃት ለማምለጥ ጥረት ማድረግ ጀመረች። በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከወዲያ ወዲህ የምትዋዥቀው የጠላት መርከብ የጎን ክፍል ለጥቃት ተጋለጠ። በትራይሪሟ ጫፍ ላይ የተተከለው በነሐስ የተለበጠ ማረሻ መሰል ጉጥ ጠንካራ ያልሆነውን የጠላት መርከብ የጎን ክፍል ቀዶ ገባ። ሳንቃዎቹ ሲሰባበሩ የሚሰማው ድምፅና በተቦረቀሰው የመርከቧ አካል የሚንዶለዶለው ውኃ የጠላት መርከብ ቀዛፊዎችን እጅግ አሸበራቸው። ከዚያም በደንብ የታጠቁ ተዋጊዎችን ያቀፈ አንድ አነስተኛ ቡድን በትራይሪሟ መሃከለኛ መተላለፊያ በኩል እየተንደረደሩ ጥቃት ወደጣሉባት መርከብ ገቡ። አዎን፣ አንዳንድ የጥንት መርከቦች በእርግጥም አስደናቂ ነበሩ!

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለ “ኪቲም” እና ስለ ‘ኪቲም መርከቦች’ የተነገሩ ትንቢቶችን ትርጉም ለማወቅ ሲጓጉ ቆይተዋል። (ዘኍልቍ 24:24፤ ዳንኤል 11:30፤ ኢሳይያስ 23:1) በእርግጥ ኪቲም የምትገኘው የት ነበር? ስለ መርከቦቿ ምን የሚታወቅ ነገር አለ? ይህን ማወቅህስ ለምን ይጠቅምሃል?

አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ፣ ኪቲምን “ሂቲሞስ” በማለት የጠራት ሲሆን ከቆጵሮስ ደሴት ጋር አያይዞም ጠቅሷታል። በደሴቲቱ ደቡባዊ ምሥራቅ የምትገኘው ኪቲዮን (ወይም ሲሸም) ኪቲምን ከቆጵሮስ ጋር ከሚያገናኙት ከተሞች መካከል አንዷ ናት። በጥንት የንግድ መስመሮች መተላለፊያ ላይ የምትገኘው ቆጵሮስ ከቅርበቷ አንጻር ሲታይ በምሥራቃዊ ሜድትራኒያን ከሚገኙት ወደቦች ጥቅም ማግኘት ነበረባት። የቆጵሮስ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በአቅራቢያው ያሉ ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች ጦርነት በሚገጥሙበት ጊዜ ከአንዱ ጋር እንድትወግን ያስገድዳታል። በመሆኑም ይህች ደሴት ለሚዋጉት ኃይሎች ጠንካራ አጋር አሊያም ትልቅ እንቅፋት መሆኗ አይቀርም ነበር።

የቆጵሮስ ነዋሪዎችና የሜድትራኒያን ባሕር

በባሕር ውስጥ ቁፋሮዎችና በመቃብሮች ላይ በተደረጉ ምርምሮች የተገኙት አርኪኦሎጂያዊ ማስረጃዎች እንዲሁም የጥንት ጽሑፎችና በሸክላ ዕቃዎች ላይ የተሳሉ ሥዕሎች የቆጵሮስ መርከቦች ምን ይመስሉ እንደነበር ለማወቅ ይረዱናል። የጥንቶቹ የቆጵሮስ ነዋሪዎች በመርከብ ሥራ የተካኑ ነበሩ። ደሴቲቱ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነች ከመሆኗም ሌላ ከወጀብ ለመሸሸግ አመቺ የሆኑት የባሕር ዳርቻዎቿ የተፈጥሮ ወደብ ሆነውላት ነበር። ዛፎቹ መርከብ ለመሥራት ብቻ ሳይሆን ቆጵሮስን በጥንቱ ዓለም ዝነኛ ያደረጋትን የተፈጥሮ ሀብት ማለትም መዳብን ለማቅለጥ ያገለግሉ ነበር።

ቆጵሮስ ምርቶቿን ወደ ውጪው ዓለም በመላክ የምታካሂደው የጦፈ ንግድ የፊንቄያውያንን ትኩረት መሳቡ አልቀረም። ፊንቄያውያን ለንግድ በሚሄዱበት አካባቢ ቅኝ ግዛቶችን የማቋቋም ልማድ የነበራቸው ሲሆን በቆጵሮስ የምትገኘው ኪቲዮን ከእነዚህ መካከል አንዷ ናት።—ኢሳይያስ 23:10-12

ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ ጢሮስ ከወደቀች በኋላ አንዳንድ ነዋሪዎቿ ወደ ኪቲም ተሰደው ነበር። በባሕር ላይ የመጓዝ ልምድ ያዳበሩት ፊንቄያውያን ለቆጵሮስ የባሕር ላይ ቴክኖሎጂ እድገት አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ አልቀሩም። በተጨማሪም ኪቲም ቁልፍ ቦታ ላይ መገኘቷ ለፊንቄያውያን መርከቦች አስተማማኝ ከለላ ሆኖላቸዋል።

ቆጵሮስ በተጧጧፈው ዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ የነበራት ተሳትፎ

በዚህ ወቅት በምሥራቃዊው ሜድትራኒያን ይደረግ የነበረው ጥንታዊ የንግድ እንቅስቃሴ ውስብስብ ነበር። ውድ የሆኑ ቁሳቁሶች በመርከብ ተጭነው ከቆጵሮስ ወደ ቀርጤስ፣ ሰርዲኒያና ሲሲሊ እንዲሁም ኤጂያን ደሴቶች ይወሰዱ ነበር። በእነዚህ አገሮች ከቆጵሮስ የመጡ ማሰሮዎችና የአበባ ማስቀመጫዎች የተገኙ ሲሆን በቆጵሮስ ደግሞ ውብ የሆኑ በርካታ የማሶናውያን (ግሪካውያን) የሸክላ ዕቃዎች ተገኝተዋል። በሰርዲኒያ በተገኙ የመዳብ ጥፍጥፎች ላይ ምርምር ያካሄዱ አንዳንድ ምሑራን ጥፍጥፎቹ ከቆጵሮስ የመጡ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በ1982 በደቡባዊ ቱርክ የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ14ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የሰጠመች አንዲት መርከብ ተገኘች። በመርከቢቷ ላይ በተደረገው አሰሳ በርካታ ውድ ቅርሶች ተገኝተዋል። ከእነዚህም መካከል ከቆጵሮስ እንደመጡ የሚታመኑ የመዳብ ጥፍጥፎች፣ አምበር የሚባል ማዕድን፣ የከነዓናውያን ማሰሮዎች፣ ኢቦኒ የተባለው ጥቁር እንጨት፣ የዝሆን ጥርስ፣ ከወርቅና ከብር የተሠሩ የከነዓናውያን ጌጣጌጦች እንዲሁም በጥንዚዛ መልክ የተሠራ ጌጥን ጨምሮ ሌሎች ከግብጽ የመጡ ቁሳቁሶች ይገኙበታል። በመርከቧ ላይ የተገኙት የሸክላ ዕቃዎች የተሠሩበትን አፈር የመረመሩ አንዳንድ ምሑራን መርከቧን የሠሯት የቆጵሮስ ሰዎች ሳይሆኑ እንደማይቀር ገልጸዋል።

በለዓም ‘በንግሩ’ ላይ ስለ ኪቲም መርከቦች የጠቀሰው ይህች መርከብ እንደሰጠመች በሚገመትበት ወቅት ላይ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዘኍልቍ 24:15, 24) የቆጵሮሳውያን መርከቦች በመካከለኛው ምሥራቅ እጅግ ዝነኞች የነበሩ ይመስላል። እነዚህ መርከቦች ምን ይመስሉ ነበር?

የንግድ መርከቦች

በቆጵሮስ በምትገኘው በጥንታዊቷ የአማተስ ከተማ ባሉ የመቃብር ቤቶች ውስጥ በሸክላ የተሠሩ የመርከብና የጀልባ ሞዴሎች ተገኝተዋል። እነዚህ ሞዴሎች የቆጵሮስ መርከቦች ምን ይመስሉ እንደነበር ጠቃሚ መረጃ የሚሰጡ ሲሆን ከእነዚህም አንዳንዶቹ ሙዚየም ውስጥ ለእይታ ቀርበዋል።

ሞዴሎቹ በጥንት ጊዜ የነበሩት መርከቦች ሰላማዊ ለሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ይውሉ እንደነበር ይጠቁማሉ። አነስተኛ የሆኑት መርከቦች አብዛኛውን ጊዜ 20 ቀዛፊዎች ይኖሯቸዋል። መርከቦቹ ሰፊና ጎድጎድ ያሉ መሆናቸው በቆጵሮስ የባሕር ጠረፍ ላይ በሚደረጉት አጫጭር ጉዞዎች ዕቃዎችንና ሰዎችን ለማጓጓዝ ታስበው የተሠሩ እንደነበር ያመለክታል። ትልቁ ፕሊኒ፣ ቆጵሮሳውያን እስከ 900 ኩንታል መሸከም የሚችሉ አነስተኛና ቀላል ክብደት ያላቸው በመቅዘፊያ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ይሠሩ እንደነበር ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ በቱርክ የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ የተገኘውን የሚመስሉ ትላልቅ የንግድ መርከቦች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እስከ 4,500 ኩንታል የሚደርስ ጭነት ተሸክመው በተንጣለለው ባሕር ላይ ይጓዛሉ። ትላልቆቹ መርከቦች በእያንዳንዱ ረድፍ 25 በጥቅሉ 50 የሚያህሉ ቀዛፊዎች ያሏቸው ሲሆን 30 ሜትር ርዝመትና ከ10 ሜትር የሚበልጥ ቁመት ያለው ቋሚ ምሰሶ ነበራቸው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ የተጠቀሱት “የኪቲም” የጦር መርከቦች

‘መርከቦች ከኪቲም ዳርቻዎች ይመጣሉ፤ አሦርንም ይይዛሉ’ የሚለው ትንቢት የተነገረው በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት ነው። (ዘኍልቍ 24:2, 24) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል? የቆጵሮስ መርከቦችስ በትንቢቱ አፈጻጸም ላይ ምን ድርሻ ነበራቸው? “ከኪቲም ዳርቻዎች ይመጣሉ” የተባሉት መርከቦች በሜድትራኒያን ባሕር ላይ የሚመላለሱት ሰላማዊ የንግድ መርከቦች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሌሎችን ለማጥቃት የተሠሩ የጦር መርከቦች ናቸው።

መርከቦቹ ለጦርነት አመቺ እንዲሆኑ ሲባል በፊት የነበራቸው ንድፍ ተቀይሮ ይበልጥ ፈጣንና ጠንካራ እንዲሆኑ ተደርገው መሠራት ጀመሩ። የጥንቶቹ የቆጵሮሳውያን መርከቦች በአማተስ የተገኘውን የመርከብ ሥዕል ሳይመስሉ አይቀሩም። በሥዕሉ ላይ ከኋላው ወደ ላይ ቆልመም ያለ ከፊንቄያውያን መርከብ ጋር የሚመሳሰል ሽንጣም መርከብ ይታያል። ይህ መርከብ ከፊቱ ወጣ ያለ ማረሻ መሰል ጉጥ ያለው ሲሆን ከወደኋላውና ከወደፊቱ አካባቢ በክብ ቅርጽ የተሠሩ ጋሻ መሰል መከላከያዎች በሁለቱም ጎን ተለጥፈውበታል።

በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የመጀመሪያዎቹ ባይሪም (ሁለት ደርብ መቅዘፊያዎች ያሏቸው) መርከቦች በግሪክ መሠራት ጀመሩ። እነዚህ መርከቦች 24 ሜትር ርዝመትና 3 ሜትር ስፋት ነበራቸው። መርከቦቹ በመጀመሪያ ያገለግሉ የነበረው ተዋጊዎችን ለማጓጓዝ ሲሆን ጦርነቱ የሚደረገው ግን በየብስ ላይ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሦስተኛ ደርብ መጨመሩ ያለውን ጠቀሜታ መገንዘብ የተቻለ ከመሆኑም በላይ ከመርከቡ ፊት በነሐስ የተለበጠ ማረሻ መሰል ጉጥ ተገጠመለት። በዚህ መንገድ የተሠራው አዲስ መርከብ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው ትራይሪም ማለትም ሦስት ደርብ መቅዘፊያዎች ያሉት መርከብ በመባል ይጠራ ጀመር። ግሪኮች የፋርስን የባሕር ኃይል ድል ያደረጉበት የስልማና ጦርነት (በ480 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተካሄደ ነው) እነዚህ መርከቦች ዝነኛ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ከጊዜ በኋላ ታላቁ እስክንድር ሌሎችን የመግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ሲል ተዋጊዎቹን የጫኑትን ትራይሪም መርከቦች ወደ ምሥራቅ አዘመተ። እነዚህ መርከቦች ረጅም የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ሳይሆን ለጦርነት ታስበው የተዘጋጁ ስለነበሩ የዕቃ መጋዘናቸው አነስተኛ ነበር። በመሆኑም ተጓዦቹ ስንቅ ለማሟላትና ለመርከቧ አንዳንድ ጥገናዎችን ለማድረግ በኤጂያን ደሴቶች ላይ መቆማቸው ግድ ነበር። የእስክንድር ዓላማ የፋርስን የጦር መርከቦች መደምሰስ ነበር። ይሁንና ይህን ለማሳካት በቅድሚያ የጢሮስን ደሴት ጠንካራ ምሽግ መደምሰስ ነበረበት። ቆጵሮስ ደግሞ ወደዚያ ለሚደረገው ጉዞ ጊዜያዊ ማረፊያ ሆና ታገለግል ነበር።

የቆጵሮስ ነዋሪዎች ታላቁ እስክንድር ጢሮስን በወረረበት ጊዜ (በ332 ከክርስቶስ ልደት በፊት) 120 የጦር መርከቦችን በመስጠት ከጎኑ ተሰልፈዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሦስት የቆጵሮስ ነገሥታት እስክንድርን በመደገፍ ሰባት ወር በዘለቀው የጢሮስ ከበባ ላይ የጦር መርከቦቻቸውን ይዘው ተሰልፈዋል። በመጨረሻም ጢሮስ ወደቀች፤ በዚህ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ። (ሕዝቅኤል 26:3, 4፤ ዘካርያስ 9:3, 4) እስክንድር ለቆጵሮስ ነገሥታት አመስጋኝነቱን ለመግለጽ ልዩ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል።

አስደናቂ ፍጻሜ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ስትሬቦ የተባለ ታሪክ ጸሐፊ እስክንድር አረቢያን ለመውረር ባካሄደው ዘመቻ ላይ የቆጵሮስና የፊንቄ መርከቦችን እርዳታ ጠይቆ እንደነበር ገልጿል። መርከቦቹ ቀላል ክብደት የነበራቸውና በቀላሉ የሚፈታቱ ስለነበሩ በሰሜናዊ ሶርያ ወደምትገኘው ታፕሲኪስ (ቲፍሳ) በሰባት ቀን ብቻ መድረስ ችለዋል። (1 ነገሥት 4:24) ከዚህ ቦታ ተነስቶ በወንዙ ላይ ወደ ባቢሎን ቁልቁል መጓዝ ቀላል ነበር።

በመሆኑም ለመረዳት አስቸጋሪ የሚመስለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ከአሥር መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ አስደናቂ ፍጻሜ አግኝቷል! በዘኍልቍ 24:24 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ የታላቁ እስክንድር ወታደራዊ ኃይል ከመቄዶንያ ተነስቶ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ምሥራቅ በመገስገስ አሦርን የወረረ ሲሆን በመጨረሻም ታላቁን የሜዶ ፋርስ ግዛት ድል አድርጓል።

ስለ ‘ኪቲም መርከቦች’ ያገኘነው መረጃ ውስን ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በማያሻማ ሁኔታ አስደናቂ ፍጻሜ ማግኘቱን ለመገንዘብ ያስችለናል። እንዲህ ያሉት የታሪክ ማስረጃዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ ያለንን እምነት ይበልጥ ያጠነክሩልናል። ይህን የመሳሰሉት በርካታ ትንቢቶች ከወደፊት ሕይወታችን ጋር የተያያዙ ስለሆኑ በቁም ነገር ልንመለከታቸው ይገባል።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጣሊያን

ሰርዲኒያ

ሲሲሊ

ግሪክ

የኤጂያን ባሕር

ቀርጤስ

ሊቢያ

ቱርክ

ቆጵሮስ

ኪቲዮን

ጢሮስ

ግብጽ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትራይሪም የሚባለው የግሪካውያን የጦር መርከብ ሞዴል

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባይሪም የሚባለው የጥንት ፊንቄያውያን የጦር መርከብ ሞዴል

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቆጵሮሳውያን መርከብ የተሳለበት አበባ ማስቀመጫ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቅርስ ጥበቃ ባለ ሥልጣንና በቆጵሮስ ሙዚየም ፈቃድ የታተመ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢሳይያስ 60:9 ላይ የተጠቀሱት ዓይነት በጥንት ዘመን የነበሩ የጭነት መርከቦች