በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ምሥራቹን ማድረስ

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ምሥራቹን ማድረስ

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ምሥራቹን ማድረስ

የጭነት መኪናችን፣ የጦር መሣሪያ የታጠቁ 60 የሚሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ወዳሉበት አንድ ኬላ ደረሰ። ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ አንዳንዶቹ የወታደር ልብስ ለብሰዋል። ብዙዎቹ አውቶማቲክ መሣሪያዎቻቸውን ወደ እኛ ደግነው ቆመዋል። ሰዎቹ የእኛን መምጣት ሲጠባበቁ የቆዩ ይመስላሉ። በጊዜው የሕዝብ ዓመጽ ተቀስቅሶ ነበር።

አንድ መቶ ኩንታል የሚመዝን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ጭነን ለአራት ቀናት ያህል ስንጓዝ ቆይተናል። ሰዎቹ እንድናልፍ ይፈቅዱልን እንደሆነና እንዳልሆነ እርግጠኞች አልነበርንም። ገንዘብ እንድንሰጣቸው ይጠይቁን ይሆን? ተልእኳችን ሰላማዊ መሆኑን ለማሳመንስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብናል?

ጥይት መተኮስ የሚወድ አንድ ወታደር የቡድኑ መሪ እሱ መሆኑን ለማሳወቅ አከታትሎ ወደ ሰማይ ተኮሰ። ከዚያም ወደ ሞባይል ስልኮቻችን በመጠቆም እንድንሰጠው ጠየቀን። ሞባይሎቹን ላለመስጠት ስናመነታ እንደሚያርደን በእጆቹ ምልክት አሳየን፤ ይህም የጠየቀንን ነገር ካልፈጸምን ምን ሊከሰት እንደሚችል በግልጽ የሚያሳይ ነበር። በመሆኑም ስልኮቹን ሰጠነው።

በዚህ ወቅት፣ የወታደር ልብስ የለበሰች አንዲት ሴት ጠመንጃዋን አንስታ ድንገት ወደ እኛ መጣች። ይህቺ ሴት “ጸሐፊ” ስትሆን እሷም የሆነ ነገር እንድንሰጣት ፈልጋ ነበር። ሕይወታችን አጣብቂኝ ውስጥ ስለገባ ለእሷም ትንሽ “ስጦታ” መስጠት ነበረብን። ከዚያ ደግሞ አንድ ሌላ ወታደር በያዘው ጀሪካን ከመኪናችን ላይ ነዳጅ መቅዳት ጀመረ። ሁኔታውን ለመቃወም ስንሞክር፣ የታዘዘውን እየፈጸመ መሆኑን ገለጸልን። በወቅቱ ማድረግ የምንችለው ነገር አልነበረም። ሌሎቹ እንዲህ ዓይነት ነገር እንደማያደርጉ ተስፋ ነበረን።

በመጨረሻም ኬላው ተከፈተልንና ጉዟችንን ቀጠልን። በዚህ ወቅት እኔና ጓደኛዬ እፎይታ ተሰማን። እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚያስጨንቅ ቢሆንም እነዚያን አስፈሪ ኬላዎች እየለመድናቸው ሄደናል። ከሚያዝያ 2002 እስከ ጥር 2004 ባሉት ጊዜያት በካሜሩን ከሚገኘው የዱዋላ ወደብ፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ እስከሆነችው ባንግዊ 18 ጊዜ ተመላልሰናል። አንድ ሺ ስድስት መቶ ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው በዚህ ጉዞ ሁልጊዜ አደገኛና ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ነበር። a

በዚህ መንገድ ላይ በተደጋጋሚ የሚመላለሱት ዦዜፍና ኢማኑዌል የተባሉ ሾፌሮች እንዲህ በማለት ይገልጻሉ:- “እነዚህ ጉዞዎች ብዙ ነገር አስተምረውናል። ደጋግሞ በልብ መጸለይና መረጋጋት አስፈላጊ ነው። መዝሙራዊው ‘በአምላክ ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል’ በማለት ጽፏል። እኛም ተመሳሳይ አመላካከት ለመያዝ ጥረት እናደርጋለን። ይሖዋ፣ ይህንን ጉዞ የምናደርገው ተስፋ ያዘለ በጣም አስፈላጊ መልእክት ለማድረስ መሆኑን እንደሚረዳልን እርግጠኞች ነን።”—መዝሙር 56:11

መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚደረግ ዓለም አቀፋዊ ጥረት

በዚህ የአፍሪካ ክፍል የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስማት ይፈልጋሉ። የምናጓጉዘው ጽሑፍ ደግሞ የእነዚህን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማርካት ታስቦ የሚዘጋጅ ነው። (ማቴዎስ 5:3፤ 24:14) በዱዋላ፣ ካሜሩን የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በአገሪቱና በሌሎች አራት ጎረቤት አገሮች ለሚኖሩ ከ30,000 የሚበልጡ አስፋፊዎችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ዘወትር ጽሑፎችን ይልካል።

እነዚህ ጽሑፎች ቀድሞውንም ቢሆን ወደ ካሜሩን የሚደርሱት ረጅም ርቀት ተጉዘው ነው። አብዛኞቹ የሚታተሙት በእንግሊዝ፣ በፊንላንድ፣ በጀርመን፣ በጣሊያንና በስፔን ነው። ከዚያም ወደ ፈረንሳይ ከሄዱ በኋላ በመርከብ ይላካሉ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የያዙ ኮንቴይነሮች በየሁለት ሳምንቱ ዱዋላ ወደብ ይደርሳሉ።

ኮንቴይነሮቹ በጭነት መኪና ላይ ተጭነው ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ይወሰዳሉ። በጽሑፍ መላኪያ ክፍል ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞች የየአገሩን ጽሑፎች እየለያዩ ያስቀምጧቸዋል። ጽሑፎቹን በእነዚህ አገሮች ውስጥ ወዳሉት ራቅ ያሉ አካባቢዎች ማድረስ ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ ተግባር ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” የማድረሱ ሂደት አንዱ ክፍል ነው። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) ጽሑፎቹን የሚያጓጉዙልን የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ እንዲህ ያለውን አደገኛ ጉዞ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ወንድሞች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በማዕከላዊ አፍሪካ ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያለማቋረጥ የሚደርሰው በዚህ መንገድ ነው።

ጉዞው ምን ይመስላል?

ጽሑፎች ወደ ቻድ፣ ካሜሩን፣ ጋቦን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እንዲሁም ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ በጭነት መኪኖች ይላካሉ። እስቲ በአንዱ የጭነት መኪና ተሳፍረን ከሾፌሮቹ ጋር አብረን እንጓዝ። ራሳችሁን፣ ከሾፌሮቹ ጋር ሆናችሁ አሥር ወይም ከዚያ የሚበልጡ ቀናት የሚፈጀውን አስቸጋሪ ጉዞ ለማድረግ እንደተዘጋጃችሁ አድርጋችሁ አስቡ።

የጭነት መኪናውን ስድስት ሾፌሮች በየተራ ያሽከረክሩታል። ሾፌሮቹ ጠንካራ፣ ጎበዝ፣ ትዕግሥተኛና ጥሩ አለባበስ ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል። በሚነዱበት ወቅት የአገራቸውን ባሕላዊ ልብስ ይለብሳሉ ወይም ሸሚዝና ከረባት ያደርጋሉ። ከዚህ ቀደም፣ አንድ የጉምሩክ ባለ ሥልጣን የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቶ ነበር:- “በንጽሕና የተያዘ የጭነት መኪናቸውን እንዲሁም የሾፌሮቹን ሥርዓታማ አለባበስና አበጣጠር ተመልከቱ፤ ልክ በጽሑፎቻቸው ላይ ያሉትን ፎቶዎች ይመስላሉ።” ከሾፌሮቹ አለባበስ ይልቅ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ሌሎችን ለማገልገል ሲሉ አስፈላጊ ወደሆነበት ወደ የትኛውም ቦታ ለመሄድ ፈቃደኛ መሆናቸው ነው።—መዝሙር 110:3

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋች በምትሄደውና ትፍግፍግ ባለችው በዱዋላ ከተማ ከሚታየው የትራፊክ መጨናነቅ ለማምለጥ ጉዞውን ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ማለትም ልክ ጎህ ሲቀድ ጀመርን። ቅርንጫፍ ቢሮው አቅራቢያ የሚገኘውን ድልድይ ከተሻገርንና ይህችን ሰውና መኪና የሚበዛባት ከተማ ካለፍን በኋላ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ በማቅናት የመጀመሪያዋ የጉዟችን መድረሻና የካሜሩን ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ያውንዴ ተጓዝን።

ስድስቱም ሾፌሮች አንድ መቶ ኩንታል የሚመዝን መጻሕፍት የጫነ መኪና ማሽከርከር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሊነግሯችሁ ይችላሉ። በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት የተጓዝነው በአስፋልት ላይ ስለነበር ያን ያህል ችግር አልገጠመንም፣ ያም ሆኖ ትኩረትን አሰባስቦ በጥንቃቄ መንዳት አስፈላጊ ነበር። ከዚያም በድንገት ኃይለኛ ዝናብ መዝነብ ጀመረ። ከዚህ በኋላ ያለው መንገድ ኮረኮንች ነው። ውጭውን በደንብ ማየት እየተሳነን የመጣ ከመሆኑም ባሻገር መንገዱ ያዳልጣል፤ ከዚህም በተጨማሪ መንገዱ ወጣ ገባ ስለሆነ በቀስታ መጓዝ አለብን። ጀንበሯ ማዘቅዘቅ ጀምራለች። አሁን መኪናችንን አቁመን ምግብ የምንቀማምስበትና እግራችንን ዳሽ ቦርዱ ላይ ሰቅለን የምንተኛበት ሰዓት ነው። በእነዚህ ጉዞዎች ላይ ሕይወት ይህን ይመስላል!

በማግስቱ ማለዳ ተነስተን ጉዟችንን ቀጠልን። ከሾፌሮቹ መካከል አንዱ የመንገዱን ሁኔታ በጥንቃቄ በመመልከት አሽከርካሪውን ይረዳዋል። መኪናው በመንገዱ ግራና ቀኝ ወዳሉት ቦዮች ሲጠጋ ወዲያውኑ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ሾፌሮቹ፣ አንዴ መኪናው ተንሸራትቶ ቦይ ውስጥ ከገባ ከዚህ ለማውጣት ቀናት ሊወስድ እንደሚችል አሳምረው ያውቃሉ። የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክን ድንበር ብናቋርጥም መንገዶቹ ስንጓዝበት ከነበረው እምብዛም አይለዩም። ቀጣዮቹን 650 ኪሎ ሜትሮች የተጓዝነው ለምለምና ተራራማ የሆኑ የገጠር አካባቢዎችን በማቆራረጥ ነው። በመንገዳችን ላይ ባሉት መንደሮች ውስጥ በዝግታ ስናልፍ ልጆች፣ አረጋውያንና ሕፃናት ያዘሉ እናቶች እጃቸውን ያውለበልቡልን ነበር። በአካባቢው ተቀስቅሶ በነበረው የሕዝብ ዓመጽ የተነሳ በመንገዱ ላይ እምብዛም መኪኖች ስለማይታዩ ሰዎቹ ትኩር ብለው ይመለከቱን ነበር።

አስደሳች ተሞክሮዎች

ከሾፌሮቹ አንዱ የሆነው ዣቪያ ፕሮግራማቸው የተጣበበ ቢሆንም እንኳ ጥቂት እረፍት ለማድረግና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማሰራጨት ትንንሽ መንደሮች ጋር ሲደርሱ ብዙውን ጊዜ እንደሚቆሙ ነገረን። ዣቪያ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ባቡዋ ስንደርስ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ካሳየ ከአንድ የሆስፒታል ሠራተኛ ጋር ለመነጋገር ሁልጊዜ ጥረት እናደርጋለን፤ አጭር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም እንመራለታለን። እንዲያውም አንድ ቀን ስለ ኖኅ ታሪክ የሚያወሳውን የቪዲዮ ፊልም ለእሱና ለቤተሰቡ እያሳየናቸው ሳለ ጓደኞቹና ጎረቤቶቹ የመጡ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ቤቱ ፊልሙን የማየት ጉጉት ባላቸው ተመልካቾች ተሞላ። ሁሉም ስለ ኖኅ ሰምተዋል፤ አሁን ደግሞ ታሪኩን በቪዲዮ መመልከት ቻሉ። አድናቆታቸውን መመልከት ልብ የሚነካ ነበር። ከዚያም፣ አመስጋኝነታቸውን ለመግለጽ አንድ ልዩ ግብዣ ያዘጋጁልን ከመሆኑም ባሻገር እዚያው እንድናድርም ለመኑን። ይሁንና ቶሎ ተሰናብተናቸው ረጅሙን ጉዟችንን መቀጠል ነበረብን። የሆነ ሆኖ ለእነዚህ ትሑት ሰዎች ምሥራቹን ማካፈል በመቻላችን ተደስተናል።”

ኢስራኤል የተባለ ሌላ ሾፌር ደግሞ፣ መዳረሻችን ወደሆነችው ወደ ባንግዊ በሌላ ወቅት ሲጓዙ ያጋጠሟቸውን ሁኔታዎች እንደሚከተለው ሲል አጫወተን:- “ወደ ባንግዊ በተቃረብን መጠን የዚያኑ ያህል ብዙ ኬላዎች አጋጠሙን። እርግጥ አብዛኞቹ ወታደሮች ተግባቢ ከመሆናቸውም ባሻገር በዚያ ስለምንመላለስ የጭነት መኪናውን በደንብ ያውቁታል። ወታደሮቹ አብረናቸው እንድንቀመጥ ጋበዙን፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በደስታ ተቀበሉ። ለሰጠናቸው መጽሐፍ ከፍተኛ ግምት ከመስጠታቸው የተነሳ እላዩ ላይ ስማቸውን፣ መጽሐፉን የተቀበሉበትን ቀን ሌላው ቀርቶ ያበረከተላቸውን ሰው ስም እንኳ ይጽፉበት ነበር። አንዳንዶቹ ወታደሮች ከእኛ ጋር የተግባቡበት ሌላው ምክንያት የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ዘመዶች ያሏቸው መሆኑ ነው።”

መኪና በማሽከርከር ከሁሉም የበለጠ ልምድ ያለው ዦዜፍ ከጉዞው ውስጥ ለእሱ በጣም አስደሳች የሆነው ወቅት ወዳሰቡበት ቦታ ሲደርሱ የሚኖረው ሁኔታ መሆኑን ይገልጻል። ዦዜፍ በአንድ ወቅት ያደረጉትን ጉዞ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ባንግዊ ለመድረስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩን በዚያ ለነበሩ ወንድሞች ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደምንደርስ ደውለን ነገርናቸው። እነሱም በከተማው ውስጥ አብረውን በመዞር ሕግ ነክ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ረዱን። ቅርንጫፍ ቢሮው ስንደርስ በዚያ የነበሩት ሁሉም ወጥተው እያቀፉ ሰላምታ ሰጡን። በአቅራቢያው ባሉት ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞች ሊያግዙን መጡ፣ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጻሕፍትን፣ ቡክሌቶችንና መጽሔቶችን የያዙ በመቶ የሚቆጠሩ ካርቶኖችን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በማውረድ በጽሑፍ ማስቀመጫው መጋዘን ውስጥ ከመሩት።”

አክሎም ዦዜፍ እንዲህ ይላል:- “አንዳንዴ ጭነን ከምናመጣቸው ነገሮች መካከል አጎራባች አገር በሆነችው በዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ለሚገኙ ወንድሞች የተላኩ አልባሳት፣ ጫማዎችና ለልጆች የሚሆኑ ቁሳቁሶች ይገኙበታል። አመስጋኝ በሆኑት ወንድሞች ፊት ላይ የሚነበበውን የደስታ ስሜት ማየት እንዴት ያስደስታል!”

ለአንድ ቀን ያህል እረፍት ካደረግን በኋላ የጭነት መኪናችንን አዘጋጅተን ወደ መጣንበት ለመመለስ ጉዞ እንጀምራለን። አሁንም ከፊታችን ችግሮች ይጠብቁናል፤ ያም ሆኖ የሚያጋጥመን የትኛውም ችግር ካገኘናቸው አስደሳች ተሞክሮዎች ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ረጅም ርቀት መጓዝ፣ ኃይለኛ ዝናብ፣ አስቸጋሪ መንገዶች፣ የጎማ መተንፈስና የመኪና ብልሽት ተስፋ አስቆራጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ሥርዓተ ቢስ ወታደሮችም ሁልጊዜ ያጋጥማሉ። ይሁን እንጂ ለእነዚህ ሾፌሮች፣ በአፍሪካ ለሚገኙ ገለልተኛ አካባቢዎች ምሥራቹን ከማዳረስና ይህ ምሥራች በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያመጣውን ለውጥ ከመመልከት የበለጠ እርካታ የሚሰጣቸው ነገር የለም።

ለምሳሌ ያህል፣ እነዚህ ሾፌሮች ባደረጉት ጥረት በሱዳን ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ገለልተኛ መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው በአሁን ወቅት በቅርቡ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማንበብ ችሏል። ባለቤቱ በቅርብ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን የምታጠና ሲሆን ልጆቹ ደግሞ ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ b (በአማርኛ አልተተረጎመም) ከሚለው መጽሐፍ ጥቅም ማግኘት ችለዋል። በትልልቅ ከተሞች እንደሚኖሩት ክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው፣ ይህ ቤተሰብም ሆነ በእነዚህ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሌሎች ሰዎች መንፈሳዊ ምግብ እያገኙ ነው። ይህ በእርግጥም ከፍተኛ ደስታ ያስገኛል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከዱዋላ እስከ ባንግዊ ባለው መንገድ ላይ የሚመላለሱ መንገደኞችን ደህንነት ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ካሜሩን

ዱዋላ

የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ

ባንግዊ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዦዜፍ

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢማኑዌል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በባንግዊ የሚገኘው የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ቅርንጫፍ ቢሮ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባንግዊ፣ ጽሑፍ ከመኪና ላይ ሲወርድ