‘ከበጉ ጋር ድል መንሳቱ’ እጅግ አስደስቶናል
‘ከበጉ ጋር ድል መንሳቱ’ እጅግ አስደስቶናል
ወንድም ኬሪ ባርበር በ1971 በጻፈው ደብዳቤ ላይ እውነተኛውን አምላክ በማገልገል ስላሳለፋቸው የመጀመሪያዎቹ 50 ዓመታት ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኳቸው 50 ዓመታት እጅግ አስደሳች ነበሩ። ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መሰብሰቤ፣ በሰይጣን ዓለም ከሚገኙ ክፉ አድራጊዎች ጥቃት ጥበቃ ማግኘቴ፣ ከበጉ ማለትም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ድል የመንሳት ተስፋ ማግኘቴና ይሖዋ ለእኔ ያለውን ፍቅር በግልጽ መመልከቴ ግሩም የሆነ ሰላምና ውስጣዊ እርካታ አስገኝቶልኛል። ይህ ደግሞ ልቤን ጠብቆልኛል እንዲሁም የመጨረሻውን ድል ስለመቀዳጀቴ አስተማማኝ ተስፋ እንዲኖረኝ አስችሎኛል።”
ቅቡዕ ክርስቲያን የሆነው ወንድም ባርበር ይህን ከጻፈ ከስድስት ዓመታት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በዚህ ቦታ ባገለገለባቸው 30 ዓመታት በሙሉ ‘ከበጉ ጋር ድል የሚነሳበትን’ ጊዜ በጉጉት ሲጠባበቅ ቆይቷል። ወንድም ባርበር እሁድ ሚያዝያ 8, 2007 በ101 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት በመጽናት ከበጉ ጋር ድል ነስቷል።—1 ቆሮንቶስ 15:57
በ1905 እንግሊዝ ውስጥ የተወለደው ወንድም ኬሪ ባርበር በ1921 በዊኒፔግ፣ ካናዳ ተጠመቀ። ከሁለት ዓመት በኋላ እሱና ኖርማን የተባለው መንትያ ወንድሙ በአንድ አዲስ ፕሮጀክት ላይ ለመካፈል ወደ ብሩክሊን ኒው ዮርክ አመሩ። በወቅቱ፣ የይሖዋ ሕዝቦች የመንግሥቱን ምሥራች “በዓለም ሁሉ” ለማዳረስ የሚያስችሏቸውን መጻሕፍት ለማተም እየተዘጋጁ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ወንድም ባርበር በመጀመሪያ ከተሰጡት የሥራ ምድቦች ውስጥ አንዱ አነስተኛ ጽሑፎችን ማተም ነበር። ከሚታተሙት ጽሑፎች መካከል በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚታዩ ሕጋዊ ጉዳዮችን የሚያብራሩ ሕግ ነክ ሰነዶች ይገኙበታል። ከጊዜ በኋላ ወንድም ባርበር የጉባኤ ጉዳዮችንና የአገሪቱን የስብከት እንቅስቃሴ በሚከታተለው የአገልግሎት ክፍል ውስጥ መሥራት ጀመረ።
ወንድም ባርበር ያካበተው ልምድ በ1948 በምዕራባዊ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ የሚደረጉ ትልልቅ ስብሰባዎችንና ጉባኤዎችን እንዲጎበኝ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ብቁ እንዲሆን አስችሎታል። ወንድም ባርበር በተለይ በመስክ አገልግሎት መካፈል እንደሚያስደስተው ይናገር ነበር። ይህ የአገልግሎት ምድቡ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከወንድም ባርበር ጋር እንዲተዋወቁ አስችሏቸዋል። ፈጣን የማሰብ ችሎታውና ለአገልግሎት የነበረው ቅንዓት ቆየት ብሎ በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 26ኛ ክፍል ሲማር እጅግ ጠቅሞታል። ወንድም ባርበር በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ በነበረበት ጊዜ ከካናዳ ከመጣች ሲድኒ ብሪወር የተባለች ተማሪ ጋር ተዋወቀ። ከጊልያድ ሲመረቁ ተጋቡና አጭር የጫጉላ ሽርሽር አደረጉ። ከዚያም በኢሊኖይ፣ ቺካጎ አካባቢ የሚገኙ ጉባኤዎችን ማገልገል ጀመሩ። እህት ሲድኒ በጉብኝት ሥራ ላይ ከወንድም ባርበር ጋር ባሳለፈቻቸው ሃያ ዓመታት ለባለቤቷ ጥሩ አጋርና የብርታት ምንጭ ሆናለታለች።
ወንድም ባርበር በአውራጃ ወይም በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ባገለገለባቸው አሊያም የበላይ አካሉ አባል ሆኖ በሠራባቸውና ወንድሞችን በጎበኘባቸው 30 ዓመታት፣ እሱን የማወቅ አጋጣሚ ያገኙ ሁሉ ንግግሮቹንና የሚሰጣቸውን ሕያው የሆኑ ሐሳቦች መቼም አይረሷቸውም። በእርግጥም ወንድም ባርበር ‘ከበጉ ጋር ድል በመንሳቱ’ የምንደሰትበት በቂ ምክንያት አለን።