በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ መብራቱ ተጓዝ

ወደ መብራቱ ተጓዝ

ወደ መብራቱ ተጓዝ

የወደብ መብራቶች የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ታድገዋል። ይሁን እንጂ በድካም ለዛለ አንድ ተጓዥ ከሩቅ የሚያየው መብራት አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ አለቶች መኖራቸውን ከማስጠንቀቅ ያለፈ ትርጉም አለው። ይህ መብራት ተጓዡ ለመድረስ ወዳሰበበት ቦታ መቃረቡን ያበስረዋል። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ጨለማ በዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚያደርጉትን ረጅም ጉዞ ወደ ማጠናቀቁ ተቃርበዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የራቀውን የሰው ዘር በጥቅሉ ‘ማዕበሉ ጭቃና ጉድፍ ከሚያወጣ እንዲሁም ጸጥ ማለት ከማይችል የሚናወጥ ባሕር’ ጋር ያመሳስለዋል። (ኢሳይያስ 57:20) የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩበት አካባቢም እንዲህ በመሰለ ሁኔታ የተሞላ ነው። ያም ሆኖ ብሩህ የሆነ የመዳን ተስፋ ያላቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ለእነሱ በምሳሌያዊ ሁኔታ አስተማማኝ መብራታቸው ነው። (ሚክያስ 7:8) በይሖዋና በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት “ብርሃን ለጻድቃን” ወጥቷል፤ “ሐሤትም ልባቸው ለቀና።”—መዝሙር 97:11 a

ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች ትኩረትን በሚከፋፍሉ ነገሮች ተታልለው ይሖዋ ከሚሰጠው ብርሃን ርቀዋል። በዚህም የተነሳ የእምነት መርከባቸው፣ እጅግ አደገኛ በሆኑ አለቶች ሊመሰሉ በሚችሉ እንደ ፍቅረ ንዋይ፣ የጾታ ብልግና አልፎ ተርፎም ክህደት ባሉ ነገሮች የመሰበር አደጋ ደርሶበታል። አዎን፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም የአንዳንዶች ‘የእምነት መርከብ ተሰብሯል።’ (1 ጢሞቴዎስ 1:19 NW፤ 2 ጴጥሮስ 2:13-15, 20-22) አዲሱ ዓለም ልንደርስበት ባሰብነው ማረፊያ ወደብ ሊመሰል ይችላል። ወደዚህ ምሳሌያዊ ወደብ በጣም እየተቃረብን ባለንበት በአሁኑ ጊዜ አንድ ሰው የይሖዋን ሞገስ ቢያጣ እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል!

‘የእምነት መርከባችሁ እንዳይሰበር’ ተጠንቀቁ

ባለፉት መቶ ዘመናት እንደታየው አንድ መርከብ በተንጣለለ ባሕር ላይ በሰላም ሊጓዝ ቢችልም ወደ ወደብ ሲቃረብ እንክትክቱ ሊወጣ ይችላል። ብዙውን ጊዜ የመርከብ ጉዞ በጣም አደገኛ የሚሆነው መርከቡ ወደ የብስ ሲቃረብ ነው። በተመሳሳይም ለብዙዎች፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጣም አደገኛ የሆነው ጊዜ የዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ወቅት፣ በተለይም ራሳቸውን ለወሰኑ ክርስቲያኖች “የሚያስጨንቅ ጊዜ” እንደሚሆን በትክክል ይገልጻል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

የመጨረሻዎቹ ቀናት ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆኑት ለምንድን ነው? ሰይጣን ከአምላክ ሕዝቦች ጋር የሚያደርገው ውጊያ ሊጠናቀቅ “ጥቂት ዘመን ብቻ” እንደቀረው ያውቃል። በዚህም የተነሳ የአምላክ ሕዝቦችን እምነት ለማጥፋት የሚያደርገውን የተንኮል ዘመቻ አጧጡፎታል። (ራእይ 12:12, 17) ይህ ሲባል ግን እርዳታም ሆነ መመሪያ የሚሰጠን አካል የለም ማለት አይደለም። ይሖዋ ምክሩን ለሚሰሙ ሰዎች ምንጊዜም መጠጊያ ነው። (2 ሳሙኤል 22:31) በመሆኑም የሰይጣንን መሠሪ የተንኮል ዘዴዎች የሚያጋልጡ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። እስቲ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱን እንመልከት። ታሪኮቹ የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በተቃረበበት ወቅት የተፈጸሙ ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 10:11፤ 2 ቆሮንቶስ 2:11

በተስፋይቱ ምድር አቅራቢያ

የእስራኤል ሕዝብ በሙሴ መሪነት ከግብጽ ነፃ መውጣት ችሎ ነበር። ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ወደ ተስፋይቱ ምድር ደቡባዊ ድንበር ተቃረቡ። ከዚያም ሙሴ ምድሪቱን እንዲሰልሉ 12 ሰዎችን ላከ። አሥሩ እምነት የለሽ ሰላዮች፣ በዚያ ያዩአቸው ሰዎች ‘ግዙፎችና’ በጦርነት ብርቱዎች ስለሆኑ እስራኤላውያን ከነዓናውያንን እንደማያሸንፏቸው የሚገልጽ ተስፋ አስቆራጭ ሪፖርት ይዘው ተመለሱ። ይህ ሪፖርት በእስራኤላውያን ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ? ታሪኩ “እግዚአብሔር ወደዚች ምድር የሚያመጣን ለምንድነው? በሰይፍ እንድንወድቅ ነውን? ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ . . . አለቃ መርጠን ወደ ግብፅ እንመለስ” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ ማጉረምረም እንደጀመሩ ይገልጽልናል።—ዘኍልቍ 13:1, 2, 28-32፤ 14:1-4

እስቲ አስበው፤ እነዚህ እስራኤላውያን፣ ይሖዋ በወቅቱ የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረችውን ታላቋን ግብጽ በአሥር መቅሠፍቶች በመምታት ሲያንበረክካት እንዲሁም በቀይ ባሕር አስደናቂ ተዓምር ሲፈጸም ተመልክተዋል። ተስፋይቱ ምድር ደግሞ ከፊት ለፊት ትታያቸው ነበር። አንድ መርከብ መድረሻውን ወደሚጠቁመው መብራት እንደሚጓዝ ሁሉ እነሱም ወደ ተስፋይቱ ምድር መጓዝ ነበረባቸው። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ እዚህ ግቡ የማይባሉ የተከፋፈሉ አነስተኛ መንግሥታት ያሉባትን ከነዓንን ማጥፋት እንደማይችል ሆኖ ተሰማቸው። ይህ ዓይነቱ እምነት የለሽ አካሄድ አምላክንም ሆነ ከነዓን “[ለእስራኤል] እንደ እንጀራ” እንደሆነች የተሰማቸውን ሁለቱን ደፋር ሰላዮች ማለትም ኢያሱንና ካሌብን ምንኛ አሳዝኗቸው ይሆን! እነዚህ ሁለት ሰዎች መላዋን ከነዓንን ተመልክተው ስለነበር ስለ ሁኔታው የተሟላ መረጃ ነበራቸው። ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ባለመግባቱ ኢያሱና ካሌብም ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በምድረ በዳ መቆየት ግድ ሆኖባቸዋል፤ ይሁንና ከእምነት የለሾቹ ጋር በምድረ በዳ አልሞቱም። እንዲያውም ኢያሱና ካሌብ ቀጣዩን ትውልድ ከምድረ በዳ ወጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ በመምራት እርዳታ አበርክተዋል። (ዘኍልቍ 14:9, 30) እስራኤላውያን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በተቃረቡበት ወቅት አንድ ሌላ ፈተና ገጠማቸው። ታዲያ ይህን ፈተና ያልፉት ይሆን?

ባላቅ የተባለ የሞዓብ ንጉሥ የሐሰት ነቢይ የሆነው በለዓም እስራኤልን እንዲረግምለት ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ይሁንና ይሖዋ፣ በለዓም እስራኤልን በመርገም ፈንታ እንዲባርክ በማድረግ የባላቅን እቅድ አከሸፈበት። (ዘኍልቍ 22:1-7፤ 24:10) በለዓም የመጀመሪያ ሙከራው በመክሸፉ ተስፋ ሳይቆርጥ የአምላክ ሕዝቦች ምድሪቱን እንዳይወርሱ ለማድረግ ሌላ ተንኮል ሸረበ። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? የጾታ ብልግና እንዲፈጽሙና በበኣል አምልኮ እንዲካፈሉ በማድረግ እስራኤላውያንን አሳታቸው። በጥቅሉ ሲታይ ይህ ዘዴውም ያልተሳካለት ቢሆንም ለ24,000 እስራኤላውያን ሞት ምክንያት ሆኗል። እስራኤላውያን ከሞዓብ ሴቶች ጋር ከማመንዘራቸውም ባሻገር ብዔልፌጎርን በማምለክ ተባብረዋል።—ዘኍልቍ 25:1-9

እስቲ ይታይህ፤ ከእነዚህ እስራኤላውያን መካከል አብዛኞቹ ይሖዋ ያንን ‘ጭልጥ ያለና የሚያስፈራ ምድረ በዳ’ በሰላም እንዳሳለፋቸው ተመልክተዋል። (ዘዳግም 1:19) ያም ሆኖ ውርሻቸውን ሊያገኙ በተቃረቡበት ወቅት 24,000 የአምላክ አገልጋዮች ለሥጋዊ ፍላጎታቸው በመሸነፋቸው በይሖዋ እጅ ጠፍተዋል። በዛሬው ጊዜ ከፍተኛ ብልጫ ያለውን ውርሻ ለመቀበል ደፍ ላይ ለደረሱት የአምላክ ሕዝቦች ይህ እንዴት ያለ ማስጠንቀቂያ ነው!

ሰይጣን፣ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮችን ሽልማታቸውን ለማሳጣት በሚያደርገው የመጨረሻ ሙከራ አዳዲስ ዘዴዎችን መፍጠር አያስፈልገውም። እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በተቃረቡበት ወቅት ከተከሰተው ሁኔታ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ሰይጣን ብዙውን ጊዜ ማስፈራሪያን፣ ስደትን አሊያም ፌዝን ተጠቅሞ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ፍርሃትና ጥርጣሬ ለመዝራት ይሞክራል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ፈተናዎች እጃቸውን ሰጥተዋል። (ማቴዎስ 13:20, 21) ሰይጣን የሚጠቀምበት ሌላው ውጤታማ የሆነ መሠሪ ዘዴ ደግሞ የሰዎችን የሥነ ምግባር አቋም ማበላሸት ነው። ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሰርገው የገቡ አንዳንዶች በመንፈሳዊ የደከሙና ከአምላክ በሚገኘው ብርሃን ተማምነው የማይመላለሱ ግለሰቦችን አቋም ለማበላሸት ሙከራ አድርገዋል።—ይሁዳ 8, 12-16

በመንፈሳዊ ጎልማሳና ንቁ ለሆኑ ግለሰቦች የዓለም የሥነ ምግባር መሥፈርት እያሽቆለቆለ መምጣቱ የሰይጣንን ተስፋ መቁረጥ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው። አዎን፣ ሰይጣን ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ላይ ጥቃት መሰንዘር እንደማይችል ያውቃል። በመሆኑም በሰይጣን ዘዴዎች እንዳንታለል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በመንፈሳዊ ንቁዎች ሆነን መኖር ያለብን አሁን መሆኑ ግልጽ ነው።

በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖር የሚረዱን ነገሮች

ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል ክርስቲያኖች የመለኮታዊውን ዓላማ አፈጻጸም እንዲያስተውሉ ስለሚረዳቸው ‘በጨለማ ሥፍራ እንደሚበራ መብራት’ አድርጎ ገልጾታል። (2 ጴጥሮስ 1:19-21) ለአምላክ ቃል ያላቸውን ፍቅር እያሳደጉ ለሚሄዱና በቃሉ መመራታቸውን ለሚቀጥሉ ሰዎች ይሖዋ ጎዳናቸውን ቀና ያደርግላቸዋል። (ምሳሌ 3:5, 6) ልባቸው በተስፋ የተሞላው እነዚህ አመስጋኝ ሰዎች ‘ከልባቸው ደስታ የተነሳ ሲዘምሩ’ ይሖዋን የማያውቁ አሊያም በመንገዱ መመላለሳቸውን የተዉ ሰዎች ደግሞ ውሎ አድሮ ‘ልባቸው ማዘኑ’ እና ‘መንፈሳቸው መሰበሩ’ አይቀርም። (ኢሳይያስ 65:13, 14) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናትና የተማርነውን ተግባራዊ በማድረግ ዓይናችን በዚህ ሥርዓት ውስጥ በሚገኘው ጊዜያዊ ደስታ ላይ ሳይሆን አስተማማኝ በሆነው ተስፋችን ላይ እንዲያተኩር እናድርግ።

በተጨማሪም ጸሎት በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖር በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ስለዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ሲናገር “ከሚመጣው ሁሉ እንድታመልጡና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ተግታችሁ ጸልዩ [“ምልጃ አቅርቡ፣” NW]” ብሏል። (ሉቃስ 21:34-36) እዚህ ላይ ኢየሱስ “ምልጃ አቅርቡ” ማለቱን ልብ በል፤ ይህ ቃል ልባዊ ጸሎት ማቅረብን የሚያመለክት ነው። ኢየሱስ በዚህ አስጨናቂ ጊዜ የዘላለም ሕይወት ተስፋችን አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ያውቃል። ታዲያ የምታቀርባቸው ጸሎቶች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነህ ለመኖር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለህ የሚያንጸባርቁ ናቸው?

ውርሻችንን ለማግኘት በምናደርገው ጉዞ በጣም አደገኛ የሆነው ወቅት በጉዞው መጨረሻ አካባቢ ያለው መሆኑን አንርሳ። በመሆኑም በሕይወት እንድንተርፍ ወደሚያስችለን አቅጣጫ የሚመራን ብርሃን ከእይታችን እንዳይሰወር መጣራችን እጅግ አስፈላጊ ነው።

ከአሳሳች መብራቶች ተጠንቀቅ

መርከቦች በነፋስ ኃይል ይንቀሳቀሱ በነበሩባቸው ዘመናት፣ ጨረቃ የማትወጣበትንና መርከበኞቹ የባሕሩን ዳርቻ ለማየት የሚቸገሩበትን ጊዜ የሚጠባበቁ አንዳንድ ክፉ ሰዎች በመርከቦቹ ላይ አደጋ ይጥሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች የመርከቡ ካፒቴን አቅጣጫውን እንዲቀይር ለማታለል ሲሉ አደገኛ በሆነው የባሕሩ ዳርቻ አካባቢ መብራቶችን ያስቀምጣሉ። በእነዚህ አሳሳች መብራቶች ተታልለው ወደዚያ አቅጣጫ የሚያመሩ መርከበኞች መርከባቸው ከአለት ጋር ሊጋጭ፣ የጫኑት ንብረት ሊዘረፍ አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።

በተመሳሳይም፣ አሳሳች “የብርሃን መልአክ” የሆነው ሰይጣን የይሖዋ ሕዝቦች ከአምላክ ጋር የመሠረቱትን ዝምድና ለመንጠቅ ወይም ለማበላሸት ይፈልጋል። ዲያብሎስ ጠንቃቃ ያልሆኑ ሰዎችን ለማሳት ‘የሐሰት ሐዋርያትንና የጽድቅ አገልጋዮች የሚመስሉ’ ከሃዲዎችን ይጠቀም ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 11:13-15) ይሁን እንጂ ንቁ የሆነና ተሞክሮ ያካበተ የመርከብ ካፒቴን እንዲሁም አብረውት ያሉት መርከበኞች በአሳሳች መብራቶች በቀላሉ እንደማይታለሉ ሁሉ ‘መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ያስለመዱ’ ክርስቲያኖችም የሐሰት ትምህርቶችንና ጎጂ ፍልስፍናዎችን በሚያስፋፉ ሰዎች አይታለሉም።—ዕብራውያን 5:14፤ ራእይ 2:2

መርከበኞች በጉዟቸው ላይ የሚያጋጥሟቸው የወደብ መብራቶች የት ቦታ ላይ እንደሚገኙ የሚገልጽ ዝርዝር ይይዛሉ። ይህ ዝርዝር የእያንዳንዱን የወደብ መብራት ልዩ ምልክት ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታውን የሚገልጽ መረጃ ይይዛል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚከተለው ሲል ይገልጻል:- “መርከበኞች የወደብ መብራቱን ምልክት በማየትና ምልክቱን ስለ እነዚህ መብራቶች ከሰፈረው ዝርዝር መግለጫ ጋር በማስተያየት ያዩት የወደብ መብራት የትኛው እንደሆነና የት አካባቢ እንዳሉ ለይተው ማወቅ ይችላሉ።” በተመሳሳይም የአምላክ ቃል፣ ልበ ቅን ሰዎች እውነተኛውን አምልኮና ተከታዮቹን ለይተው እንዲያውቁ ይረዳቸዋል። በተለይም ደግሞ ይሖዋ እውነተኛው ሃይማኖት ከሐሰተኛው ከፍ ብሎ እንዲታይ ባደረገበት በዚህ የመጨረሻ ቀን ይህ እውነት መሆኑ በግልጽ ይታያል። (ኢሳይያስ 2:2, 3፤ ሚልክያስ 3:18) ኢሳይያስ 60:2, 3 በእውነተኛና በሐሰተኛ አምልኮ መካከል ያለውን ልዩነት ሕያው በሆነ መንገድ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም ሕዝቦችን ይሸፍናል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ወጥቶልሻል፤ ክብሩንም ይገልጥልሻል። ሕዝቦች ወደ ብርሃንሽ፣ ነገሥታትም ወደ ንጋትሽ ጸዳል ይመጣሉ።”

ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በይሖዋ ብርሃን መመራታቸውን እስከቀጠሉ ድረስ ጉዟቸው ሊጠናቀቅ በተቃረበበት በዚህ ወቅት የእምነት መርከብ መሰበር አደጋ አይገጥማቸውም። እንዲያውም ይህ ሥርዓት እስከሚጠፋ ድረስ ባለው ቀሪ ጊዜና በሚመጣው ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ያለ ስጋት መጓዛቸውን ይቀጥላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a መጽሐፍ ቅዱስ “ብርሃን” የሚለውን ቃል በተለያዩ ምሳሌያዊ መንገዶች ይጠቀምበታል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን ከብርሃን ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። (መዝሙር 104:1, 2፤ 1 ዮሐንስ 1:5) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መንፈሳዊ እውቀት በብርሃን ተመስሏል። (ኢሳይያስ 2:3-5፤ 2 ቆሮንቶስ 4:6) ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ብርሃን ነበር። (ዮሐንስ 8:12፤ 9:5፤ 12:35) እንዲሁም የኢየሱስ ተከታዮች ብርሃናቸውን እንዲያበሩ ታዘዋል።—ማቴዎስ 5:14, 16

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ እንደ መርከበኞች ክርስቲያኖችም በአሳሳች መብራቶች እንዳይታለሉ ይጠነቀቃሉ