በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምትኖረው ለዛሬ ብቻ ነው?

የምትኖረው ለዛሬ ብቻ ነው?

የምትኖረው ለዛሬ ብቻ ነው?

“ስለ ወደፊቱ ጊዜ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። ነገ በራሱ ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።” ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱት እነዚህ ቃላት ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን የተናገራቸው ናቸው። በርካታ ሰዎችም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ስሜት አላቸው። እነዚህ ሰዎች “ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጨነቅ ለምን አስፈለገ?” ይሉ ይሆናል። ወይም ደግሞ “ዝም ብለህ ሕይወትህን ምራ”፣ “ዛሬን ኑር”፣ “ለነገ አትጨነቅ” እንደሚሉት ያሉ አባባሎችን ሰምተህ ይሆናል።

እርግጥ ነው፣ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ዛሬ የተጀመረ አይደለም። በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩት ኤፊቆሮሳውያን “ብላ፣ ጠጣ፣ ተደሰት። ሌላው ሁሉ ከንቱ ነው” የሚል መርሕ ነበራቸው። በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎችም “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል ተመሳሳይ አመለካከት ነበራቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:32) እነዚህ ሰዎች አሁን ከምንኖራት አጭር ሕይወት በቀር ሌላ ሕይወት ሊኖረን እንደማይችል ሆኖ ይሰማቸዋል፤ በመሆኑም የቻልነውን ያህል በሕይወታችን መጠቀም አለብን የሚል ሐሳብ ያስፋፉ ነበር።

ይሁንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምድር ነዋሪዎች የቻሉትን ያህል በሕይወታቸው ለመጠቀም ይጣጣራሉ ሲባል ደስታን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመራሉ ማለት አይደለም። ብዙዎች ያሉበት አስከፊ ሁኔታ ሕይወታቸው አድካሚ በሆነ እሽክርክሪትና ለመኖር በሚደረግ መራራ ትግል እንዲሞላ አድርጎታል። ታዲያ ጭጋግ ያጠላበትና የተስፋ ጭላንጭል የሌለበት ስለሚመስለው የወደፊቱ ጊዜ ማለትም “ስለ ነገ” የሚጨነቁበት ምን ምክንያት አለ?

ለነገ እቅድ ማውጣት ይኖርብን ይሆን?

ብዙውን ጊዜ፣ በተደላደለ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ለነገ እቅድ ማውጣት ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች “ምን አስጨነቀኝ?” በማለት ይጠይቁ ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ ከዚህ ቀደም እቅድ አውጥተው የነበሩ ሰዎች ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆኑላቸው እንደቀሩ ብሎም ለሐዘን እንደተዳረጉ ማየታቸውን ይገልጻሉ። ሌላው ቀርቶ በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው የእምነት አባት ኢዮብ፣ ለእሱም ሆነ ለቤተሰቡ ደስታ ያስገኛል ብሎ ተስፋ ያደረገው እቅድ ‘በመክሸፉ’ ከባድ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰምቶታል።—ኢዮብ 17:11፤ መክብብ 9:11

ስኮትላንዳዊው ገጣሚ ሮበርት በርንስ ያለንበትን አስጨናቂ ሁኔታ፣ ጎሬዋ በማረሻ ከተማሰባት አይጠ መጎጥ ጋር አመሳስሎታል። አይጠ መጎጧ መኖሪያዋ ድርምስምሱ ሲወጣ ስትመለከት ሕይወቷን ለማትረፍ እግሬ አውጪኝ አለች። ከዚያም ገጣሚው እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቷል:- ‘አዎን፣ እኛም ከቁጥጥራችን ውጪ የሆኑ ነገሮች በጥንቃቄ የነደፍነውን እቅድ እንኳ ከንቱ አድርገው እንዳስቀሩብን ስንመለከት ብዙውን ጊዜ አቅመ ቢስ እንደሆንን ይሰማናል።’

ታዲያ ይህ ሲባል ‘ስለ ወደፊቱ ጊዜ እቅድ ማውጣት ከንቱ ልፋት ነው’ ማለት ነው? ኃይለኛ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ ወይም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች በደረሱ ጊዜ የተከሰተው ሁኔታ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተሟላ እቅድ አለማውጣት አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አሳይቷል። ካትሪና የተባለውን ኃይለኛ ዝናብ የቀላቀለ ከባድ አውሎ ነፋስ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ማንኛውም ሰው ይህን የተፈጥሮ አደጋ ሊያስቆመው አይችልም ነበር። ይሁንና የወደፊቱን ጊዜ አርቆ በመመልከትና እቅድ በማውጣት በከተማዋም ሆነ በነዋሪዎቿ ላይ የደረሰውን ጉዳት መቀነስ አይቻልም ነበር?

አንተስ ምን ትላለህ? ለዛሬ ብቻ መኖርና የወደፊቱን አለማሰብ ምክንያታዊ ሆኖ ይታይሃል? የሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ተመልከት።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ብላ፣ ጠጣ፣ ተደሰት። ሌላው ሁሉ ከንቱ ነው”

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አርቆ በማየትና እቅድ በማውጣት ካትሪና ያደረሰውን ጉዳት መቀነስ አይቻልም ነበር?

[ምንጭ]

U.S. Coast Guard Digital