በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ እምነትህ ለመናገር የምታገኛቸውን አጋጣሚዎች ትጠቀማለህ?

ስለ እምነትህ ለመናገር የምታገኛቸውን አጋጣሚዎች ትጠቀማለህ?

ስለ እምነትህ ለመናገር የምታገኛቸውን አጋጣሚዎች ትጠቀማለህ?

“ፍጹም እውነት አለ?” በሚል ርዕስ በፖላንድ ብሔራዊ የሥነ ጽሑፍ ውድድር ተደርጎ ነበር። የሥነ ጽሑፉን ውድድር በተመለከተ እንዲህ የሚል መመሪያ ተሰጥቶ ነበር:- “ፍጹም እውነት አያስፈልገንም። ማንም ሰው ይህ እውነት አያስፈልገውም። ፍጹም እውነት የሚባል ነገር የለም።” የይሖዋ ምሥክርና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆነችው የ15 ዓመቷ አጋታ በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ሃይማኖታዊ እምነቷን ለሌሎች ለማካፈል ወሰነች።

አጋታ ጽሑፏን ከማዘጋጀቷ በፊት ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጣት የጸለየች ሲሆን ይህን ርዕስ አስመልክቶ የተዘጋጁ ጽሑፎችንም ማሰባሰብ ጀመረች። ከዚህ ርዕስ ጋር ተዛማጅነት ያለው ሐሳብ በሐምሌ 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ አገኘች። በጽሑፏ ላይ ጳንጢዮስ ጲላጦስ “እውነት ምንድን ነው?” በማለት ለኢየሱስ ያቀረበለትን ጥያቄ ጠቀሰች። (ዮሐንስ 18:38) ይህ ጥያቄ ‘እውነት? እውነት ደግሞ ምንድን ነው? እንዲህ ብሎ ነገር የለም!’ የሚል አንድምታ ያለው የምጸት ጥያቄ እንደነበር አጋታ ገልጻለች። አክላም “የጲላጦስ ጥያቄ የሥነ ጽሑፉን መመሪያ አስታወሰኝ” ብላለች።

አጋታ በመቀጠልም እውነት አንጻራዊ እንደሆነ የሚገልጽ አመለካከት ተሰሚነት እያገኘ እንደመጣ አብራርታለች፤ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ለአንድ ሰው እውነት የሆነው ነገር ለሌላው እውነት ላይሆን እንደሚችል እንዲሁም ሁለቱም ሐሳቦች “ትክክል” ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻል። በመቀጠልም “የኤሮዳይናሚክስ (ነገሮች በአየር ላይ ስለሚንሳፈፉበት መንገድ የሚደረግ ጥናት) ሕግጋት እውነት መሆናቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ባንሆን ኖሮ ማንኛችን ነን በአውሮፕላን ለመጓዝ የምንደፍረው?” የሚል ጥያቄ አቅርባለች። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን እያሳየች “በአምላክ ቃል የምንታመነው ትክክለኛነታቸው ሊረጋገጥ በሚችል እውነታዎች ላይ ተመሥርተን ነው” በማለት ተናግራለች። አክላም ፍጹም የሆነውን እውነት በቅንነት የሚፈልጉ ሰዎች ትዕግሥት ካላቸው ሊያገኙት እንደሚችሉ ገልጻለች።

አጋታ ልዩ የሆነ የምሥክር ወረቀት የተሰጣት ከመሆኑም በላይ ድርሰቷን በክፍሏ ተማሪዎች ፊት የማቅረብ አጋጣሚ አግኝታለች። አብዛኞቹ የትምህርት ቤቷ ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ያቀረበችላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል። አጋታ በዚህ አጋጣሚ ተጠቅማ እምነቷን ለሌሎች ማካፈል ስለቻለች ይሖዋን ታመሰግናለች። አዎን፣ ስለ እምነትህ ለሌሎች ሰዎች ለመናገር የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ለመጠቀም ንቁ መሆንህ ፍሬ እንድታፈራ ያስችልሃል። አንተስ ስለ እምነትህ ለሌሎች ሰዎች ለመናገር የሚያስችሉ ምን አጋጣሚዎች አሉህ?