በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንን ተምሬያለሁ

በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንን ተምሬያለሁ

የሕይወት ታሪክ

በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንን ተምሬያለሁ

ኦብሪ ባክስተር እንደተናገረው

በ1940 አንድ ቅዳሜ ምሽት፣ ሁለት ሰዎች ጥቃት ሰነዘሩብኝ፤ ሰዎቹ በኃይል ስለደበደቡኝ መሬት ላይ ተዘረርኩ። ሁለት ፖሊሶች በአቅራቢያው ቆመው የነበሩ ቢሆንም እኔን ከመርዳት ይልቅ ይሰድቡኝና የሚደበድቡኝን ሰዎች ያበረታቷቸው ነበር። እንዲህ ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እንዲፈጸምብኝ ምክንያት የሆነው ከአምስት ዓመታት በፊት በከሰል ማውጫ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ ስሠራ ያጋጠመኝ ሁኔታ ነበር። እስቲ ሁኔታውን ላውጋችሁ።

የተወለድኩት ስዋንዚ በተባለች በኒው ሳውዝ ዌልስ፣ አውስትራሊያ በምትገኝ የወደብ ከተማ በ1913 ሲሆን በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት አራት ወንዶች ልጆች ሦስተኛው ነኝ። የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ ቤተሰባችን በሙሉ በኅዳር በሽታ ተያዘ፤ ይህ አስፈሪ በሽታ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ይገመታል። የሚያስደስተው ግን ሁላችንም ተረፍን። ሆኖም በ1933 እናታችን በ47 ዓመቷ ስትሞት ቤተሰባችን በሐዘን ተደቆሰ። አምላካዊ ፍርሃት የነበራት እናቴ ብርሃን (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ ባለ ሁለት ጥራዝ መጽሐፍ ከይሖዋ ምሥክሮች ተቀብላ ነበር።

በዚያን ጊዜ በከሠል ማውጫ ድርጅት ውስጥ እሠራ ነበር። የሥራዬ ጠባይ ለተወሰነ ጊዜ ውጥረት የሚበዛበት ሲሆን በሌሎች ጊዜያት ግን ፋታ አገኛለሁ፤ በመሆኑም እነዚህን መጻሕፍት ወደምሠራበት ቦታ ይዤ በመሄድ በማደርገው የራስ ቁር ላይ ባለው ባትሪ እየተጠቀምኩ አነባቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ እውነትን እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ። በይሖዋ ምሥክሮች የሬድዮ ጣቢያ የሚተላለፉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችንም አዳምጥ ነበር። አባቴና ወንድሞቼ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ማሳየታቸው ደስታዬን እጥፍ አደረገው።

በ1935 ታናሽ ወንድሜ ቢሊ በ16 ዓመቱ በሳምባ ምች ሲሞት በድጋሚ በቤተሰባችን ውስጥ አሳዛኝ ሁኔታ ተከሰተ። በዚህ ጊዜ ግን ቤተሰባችን በትንሣኤ ተስፋ ተጽናና። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ከጊዜ በኋላ አባቴ እንዲሁም ቨርነር እና ሃሮልድ የተባሉት ታላላቅ ወንድሞቼ ከነባለቤቶቻቸው ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ተጠመቁ። ከቅርብ ቤተሰቦቼ መካከል አሁን በሕይወት ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ። ሆኖም የቨርነር ሁለተኛ ሚስት ማርጅሪ እንዲሁም የሃሮልድ ሚስት ኤልዛቤት አሁንም ይሖዋን በቅንዓት እያገለገሉ ነው።

በይሖዋ መታመንን መማር

ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በአካል የተገናኘሁት በ1935 መገባደጃ አካባቢ አንዲት ዩክሬናዊት ሴት በብስክሌት ቤታችን ሲመጡ ነበር። በቀጣዩ እሁድ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሄድኩ ሲሆን በሳምንቱ ደግሞ በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። የሚገርመው የስምሪት ስብሰባውን የመራው ወንድም ጥቂት ቡክሌቶችን ከሰጠኝ በኋላ ብቻዬን እንዳገለግል ላከኝ! የመጀመሪያውን ቤት ሳንኳኳ በጣም ከመፍራቴ የተነሳ መሬት ተሰንጥቆ ቢውጠኝ ደስ ይለኝ ነበር! የቤቱ ባለቤት ግን በጥሩ ሁኔታ የተቀበለኝ ሲሆን ጽሑፎችንም ወሰደ።

እንደ መክብብ 12:1 እና ማቴዎስ 28:19, 20 ያሉት ጥቅሶች ልቤን ስለነኩት አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን ፈለግሁ። አባቴም ቢሆን በውሳኔዬ ተስማማ። ያልተጠመቅሁ ብሆንም ሐምሌ 15, 1936 አቅኚነትን ለመጀመር ወሰንኩ። በወሰንኩት ዕለት በሲድኒ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሄድኩ ሲሆን በሲድኒ አቅራቢያ በሚገኘው ደሊጅ ሂል በተባለ አካባቢ ከ12 አቅኚዎች ጋር እንድሠራ ተመደብኩ። እነዚህ አቅኚዎች በእጅ በሚሠራ የስንዴ መፍጫ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል አሳዩኝ፤ በዚያን ጊዜ አቅኚዎች ወጪ ለመቀነስ ዱቄት በዚህ መንገድ ያዘጋጁ ነበር።

ከከተማ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች አቅኚ ሆኖ ማገልገል

በዚያው ዓመት ከተጠመቅሁ በኋላ ኦብሪ ዊልስ እና ክላይቭ ሼድ ከተባሉ ሌሎች ሁለት አቅኚዎች ጋር በማዕከላዊ ኩዊንስላንድ እንዳገለግል ተመደብኩ። ወደ ምድባችን ስንሄድ የኦብሪን መኪና፣ ጥቂት ብስክሌቶችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን የምናሰማበትን ቀለል ያለ የሸክላ ማጫወቻ፣ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት እንደ ቤት ሆኖ ያገለገለንን ድንኳን፣ ሦስት አልጋዎች፣ አንድ ጠረጴዛና ምግብ ማብሰያ ብረት ድስት ይዘን ነበር። አንድ ምሽት ምግብ የማብሰል ተራ ሲደርሰኝ ከአትክልትና ከስንዴ የተዘጋጀ “ልዩ” እራት ለመሥራት አሰብኩ። ሆኖም ያዘጋጀሁትን ምግብ ማናችንም ልንበላው ስላልቻልን በአቅራቢያችን ለነበረ ፈረስ ሰጠሁት። ፈረሱም ምግቡን ካሸተተው በኋላ ትቶት ሄደ! ምግብ ከማብሰል ጋር በተያያዘ ያደረግሁት ሙከራ በዚሁ አበቃ።

ከጊዜ በኋላ፣ ክልላችንን በፍጥነት ለመሸፈን ስንል ለሦስት ከከፈልነው በኋላ ሦስታችንም አንድ አንድ ምድብ ለመሥራት ወሰንን። ብዙውን ጊዜ ከምንኖርበት ድንኳን ርቄ እያለሁ ቀኑ ስለሚመሽ እንግዳ ተቀባይ የሆኑ የገጠር ነዋሪዎች ጋር አንዳንድ ጊዜ አድር ነበር። በአንድ አጋጣሚ በአንድ የከብት እርባታ ጣቢያ በእንግዶች ማረፊያ ክፍል ውስጥ ምቹ በሆነ አልጋ ላይ ያደርኩ ሲሆን በነጋታው ደግሞ በአንድ የካንጋሮ አዳኝ ጎጆ ውስጥ በዙሪያዬ የሚገማ ቆዳ ተቆልሎ መሬት ላይ ተኛሁ። ብዙ ጊዜ በጫካ ውስጥ አድሬያለሁ። አንድ ቀን ዲንጎዎች (የዱር ውሾች) በርቀት ከበቡኝ፤ በጨለማ ውስጥ የሚያሰሙት ጩኸት ያስፈራ ስለነበር ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ነጋ። በነጋታው ግን ውሾቹ የፈለጉት እኔን ሳይሆን በአካባቢው የተጣለውን የእንስሳት የሆድ ዕቃ እንደነበር አወቅሁ።

የድምፅ መሣሪያ በተገጠመለት መኪና ተጠቅሞ መስበክ

ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ የድምፅ መሣሪያ በተገጠመለት መኪና እንጠቀም ነበር። በሰሜናዊ ክዊንስላንድ በምትገኘው በታውንስቪል፣ ፖሊሶች መኪናችንን መሃል ከተማ አቁመን ንግግሮች እንድናሰማ ፈቀዱልን። ሆኖም በሸክላ ማጫወቻ የምናሰማው ንግግር ሳልቬሽን አርሚ የተባለውን ድርጅት አንዳንድ አባላት ስላስቆጣቸው ከተማውን ለቀን እንድንወጣ ነገሩን። ሆኖም ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆናችን የዚህ ድርጅት አባላት የሆኑ አምስት ሰዎች መኪናችንን ደህና አድርገው ናጧት። በዚህ ጊዜ መኪናው ውስጥ ሆኜ የድምፅ መሣሪያውን እያስተካከልኩ ነበር! መብታችንን ለማስከበር መከራከሩ ጥበብ መስሎ ስላልታየን ሰዎቹ ሲተዉን አካባቢውን ለቀን ሄድን።

በበንደበርግ፣ በከተማው መሃል በሚያልፈው በበርነት ወንዝ ላይ ሆነን ንግግሮቹን ማሰማት እንድንችል አንድ ፍላጎት ያሳየ ሰው ጀልባውን አዋሰን። ኦብሪ እና ክላይቭ የድምፅ መሣሪያውን ይዘው በጀልባው ሲሄዱ እኔ በተከራየነው አዳራሽ ውስጥ ቆየሁ። በዚያን ዕለት ምሽት፣ በሸክላ የተቀረጸው የወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ ኃይለኛ ድምፅ በበንደበርግ ከተማ አስተጋባ፤ የወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ጠንካራ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የያዘ ነበር። በእርግጥም በእነዚያ አስደሳች ዓመታት የአምላክ ሕዝቦች ድፍረትና እምነት ማሳየት አስፈልጓቸው ነበር።

ጦርነት ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አስከተለ

በመስከረም ወር 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ፣ ክርስቲያኖች በፖለቲካና በጦርነት ረገድ ያላቸው የገለልተኝነት አቋም ምን ነገሮችን እንደሚጨምር የሚገልጽ ሐሳብ በኅዳር 1 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጣ። በወቅቱ የወጣውን ይህን ትምህርት ማጥናቴ ከጊዜ በኋላ በጣም ጠቅሞኛል። በዚህ መሃል፣ ከኦብሪ እና ከክላይቭ ጋር ለሦስት ዓመታት አብረን ካገለገልን በኋላ ወደ ተለያየ አቅጣጫ የሚወስደን ምድብ ተሰጠን። እኔ በሰሜናዊ ክዊንስላንድ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል የተመደብኩ ሲሆን ይህን ኃላፊነት ስወጣ በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት በተደጋጋሚ ጊዜያት ተፈትኗል።

በነሐሴ ወር 1940 በታውንስቪል በሚገኘው ጉባኤ አገለግል ነበር፤ በዚህ ጉባኤ ውስጥ ፐርሲ እና ኢልማ ኢዝሎብ a እንዲሁም ኖርማን እና ቢያትሪስ ቤሎቲ የተባሉ አራት አቅኚዎች ነበሩ። ኖርማንና ቢያትሪስ ወንድምና እህት ሲሆኑ ከስድስት ዓመታት በኋላ ከቢያትሪስ ጋር ተጋባን። በታውንስቪል አንድ ቅዳሜ ምሽት በቡድን ሆነን መንገድ ላይ ስናገለግል ከቆየን በኋላ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ጥቃት ተፈጸመብኝ። ሆኖም ይህ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ እንድገፋ አነሳስቶኛል።

ዩነ እና መርል ኪልፓትሪክ የተባሉ እህትማማቾች የሆኑ አቅኚዎች በሰሜናዊው ክፍል በቅንዓት ይሰብኩ ነበር። አንድ ቀን ከእነዚህ እህቶች ጋር በአገልግሎት አስደሳች ጊዜ ካሳለፍኩ በኋላ ከወንዙ ማዶ ወደሚገኝ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ያሳየ ቤተሰብ ጋ ለመሄድ እንዲችሉ ወንዙን በጀልባ እንዳሻግራቸው ጠየቁኝ። ይህን ለማድረግ ወንዙን በዋና አቋርጬ በሌላኛው አቅጣጫ የታሰረውን ጀልባ ካመጣሁ በኋላ እህቶችን ማሻገር ነበረብኝ። ይሁን እንጂ ጀልባው ያለበት ቦታ ስደርስ መቅዘፊያዎቹ አልነበሩም! አንድ ተቃዋሚ መቅዘፊያዎቹን እንደደበቃቸው በኋላ ላይ አወቅን። ሆኖም የሰውየው ተንኮል ሥራችንን ከማከናወን አላገደንም። ለበርካታ ዓመታት ሕይወት አዳኝ ሆኜ በመሥራቴ ጎበዝ ዋናተኛ ነበርኩ። የመልሕቁን ገመድ ወገቤ ላይ አስሬ ጀልባውን እየጎተትኩ ከተሻገርኩ በኋላ እህቶችን አሳፍሬ እንደገና ጀልባውን እየሳብኩ አደረስኳቸው። ይሖዋም ያደረግነውን ጥረት ባረከልን፤ ከጊዜ በኋላ የዚህ ቤተሰብ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።

የይሖዋን ጥበቃ ማግኘት

ወታደሮች፣ የአካባቢውን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲሉ ከኢነስፌል ከተማ ወጣ ብለው ኬላ ሠርተው ነበር። የከተማው ነዋሪ ስለሆንኩ ወደዚህ አካባቢ ለመግባት ፈቃድ ማግኘት እችል ነበር፤ ይህ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች የሆኑ ወንድሞች ሲመጡ በጣም ጠቅሞናል። እነዚህ ወንድሞች ኬላውን እንዲያልፉ ለማድረግ ከመኪናዬ የኋላ መቀመጫ በታች የማይታይ ቦታ ውስጥ እደብቃቸው ነበር።

በዚያን ጊዜ ነዳጅ የሚገኘው በራሽን ሲሆን በርካታ ተሽከርካሪዎችም ነዳጅ የሚሠራ መሣሪያ ይገጠምላቸዋል። ይህ መሣሪያ ከከሰል ፍም በሚያገኘው ጋዝ አማካኝነት ሞተሩን ያንቀሳቅሰው ነበር። ከቅርንጫፍ ቢሮ የመጡ ወንድሞችን ማሳለፍ ስፈልግ ወንድም በተደበቀበት ቦታ በከሰል የተሞሉ ከረጢቶችን ከምሬ ምሽት ላይ እጓዝ ነበር። ኬላው ጋ ስደርስ ጠባቂዎቹ መኪናዋን በደንብ እንዳይፈትሿት ለማድረግ ስል ሞተሩን ሳላጠፋ በመቆም ከሰሉ የሚቀጣጠልበት ክፍል በጣም እንዲግል አደርገዋለሁ። እንደዚህ ዓይነት ጉዞ በማደርግበት አንድ ምሽት ላይ ለጠባቂዎቹ ድምፄን ከፍ አድርጌ “ሞተሩን ካጠፋሁት እንደገና ማስነሳት አስቸጋሪ ይሆናል” አልኳቸው። ጠባቂዎቹ የመኪናው ግለት፣ ጩኸቱና ጥላሸቱ ስላማረራቸው መኪናዋን በችኮላ አየት አድርገው ጉዞዬን እንድቀጥል ፈቀዱልኝ።

በእነዚያ ጊዜያት በታውንስቪል አካባቢ ላሉ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ እንዳደራጅ ተመድቤ ነበር። ምግብ የሚከፋፈለው በራሽን ስለነበር የምንፈልገውን ለማግኘት ከአካባቢው ባለ ሥልጣን ፈቃድ ያስፈልገን ነበር። በዚህ ጊዜ ክርስቲያን ወንድሞቻችን በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ይታሠሩ ስለነበር ባለ ሥልጣኑ ዘንድ ለመቅረብ ቀጠሮ ሳስይዝ ‘እንዲህ ማድረጌ ጥበብ ነው ወይስ ነብርን እንደመጎንተል ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ያም ቢሆን በታዘዝኩት መሠረት ወደ ባለ ሥልጣኑ ሄድኩ።

ትልቅና የሚያምር ጠረጴዛ በሚገኝበት ቢሮ ውስጥ የተቀመጠው ባለ ሥልጣን፣ ስገባ አረፍ እንድል ነገረኝ። የመጣሁበትን ጉዳይ ስገልጽለት ግን ፊቱን አኮሳትሮ ረዘም ላለ ጊዜ አትኩሮ ተመለከተኝ። ከዚያም ዘና በማለት “ምን ያህል ምግብ ነው የምትፈልገው?” አለኝ። ከሚያስፈልገን ምግብ በጣም አነስተኛ መጠን የሰፈረበትን ዝርዝር ሰጠሁት። ዝርዝሩን በደንብ ከተመለከተው በኋላ “ይህ በቂ አይመስልም። እጥፍ ብናደርገው ይሻላል” አለኝ። የባለ ሥልጣኑን ቢሮ ለቅቄ ስወጣ፣ ይሖዋ በእሱ ላይ በመታመን ረገድ ተጨማሪ ትምህርት ስለሰጠኝ አመሰገንኩት።

በጥር ወር 1941 የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በአውስትራሊያ ታገደ። በርካታ ሰዎች እኛን በጥርጣሬ መመልከት የጀመሩ ከመሆኑም በላይ የጃፓን ሰላዮች እንደሆንን አድርገው ይወነጅሉን ነበር! በአንድ ወቅት በሁለት መኪኖች የታጨቁ ፖሊሶችና ወታደሮች በአተርተን ፕላቶ ምግብ ለማምረት እንዲያገለግለን የገዛነውን የይሖዋ ምሥክሮች እርሻ ከበቡት። ለጠላት ምልክት ለመስጠት እንደምንጠቀምበት ያሰቡትን ባውዛ መብራት ፈልገው ነበር። ከዚህም በላይ በቆሎ የተከልነው፣ ጠላት በአውሮፕላን ከላይ ሆኖ ሊያነበው የሚችል ምልክት በሚሰጥ መንገድ እንደሆነ በመግለጽ ይወነጅሉን ነበር! እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሁሉ ውንጀላዎች ሐሰት መሆናቸው ታይቷል።

በእገዳው ምክንያት፣ ጽሑፍ ስናደርስ ጠንቃቆችና ዘዴኞች መሆን ነበረብን። ለአብነት ያህል፣ ችልድረን የተባለው መጽሐፍ ሲወጣ ከብሪስበን በካርቶን የታሸገውን መጽሐፍ ይዤ ወደ ሰሜናዊው ክፍል በባቡር በመጓዝ ጉባኤ ባለባቸው ቦታዎች መጻሕፍቱን እየተውኩ አልፍ ነበር። ፖሊሶችና የሠራዊቱ መርማሪዎች ካርቶኖቹን ለመክፈት እንዳይሞክሩ ለማድረግ ስል ክብ ቅርጽ ያለው መጋዝ እይዝና ከመውረዴ በፊት ካርቶኑ ላይ አስረዋለሁ። ይህ ዘዴ ቀላል ቢሆንም ሁልጊዜ ይሠራልኝ ነበር። ሰኔ 1943 እገዳው ሲነሳ የይሖዋ ሕዝቦች እፎይታ አገኙ፤ የፍርድ ቤቱ ዳኛ እገዳው “በሕግ ላይ ያልተመሠረተ፣ ያልታሰበበት እንዲሁም ጨቋኝ” እንደነበረ ገልጸዋል።

ለውትድርና አገልግሎት መጠራት

ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት እኔ፣ ኦብሪ ዊልስ እና ኖርማን ቤሎቲ ለውትድርና አገልግሎት ተጠርተን ነበር። ኦብሪ እና ኖርማን ከእኔ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ መጥሪያ የደረሳቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱ የስድስት ወራት እስራት በየነባቸው። በዚያን ጊዜ ፖስታ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ለሚታወቁ ግለሰቦች የሚላኩ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶችን ይወርስ የነበረ ቢሆንም የመጽሔቱ ኮንትራት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ግን ጽሑፋቸው ይደርሳቸው ነበር። እኛም መጽሔቱ ከሚደርሳቸው ሰዎች መካከል አንዳቸውን ካገኘን በኋላ መጽሔቶቹን በማባዛት ለእምነት ባልንጀሮቻችን እናሰራጫለን። በዚህ መንገድ መንፈሳዊ ምግብ አዘውትረን እናገኝ ነበር።

እንደጠበቅሁት የስድስት ወራት እስራት ሲፈረድብኝ በሲድኒ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በሰጠኝ መመሪያ መሠረት ወዲያውኑ ይግባኝ ጠየቅሁ። ዓላማችን ሥራውን የሚያከናውን ሌላ ሰው እስኪመደብ ድረስ እስራቱን ማዘግየት ነበር። በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም በሰሜናዊ ክዊንስላንድ የታሰሩትን 21 ወንድሞች ጠየቅኳቸው። አብዛኞቹ በአንድ እስር ቤት የነበሩ ሲሆን የወኅኒ ቤቱ ኃላፊ ደግሞ ይጠላን ነበር። የሌሎች ሃይማኖቶች አገልጋዮች አባላቶቻቸውን መጠየቅ እንደሚችሉ ስገልጽለት በጣም ተቆጥቶ “ሥልጣን ቢኖረኝ ኖሮ የይሖዋ ምሥክሮችን በጠቅላላ አሰልፌ እረሽናቸው ነበር!” አለኝ። ጠባቂዎቹም አዋክበው አስወጡኝ።

ያቀረብኩት ይግባኝ የሚሰማበት ጊዜ ሲደርስ በሕጉ መሠረት ጠበቃ ተመደበልኝ። ይሁን እንጂ ጉዳዬን የተከታተልኩት እኔው ራሴ ነበርኩ፤ ይህ ደግሞ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንን የጠየቀብኝ ሲሆን እሱም አላሳፈረኝም። (ሉቃስ 12:11, 12፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) የሚገርመው ነገር በክሱ ወረቀት ላይ የአጻጻፍ ስህተት በመገኘቱ ያቀረብኩት ይግባኝ ተቀባይነት አገኘ!

በ1944 ጠቅላላ ደቡብ አውስትራሊያን፣ የቪክቶሪያን ሰሜናዊ ክፍል እንዲሁም የኒው ሳውዝ ዌልስ ከተማ የሆነችውን ሲድኒን በሚሸፍን ሰፊ ወረዳ ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። በቀጣዩ ዓመት በዓለም ዙሪያ የሕዝብ ንግግር መስጠት ተጀመረ፤ እያንዳንዱ ተናጋሪ ድርጅቱ በሚሰጠው አንድ ገጽ የሚሆን አስተዋጽኦ ላይ ተመሥርቶ ንግግሩን መዘጋጀት ነበረበት። የአንድ ሰዓት ንግግር መስጠት መጀመሪያ ላይ ፈታኝ ቢሆንብንም በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመን ሥራውን ማከናወን የጀመርን ሲሆን እሱም ጥረታችንን ባርኮታል።

ትዳርና አዳዲስ ኃላፊነቶች

ሐምሌ 1946 እኔና ቢያትሪስ ቤሎቲ ተጋባንና አብረን በአቅኚነት ማገልገል ቀጠልን። የምንኖረው ከእንጨት በተሠራ ተጎታች ቤት ውስጥ ነበር። ታኅሣሥ 1950 አንድ ልጃችን የሆነችው ጃነስ (ጃን) ተወለደች። ከምፕሲ፣ ኒው ሳውዝ ዌልስን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች በአቅኚነት አገልግለናል፤ በዚህ ከተማ የነበርነው የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ብቻ ነበርን። እሁድ እሁድ በአካባቢው ወደሚገኘው የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ እንሄድና በመጋበዣ ወረቀት ያስተዋወቅነውን የሕዝብ ንግግር አቀርብ ነበር። ለተወሰኑ ወራት ንግግሩን የሚያዳምጡት ቢያትሪስ እና ሕፃኗ ልጃችን ጃን ብቻ ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ግን ሌሎች ሰዎች ቀስ በቀስ መምጣት ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ በከምፕሲ ከተማ እድገት የሚያደርጉ ሁለት ጉባኤዎች አሉ።

ጃን ሁለት ዓመት ሲሞላት በብሪስበን መኖር ጀመርን። ከዚያም ትምህርቷን ስትጨርስ በኒው ሳውዝ ዌልስ በሚገኘው በሴስኖክ ከተማ ለአራት ዓመታት ሁላችንም አቅኚ ሆነን አገለገልን፤ ከጊዜ በኋላ የቢያትሪስን እናት ለማስታመም ወደ ብሪስበን ተመለስን። በአሁኑ ጊዜ በቸርምሳይድ ጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።

እኔና ቢያትሪስ 32 ሰዎች አምላክን እንዲያውቁ የመርዳት መብት ከማግኘታችንም በላይ ሌሎች ተቆጥረው የማያልቁ በረከቶች ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን። በግሌ ደግሞ ይሖዋ ቢያትሪስን የመሰለች ሚስት ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ፤ ውዷ ባለቤቴ ለስላሳና ገር ብትሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጎን ለመቆም ደፋር ናት። ቢያትሪስ አምላክን የምትወድና በእሱ ላይ የምትታመን ከመሆኑም በላይ ‘ጤናማ ዓይን’ ያላት መሆኗ መልካም ሚስትና እናት እንድትሆን አድርጓታል። (ማቴዎስ 6:22, 23፤ ምሳሌ 12:4) እኔና ቢያትሪስ በአንድነት ሆነን ከልብ በመነጨ ስሜት “በእግዚአብሔር የሚታመን፣ . . . ሰው ቡሩክ ነው” ማለት እንችላለን።—ኤርምያስ 17:7

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የፐርሲ ኢዝሎብ የሕይወት ታሪክ በግንቦት 15, 1981 (እንግሊዝኛ) መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሰሜናዊ ክዊንስላንድ ስናገለግል የድምፅ መሣሪያ በተገጠመለት በዚህ መኪና እንጠቀም ነበር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዩነ እና መርል ኪልፓትሪክ የተባሉትን እህትማማቾች በሰሜናዊው ክዊንስላንድ በክረምቱ ወቅት መኪናቸውን በመግፋት ሳግዛቸው

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሠርጋችን ዕለት