“ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው”
“ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው”
በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ የአምላክን ሕዝቦች ከባቢሎን ምርኮ ነጻ አወጣቸው። በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ፈርሶ የነበረውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና ለመገንባት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን የገንዘብ ችግር የነበረባቸው ከመሆኑም በላይ በዙሪያቸው ያሉት ጠላቶቻቸው ቤተ መቅደሱ እንደገና መገንባቱን ይቃወሙ ነበር። በዚህም ምክንያት ግንባታውን ያከናውኑ ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ታላቅ ሥራ ማጠናቀቅ መቻላቸው አሳስቧቸው ነበር።
ይሖዋ የግንባታውን ሥራ ለሚያከናውኑት ሰዎች ከእነሱ ጋር እንደሚሆን በነቢዩ ሐጌ አማካኝነት እንዲህ በማለት አረጋገጠላቸው:- “ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ።” ሰዎቹ የነበረባቸውን የገንዘብ ችግር በተመለከተ ደግሞ ሐጌ “‘ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት” አላቸው። (ሐጌ 2:7-9) ሐጌ ይህንን የሚያበረታታ ሐሳብ በተናገረ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቀቀ።—ዕዝራ 6:13-15
በዘመናችን የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮችም ከይሖዋ አምልኮ ጋር የተያያዙ ታላላቅ ሥራዎችን ሲያከናውኑ የሐጌ ትንቢት አበረታቷቸዋል። በ1879 ታማኝና ልባም ባሪያ በወቅቱ የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ ይባል የነበረውን ይህን መጽሔት ማዘጋጀት ሲጀምር በመጽሔቱ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር:- “‘የጽዮን መጠበቂያ ግንብ’ ደጋፊ ይሖዋ ራሱ እንደሆነ እናምናለን። ይህ በመሆኑም ከሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በፍጹም አይለምንም ወይም አይማጠንም። ‘የተራሮች ወርቅና ብር ሁሉ የእኔ ነው’ ያለው አምላክ የሚያስፈልገንን ገንዘብ ማስገኘት ካቃተው ያን ጊዜ መጽሔቱን ማተም ማቆም እንደሚኖርብን እናውቃለን።”
የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሕትመት ፈጽሞ ተቋርጦ አያውቅም። የመጀመሪያው እትም የተዘጋጀው በእንግሊዝኛ ብቻ ሲሆን በ6,000 ቅጂዎች ታትሞ ነበር። በዛሬው ጊዜ እያንዳንዱ እትም በ161 ቋንቋዎች በአማካይ በ28,578,000 ቅጂዎች ይዘጋጃል። a ንቁ! የተባለው መጽሔት ደግሞ በ80 ቋንቋዎች በአማካይ በ34,267,000 ቅጂዎች ይዘጋጃል።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ እንደ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሁሉ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ መሆኑን የማሳወቅና የመንግሥቱን ምሥራች የማወጅ ዓላማ ያላቸው በርካታ ሥራዎችን ያከናውናሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 4:11) በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በ1879 በዚህ መጽሔት ላይ የወጣው ዓይነት አቋም አላቸው። አምላክ ሥራቸውን እንደሚደግፈውና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሥራዎች ለማከናወን የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ እንደሚያገኙ ያምናሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸውን ለማከናወን የሚያስችላቸውን ገንዘብ የሚያገኙት ከየት ነው? በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን ለመስበክስ ምን ዓይነት ሥራዎችን ያከናውናሉ?
ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ሲሰብኩ “ለምትሠሩት ሥራ ይከፈላችኋል?” የሚል ጥያቄ አብዛኛውን ጊዜ ይቀርብላቸዋል። ለሚያከናውኑት ሥራ አይከፈላቸውም። በስብከቱ ሥራ ላይ ለሚያውሉት ጊዜ ገንዘብ አይሰጣቸውም። እነዚህ ወንጌላውያን ለሰዎች ስለ ይሖዋና ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ስለሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለመስበክ በርካታ ሰዓታት እንዲያሳልፉ የሚገፋፋቸው አመስጋኝነት ነው። አምላክ ያደረገላቸውን ነገሮች እንዲሁም ምሥራቹ ሕይወታቸውንና አመለካከታቸውን ምን ያህል እንዳሻሻለው ሲያስቡ አድናቆት ያድርባቸዋል። በመሆኑም እነዚህን መልካም ነገሮች ለሌሎች ሰዎች ለመናገር ይፈልጋሉ። ይህን ሲያደርጉ ኢየሱስ “በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ” በማለት ለተከታዮቹ የሰጠውን መመሪያ ይከተላሉ። (ማቴዎስ 10:8) የይሖዋና የኢየሱስ ምሥክሮች ለመሆን ያላቸው ፍላጎት ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች እንኳ በራሳቸው ወጪ እምነታቸውን እንዲያካፍሉ ያነሳሳቸዋል።—ኢሳይያስ 43:10፤ የሐዋርያት ሥራ 1:8
የስብከቱ ሥራ በስፋት መከናወኑ እንዲሁም ይህን ሥራ ለማከናወን ማተሚያዎች፣ ቢሮዎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የሚስዮናውያን ቤቶችና የመሳሰሉት ነገሮች ጥቅም ላይ መዋላቸው ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። ታዲያ ለዚህ ሁሉ የሚሆን ገንዘብ ከየት ይመጣል? ገንዘቡ የሚገኘው በፈቃደኝነት ከሚደረጉት መዋጮዎች ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የድርጅቱን እንቅስቃሴ ለመደገፍ የጉባኤ አባላት ገንዘብ እንዲሰጡ አይጠይቁም፤ ለሚያሰራጯቸው ጽሑፎችም አያስከፍሉም። ማንም ሰው የይሖዋ ምሥክሮችን የስብከት ሥራ ለመደገፍ መዋጮ ለማድረግ ከፈለገ በደስታ ይቀበሉታል። ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ ለመስበክ የሚደረገው ጥረት አንድ ዘርፍ የሆነው የትርጉም ሥራ ብቻ እንኳ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት እስቲ እንመልከት።
በ437 ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ጽሑፎች
ለብዙ ዓመታት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች በዓለም ዙሪያ በስፋት ከሚተረጎሙት ጽሑፎች መካከል የሚጠቀሱ ሆነው ቆይተዋል። ትራክቶች፣ ብሮሹሮች፣ መጽሔቶችና መጻሕፍት በ437 ቋንቋዎች ይተረጎማሉ። እርግጥ ነው፣ ምሥራቹን ለመስበክ እንደሚረዱት ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሁሉ የትርጉም ሥራም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። ይህ ሥራ ምን ነገሮችን ያካትታል?
የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች የሚያዘጋጁት ሰዎች የእንግሊዝኛውን ጽሑፍ አዘጋጅተው ሲጨርሱ ጽሑፉ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የሠለጠኑ ተርጓሚዎችን ያቀፉ ቡድኖች በኢሜይል ይላካል። ከዚያም እያንዳንዱ የትርጉም ቡድን ጽሑፎቻችን ከሚዘጋጁባቸው ቋንቋዎች በአንዱ ጽሑፉን ይተረጉማል። እነዚህ የትርጉም ቡድኖች ከ5 እስከ 25 አባላት ሊኖሯቸው የሚችል ሲሆን የቡድኑ አባላት ቁጥር በሚያከናውኗቸው ሥራዎች ብዛትና በሚተረጉሙበት ቋንቋ ክብደት ላይ የተመካ ነው።
የተተረጎመው ጽሑፍ የእንግሊዝኛውን ሐሳብ በተቻለ መጠን በትክክልና በግልጽ ማስተላለፉን ለማረጋገጥ ሲባል ከእንግሊዝኛው ጋር በማመሳከር ከታረመ በኋላ የማጣሪያ ንባብ ይደረግለታል። ተርጓሚዎቹ ይህን ሥራ ሲያከናውኑ የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ
ጽሑፍ በሚተረጎምበት ጊዜ ተርጓሚዎቹና አራሚዎቹ ሐሳቡን በትክክል ለማስተላለፍ ሲሉ በእንግሊዝኛም ሆነ በቋንቋቸው ሰፊ ምርምር ማድረግ ይኖርባቸው ይሆናል፤ አብዛኞቹ ቡድኖች ለትርጉም ሥራቸው መሠረት የሚሆናቸው ቋንቋ እንግሊዝኛ ሲሆን አንዳንድ ቡድኖች ደግሞ እንደ ፈረንሳይኛ ወይም የሩስያና የስፔን ቋንቋ ከመሳሰሉት ቋንቋዎች ወደ ራሳቸው ቋንቋ ይተረጉማሉ። ለአብነት ያህል፣ በንቁ! መጽሔት ላይ ከቴክኒካዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ወይም ታሪካዊ የሆነ ርዕስ በሚወጣበት ጊዜ ተርጓሚዎቹ ሰፊ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።አብዛኞቹ ተርጓሚዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ወይም በሳምንት ውስጥ የተወሰኑ ቀናትን በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ለትርጉም ሥራ ያውላሉ። ሌሎች ደግሞ የሚተረጉሙበት ቋንቋ በሚነገርበት አካባቢ ሆነው ይሠራሉ። እነዚህ ተርጓሚዎች ለሚያከናውኑት ሥራ አይከፈላቸውም። ሙሉ ጊዜያቸውን ለትርጉም ሥራ የሚያውሉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ መኖሪያና ምግብ እንዲሁም የግል ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን የሚያስችል አነስተኛ የወጪ መተኪያ ይሰጣቸዋል። በዓለም ዙሪያ 2,800 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ተርጓሚዎች ሆነው ይሠራሉ። በአሁኑ ጊዜ በ98 የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የትርጉም ሥራዎች ይከናወናሉ፤ እነዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በሌላ ቦታ የሚገኙ የትርጉም ቡድኖችን ሥራም ይከታተላሉ። ለምሳሌ የሩስያ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ከ30 ወደሚበልጡ ቋንቋዎች የሚተረጉሙ ከ230 በላይ የሚሆኑ ተርጓሚዎችን ሥራ የሚከታተል ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከሚነገሩባቸው አካባቢዎች ውጭ በስፋት የማይታወቁት እንደ ቹቫሽ፣ ኦሲሻ እና ዊጉር የመሳሰሉ ቋንቋዎች ይገኙበታል። ከእነዚህ ተርጓሚዎች አንዳንዶቹ በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት ሲሠሩ ሌሎቹ ግን ሙሉ ጊዜያቸውን በዚህ ሥራ ላይ ያውላሉ።
የትርጉሙን ጥራት ማሻሻል
ሌላ ቋንቋ ለመማር የሞከረ ማንኛውም ሰው እንደሚያውቀው ውስብስብ ሐሳቦችን በትክክል መተርጎም ቀላል አይደለም። የተርጓሚዎቹ ዓላማ በእንግሊዝኛ የተገለጹትን መረጃዎችና ሐሳቦች በሚተረጉሙበት ቋንቋ በትክክል ማስተላለፍ ሲሆን ይህንንም በሚያደርጉበት ጊዜ ጽሑፉ በራሳቸው ቋንቋ የተዘጋጀ ያህል የቋንቋውን ለዛ ሳያጣ እንዲቀመጥ ለማድረግ ይጥራሉ። ይህንን ሁሉ ማድረግ ችሎታ ይጠይቃል። አዳዲስ ተርጓሚዎች በትርጉም ሥራቸው ብቁ ለመሆን በርካታ ዓመታት የሚወስድባቸው ሲሆን ቀጣይነት ያለው
ሥልጠናም ይሰጣቸዋል። አልፎ አልፎ ቡድኖቹ የትርጉም ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ለመርዳትና የኮምፒውተር አጠቃቀም ለማስተማር ብቃት ያላቸው ወንድሞች ይላካሉ።ይህ የሥልጠና ፕሮግራም ደግሞ ግሩም ውጤቶችን አስገኝቷል። ለአብነት ያህል፣ የኒካራጓ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚከተለው በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “ለሚስኪቶ ቋንቋ ተርጓሚዎቻችን ከትርጉም ጋር የተያያዘ ሥልጠና ለመስጠት ከሜክሲኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተማሪ መጥቶ ነበር። ይህ ደግሞ ተርጓሚዎቻችን ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መንገድ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። የትርጉሙም ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል።”
ልብ የሚነኩ ቃላት
ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲያገኙ ጥረት የሚደረገው ልባቸውን ለመንካት ሲሆን ይህንንም ለማድረግ ተችሏል። በ2006 በቡልጋርያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የአዲስ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በቋንቋቸው መዘጋጀቱ በጣም አስደስቷቸው ነበር። የቡልጋርያ ቅርንጫፍ ቢሮም በርካታ የአድናቆት መግለጫዎች እንደደረሱት ሪፖርት አድርጓል። የጉባኤ አባላትም “አሁን መጽሐፍ ቅዱስ አእምሯቸውን ብቻ ሳይሆን ልባቸውንም እንደነካው” ገልጸዋል። በሶፊያ ከተማ የሚኖሩ አንድ አረጋዊ ሰው “ለበርካታ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ያነበብኩ ቢሆንም እንደዚህ ዓይነት ለመረዳት ቀላል የሆነና ልብ የሚነካ ትርጉም አንብቤ አላውቅም” ብለዋል። በተመሳሳይም በአልባኒያ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር ሙሉውን የአዲስ ዓለም ትርጉም በቋንቋዋ ካገኘች በኋላ እንዲህ ብላለች:- “የአምላክን ቃል በአልባኒያ ቋንቋ ማንበብ እንዴት ያስደስታል! ይሖዋ በገዛ
ቋንቋችን ሲያናግረን ማዳመጥ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!”አንድ የትርጉም ቡድን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ለመተርጎም ብዙ ዓመታት ሊፈጅበት ይችላል። ይሁን እንጂ የተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የአምላክን ቃል እንዲረዱ ስለሚያስችላቸው የሚደረገው ጥረት ሁሉ አያስቆጭም።
‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን’
ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስበክ ከሚረዱ በርካታ ሥራዎች መካከል የትርጉም ሥራ አንዱ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን መጻፍ፣ ማተምና ወደተለያዩ ቦታዎች መላክ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ ወረዳዎችና ጉባኤዎች የሚያከናውኗቸው ከስብከቱ ሥራ ጋር የተያያዙ በርካታ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ጥረትና ወጪ ይጠይቃሉ። ያም ሆኖ የአምላክ ሕዝቦች ይህን ሥራ ለማከናወን ‘በገዛ ፈቃዳቸው’ ራሳቸውን ያቀርባሉ። (መዝሙር 110:3) ይህን ሥራ ለማከናወን የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንደ መብት የሚቆጥሩት ሲሆን ይሖዋም ‘ከእሱ ጋር አብረው እንደሚሠሩ’ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ክብር እንዳገኙ ይሰማቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 3:5-9
“ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው” ያለው አምላክ የሚያከናውነው ሥራ እኛ በምናደርገው የገንዘብ ድጋፍ ላይ የተመካ እንዳልሆነ አይካድም። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ “ለሕዝብ ሁሉ” ሕይወት አድን የሆኑትን እውነቶች ለመስበኩ ሥራ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ ስሙን የማስቀደስ ልዩ መብት እንዲኖራቸው በማድረግ አክብሯቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) አንተስ በድጋሚ የማይከናወነውን ይህን ሥራ ለመደገፍ የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ አትነሳሳም?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህ መጽሔት የሚታተምባቸው ቋንቋዎች በገጽ 2 ላይ ተዘርዝረዋል።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“በቁም ነገር እንድናስብ ያደርጉናል”
አንዲት የ14 ዓመት ልጅ በካሜሩን ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንደሚከተለው በማለት ጽፋለች:- “በዚህ ዓመት የሚያስፈልጉኝን የትምህርት መሣሪያዎች ከገዛሁ በኋላ ባለፈው ዓመት የተጠቀምኩባቸውን ሁለት መጻሕፍት በ2,500 ፍራንክ [45 ብር ገደማ] ሸጥኩ። ይህንን ገንዘብና ያጠራቀምኩትን 910 ፍራንክ [16 ብር ገደማ] መዋጮ አድርጌያለሁ። በምታከናውኑት መልካም ሥራ እንድትቀጥሉበት ላበረታታችሁ እፈልጋለሁ። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ስለምታዘጋጁልን አመሰግናችኋለሁ። በቁም ነገር እንድናስብ ያደርጉናል።”
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለየት ያለ መዋጮ
ማኑዌል የተባለ በቺያፓስ ግዛት የሚኖር አንድ የስድስት ዓመት ልጅ በሜክሲኮ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ደብዳቤ ላከ። ይህ ልጅ ገና መጻፍ ስለማይችል አድናቆቱን የሚገልጸውን ደብዳቤ የጻፈለት ጓደኛው ነበር። ማኑዌል እንዲህ ይላል:- “አያቴ አንዲት አሳማ ሰጠችኝ። ይህች አሳማ ግልገሎችን ስትወልድ የተሻለውን መርጬ ወንድሞች እየረዱኝ አሳደግሁት። ይህንን አሳማ ሸጬ ያገኘሁትን ገንዘብ ልኬላችኋለሁ፤ በጣም እወዳችኋለሁ። የዚህ አሳማ ክብደት 100 ኪሎ ግራም ሲሆን በ1,250 ፔሶ [990 ብር ገደማ] ሸጥኩት። እባካችሁ ገንዘቡን ለይሖዋ ተጠቀሙበት።”
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘ይህንን ገንዘብ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ተጠቀሙበት’
በ2005 በዩክሬን በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ የአዲስ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በዩክሬን ቋንቋ የወጣ ሲሆን በቀጣዩ ቀን በስብሰባው ቦታ በሚገኝ የመዋጮ ሳጥን ውስጥ የሚከተለው መልእክት ተገኘ:- “ዘጠኝ ዓመቴ ነው። የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ስለተረጎማችሁልን በጣም እናመሰግናለን። እናታችን ለእኔና ለትንሽ ወንድሜ ይህን ገንዘብ የሰጠችን በአውቶቡስ ወደ ትምህርት ቤት እንድንሄድ ነበር። ሆኖም ዝናብ በማይዘንብበት ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት በእግራችን በመሄድ ይህንን 50 ህርቭንያ [90 ብር ገደማ] አጠራቅመናል። እኔና ወንድሜ ይህንን ገንዘብ፣ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በዩክሬን ቋንቋ ለመተርጎም እንድትጠቀሙበት እንፈልጋለን።”
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች
ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉ መዋጮዎች
ብዙዎች “ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩት የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ።
ጉባኤዎች የተዋጣውን ገንዘብ በአገራቸው ሥራውን ለሚቆጣጠረው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በየወሩ ይልካሉ። ከዚህ በተጨማሪ በፈቃደኝነት የሚደረጉ የገንዘብ መዋጮዎችን በቀጥታ Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, Attention Treasurer’s Office, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገራችሁ ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ቼኮች ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት። ከውድ ማዕድናት የተሠሩ ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም መስጠት ይቻላል። የተላከው ዕቃ ሙሉ በሙሉ ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ ተያይዞ መላክ ይኖርበታል።
ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ የሚሰጥበት ዝግጅት
አንድ ሰው ገንዘቡን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዓለም አቀፉን ሥራ ለማካሄድ እንዲጠቀምበት በአደራ መልክ ሊሰጥና ሲያስፈልገው ማኅበሩን በመጠየቅ መልሶ ማግኘት ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።
በእቅድ የሚደረግ ስጦታ
ገንዘብ በስጦታ ከመለገስ በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። እነዚህም የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ:-
ኢንሹራንስ፦ የፔንስልቬንያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።
የባንክ ሒሳብ፦ የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለፔንስልቬንያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።
አክሲዮኖችና ቦንዶች፦ አክሲዮኖችንና ቦንዶችን በስጦታ መልክ ለፔንስልቬንያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር መስጠት ይቻላል።
የማይንቀሳቀስ ንብረት፦ ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል ቋሚ ንብረት በስጦታ መስጠት ወይም መኖሪያ ቤት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ባለ ንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ተጠቅሞበት ከዚያ በኋላ ማውረስ ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ከማዛወሩ በፊት በአገሩ ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር መነጋገር ይኖርበታል።
የስጦታ አበል፦ የስጦታ አበል አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም የባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን የይሖዋ ምሥክሮችን ወክሎ ለሚሠራው ማኅበር ለማዛወር የሚያደርገውን ዝግጅት ያመለክታል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እሱ የወከለው ግለሰብ በሕይወት እስካለበት ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈለዋል። ለጋሹ የስጦታ አበሉን ለማስተላለፍ በተስማማበት ዓመት የገቢ ግብር ቅናሽ ያገኛል።
ኑዛዜዎችና አደራዎች፦ ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተቀባይነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለፔንስልቬንያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በውርስ ሊሰጥ ወይም የፔንስልቬንያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዛወር ይችላል። አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች አሉ።
“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች ሰጪው እቅድ ማድረግ ያስፈልገዋል። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደገፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ዓለም አቀፉን የመንግሥት ሥራ ለመደገፍ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፔን ቋንቋ ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በኑዛዜ ውርስ ለመተው የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች አስመልክቶ መረጃ ለመስጠት ነው። ብዙዎች ይህን ብሮሹር ካነበቡ በኋላ ከሕግ ወይም ከቀረጥ አማካሪዎቻቸው ጋር በመማከር በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴና ሰብዓዊ እርዳታ ለመደገፍ ከመቻላቸውም በላይ ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ችለዋል። ይህን ብሮሹር ለማግኘት በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ በቀጥታ መጠየቅ ይቻላል።
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታች ያለውን አድራሻ ወይም ስልክ ቁጥር ተጠቅመህ በእቅድ የሚደረገውን ስጦታ ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ መጠየቅ ትችላለህ። አሊያም በአገርህ ለሥራው አመራር ወደሚሰጠው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሄደህ ማነጋገር ትችላለህ።
Charitable Planning Office
Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
100 Watchtower Drive,
Patterson, New York 12563-9204
ስልክ:- (845) 306-0707
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኒካራጓ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኙ የሚስኪቶ ቋንቋ ተርጓሚዎች