በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ትሕትናን ልበሱ’

‘ትሕትናን ልበሱ’

‘ትሕትናን ልበሱ’

ግለሰቡ የመጣው ከታወቀ ከተማ ነው። በትውልዱ ሮማዊ ሲሆን ቤተሰቡም ስመጥር ሳይሆኑ አይቀሩም። ሳውል የተባለው ይህ ሰው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ከፍተኛ ትምህርት የተከታተለ ሲሆን ቢያንስ ሁለት ቋንቋዎች ይናገራል፤ እንዲሁም ፈሪሳውያን ከሚባሉት ታዋቂ የሆኑ የአይሁድ የሃይማኖት ሰዎች አንዱ ነበር።

ሳውል፣ ተራውን ሕዝብ መናቅንና በራሱ ጽድቅ መኩራራትን ከእነዚህ ሰዎች ሳይማር አልቀረም። (ሉቃስ 18:11, 12፤ የሐዋርያት ሥራ 26:5) የሳውል ባልንጀሮች የነበሩት ፈሪሳውያን ከሌሎች እንደሚበልጡ የሚሰማቸው ከመሆኑም በላይ የከበሬታ ሥፍራና ማዕረግ ይወዱ ነበር። (ማቴዎስ 23:6, 7፤ ሉቃስ 11:43) የእነዚህ ሰዎች ወዳጅ መሆኑ ሳውልን ትዕቢተኛ እንዲሆን ሳያደርገው አልቀረም። ሳውል ክርስቲያኖችን በቅንዓት ያሳድድ እንደነበር እናውቃለን። ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለ ሲሆን ከበርካታ ዓመታት በኋላ ስለ ራሱ ሲጽፍ “ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና ዐመፀኛ” እንደነበረ ገልጿል።—1 ጢሞቴዎስ 1:13

አዎን፣ ሳውል ወደ ክርስትና እምነት ተለውጦ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለ ሲሆን ባሕርይውም ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ሐዋርያ ከሆነ በኋላ ‘ከቅዱሳን ሁሉ ያነሰ’ እንደሆነ በትሕትና ተናግሯል። (ኤፌሶን 3:8) ጳውሎስ የተዋጣለት ወንጌላዊ የነበረ ቢሆንም በዚህ ሥራው ራሱ ለመመስገን ከመፈለግ ይልቅ ሊከበር የሚገባው አምላክ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 3:5-9፤ 2 ቆሮንቶስ 11:7) ለእምነት ባልንጀሮቹ “ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” የሚል ምክር የሰጠውም ጳውሎስ ነበር።—ቈላስይስ 3:12

ይህ ምክር በዚህ ዘመን ተግባራዊ ሊሆን ይችላል? ትሑት መሆን ምን ጥቅም አለው? ትሕትና የጥንካሬ ምልክት ሊሆን ይችላል?

ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ ትሑት ነው?

ስለ ትሕትና ስናነሳ የአምላክን አመለካከት ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እሱ ሉዓላዊ ገዥያችንና ፈጣሪያችን ነው። እኛ ግን ከእሱ በተቃራኒ አቅማችን ውስን መሆኑን መገንዘብ አለብን። ሕይወታችን በእሱ ላይ የተመካ ነው። በጥንት ዘመን የነበረ ኤሊሁ የተባለ ጥበበኛ ሰው “ሁሉን የሚችል አምላክ ከአእምሯችን በላይ ነው፤ በኀይል . . . ታላቅ ነው” ብሏል። (ኢዮብ 37:23) በእርግጥም ግዙፍ ስለሆነው አጽናፈ ዓለም ማሰላሰላችን ብቻ እንኳ ትሑት እንድንሆን ይረዳናል! ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል ግብዣ አቅርቧል:- “ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።”—ኢሳይያስ 40:26

ይሖዋ አምላክ ሁሉን ቻይ ከመሆኑም ሌላ ትሑት ነው። ንጉሥ ዳዊት “የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ድጋፍህ [“ትሕትናህ፣” NW] ታላቅ አድርጎኛል” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (2 ሳሙኤል 22:36) አምላክ ትሑት ነው የምንለው እሱን ለማስደሰት ለሚጥሩ ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች ስለሚያስብና ምሕረት ስለሚያሳያቸው ነው። ይሖዋ እሱን ለሚፈሩ ሰዎች ደግነት ለማሳየት ሲል በምሳሌያዊ አነጋገር ከሰማይ ራሱን ዝቅ ያደርጋል።—መዝሙር 113:5-7

ከዚህም በላይ ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ የሚያሳዩትን ትሕትና ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 5:5) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ አምላክ ለትዕቢት ያለውን አመለካከት ሲገልጽ “እግዚአብሔር በልብ የሚታበዩትን ሁሉ ይጸየፋል” ብሏል። (ምሳሌ 16:5) ይሁን እንጂ ትሕትና የጥንካሬ ምልክት የሚሆነው እንዴት ነው?

ትሑት መሆን ሲባል ምን ማለት አይደለም

ትሑት መሆን ሲባል ራስን ማዋረድ ማለት አይደለም። በአንዳንድ የጥንት ባሕሎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ትሑት የሚሆነው ባሪያ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ ደግሞ ሽቁጥቁጥ፣ አሳዛኝና የተናቀ ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ትሑት መሆን ክብር እንደሚያስገኝ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ጠቢቡ ሰው “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 22:4) እንዲሁም መዝሙር 138:6 “እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤ ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል” ይላል።

ትሑት የሆነ ሰው ስኬታማ አይደለም ወይም ምንም ችሎታ የለውም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የይሖዋ አንድያ ልጅ እንዳልሆነ እንዲሁም በምድር ላይ የሚያከናውነው አገልግሎት አስፈላጊ እንዳልሆነ ፈጽሞ ተናግሮ አያውቅም። (ማርቆስ 14:61, 62፤ ዮሐንስ 6:51) ያም ሆኖ ኢየሱስ ለሚያከናውነው ሥራ ሊመሰገን የሚገባው አባቱ እንደሆነ በመናገር እንዲሁም ኃይሉን ሌሎችን ለመግዛትና ለመጨቆን ሳይሆን ለማገልገልና ለመርዳት በመጠቀም ትሑት መሆኑን አሳይቷል።

የጥንካሬ ምልክት

ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ በነበሩት ሰዎች ዘንድ የሚታወቀው ‘ታምራትን በማድረግ’ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:22) ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘ከሰዎች የተናቀ’ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውታል። (ዳንኤል 4:17) ኢየሱስ በአኗኗሩ ትሑት የነበረ ከመሆኑም በላይ የትሕትናን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ጊዜያት አስተምሯል። (ሉቃስ 9:48፤ ዮሐንስ 13:2-16) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ትሑት መሆኑ ደካማ እንዲሆን አላደረገውም። ለአባቱ ስም ጥብቅና በመቆምም ሆነ አገልግሎቱን በማከናወን ረገድ ደፋር ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:6-8) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ እንደ ደፋር አንበሳ ተደርጎ ተገልጿል። (ራእይ 5:5) ከኢየሱስ ምሳሌ እንደምንመለከተው ትሕትና ከሞራል ጥንካሬ ጋር የተያያዘ ነው።

እውነተኛ ትሕትናን ለማዳበር ስንሞክር ይህን ባሕርይ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ማንጸባረቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅ እንገነዘባለን። ትሑት መሆን፣ ቀላል የመሰለንን መንገድ ከመከተል ወይም ለሥጋዊ ምኞቶቻችን ከመሸነፍ ይልቅ ሁልጊዜ ለአምላክ ፈቃድ መገዛትን ይጠይቃል። ይሖዋንና ሌሎች ሰዎችን ከራስ ወዳድነት በራቀ መንፈስ ለማገልገል ስንል ለግል ፍላጎቶቻችን ሁለተኛ ቦታ መስጠት ስለሚኖርብን ትሕትናን ለማዳበር የመንፈስ ጥንካሬ ያስፈልገናል።

ትሑት መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

ትሑት ለመሆን ኩራትን ወይም ለራስ ከልክ ያለፈ ግምት መስጠትን ማስወገድ ይኖርብናል። ትሕትና አስተሳሰባችንን እንዲቆጣጠረው ከፈለግን ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኸውም ጠንካራና ደካማ ጎናችንን እንዲሁም ስኬታማ የሆንባቸውንና ያልሆንባቸውን ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል። ጳውሎስ “ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ” በማለት በዚህ ረገድ ግሩም ምክር ሰጥቷል። (ሮሜ 12:3) ይህን ምክር ተግባራዊ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ትሑት ነው።

ትሕትና የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ ከራሳችን ይልቅ የሌሎች ሰዎችን ጥቅም ለማስቀደም ከልባችን በመጣር ነው። ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት መክሯቸዋል:- “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ።” (ፊልጵስዩስ 2:3) ይህ ደግሞ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ለተከታዮቹ ከሰጣቸው ትእዛዝ ጋር ይስማማል:- “ከመካከላችሁ ከሁላችሁ የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፣ ራሱን የሚያዋርድ ግን ይከበራል።”—ማቴዎስ 23:11, 12

በእርግጥም አምላክ ትሑት የሆኑ ሰዎችን ያከብራቸዋል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፣ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል” በማለት ሲጽፍ ይህን ነጥብ አጉልቶታል። (ያዕቆብ 4:10) አምላክ ከፍ እንዲያደርገው የማይፈልግ ማን አለ?

ሰዎች ትሑት አለመሆናቸው በተለያዩ ቡድኖችም ሆነ በግለሰቦች መካከል ረብሻና ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል። በሌላ በኩል ግን ትሑት መሆን ጥቅም አለው። የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንችላለን። (ሚክያስ 6:8) ትሑት የሆነ ሰው ከትዕቢተኛ ግለሰብ ይልቅ ደስታና እርካታ ስለሚያገኝ ይህን ባሕርይ ካዳበርን የአእምሮ ሰላም ይኖረናል። (መዝሙር 101:5) ከቤተሰባችን አባላት፣ ከጓደኞቻችን፣ ከሥራ ባልደረቦቻችንና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት እምብዛም ችግር የሌለበትና ይበልጥ አስደሳች ይሆናል። ትሑት የሆኑ ሰዎች አስቸጋሪ የሆነ ባሕርይንና እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል አመለካከትን ያስወግዳሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ባሕርያት ሌሎችን በቀላሉ ያስቆጣሉ፣ ወዳጅነትን ያሻክራሉ እንዲሁም ቅራኔና ምሬት ይፈጥራሉ።—ያዕቆብ 3:14-16

አዎን፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ከፈለግን ትሕትናን ማዳበር በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ባሕርይ ራስ ወዳድነትና ፉክክር በሚንጸባረቅበት ዓለም ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ቀድሞ የነበረውን የትዕቢትና የኩራት ዝንባሌ በአምላክ እርዳታ ማስወገድ ችሏል። በተመሳሳይ እኛም ማንኛውንም የትዕቢት ወይም ከሌሎች እንደምንሻል የማሰብ ዝንባሌ መቅረፍ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 16:18) የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ስንከተልና ምክሩን ተግባራዊ ስናደርግ ‘ትሕትናን መልበስ’ የጥበብ አካሄድ መሆኑን እንገነዘባለን።—ቈላስይስ 3:12

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ የትዕቢትና የኩራት ዝንባሌን ማስወገድ ችሏል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Anglo-Australian Observatory/David Malin Images

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትሑት መሆናችን ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል