በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ መመርመር

‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ መመርመር

‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ መመርመር

‘መንፈስም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል።’—1 ቆሮንቶስ 2:10

1. ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት የተማሩ ሰዎች እንዲደሰቱ የሚያደርጓቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የትኞቹ ናቸው?

 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የምንገኘው አብዛኞቻችን መጀመሪያ እውነትን ስንሰማ ምን ያህል እንደተደሰትን ማስታወስ እንችላለን። የይሖዋ ስም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት፣ አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ፣ አንዳንድ ሰዎች ለምን ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ እንዲሁም ታማኝ የሆኑ የሰው ዘሮች በሙሉ የወደፊት ተስፋቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ችለን ነበር። ከዚያ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ያነበብን ቢሆንም እንደ አብዛኛው የሰው ዘር ሁሉ እኛም እነዚህ ነገሮች ተሰውረውብን ነበር። የነበርንበት ሁኔታ ማለዳ ላይ ገና ጎህ ሳይቀድ ጉዞ ከጀመረ ሰው ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሰውየው ጉዞ ሲጀመር ገና ጨለማ ስለሚሆን ብዙ ነገር ማየት አይችልም። ፀሐይዋ እየወጣች ስትሄድ ግን አካባቢውን ይበልጥ ማየት ይችላል። በመጨረሻም ፀሐይዋ አናት ላይ ስትሆን በዙሪያው ያሉትን ብቻ ሳይሆን በርቀት ያሉትንም ነገሮች በግልጽ መመልከት ይችላል። በተመሳሳይም አንድ ሰው መጀመሪያ ላይ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንድናውቅ ሲረዳን ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ በተወሰነ መጠን መረዳት ችለናል።—1 ቆሮንቶስ 2:8-10

2. የአምላክን ቃል በመማር ያገኘነው ደስታ ዘላቂ ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

2 ታዲያ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተወሰነ እውቀት በማግኘታችን ብቻ ልንረካ ይገባል? ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ የሚለው አገላለጽ ከሌሎች ሰዎች የተሰወረውንና ለክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተገለጠላቸውን የአምላክ ጥበብ መረዳትን ያካትታል። (1 ቆሮንቶስ 2:7) የአምላክ ጥበብ ጥልቅ ሲሆን የእሱን መንገድ በመመርመር ደስታ ማግኘት እንችላለን! እርግጥ ነው፣ መቼም ቢሆን የአምላክ ጥበብ የሚገለጽባቸውን መንገዶች ሙሉ በሙሉ ማወቅ አንችልም። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ስንማር ያገኘነውን ደስታ ጠብቀን ለመኖር ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ አዘውትረን መመርመራችንን መቀጠል ይኖርብናል።

3. ለእምነታችን መሠረት የሆኑንን ነገሮች በሚገባ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 እነዚህን ‘ጥልቅ ነገሮች’ መረዳታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የምናምንባቸውን ነገሮች ከማወቅም አልፈን ለምን እንደምናምንባቸው ማለትም ለእምነታችን መሠረት የሆኑንን ነገሮች መረዳታችን እምነታችንን ያጠናክርልናል። ቅዱሳን መጻሕፍት ‘በአእምሯችን’ በመጠቀም ‘መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትነን እንድናውቅ’ ያበረታቱናል። (ሮሜ 12:1, 2) ይሖዋ እሱ በሚፈልገው መንገድ እንድንኖር የሚጠይቀን ለምን እንደሆነ መረዳታችን እሱን ለመታዘዝ ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ እንድንጸና ያስችለናል። በመሆኑም ‘ጥልቅ ነገሮችን’ ማወቃችን በክፉ ድርጊቶች እንድንካፈል የሚደርስብንን ፈተና እንድንቋቋም ሊያጠናክረንና ‘መልካም የሆነውን ለማድረግ እንድንተጋ’ ሊያነሳሳን ይችላል።—ቲቶ 2:14

4. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ምን ነገሮችን ያካትታል?

4 ጥልቀት ያላቸውን ነገሮች ለመረዳት ማጥናት ያስፈልገናል። ጥናት ሲባል ግን አንድን ነገር ላይ ላዩን ከማንበብ የተለየ ነው። የምናጠናው ርዕስ ከአሁን ቀደም ከምናውቀው ነገር ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ለማወቅ መረጃዎችን በጥንቃቄ መመርመርን ያካትታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) ጥናት፣ አንድ ነገር የተባለበትን ምክንያት ማስተዋልን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ባወቅነው ነገር ላይ፣ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግና ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት እንዴት ልንጠቀምበት እንደምንችል ማሰላሰል ይገባናል። ከዚህም በተጨማሪ ‘ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው እንዲሁም ጠቃሚ’ በመሆናቸው የምናደርገው ጥናት ‘ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣውን ቃል ሁሉ’ ያካተተ መሆን አለበት። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ ማቴዎስ 4:4) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ይህ ዓይነቱ ጥናት አስደሳች ሊሆን ይችላል፤ ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ መረዳትም በጣም አስቸጋሪ አይደለም።

ይሖዋ ለትሑታን ማስተዋል ይሰጣቸዋል

5. ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ መረዳት የሚችሉት እነማን ናቸው?

5 በትምህርት ቤት ጎበዝ ተማሪ አልነበርክ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ የማጥናት ልማድ አይኖርህ ይሆናል። ያም ቢሆን ግን ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ ለመረዳት እንደማትችል አታስብ። በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ይሖዋ ዓላማውን የገለጠው ለጥበበኞችና ለአዋቂዎች ሳይሆን በትሕትና ከአምላክ አገልጋዮች ለመማር ፈቃደኛ ለሆኑ ያልተማሩና ተራ ሰዎች ነበር። እነዚህ ሰዎች ትምህርት ቤት ገብተው ከተማሩት ግለሰቦች ጋር ሲወዳደሩ እንደ ሕፃናት ነበሩ። (ማቴዎስ 11:25፤ የሐዋርያት ሥራ 4:13) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውን ነገር’ በተመለከተ ለእምነት ባልንጀሮቹ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል።”—1 ቆሮንቶስ 2:9, 10

6. በ1 ቆሮንቶስ 2:10 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ምን ትርጉም አለው?

6 የአምላክ መንፈስ ‘የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን የሚመረምረው’ እንዴት ነው? ይሖዋ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን እውነትን በግለሰብ ደረጃ ከመግለጥ ይልቅ በመንፈሱ አማካኝነት ድርጅቱን ይመራል፤ ድርጅቱ ደግሞ ይሖዋን በአንድነት የሚያገለግሉት ሕዝቦቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዱ ያስችላቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28፤ ኤፌሶን 4:3-6) በዓለም ዙሪያ ሁሉም ጉባኤዎች ተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም አላቸው። እነዚህ ጉባኤዎች በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን በሙሉ ይሸፍናሉ። ሰዎች ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ ለማስተዋል የሚያስፈልጋቸውን አመለካከት እንዲያዳብሩ ለመርዳት መንፈስ ቅዱስ በጉባኤዎች ይጠቀማል።—የሐዋርያት ሥራ 5:32

‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ ምንን ይጨምራሉ?

7. ብዙ ሰዎች ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ የማይረዱት ለምንድን ነው?

7 ‘ጥልቅ’ የተባሉት ‘ነገሮች’ ለመረዳት እንደሚከብዱ አድርገን ማሰብ የለብንም። አብዛኞቹ ሰዎች ‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ እውቀት የተሰወረባቸው የአምላክ ጥበብ ለመረዳት በጣም ከባድ ስለሆነ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን እርዳታ ሰዎች እንዳይቀበሉ ሰይጣን ስለሚያታልላቸው ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:3, 4

8. ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ የገለጸው የትኞቹን ጥልቅ ነገሮች ነው?

8 ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ እንደጠቆመው ‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች በሚገባ የተረዷቸውን በርካታ እውነቶች ያካትታሉ፤ ከእነዚህም መካከል እንደሚመጣ ቃል ስለተገባለት ዘር ማንነት፣ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ከሰው ዘሮች መካከል ስለመመረጣቸው እንዲሁም ስለ መሲሐዊው መንግሥት የሚገልጹት እውነቶች ይገኙበታል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህም ምስጢር አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋርያትና ነቢያት የተገለጠውን ያህል ባለፉት ዘመናት ለነበሩ ሰዎች አልተገለጠም ነበር። ይህም ምስጢር አሕዛብ . . . ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው።” ጳውሎስ አክሎም “በእግዚአብሔር ላለፉት ዘመናት የተሰወረውን የዚህን ምስጢር [“ቅዱስ ምስጢር፣” NW] አሠራር ለሁሉም እገልጥ ዘንድ ተሰጠኝ” ብሏል።—ኤፌሶን 3:5-9

9. ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ መረዳታችን ታላቅ መብት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

9 ጳውሎስ በመቀጠልም የአምላክን ፈቃድ ሲያብራራ “በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ . . . ይታወቅ ዘንድ ነው” ብሏል። (ኤፌሶን 3:10) መላእክት፣ ይሖዋ ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ የሚታየውን ጥበብ በመመልከትና በመረዳት ትምህርት ያገኛሉ። የመላእክትን እንኳ ትኩረት የሳቡትን ነገሮች መረዳታችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (1 ጴጥሮስ 1:10-12) ጳውሎስ ቀጥሎም የክርስትና እምነት “ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር የመገንዘብ ኀይልን” ለማግኘት መጣር እንዳለብን ተናግሯል። (ኤፌሶን 3:11, 18) እስቲ ከዚህ ቀደም አስበንባቸው የማናውቃቸውን አንዳንድ ጥልቅ ነገሮች እንደ ምሳሌ እንመልከት።

የአምላክ ጥልቅ ነገሮች አንዳንድ ምሳሌዎች

10, 11. በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊት ‘ሴት’ ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል የሆነው መቼ ነበር?

10 በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸችው የአምላክ ሰማያዊት ‘ሴት’ ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል ኢየሱስ እንደሆነ እናውቃለን። ስለዚህ ጉዳይ ያለንን ግንዛቤ ይበልጥ ለማስፋት እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ እንችላለን:- ‘ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት ዘር የሆነው መቼ ነበር? ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ነው ወይስ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት? ሲጠመቅ ነው ወይስ ከሞት ሲነሳ?’

11 በትንቢቱ ላይ ‘ሴት’ ተብላ የተገለጸችው የድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል የእባቡን ጭንቅላት የሚቀጠቅጥ ‘ዘር’ እንደምትወልድ አምላክ ቃል ገብቶ ነበር። ሆኖም የአምላክ ሴት ሰይጣንንም ሆነ ሥራዎቹን ለማጥፋት የሚችል ዘር ሳትወልድ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት አለፉ። በዚህም የተነሳ ይህች ሴት በኢሳይያስ ትንቢት ላይ “መካን” እንዲሁም ‘ከልቧ ያዘነች’ ተብላ ተጠርታለች። (ኢሳይያስ 54:1, 5, 6) ከጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ በቤተ ልሔም ተወለደ። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ኢየሱስን “ልጄ ይህ ነው” ያለው በተጠመቀበት ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ከተቀባ በኋላ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና መሥርቷል። (ማቴዎስ 3:17፤ ዮሐንስ 3:3) በመጨረሻም የሴቲቱ ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል ማንነት ታወቀ። ቆየት ብሎ የኢየሱስ ተከታዮችም በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው የአምላክ ልጆች ሆኑ። ‘ልጅ ወልዳ እንደማታውቅ’ ይሰማት የነበረችው የይሖዋ ‘ሴት’ በመጨረሻ ‘እልል’ ማለት ችላለች።—ኢሳይያስ 54:1፤ ገላትያ 3:29

12, 13. በምድር ላይ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሆኑ የሚያሳዩት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

12 ከተገለጡልን ጥልቅ ነገሮች መካከል ልንጠቅሰው የምንችለው ሁለተኛ ምሳሌ ደግሞ አምላክ ከሰው ልጆች መካከል 144,000ዎቹን ለመምረጥ ያለው ዓላማ ነው። (ራእይ 14:1, 4) በአንድ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ በምድር ላይ የሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ ኢየሱስ ለቤተሰቡ “ምግባቸውን” በጊዜው እንደሚሰጥ የተናገረለት “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሆኑ የሚገልጸውን ትምህርት እንቀበላለን። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ሆኖም ይህ ትምህርት ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጡት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው? ኢየሱስ ወንድሞቹን በመንፈሳዊ የሚመግብን ማንኛውንም ክርስቲያን መጥቀሱ ሊሆን ይችላል?

13 አምላክ ለእስራኤል ብሔር “እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ብሏቸው ነበር። (ኢሳይያስ 43:10) ሆኖም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኒሳን 11 ላይ አምላክ፣ የእስራኤል ብሔር የእሱ ባሪያ እንዳይሆን እንደተወው ኢየሱስ ለብሔሩ መሪዎች ነገራቸው። “የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች” አላቸው። ኢየሱስ ሕዝቡን “እነሆ፣ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል!” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 21:43፤ 23:38) የይሖዋ ባሪያ የነበረው የእስራኤል ቤት ታማኝም ሆነ ልባም አልነበረም። (ኢሳይያስ 29:13, 14) በዚያው ዕለት ኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ‘እስራኤልን በመተካት የአምላክ ታማኝ ባሪያ የሚሆነው የትኛው ልባም ሕዝብ ነው?’ ብሎ የጠየቀ ያህል ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ላቀፈው ጉባኤ “እናንተ. . . ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ” ብሎ በጻፈ ጊዜ መልሱን ሰጥቷል። (1 ጴጥሮስ 1:4፤ 2:9) ይህ መንፈሳዊ ሕዝብ ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ በሥጋዊ እስራኤላውያን ምትክ የይሖዋ ባሪያ ሆነ። (ገላትያ 6:16) የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ አባላት በሙሉ እንደ አንድ “ባሪያ” ተደርገው እንደተገለጹ ሁሉ በምድር ላይ የሚኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ እንደ አንድ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ይቆጠራሉ። በአምላክ ባሪያ አማካኝነት መንፈሳዊ ‘ምግብ’ በማግኘታችን ምንኛ ተባርከናል!

የግል ጥናት አስደሳች ሊሆን ይችላል

14. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲሁ ላይ ላዩን ከማንበብ ይበልጥ አስደሳች ነው የምንለው ለምንድን ነው?

14 ከቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ እውቀት ስናገኝ ትምህርቱ እምነታችንን ስለሚያጠናክርልን እንደምንደሰት ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንዲሁ ላይ ላዩን ከማንበብ ይበልጥ አስደሳች የሆነውም ለዚህ ነው። እንግዲያው ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ስታነብ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ይህ ማብራሪያ ከዚህ ቀደም ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ከማውቀው ነገር ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች የሚደግፉ ምን ተጨማሪ ጥቅሶች ወይም ነጥቦች አሉ?’ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ የሚያስፈልግህ ከሆነ መልስ የሚያሻውን ጥያቄ በማስታወሻህ ላይ ካሰፈርክ በኋላ በሌላ ጊዜ ጥናት አድርግበት።

15. ስለ የትኞቹ ጉዳዮች በማጥናት ደስታ ማግኘት ትችላለህ? ያደረግኸው ጥናት ዘላቂ ጥቅም እንዲኖረው ምን ማድረግ ትችላለህ?

15 አዲስ እውቀት በማግኘት መደሰት የምትችለው ስለ የትኞቹ ጉዳዮች በማጥናት ነው? ለምሳሌ፣ ወደ ይሖዋ ቅረብ a በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 19 ተጠቅመህ አምላክ ለሰው ልጆች ጥቅም ሲል ስለገባቸው የተለያዩ ቃል ኪዳኖች በጥልቀት በማጥናት እውቀትህን ማስፋት ትችላለህ። እንዲሁም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩትን ትንቢቶች ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት መጻሕፍት አንዱን ቁጥር በቁጥር በማጥናት እምነትህን ማጠናከር ትችላለህ። የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች b (እንግሊዝኛ) ከተባለው መጽሐፍ ላይ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ ማንበብም እምነትህን ሊያጠናክርልህ ይችላል። ከዚህም ሌላ ባለፉት ዓመታት በመጠበቂያ ግንብ ላይ “የአንባቢያን ጥያቄዎች” በሚል ርዕስ የወጡ ትምህርቶችን ማጥናት አንዳንድ ጥቅሶችን ይበልጥ በግልጽ ለመረዳት ያስችልሃል። በርዕሶቹ ላይ ለቀረቡት መልሶች የተሰጡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ለየት ያለ ትኩረት ስጣቸው። ይህም ‘የማስተዋል ችሎታህን’ ለማሠልጠን እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታ ለማዳበር ያስችልሃል። (ዕብራውያን 5:14 NW) በምታጠናበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስህ ወይም በወረቀት ላይ ማስታወሻ ያዝ፤ ይህም ያደረግኸው ጥናት ለራስህም ሆነ ለሌሎች ዘላቂ ጥቅም እንዲኖረው ያደርጋል።

ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስደሳች እንዲሆንላቸው እርዷቸው

16. ልጆቻችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስደሳች እንዲሆንላቸው ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

16 ወላጆች፣ ልጆቻቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ፍላጎት እንዲያድግ ለመርዳት ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት ይችላሉ። ልጆቻችሁ ጥልቅ ነገሮችን ለመረዳት እንደሚከብዳቸው አድርጋችሁ አታስቡ። በአንድ ርዕስ ላይ ምርምር አድርገው ለቤተሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲዘጋጁ ለልጆቻችሁ ከነገራችኋቸው በኋላ ካደረጉት ምርምር ምን ትምህርት እንዳገኙ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። ልጆች እምነታቸውን ማስረዳት እንዲሁም የተማሩት ነገር እውነት ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ እንዲችሉ ለመርዳት በቤተሰብ ጥናት ወቅት የልምምድ ፕሮግራምም ማካተት ይቻላል። ከዚህም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ቦታዎች መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለማስተማር እንዲሁም በሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ነገር ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ‘መልካሚቱን ምድር ተመልከቱ’ c (እንግሊዝኛ) በሚለው ብሮሹር መጠቀም ትችላላችሁ።

17. የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስናደርግ ሚዛናዊ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

17 የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስደሳችና እምነት የሚያጠናክር ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም የምታደርገው ምርምር ለጉባኤ ስብሰባዎች ለመዘጋጀት ጊዜ እንዳያሳጣህ መጠንቀቅ አለብህ። የጉባኤ ስብሰባ፣ ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል የሚያስተምርበት አንዱ መንገድ ነው። ተጨማሪ ምርምር ማድረግህ በጉባኤ ስብሰባዎች፣ ለምሳሌ በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ ወይም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች ሲቀርቡ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል።

18. ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ ለማጥናት ጥረት ማድረጋችን የሚክስ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

18 የአምላክን ቃል በጥልቀት ማጥናትህ ወደ ይሖዋ እንድትቀርብ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱ ጥናት ያለውን ጥቅም ሲገልጽ እንደሚከተለው ይላል:- “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው።” (መክብብ 7:12) በመሆኑም መንፈሳዊ ነገሮችን በጥልቀት ለመረዳት የምታደርገው ጥረት የሚክስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምርምር የሚያደርጉ ሰዎች ‘የአምላክን እውቀት እንደሚያገኙ’ ያረጋግጥልናል።—ምሳሌ 2:4, 5 የ1954 ትርጉም

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

c በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ‘የአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ ምንድን ናቸው?

• ስለ ጥልቅ ነገሮች ማጥናታችንን ማቆም የሌለብን ለምንድን ነው?

• ‘የአምላክን ጥልቅ ነገሮች’ መረዳት የሚያመጣውን ደስታ ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያገኙት ይችላሉ የምንለው ለምንድን ነው?

• ‘ከአምላክ ጥልቅ ነገሮች’ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት ዘር የሆነው መቼ ነበር?

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች፣ ልጆቻቸው ለቤተሰቡ ጥናት ምርምር አድርገው የሚዘጋጁባቸውን ርዕሶች ሊሰጧቸው ይችላሉ