በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአብድዩ፣ የዮናስ እና የሚክያስ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

የአብድዩ፣ የዮናስ እና የሚክያስ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የአብድዩ፣ የዮናስ እና የሚክያስ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

“የአብድዩ ራእይ።” (አብድዩ 1) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የአብድዩ መጽሐፍ የሚጀምረው በዚህ መንገድ ነው። ነቢዩ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሰፈረው በዚህ መጽሐፍ ላይ ከስሙ በስተቀር ስለራሱ ምንም አልገለጸም። የአብድዩ መጽሐፍ ከመጻፉ ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት፣ ነቢዩ ዮናስ ባጠናቀቀው መጽሐፍ ላይ በሚስዮናዊነት ተልእኮው ያጋጠመውን ሁኔታ በሐቀኝነት ዘግቧል። ሚክያስ ትንቢት የተናገረው አብድዩና ዮናስ በነበሩባቸው ጊዜያት መሃል ባለው ጊዜ ውስጥ ማለትም ከ777 እስከ 717 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሉት 60 ዓመታት ውስጥ ነው። ሚክያስ ‘ከሞሬት’ ከተማ እንደመጣና የይሖዋ ቃል የተገለጠለት “በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን” እንደሆነ ከመግለጹ በቀር ስለ ራሱ የተናገረው ነገር የለም። (ሚክያስ 1:1) ነቢዩ መልእክቱን ለማጉላት የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች፣ የገጠሩን ሕይወት በሚገባ ያውቅ እንደነበር ያሳያሉ።

ኤዶም ‘ለዘላለም ይጠፋል’

(አብድዩ 1-21)

አብድዩ፣ ኤዶምን በተመለከተ “በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፣ በዕፍረት ትሸፈናለህ፤ ለዘላለምም ትጠፋለህ” ብሏል። ነቢዩ መጽሐፉን ከመጻፉ ጥቂት ቀደም ብሎ ኤዶማውያን በያዕቆብ ልጆች ማለትም በእስራኤላውያን ላይ የፈጸሙት ግፍ ገና ከአእምሮው አልጠፋም ነበር። በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን፣ ኢየሩሳሌምን ሲያጠፉ ኤዶማውያን ‘ገለልተኛ ሆነው’ ከመመልከታቸውም በላይ ከወራሪዎቹ ‘ባዕዳን’ ጋር ተባብረዋል።—አብድዩ 10, 11

ከዚህ በተቃራኒ ግን የያዕቆብ ቤት እንደገና እንደሚቋቋም ትንቢት ተነግሯል። የአብድዩ ትንቢት “በጽዮን ተራራ ነጻ መውጣት ይሆናል፤ የያዕቆብ ቤትም እርሷ የተቀደሰች ትሆናለች” ይላል።—አብድዩ 17

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

5-8—የኤዶም ጥፋት፣ ሌሊት ከሚመጡ ዘራፊዎችና ከወይን ለቃሚዎች ጋር መነጻጸሩ ምን ትርጉም አለው? ሌቦች ወደ ኤዶም ቢመጡ የሚወስዱት የሚፈልጉትን ብቻ ነው። ወይን ለቃሚዎችም ቢመጡ ከሰብሉ የተወሰነውን ለቃርሚያ ይተዉ ነበር። ኤዶም ሲወድቅ ግን ሀብቱ አንድም ሳይቀር ይመዘበራል፤ እንዲሁም ‘ወዳጆቹ’ ማለትም ባቢሎናውያን ሙሉ በሙሉ ይዘርፉታል።—ኤርምያስ 49:9, 10

10—ኤዶም ‘ለዘላለም እንደሚጠፋ’ የተነገረው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነበር? በምድር ላይ በአንድ አካባቢ የሚኖር ሕዝብና መንግሥት የነበረው የኤዶም ብሔር አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ጠፍቷል። የባቢሎን ንጉሥ ናቦኒደስ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት አጋማሽ አካባቢ ኤዶምን ድል አድርጎታል። በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ናባቲያውያን በኤዶም ግዛት መኖር ሲጀምሩ ኤዶማውያን በደቡባዊ የይሁዳ ክፍል በኔጌብ ለመኖር ተገደዱ፤ ይህ አካባቢ ከጊዜ በኋላ ኤዶምያስ ተብሎ ተጠርቷል። ሮማውያን በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌምን ሲያጠፏት ኤዶማውያን ከምድር ገጽ ጠፉ።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

3, 4፦ ኤዶማውያን ከፍ ያሉ ተራሮችና ገደሎች ባሉት ወጣ ገባ በሆነና ወታደራዊ ጠቀሜታ ባለው አካባቢ መኖራቸው ከመጠን በላይ በራሳቸው በመተማመን ምንም ነገር እንደማይደርስባቸው እንዲያስቡ ሳያደርጋቸው አልቀረም። ሆኖም ከይሖዋ ፍርድ ማምለጥ አይቻልም።

8, 9, 15፦ ሰብዓዊ ጥበብና ኃይል ‘በይሖዋ ቀን’ ምንም ጥበቃ አያስገኝም።—ኤርምያስ 49:7, 22

12-14፦ በኤዶማውያን ላይ የደረሰው ጥፋት የአምላክ አገልጋዮች በሚያጋጥማቸው ችግር ለሚደሰቱ ሁሉ ማስጠንቀቂያ ይሆናል። ይሖዋ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰውን እንግልት አቅልሎ አይመለከተውም።

17-20፦ የያዕቆብ ልጆች እንደገና እንደሚቋቋሙ የተነገረው ይህ ትንቢት በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ቀሪዎቹ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ መፈጸም ጀምሯል። የይሖዋ ቃል ምንጊዜም ይፈጸማል። ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ሙሉ እምነት ማሳደር እንችላለን።

‘ነነዌ ትገለበጣለች’

(ዮናስ 1:1 እስከ 4:11)

ዮናስ ‘ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄዶ’ የይሖዋን የፍርድ መልእክት ‘በእሷ ላይ እንዲሰብክ’ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ከመፈጸም ይልቅ በተቃራኒው አቅጣጫ ኰበለለ። ይሖዋም “በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን” በመላክ እንዲሁም ዮናስን “ትልቅ ዓሣ” እንዲውጠው በማድረግ አቅጣጫውን ካስቀየረው በኋላ ወደ አሦር ዋና ከተማ እንዲሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ላከው።—ዮናስ 1:2, 4, 17፤ 3:1, 2

ዮናስ ወደ ነነዌ ከተማ ገብቶ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” በማለት ቀጥተኛ መልእክት አወጀ። (ዮናስ 3:4) ሆኖም የስብከት ተልእኮው የጠበቀውን ዓይነት ውጤት ባለማስገኘቱ እጅግ “ተቈጣ።” ይሖዋም “የቅል ተክል” በማብቀል ዮናስን ስለ ምሕረት አስተማረው።—ዮናስ 4:1, 6

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

3:3 የ1954 ትርጉም—በእርግጥ የነነዌ ከተማ “የሦስት ቀን መንገድ” ያህል የሚያስኬድ ስፋት ነበራት? አዎን። በጥንት ጊዜ፣ ነነዌ በስተ ሰሜን ከሚገኘው ኮርሳባድ አንስቶ በስተ ደቡብ እስከሚገኘው እስከ ናምሩድ ድረስ ያሉትን መንደሮች እንደምታጠቃልል ይታሰብ ነበር። ከነነዌ ጋር አብረው የሚቆጠሩት መንደሮች በሙሉ አጠቃላይ ዙሪያቸው 100 ኪሎ ሜትር ነበር።

3:4—ዮናስ ለነነዌ ሕዝብ ለመስበክ የአሦራውያንን ቋንቋ መማር አስፈልጎት ነበር? ዮናስ የአሦራውያንን ቋንቋ መናገር ይችል ይሆናል፤ አሊያም ይህንን ቋንቋ የመናገር ችሎታ በተአምር ተሰጥቶት ሊሆን ይችላል። ሌላው አማራጭ ደግሞ ዮናስ ቀጥተኛ የሆነውን መልእክቱን በዕብራይስጥ ሲናገር ሌላ ሰው አስተርጉሞለት ይሆናል። ዮናስ በአስተርጓሚ ተጠቅሞ ከነበረ የሚናገራቸው ቃላት ሕዝቡ ለመልእክቱ የበለጠ ጉጉት እንዲያድርባቸው አድርገው ሊሆን ይችላል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:1-3 ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሙሉ በሙሉ ላለመካፈል ስንል በሌሎች እንቅስቃሴዎች ለመሳተፍ ፕሮግራም የምናወጣ ከሆነ ይህ የተሳሳተ የልብ ዝንባሌ እንዳለን ይጠቁማል። እንዲህ የሚያደርግ ሰው አምላክ የሰጠውን ሥራ ላለማከናወን የኰበለለ ያህል ነው።

1:1, 2፤ 3:10 ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ለአንድ ብሔር ወይም ዘር አሊያም ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ አይደለም። “እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው።”—መዝሙር 145:9

1:17፤ 2:10 ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት መቆየቱ ለኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ትንቢታዊ ጥላነት አለው።—ማቴዎስ 12:39, 40፤ 16:21

1:17፤ 2:10፤ 4:6 ይሖዋ ዮናስን በማዕበል ከሚናወጠው ባሕር አድኖታል። ከዚህም በላይ አምላክ “የቅል ተክል አብቅሎ፣ የዮናስ ራስ ጥላ እንዲያገኝና ሙቀትም እንዳያስጨንቀው ከበላዩ እንዲያድግ [አድርጓል]።” በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አምላኪዎችም በአምላካቸው ሊመኩ እንዲሁም በጸና ፍቅሩ ወይም በፍቅራዊ ደግነቱ ሊጠብቃቸውና ሊያድናቸው እንደሚችል ሊታመኑ ይችላሉ።—መዝሙር 13:5፤ 40:11 NW

2:1, 2, 9, 10 ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጸሎት የሚሰማ ሲሆን ለልመናቸውም ትኩረት ይሰጣል።—መዝሙር 120:1፤ 130:1, 2

3:8, 10 እውነተኛው አምላክ ለነነዌ ሰዎች ‘በመራራት’ እንደሚያመጣ የተናገረውን “ጥፋት አላደረገም።” ለምን? ይህ የሆነው የነነዌ ሰዎች ‘ከክፉ መንገዳቸው ስለተመለሱ’ ነው። በተመሳሳይ ዛሬም አንድ ኃጢአተኛ ከልቡ ንስሐ ከገባ ከአምላክ የጥፋት ፍርድ ማምለጥ ይችላል።

4:1-4 ማንም ሰው፣ ምሕረት እንዳያሳይ አምላክን ሊያግደው አይችልም። እኛም የይሖዋን ምሕረት ላለመንቀፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል።

4:11 ይሖዋ በነነዌ ለነበሩት ከ120,000 የሚበልጡ ሰዎች እንዳደረገው ሁሉ ‘ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር ለማይችሉ’ ሰዎች ስለሚያዝን ታጋሽ በመሆን የመንግሥቱ መልእክት በምድር ዙሪያ እንዲሰበክ እያደረገ ነው። እኛስ በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች በማዘን ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት መካፈል አይገባንም?—2 ጴጥሮስ 3:9

‘ራሳቸው ይመለጣል’

(ሚክያስ 1:1 እስከ 7:20)

ሚክያስ የእስራኤልንና የይሁዳን ኃጢአት አጋልጧል፤ ዋና ከተሞቻቸውም እንደሚጠፉ ተናግሯል። እንዲሁም ተመልሰው እንደሚቋቋሙ ተስፋ ሰጥቷል። ሰማርያ “የፍርስራሽ ክምር” ትሆናለች። እስራኤልና ይሁዳ ደግሞ ጣዖት አምላኪዎች በመሆናቸው ‘ይመለጣሉ’ ወይም ኃፍረት ይከናነባሉ። ሕዝቡ በምርኮ በመወሰዳቸው “እንደ አሞራ” (አናቱ ላይ ስስ ጸጉር ያለው የጥንብ አንሳ ዝርያ ሳይሆን አይቀርም) ራሳቸው ይመለጣል። ይሁን እንጂ ይሖዋ “ያዕቆብ ሆይ፤ በእርግጥ ሁላችሁንም እሰበስባለሁ” የሚል ተስፋ ሰጥቷል። (ሚክያስ 1:6, 16፤ 2:12) ኢየሩሳሌምም በምግባረ ብልሹ መሪዎቿና በቸልተኛ ነቢያቶቿ የተነሳ “የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።” ይሖዋ ግን ሕዝቡን ‘ይሰበስባል።’ እንዲሁም ‘ከቤተ ልሔም ኤፍራታ የእስራኤል ገዥ ይወጣል።’—ሚክያስ 3:12፤ 4:12፤ 5:2

ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን የያዘበት መንገድ ፍትሐዊ አልነበረም? መመሪያዎቹስ በጣም ጥብቅ ነበሩ? በፍጹም። ይሖዋ ከአምላኪዎቹ የሚፈልገው ‘ፍትሕን እንዲያደርጉ፣ ምሕረትንም እንዲወድዱ እንዲሁም በአምላካቸው ፊት በትሕትና እንዲራመዱ’ ብቻ ነው። (ሚክያስ 6:8) ሆኖም በሚክያስ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ሰዎች እጅግ ምግባረ ብልሹ በመሆናቸው “ከእነርሱ ይሻላል የተባለው እንደ አሜከላ፣ እጅግ ቀና የተባለውም እንደ ኵርንችት” በመሆን በሚጠጋቸው ሁሉ ላይ ጉዳትና ሥቃይ ያስከትላሉ። ነቢዩ “እንደ [ይሖዋ] ያለ አምላክ ማነው?” በማለት ጠይቋል። አምላክ ለሕዝቡ እንደገና ምሕረት በማሳየት ‘በደላቸውን ሁሉ ወደ ጥልቁ ባሕር ይጥላል።’—ሚክያስ 7:4, 18, 19

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

2:12—ይሖዋ ‘የእስራኤልን ትሩፍ በአንድነት እንደሚሰበስብ’ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነበር? በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት አይሁዳውያን ቀሪዎች ከባቢሎን ግዞት ነጻ ወጥተው ወደ አገራቸው በተመለሱበት ጊዜ የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል። በዘመናችን ደግሞ ትንቢቱ ተፈጻሚነቱን ያገኘው ‘በአምላክ እስራኤል’ ላይ ነው። (ገላትያ 6:16) ከ1919 ጀምሮ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “በጕረኖ ውስጥ እንዳሉ በጎች” ሲሰበሰቡ ቆይተዋል። የቅቡዓኑ ክፍል፣ በተለይ ከ1935 ወዲህ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል ከሆኑት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ጋር ስለተቀላቀለ ‘በሕዝብ ተሞልቷል።’ (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ክርስቲያኖች አንድ ላይ ሆነው እውነተኛውን አምልኮ በቅንዓት እያስፋፉ ነው።

4:1-4—“በመጨረሻው ዘመን” ይሖዋ ‘በብዙ ሕዝብ መካከል የሚፈርደውና በኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት የሚያቆመው’ እንዴት ነው? “ብዙ ሕዝብ” እና “ኀያላን መንግሥታት” የሚሉት አገላለጾች ብሔራትን ወይም የፖለቲካ ድርጅቶችን አያመለክቱም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ አገላለጾች የሚያመለክቱት ከሁሉም ብሔራት ተውጣጥተው የይሖዋ አምላኪዎች የሆኑትን ሰዎች ነው። ይሖዋ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በተያያዘ የሚፈርደው እንዲሁም ግጭቶችን የሚያስቆመው በመንፈሳዊ ሁኔታ ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:6, 9፤ 3:12፤ 5:2 ሰማርያ፣ በሚክያስ የሕይወት ዘመን በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሦራውያን ጠፍታለች። (2 ነገሥት 17:5, 6) አሦራውያን በሕዝቅያስ የግዛት ዘመን እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ዘልቀው ገብተው ነበር። (2 ነገሥት 18:13) በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በእሳት አጋዩዋት። (2 ዜና መዋዕል 36:19) በትንቢት እንደተነገረው መሲሑ የተወለደው ‘በቤተ ልሔም ኤፍራታ’ ነበር። (ማቴዎስ 2:3-6) ይሖዋ ያስነገረው ትንቢት አንዱም ሳይፈጸም አይቀርም።

2:1, 2 ይሖዋን እናገለግላለን እያልን የአምላክን ‘መንግሥትና ጽድቁን’ ከማስቀደም ይልቅ ሀብትን ማሳደድ ምንኛ አደገኛ ነው!—ማቴዎስ 6:33፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

3:1-3, 5 ይሖዋ በሕዝቡ መካከል ያሉት ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ፍትሕን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል።

3:4 ይሖዋ ጸሎታችንን እንዲሰማን ከፈለግን ኃጢአት መሥራትም ሆነ ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር የለብንም።

3:8 የፍርድ መልእክት መናገርን የሚጨምረውን ምሥራች እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልእኮ መፈጸም የምንችለው ከይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ብርታት ካገኘን ብቻ ነው።

5:5 ይህ መሲሐዊ ትንቢት የአምላክ ሕዝቦች ከጠላቶቻቸው ጥቃት ሲሰነዘርባቸው “ሰባት [ሙላትን ያመለክታል] እረኞች” እንዲሁም “ስምንት አለቆች” ማለትም በርከት ያሉ ብቃት ያላቸው ወንዶች በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ኃላፊነት ለመውሰድ እንደሚነሱ ያረጋግጥልናል።

5:7, 8 በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል” ለብዙዎች ከአምላክ የተገኘ በረከት ሆነውላቸዋል። ይህ የሆነው ይሖዋ የመንግሥቱን ምሥራች ለማወጅ በቅቡዓኑ ስለሚጠቀም ነው። “ሌሎች በጎች” በስብከቱ ሥራ ከቅቡዓኑ ጋር በቅንዓት በመካፈል ሰዎች ከአምላክ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ይረዳሉ። (ዮሐንስ 10:16) ሌሎችን በመንፈሳዊ በሚያድሰው በዚህ ሥራ መካፈል እንዴት ያለ መብት ነው!

6:3, 4 በመንፈሳዊ ለደከሙ ወይም በጣም አስቸጋሪ ለሆኑ ሰዎች ደግነትና ርኅራኄ በማሳየት ይሖዋ አምላክን መምሰል አለብን።

7:7 በዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ ላይ ስንኖር በሚያጋጥሙን ችግሮች ተስፋ መቁረጥ የለብንም። ከዚህ ይልቅ እንደ ሚክያስ ‘አምላካችንን ልንጠብቅ’ ይገባል።

7:18, 19 ይሖዋ ስሕተቶቻችንን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ ሁሉ እኛም ሌሎች ሲበድሉን ይቅር ለማለት ፈቃደኞች መሆን አለብን።

‘በይሖዋ ስም መሄዳችንን’ እንቀጥል

ከአምላክና ከሕዝቦቹ ጋር የሚዋጉ ሰዎች ‘ለዘላለም ይጠፋሉ።’ (አብድዩ 10) ሆኖም የይሖዋን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ሰምተን ‘ከክፉ መንገድ ከተመለስን’ የይሖዋ ቁጣ ይመለሳል። (ዮናስ 3:10) በምንኖርበት ‘የመጨረሻ ዘመን’ እውነተኛው አምልኮ ከሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ልቆ የሚታይ ሲሆን ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ደግሞ ወደ እውነተኛው አምልኮ እየጎረፉ ነው። (ሚክያስ 4:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) በመሆኑም ‘በአምላካችን በይሖዋ ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለመሄድ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!—ሚክያስ 4:5

የአብድዩ፣ የዮናስና የሚክያስ መጻሕፍት እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ይዘውልናል! ከ2,500 ዓመታት በፊት የተጻፉ ቢሆንም የያዙት መልእክት በጊዜያችንም እንኳ “ሕያውና የሚሠራ” ነው።—ዕብራውያን 4:12

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤዶም ‘ለዘላለምም እንደሚጠፋ’ አብድዩ ትንቢት ተናግሯል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚክያስ ይሖዋን ‘እንደጠበቀ’ ሁሉ አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስብከቱ ሥራ ከፍ አድርገን ልንመለከተው የሚገባ ታላቅ መብት ነው