በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ቃል ምንጊዜም ይፈጸማል

የይሖዋ ቃል ምንጊዜም ይፈጸማል

የይሖዋ ቃል ምንጊዜም ይፈጸማል

‘አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ አላስቀረባችሁም፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።’—ኢያሱ 23:14

1. ኢያሱ ማን ነበር? ወደ ሕይወቱ መገባደጃ ሲቃረብስ ምን አደረገ?

 ኃያልና ደፋር የጦር አዛዥ ከመሆኑም በላይ ጽኑ አቋም ያለው የእምነት ሰው ነበር። ይህ ሰው ከሙሴ ጋር የነበረ ሲሆን ይሖዋም የእስራኤልን ብሔር እየመራ አስፈሪ የሆነውን ምድረ በዳ አሻግሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲያስገባቸው መርጦታል። ኢያሱ የተባለው ይህ እጅግ የተከበረ ሰው ወደ ሕይወቱ መገባደጃ ሲዳረስ ለእስራኤል አለቆች ልብ የሚነካ የመሰናበቻ ንግግር አቀረበ። በዚያን ጊዜ ንግግሩ የአድማጮቹን እምነት እንዳጠናከረላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ንግግሩ የአንተንም እምነት ሊያጠናክርልህ ይችላል።

2, 3. ኢያሱ ለእስራኤል አለቆች ንግግር ባቀረበበት ወቅት እስራኤላውያን በምን ሁኔታ ላይ ይገኙ ነበር? እሱስ ምን አላቸው?

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት:- “እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው እነሆ፣ ብዙ ዘመን አለፈ፤ በዚህ ጊዜ ኢያሱ በጣም አርጅቶ፣ ዕድሜውም ገፍቶ ነበር፤ ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ አለቆቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ፈራጆቻቸውንና ሹማምንታቸውን በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ ‘እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቶአል።’”—ኢያሱ 23:1, 2

3 ኢያሱ በአምላክ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ክስተቶች በተከናወኑበት ዘመን የኖረ ሲሆን ዕድሜው ወደ 110 ዓመት እየተጠጋ ነበር። ይሖዋ ታላላቅ ሥራዎችን ሲያከናውን እንዲሁም ቃል የገባቸውን ነገሮች ሲፈጽም ተመልክቷል። በመሆኑም ከግል ተሞክሮው በመነሳት እንደሚከተለው በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል:- “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።”—ኢያሱ 23:14

4. ይሖዋ ለእስራኤላውያን ምን ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር?

4 ይሖዋ ከሰጣቸው ተስፋዎች መካከል ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኙት የትኞቹ ናቸው? ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሦስት ተስፋዎች እንመረምራለን። በመጀመሪያ አምላክ ከባርነት ነጻ አውጥቷቸዋል። ሁለተኛ፣ ለሕዝቦቹ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። ሦስተኛ ደግሞ ሕዝቦቹን ተንከባክቧቸዋል። ይሖዋ በዘመናችንም ለሕዝቦቹ ተመሳሳይ ቃል የገባላቸው ሲሆን እኛም እነዚህ ተስፋዎች ሲፈጸሙ በሕይወታችን ውስጥ ተመልክተናል። ይሖዋ በዘመናችን ያከናወናቸውን ነገሮች ከማየታችን በፊት በኢያሱ ጊዜ ምን እንዳደረገ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ ሕዝቡን ነጻ ያወጣል

5, 6. ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣቸው እንዴት ነበር? ይህስ ምን አሳይቷል?

5 እስራኤላውያን በግብጽ ባሪያዎች በነበሩበት ወቅት ከደረሰባቸው ግፍ የተነሳ ወደ አምላክ የጮኹ ሲሆን እሱም ሰምቷቸዋል። (ዘፀአት 2:23-25) ይሖዋ በእሳት ከተያያዘው ቁጥቋጦ መሃል ለሙሴ እንዲህ አለው:- “[ሕዝቤን] ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈሰው ሰፊና ለም ወደ ሆነችው . . . ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ።” (ዘፀአት 3:8) ይሖዋ ይህንን ሲፈጽም መመልከት ምንኛ አስደሳች ይሆን! ፈርዖን፣ እስራኤላውያን ግብጽን ለቅቀው እንዲወጡ ለመፍቀድ እምቢተኛ ሲሆን አምላክ የአባይን ወንዝ ወደ ደም እንደሚለውጠው በሙሴ በኩል ነገረው። ይሖዋ የተናገረውም ተፈጽሟል። የአባይ ወንዝ ወደ ደም ተለወጠ። በዚህ ምክንያት ዓሦቹ የሞቱ ሲሆን ግብጻውያንም ውኃውን ሊጠጡት አልቻሉም። (ዘፀአት 7:14-21) ፈርዖን ግን ልቡን በማደንደኑ ይሖዋ ሌሎች ዘጠኝ መቅሠፍቶችን አመጣበት፤ እያንዳንዱን መቅሠፍት ከማምጣቱ በፊት አስቀድሞ ያስጠነቅቀው ነበር። (ዘፀአት ምዕራፍ 8 እስከ 12) በአሥረኛው መቅሠፍት የግብጻውያን የበኩር ልጆች ከሞቱ በኋላ ግን ፈርዖን፣ እስራኤላውያን እንዲወጡ አዘዘ፤ እነሱም ግብጽን ለቅቀው ወጡ!—ዘፀአት 12:29-32

6 ይሖዋ እስራኤላውያንን በዚህ ሁኔታ ነጻ ማውጣቱ የተመረጡ ሕዝቦቹ አድርጎ እንዲቀበላቸው መንገድ ከፈተ። ይህ ክንውን ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም አምላክ እንደሆነና የተናገረው ነገር አንድም ሳይቀር እንደሚፈጸም ጎላ አድርጎ አሳይቷል። እንዲሁም ይሖዋ ከአሕዛብ አማልክት የላቀ እንደሆነ አመልክቷል። ሕዝቦቹን ነጻ ስላወጣበት መንገድ የሚናገረውን ይህን ታሪክ ስናነብ የእኛም እምነት ይጠናከራል። ይህ ሁኔታ ሲፈጸም የተመለከቱት ሰዎች ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል አስበው! ይሖዋ “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” መሆኑን ኢያሱ ተመልክቷል።—መዝሙር 83:18

ይሖዋ ሕዝቡን ይጠብቃል

7. የፈርዖን ሠራዊት፣ እስራኤላውያንን ድል እንዳያደርጋቸው ይሖዋ ጥበቃ ያደረገላቸው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ስለሚገልጸው ስለ ሁለተኛው ማረጋገጫስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ፣ ሕዝቡን ከግብጽ ነጻ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚያስገባቸው ቃል ሲገባ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸውም ማረጋገጫ መስጠቱ ነበር። በንዴት የበገነው ፈርዖን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠረገሎች ያሉትን ኃያል ሠራዊቱን አስከትሎ እስራኤላውያንን እንዳሳደዳቸው አስታውስ። በተለይ እስራኤላውያን በተራሮቹና በባሕሩ መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ በመሰለበት ወቅት ይህ እብሪተኛ ሰው ምን ያህል በራሱ ተማምኖ እንደነበር ማሰብ ይቻላል! በዚህ ወቅት አምላክ ሕዝቡን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲል በእስራኤላውያንና በግብጻውያን መካከል ደመና እንዲኖር አደረገ። በግብጻውያን በኩል ጨለማ ሲሆን በእስራኤላውያን ወገን ግን ብርሃን ነበር። ደመናው ግብጻውያኑ ወደፊት እንዳይገፉ ሲያግዳቸው ሙሴ በትሩን በማንሳት ቀይ ባሕርን ከፈለው፤ በዚህ ሁኔታ እስራኤላውያን የሚያመልጡበት መንገድ ሲከፈትላቸው ለግብጻውያን ግን ወጥመድ ተዘጋጀላቸው። ይሖዋ የፈርዖንን ኃያል ሠራዊት ድምጥማጡን በማጥፋት እስራኤላውያንን ግብጻውያን ድል እንዳያደርጓቸው ጥበቃ አድርጎላቸዋል።—ዘፀአት 14:19-28

8. እስራኤላውያን (ሀ) በምድረ በዳ እያሉ (ለ) ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ ይሖዋ ጥበቃ ያደረገላቸው እንዴት ነበር?

8 እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ከተሻገሩ በኋላ “ጭልጥ ባለና አስፈሪ ምድረ በዳ፣ . . . በሚያስጠማና ውሃ በማይገኝበት ደረቅ መሬት፣ መርዘኛ እባብና ጊንጥ ባለበት ምድረ በዳ” ተጉዘዋል። (ዘዳግም 8:15) በዚያ ምድረ በዳም ቢሆን ይሖዋ ለሕዝቦቹ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡስ ይሖዋ ጥበቃ አድርጎላቸው ነበር? ኃያል የሆኑ የከነዓናውያን ሠራዊቶች ጥቃት ቢሰነዝሩባቸውም ይሖዋ ኢያሱን እንዲህ አለው:- “አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሡ፤ ለእሥራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ። በሕይወት በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ሁሉ ከአንተም ጋር እሆናለሁ፤ ከቶ አልጥልህም፤ አልተውህም።” (ኢያሱ 1:2, 5) ይሖዋ ይህንን ቃሉን ፈጽሟል። ኢያሱ ወደ ስድስት ዓመት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ 31 ነገሥታትን ድል ያደረገ ሲሆን አብዛኛውን የተስፋይቱን ምድርም ተቆጣጥሯል። (ኢያሱ 12:7-24) ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ ባያደርግላቸው ኖሮ እንዲህ ያለ ድል መቀዳጀት ፈጽሞ አይችሉም ነበር።

ይሖዋ ሕዝቡን ይንከባከባል

9, 10. ይሖዋ ሕዝቡን በምድረ በዳ የተንከባከበው እንዴት ነበር?

9 ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚንከባከብ የሰጠውን ሦስተኛውን ማረጋገጫ ደግሞ እንመልከት። እስራኤላውያን ከግብጽ ነጻ ከወጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አምላክ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ። ሕዝቡም በየቀኑ እየወጡ ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰበስቡ” በማለት ቃል ገባላቸው። በእርግጥም አምላክ “ከሰማይ እንጀራ” አዝንቦላቸዋል። “እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ . . . እርስ በርሳቸው፣ ‘ይህ ነገር ምንድን ነው?’ ተባባሉ።” እስራኤላውያን ያዩት ይሖዋ ቃል የገባላቸውን እንጀራ ማለትም መና ነበር።—ዘፀአት 16:4, 13-15

10 እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ይሖዋ ምግብና ውኃ በመስጠት ተንከባክቧቸዋል። ሌላው ቀርቶ ልብሳቸው እንዳያልቅና እግራቸው እንዳያብጥ አድርጓል። (ዘዳግም 8:3, 4) ኢያሱም ይህንን ሁሉ ተመልክቷል። ይሖዋ፣ ቃል በገባው መሠረት ሕዝቡን ነጻ አውጥቷቸዋል፣ ጥበቃ አድርጎላቸዋል እንዲሁም ተንከባክቧቸዋል።

ይሖዋ በዘመናችን ሕዝቡን ነጻ አውጥቷል

11. በ1914 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወንድም ራስል ምን ማስታወቂያ ተናገረ? የትኛው ክንውን የሚፈጸምበት ጊዜ ደርሶ ነበር?

11 ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? ጥቅምት 2, 1914 ዓርብ ዕለት በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ሥራ በበላይነት ይከታተል የነበረው ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ቤቴል ወደሚገኘው የመመገቢያ አዳራሽ ከገባ በኋላ ፈገግ ብሎ “እንደምን አደራችሁ” አለ። ከዚያም ከመቀመጡ በፊት “የአሕዛብ ዘመን ተፈጸመ፤ ነገሥታቶቻቸውም ጊዜያቸው አበቃ” በማለት በደስታ ተናገረ። የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል እንደገና እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ደርሶ ነበር። በእርግጥም ይሖዋ እርምጃ ወስዷል!

12. በ1919 ይሖዋ ሕዝቦቹን ከምን ነጻ አውጥቷቸዋል? ይህስ ምን ውጤቶች አስገኝቷል?

12 ወንድም ራስል ከላይ ያለውን ከተናገረ ከአምስት ዓመታት በኋላ ይሖዋ፣ ሕዝቡን “ታላቂቱ ባቢሎን” ከተባለችው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ነጻ አወጣቸው። (ራእይ 18:2) አብዛኞቻችን ይሖዋ ሕዝቡን ነጻ ያወጣበትን ይህን አስደሳች ክንውን አላየንም። ያም ሆኖ፣ ይህ ክንውን ያስከተላቸውን ውጤቶች በግልጽ እየተመለከትን ነው። ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ መልሶ ያቋቋመ ሲሆን እሱን ለማምለክ የሚናፍቁ ሰዎችም አንድነት እንዲኖራቸው አድርጓል። ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን ሁኔታ እንደሚከተለው በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር:- “በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ።”—ኢሳይያስ 2:2

13. የይሖዋ ሕዝቦች ምን ያህል ጭማሪ ሲያደርጉ ተመልክተሃል?

13 ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። በ1919 በመንፈስ የተቀቡት ቀሪዎች በዓለም ዙሪያ በድፍረት መስበክ የጀመሩ ሲሆን ይህም የእውነተኛው አምላክ አምልኮ ከፍ እንዲል አድርጓል። በ1930ዎቹ ዓመታት “ሌሎች በጎች” እየተሰበሰቡ እንደሆነ ግልጽ ሆነ። (ዮሐንስ 10:16) በመጀመሪያ በሺዎች፣ ከዚያም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጎረፉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከንጹሕ አምልኮ ጎን እየተሰለፉ ነው! እነዚህ ሰዎች ሐዋርያው ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ “ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተብለው ተገልጸዋል። (ራእይ 7:9) በአንተ የሕይወት ዘመንስ ምን ሲከናወን ተመልክተሃል? መጀመሪያ እውነትን ስትሰማ በምድር ዙሪያ ምን ያህል የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ? በዛሬው ጊዜ ይሖዋን የሚያገለግሉ ከ6,700,000 የሚበልጡ ሰዎች አሉ። ይሖዋ፣ ሕዝቡን ከታላቂቱ ባቢሎን ነጻ በማውጣቱ በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ለሚታየው አስደናቂ ጭማሪ መንገድ ከፍቷል።

14. ይሖዋ ወደፊት ምን የማዳን እርምጃ ይወስዳል?

14 በምድር ዙሪያ የሚገኙትን የሰው ዘሮች በሙሉ የሚያካትት ሌላ የማዳን ድርጊትም በቅርቡ ይፈጸማል። ይሖዋ በጣም አስደናቂ የሆነውን ኃይሉን በመጠቀም የሚቃወሙትን በሙሉ ያጠፋል፤ እንዲሁም ሕዝቡን በማዳን ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። ክፋት በሙሉ ተወግዶ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ልዩ የሆነ አስደናቂ ዘመን ሲጠባ ማየት እንዴት የሚያስደስት ይሆናል!—ራእይ 21:1-4

ይሖዋ በዘመናችን ለሕዝቡ ጥበቃ ያደርጋል

15. በዘመናችን የይሖዋን ጥበቃ ማግኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው በኢያሱ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን የይሖዋ ጥበቃ አስፈልጓቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች ሁኔታስ ከዚህ የተለየ ነው? በፍጹም! ኢየሱስ ተከታዮቹን “ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል፣ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴዎስ 24:9) ባለፉት ዓመታት፣ በበርካታ አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ተቃውሞና ጭካኔ የተሞላበት ስደት ደርሶባቸዋል። ያም ሆኖ በግልጽ ለማየት እንደምንችለው ይሖዋ ሕዝቡን እየደገፋቸው ነው። (ሮሜ 8:31) ‘በእኛ ላይ የተበጀ [ማንኛውም] መሣሪያ’ ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክና የማስተማር ሥራችንን እንደማያስቆመው የአምላክ ቃል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ኢሳይያስ 54:17

16. ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ምን ማስረጃ ተመልክተሃል?

16 የይሖዋ ሕዝቦች፣ ዓለም ቢጠላቸውም ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በ236 አገሮች ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ሥራቸውን እያከናወኑ ሲሆን ይህም ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነና እኛን ለማጥፋትም ሆነ ዝም ለማሰኘት ከሚጥሩ ሰዎች እንደሚጠብቀን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው። በአንተ የሕይወት ዘመን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ጭቆና ያደረሱ ኃያል የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት መሪዎችን ስም መጥቀስ ትችላለህ? እነዚህ ሰዎች ምን ደርሶባቸዋል? በአሁኑ ጊዜስ የት ናቸው? ብዙዎቹ በሙሴና በኢያሱ ዘመን እንደነበረው ፈርዖን አሁን በሕይወት የሉም። ይሁን እንጂ በዘመናችን ታማኝነታቸውን ጠብቀው ስለሞቱት የአምላክ አገልጋዮችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ክርስቲያኖች በይሖዋ የመታሰቢያ መዝገብ ላይ ሰፍረዋል። ደግሞም ከዚህ የተሻለ አስተማማኝ ቦታ የለም። በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ይሖዋ ለሕዝቦቹ ጥበቃ እንደሚያደርግ የገባውን ቃል ፈጽሟል።

ይሖዋ በዘመናችን ሕዝቡን ይንከባከባል

17. ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ እንደምናገኝ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?

17 ይሖዋ ሕዝቡን በምድረ በዳ እንደተንከባከባቸው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ይንከባከባቸዋል። ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ እያገኘን ነው። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ለዘመናት ምስጢር የነበሩ መንፈሳዊ እውነቶችን ማወቅ ችለናል። አንድ መልአክ ዳንኤልን እንዲህ ብሎት ነበር:- “እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የመጽሐፉን ቃል ዝጋ፤ አትመውም። ብዙዎች ወዲያ ወዲህ ይራወጣሉ፤ ዕውቀትም ይበዛል።”—ዳንኤል 12:4

18. በዛሬው ጊዜ እውነተኛ እውቀት በዝቷል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

18 የምንኖረው በፍጻሜው ዘመን ሲሆን እውነተኛ እውቀትም እየበዛ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ፣ እውነትን የሚወዱ ሰዎች ስለ እውነተኛው አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ መንፈስ ቅዱስ ረድቷቸዋል። በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ውድ እውነት እንዲረዱ የሚያስችሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በምድር ዙሪያ በስፋት ተሰራጭተዋል። ለአብነት ያህል፣ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? a የተባለውን የማስጠኛ መጽሐፍ ማውጫ ተመልከት። በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኙት ምዕራፎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- “አምላክን በተመለከተ ትክክለኛው ትምህርት የቱ ነው?”፣ “ሙታን የት ናቸው?”፣ “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” እንዲሁም “አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሰው ልጆች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት እነዚህን ጥያቄዎች ሲያነሱ ቆይተዋል። አሁን ግን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሳያውቁ በርካታ ዘመናት ከማለፋቸውም በላይ ሕዝበ ክርስትና የክህደት ትምህርት ስታስተምር ቆይታለች፤ ያም ሆኖ የአምላክ ቃል ይሖዋን ለማገልገል የሚናፍቁ ሰዎች በሙሉ እውቀት እንዲያገኙ በማድረግ እያሸነፈ ነው።

19. የትኞቹ ተስፋዎች ሲፈጸሙ ተመልክተሃል? ከዚህ አንጻር ምን ድምዳሜ ላይ ደርሰሃል?

19 በእርግጥም እኛ ራሳችን ከተመለከትናቸው ነገሮች አንጻር እንዲህ ማለት እንችላለን:- “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ . . . ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 23:14) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹን ነጻ ያወጣቸዋል፣ ጥበቃ ያደርግላቸዋል እንዲሁም ይንከባከባቸዋል። ይሖዋ በቀጠረው ጊዜ ሳይፈጽመው የቀረ ተስፋ ልትጠቅስ ትችላለህ? በፍጹም አትችልም። በመሆኑም አስተማማኝ በሆነው የአምላክ ቃል ላይ ሙሉ እምነት ማሳደራችን አስተዋይነት ነው።

20. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

20 ስለ ወደፊቱ ጊዜስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ፣ አብዛኞቻችን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንደምንኖር ተስፋ ሰጥቶናል። ከመካከላችን ጥቂቶች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ አላቸው። ተስፋችን ምንም ይሁን ምን እንደ ኢያሱ ታማኝ ሆነን ለመኖር የሚያበቃ ምክንያት አለን። ተስፋችን እውን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። ያን ጊዜ ይሖዋ የሰጠንን ተስፋዎች መለስ ብለን በማሰብ እኛም “አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል” እንላለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ኢያሱ፣ ይሖዋ የሰጣቸው የትኞቹ ተስፋዎች ሲፈጸሙ ተመልክቷል?

• አንተ በግልህ የትኞቹ መለኮታዊ ተስፋዎች ሲፈጸሙ ተመልክተሃል?

• የአምላክን ቃል በተመለከተ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት ጣልቃ ገብቷል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በቀይ ባሕር ለሕዝቡ ጥበቃ ያደረገላቸው እንዴት ነበር?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ሕዝቡን በምድረ በዳ የተንከባከበው እንዴት ነበር?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ሕዝቡን ይንከባከባል