ሉቃስ—የተወደደው የሥራ ባልደረባ
ሉቃስ—የተወደደው የሥራ ባልደረባ
ጊዜው 65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲሆን ቦታው ደግሞ ሮም ነው። ሉቃስ፣ በእምነቱ ምክንያት ለፍርድ ቀርቦ የነበረው የጳውሎስ ጓደኛ መሆኑን ሰዎች ማወቃቸው አደጋ እንዳለው ተገንዝቧል። ጳውሎስ የሞት ፍርድ ሳይበየንበት አልቀረም። ይሁንና በዚህ አደገኛ ወቅት ከጎኑ የነበረው ሉቃስ ብቻ ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 4:6, 11
ሉቃስ የጻፈው ወንጌል በስሙ ስለተሰየመ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ይህን ስም በደንብ ያውቁታል። ሉቃስ፣ ‘የተወደደው ሐኪም’ እና ‘አብሮኝ የሚሠራ’ ብሎ ከጠራው ከጳውሎስ ጋር ረጃጅም ጉዞዎችን አድርጓል። (ቈላስይስ 4:14፤ ፊልሞና 24) ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ ሉቃስ የሚሰጡት መረጃ ውስን ሲሆን ስሙ ተጠቅሶ የሚገኘውም ሦስት ጊዜ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ሉቃስን የተመለከቱ አንዳንድ ሐሳቦችን ስትመረምር አንተም ጳውሎስ ለዚህ ታማኝ ክርስቲያን የነበረውን አድናቆት እንደምትጋራ አያጠራጥርም።
ጸሐፊና ሚስዮናዊ
የሉቃስ ወንጌልም ሆነ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተጻፉት ለቴዎፍሎስ መሆኑ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን እነዚህን መጻሕፍት ያጠናቀረው ሉቃስ እነደሆነ ይጠቁማል። (ሉቃስ 1:3፤ የሐዋርያት ሥራ 1:1) ሉቃስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን ሲያከናውን አብሮት እንደነበር አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ መረጃውን ያገኘው ከዓይን ምሥክሮች እንደሆነና ‘ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ መርምሮ’ እንደጻፈ ገልጿል። (ሉቃስ 1:1-3) በመሆኑም ሉቃስ የክርስቶስ ተከታይ የሆነው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ33 የጰንጠቆስጤ በዓል ከተከበረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሳይሆን አይቀርም።
አንዳንዶች ሉቃስ በሶርያ የምትገኘው አንጾኪያ ተወላጅ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በአንጾኪያ ስለተከናወኑት ነገሮች ዝርዝር ሐሳቦችን መያዙን እንዲሁም ‘ስለተመሰከረላቸው’ ሰባት ሰዎች ሲናገር ስድስቱ የመጡበትን ከተማ ሳይገልጽ አንደኛው ግን ‘ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረ አንጾኪያዊ’ እንደሆነ መግለጹን ምክንያት አድርገው ያቀርባሉ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ነገሮች አንጾኪያ የሉቃስ የትውልድ ቦታ ነች ብለን በእርግጠኝነት እንድንናገር አያስችሉንም።—የሐዋርያት ሥራ 6:3-6
የሉቃስ ስም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ ባይገኝም በዘገባቸው አንዳንድ ክንውኖች ላይ ተካፋይ እንደነበር የሚጠቁሙ ሐሳቦችን አስፍሯል። ሉቃስ፣ ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ በትንሿ እስያ ስላደረጉት ጉዞ ሲገልጽ “በሚስያ በኩል አድርገው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ” ብሏል። ጳውሎስ፣ አንድ የመቄዶንያ ሰው “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” በማለት ሲማጸነው በራእይ የተመለከተው በጢሮአዳ ሳለ ነበር። አክሎም ሉቃስ “ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ፣ . . . ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 16:8-10) ሉቃስ ‘እነሱ’ ሲል ቆይቶ በኋላ ላይ ‘እኛ’ ማለቱ ከጳውሎስና ከጉዞ ጓደኞቹ ጋር አብሮ ማገልገል የጀመረው በጢሮአዳ እንደነበር ያመለክታል። ከዚያም ሉቃስ በፊልጵስዩስ ስለተከናወነው የስብከት እንቅስቃሴ ሲዘግብ በሥራው ላይ ተካፋይ እንደነበር የሚያሳይ አገላለጽ ተጠቅሟል። እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “በሰንበት ቀንም፣ የጸሎት ስፍራ በመፈለግ፣ ከከተማዪቱ በር ወጥተን ወደ አንድ ወንዝ ወረድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን።” በዚህም የተነሳ ልድያ እና ቤተሰቦቿ ምሥራቹን ተቀብለው ተጠመቁ።—የሐዋርያት ሥራ 16:11-15
ጳውሎስ “በጥንቈላ መንፈስ” ትንቢት የምትናገርን አንዲት የሐዋርያት ሥራ 16:16-40፤ 20:5, 6) በመሆኑም ሉቃስ በፊልጵስዩስ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ በበላይነት ለመከታተል እዚያው ቆይቶ ሊሆን ይችላል።
አገልጋይ በፈወሰበት በፊልጵስዩስ ከተማ ተቃውሞ ገጠማቸው። የልጅቷ አሳዳሪዎች የገቢ ምንጫቸው እንደተቋረጠ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ያዟቸው፤ ከዚያም ሕዝቡ ከደበደባቸው በኋላ ወደ ወኅኒ አስገባቸው። ሉቃስ የአገልግሎት ጓደኞቹ ስለደረሰባቸው እንግልት ሲገልጽ ራሱን አለመጨመሩ አብሯቸው አለመታሰሩን ያሳያል። ጳውሎስና ሲላስ ከእስር ሲፈቱ “ወንድሞችን አግኝተው አበረታቷቸው፤ ከዚያም በኋላ ሄዱ።” ከዚያ በኋላ ሉቃስ በዘገባው ውስጥ ራሱን እያስገባ መጻፍ የጀመረው ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ በተመለሰበት ወቅት ነበር። (መረጃ ማሰባሰብ
ሉቃስ በጻፈው ወንጌልም ሆነ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ያሰፈረውን መረጃ ያገኘው እንዴት ነው? ሉቃስ ራሱን በታሪኩ ውስጥ እንዳለ አድርጎ የጻፋቸው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ክፍሎች ጳውሎስ ከፊልጵስዩስ ተነስቶ ዳግመኛ ለእስር ወደተዳረገባት ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው ጉዞ አብሮት እንደነበር ይጠቁማሉ። ጳውሎስና አብረውት የነበሩት ሰዎች በጉዟቸው ወቅት በቂሳርያ በሚኖረው በወንጌላዊው ፊሊጶስ ቤት ለተወሰኑ ቀናት ተቀምጠዋል። (የሐዋርያት ሥራ 20:6፤ 21:1-17) ሉቃስ በሰማርያ ስለተከናወነው የቀድሞ ሚስዮናዊ እንቅስቃሴ የሚገልጸውን መረጃ ለማግኘት በከተማዋ የተካሄደውን የስብከት ሥራ በግንባር ቀደምትነት ሲያከናውን ከነበረው ከፊሊጶስ መጠየቅ ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 8:4-25) ይሁንና ሉቃስ ሌሎች መረጃዎችን ያገኘው ከየት ነው?
ጳውሎስ በቂሳርያ ታስሮ የቆየባቸው ሁለት ዓመታት ሉቃስ በወንጌል መጽሐፉ ውስጥ ያሰፈራቸውን መረጃዎች ለማሰባሰብ አጋጣሚ ሳይሰጡት አልቀሩም። ኢየሩሳሌም ከቂሳርያ ብዙም ስለማትርቅ ሉቃስ የኢየሱስን የዘር ሐረግ የሚገልጹ ዘገባዎችን ማግኘት ይችል ነበር። ሉቃስ፣ እሱ በጻፈው ወንጌል ውስጥ ብቻ የሚገኙ ከኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ጋር የተያያዙ በርካታ ክንውኖችን ዘግቧል። አንድ ምሑር በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ብቻ የሚገኙ ከ82 ያላነሱ ክንውኖችን ዘርዝረዋል።
ሉቃስ፣ አጥማቂው ዮሐንስ ሲወለድ ስለነበሩት ሁኔታዎች ያወቀው ከዮሐንስ እናት ማለትም ከኤልሳቤጥ ጠይቆ ሊሆን ይችላል። ስለ ኢየሱስ አወላለድና የልጅነት ሕይወት ዝርዝር መረጃዎችን ያገኘው እናቱን ማርያምን በመጠየቅ ይሆናል። (ሉቃስ 1:5 እስከ 2:52) በተአምር ስለተያዙት ዓሦች የነገረው ጴጥሮስ ወይም ያዕቆብ አሊያም ዮሐንስ ሳይሆን አይቀርም። (ሉቃስ 5:4-10) ኢየሱስ የተናገራቸው አንዳንድ ምሳሌዎች በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ብቻ የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ስለ ደጉ ሳምራዊ፣ በጠባቡ በር ለመግባት ስለመጣጣር፣ ስለ ጠፋው የብር ሳንቲም፣ ስለ አባካኙ ልጅ እንዲሁም ስለ ሀብታሙ ሰውና ስለ አልዓዛር የሚናገሩት ምሳሌዎች ይገኙበታል።—ሉቃስ 10:29-37፤ 13:23, 24፤ 15:8-32፤ 16:19-31
ሉቃስ ሰዎች ስላደረጓቸው ዝርዝር ጉዳዮች የማወቅ ጉጉት ነበረው። ማርያም ስላቀረበችው የመንጻት መሥዋዕት፣ ከሞት ስለተነሳው የአንዲት መበለት ልጅ እንዲሁም የኢየሱስን እግር ሽቶ ስለቀባች አንዲት ሴት ዘግቧል። ሉቃስ ክርስቶስን ያገለግሉ ስለነበሩ ሴቶች እንዲሁም ማርታና ማርያም ኢየሱስን በእንግድነት ስለመቀበላቸው ጽፏል። የሉቃስ ወንጌል አንዲት የጎበጠች ሴት እና ሰውነቱ ያበጠ አንድ ሰው ስለመፈወሳቸው እንዲሁም ለምጽ የነበረባቸው አሥር ሰዎች ስለመንጻታቸው ይናገራል። በተጨማሪም ኢየሱስን ለማየት ዛፍ ላይ ስለወጣው አጭሩ ዘኬዎስና ከክርስቶስ ጎን ተሰቅሎ የነበረው ወንጀለኛ ስላሳየው የንስሐ ዝንባሌ ዘግቧል።—ሉቃስ 2:24፤ 7:11-17, 36-50፤ 8:2, 3፤ 10:38-42፤ 13:10-17፤ 14:1-6፤ 17:11-19፤ 19:1-10፤ 23:39-43
የሉቃስ ወንጌል፣ ስለ ደጉ ሳምራዊ በሚገልጸው የኢየሱስ ምሳሌ ላይ ሳምራዊው የተጎዳውን ሰው ለማከም ስላደረጋቸው ነገሮች ዝርዝር መረጃ የሰፈረበት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ሉቃስ ሐኪም ስለነበር ትኩረቱ በመሳቡ ሳይሆን አይቀርም ኢየሱስ፣ ደጉ ሳምራዊ ሰውየውን ለማከም ስላደረጋቸው ጥረቶች የተናገራቸውን ዝርዝር ሐሳቦች አስፍሯል። ዘገባው ሳምራዊው ለቁስል ማጠቢያነት የሚያገለግለውን ወይንና ሕመም ሊያስታግስ የሚችለውን ዘይት መጠቀሙን ጨምሮ የሰውየውን ቁስል በጨርቅ ማሰሩን ይገልጻል።—ሉቃስ 10:30-37
ሉቃስ በእስር ላይ የነበረውን ጳውሎስን ተንከባክቦታል
ሉቃስ የሐዋርያው ጳውሎስ ሁኔታ ያሳስበው ነበር። ጳውሎስ በቂሳርያ ታስሮ በነበረበት ወቅት ሮማዊው አገረ ገዥ ፊልክስ ‘ወዳጆቹ እንዲጠይቁት ፈቃድ’ ሰጥቶ ነበረ። (የሐዋርያት ሥራ 24:23) ከእነዚህ መካከል ሉቃስ እንደሚገኝበት አያጠራጥርም። ጳውሎስ ብዙም ጤና ስላልነበረው ይህ ‘የተወደደ ሐኪም’ ከሚያደርግለት እርዳታ መካከል አንዱ ጤንነቱን መንከባከብ ሳይሆን አይቀርም።—ቈላስይስ 4:14፤ ገላትያ 4:13
ጳውሎስ ለቄሳር ይግባኝ ሲል ሮማዊው ገዥ ፊስጦስ ሐዋርያውን ወደ ሮም ላከው። ሉቃስ፣ ጳውሎስ ወደ ጣሊያን ባደረገው በዚህ ረዥም ጉዞ ከጎኑ የነበረ ሲሆን በጉዞው ላይ ስላጋጠማቸው የመርከብ መሰበር አደጋም በዝርዝር ጽፏል። (የሐዋርያት ሥራ 24:27፤ 25:9-12፤ 27:1, 9-44) ጳውሎስ በሮም በቁም እስር በነበረበት ወቅት በመንፈስ ተነሳስቶ በርካታ ደብዳቤዎችን የጻፈ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በሁለቱ ላይ የሉቃስን ስም ጠቅሷል። (የሐዋርያት ሥራ 28:30፤ ቈላስይስ 4:14፤ ፊልሞና 24) ሉቃስ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው ጳውሎስ በእስር በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም።
ጳውሎስ በሮም ያሳለፈው ጊዜ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ የተሞላ መሆን አለበት። በዚያም ሉቃስ ከሌሎቹ የጳውሎስ የሥራ ባልደረቦች ጋር ሳይገናኝ አልቀረም። ከእነዚህ መካከል ቲኪቆስ፣ አርስጥሮኮስ፣ ማርቆስ፣ ኢዮስጦስ፣ ኤጳፍራ እና አናሲሞስ ይገኙበታል።—ቈላስይስ 4:7-14
ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ በታሰረበትና ሊሞት እንደተቃረበ ሆኖ በተሰማው ወቅት ምንም እንኳን ሌሎቹ ትተውት ቢሄዱም ታማኝና ደፋር የሆነው ሉቃስ ግን ከጎኑ አልራቀም ነበር። ሉቃስ በዚያ የቆየው ከፊቱ የመታሰር አደጋ ተደቅኖበት ሳይሆን አይቀርም። ምናልባትም ሉቃስ እንደ ጸሐፊ ሆኖ በማገልገል “ከእኔ ጋር ያለው ሉቃስ ብቻ ነው” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት ሳይጽፍ አልቀረም። ጳውሎስ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አንገቱ ተቀልቶ መሞቱ በአፈ ታሪክ ይነገራል።—2 ጢሞቴዎስ 4:6-8, 11, 16
ሉቃስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግና ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። የተማረ ሰው መሆኑ እንዲታወቅለት አልፈለገም ወይም የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ አልጣረም። አዎን፣ ሉቃስ በሕክምናው ዘርፍ ተሰማርቶ ሕይወቱን መምራት ይችል ነበር። ሆኖም ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠትን መርጧል። እኛም ልክ እንደ ሉቃስ የራሳችንን ጥቅም በመሠዋት ምሥራቹን እናውጅ እንዲሁም በትሕትና በማገልገል ይሖዋን እናስከብር።—ሉቃስ 12:31
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቴዎፍሎስ ማን ነበር?
ሉቃስ ወንጌሉንም ይሁን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው ለቴዎፍሎስ ነው። ይህ ሰው በሉቃስ ወንጌል ውስጥ “ክቡር ቴዎፍሎስ” ተብሎ ተጠርቷል። (ሉቃስ 1:3) “ክቡር” የሚለው ቃል እጅግ ሀብታም የሆኑ ታዋቂ ሰዎችና በሮም መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ግለሰቦች የሚጠሩበት የማዕረግ ስም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ የይሁዳ ገዥ የነበረውን ሮማዊው ፊስጦስን የጠራው በተመሳሳይ የማዕረግ ስም ነው።—የሐዋርያት ሥራ 26:25
ቴዎፍሎስ ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች የሰማ ሲሆን ይበልጥ የማወቅ ጉጉት እንደነበረውም በግልጽ ማየት ይችላል። ሉቃስ የጻፈው የወንጌል ዘገባ ቴዎፍሎስ በቃል ‘የተማረው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንዲያውቅ’ እንደሚረዳው እምነት ነበረው።—ሉቃስ 1:4
የጥንት ግሪክኛ ሥነ ጽሑፎች ተመራማሪ የሆኑት ሪቻርድ ሌንስኪ እንደገለጹት ከሆነ ሉቃስ “ክቡር” ብሎ በጠራው ጊዜ ቴዎፍሎስ አማኝ አልነበረም፤ ምክንያቱም “ክርስቲያኖች በጻፏቸው ጽሑፎች ውስጥ . . . የትኛውንም ክርስቲያን ወንድማቸውን እንዲህ ባለ የክብር ስም ጠርተው አያውቁም።” ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሉቃስ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ሲጽፍ ቴዎፍሎስን “ክቡር” በሚለው የማዕረግ ስም ከመጥራት ይልቅ “ቴዎፍሎስ ሆይ” ብቻ ብሎታል። (የሐዋርያት ሥራ 1:1) ሪቻርድ ሌንስኪ እንደሚከተለው በማለት ደምድመዋል:- “ሉቃስ ወንጌሉን ለቴዎፍሎስ በጻፈለት ወቅት ይህ ታዋቂ ግለሰብ ክርስቲያን ያልነበረ ቢሆንም ከክርስትና ጋር ለተያያዙ ጉዳዮችን የማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፤ ይሁንና ሉቃስ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን በጻፈለት ወቅት ቴዎፍሎስ ክርስቲያን ሆኖ ነበር።”