በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው?
በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው?
ኬኒ ከአንድ ትልቅ ኩባንያ ጋር የንግድ ግንኙነት ያለው የናጠጠ ሀብታም ነው። በጣም ውድ መኪና የሚይዝ ሲሆን የሀብታሞች ሰፈር ውስጥ በሚገኝ አንድ ግዙፍ ሕንፃ ላይ ትልቅ ቤት አለው። ከዚህም በተጨማሪ ኬኒ፣ ከምድር ብዙ ሺህ ጫማ ከፍ ብሎ ከአውሮፕላን በመወርወር በአየር ላይ የመንሳፈፍ ጥሩ ችሎታ ስለነበረው በዚህ የስፖርት ዓይነት ይዝናና ነበር። ታዲያ ይህ ሁሉ ደስታ አስገኝቶለታል? ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ኬኒ እንዲህ ብሏል:- “አሁን 45 ዓመት ሆኖኛል። ይሁንና ብሩህ ተስፋ አይታየኝም። . . . ሕይወቴ ባዶ ነው።”
ኤለን በበረዶ ሸርተቴ ስፖርት ታዋቂ ለመሆን በትጋት ትለማመድ ነበር። በመጨረሻም ያለመችው ተሳካላትና ዝነኛ ሆነች። ይሁንና “የጓጓሁለት ያ ሁሉ ደስታ የት ሄደ?” ስትል በምሬት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች:- “ከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት ይሰማኛል። አሁን አርጅቻለሁ፤ ብዙ ሀብት ያለኝ ቢሆንም እንኳ የሕይወት ትርጉሙ ይህ ብቻ ከሆነ መኖር ከንቱ ነው ማለት ነው።”
በሥዕል ሥራው ታዋቂነትን ያተረፈው ሂዲዮ መላ ሕይወቱን ለሥነ ጥበብ የሰጠ ሰው ነበር። ሂዲዮ የሥዕል ሥራዎቹን ለሽያጭ ማቅረብ ሥነ ጥበብን እንደማራከስ አድርጎ ይመለከተው ስለነበር ሥዕሎቹን ለሽያጭ አያቀርብም ነበር። ሂዲዮ በ98 ዓመቱ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ አብዛኞቹን የሥነ ጥበብ ሥራዎቹን ለአንድ ሙዚየም በስጦታ መልክ አበርክቷል። መላ ሕይወቱን ለሥነ ጥበብ አሳልፎ የሰጠው ይህ ሰው መቼም ቢሆን እንከን የለሽ ሥራ መሥራት እንደማይችል ሆኖ ስለሚሰማው ሕይወቱ እርካታ አልነበረውም።
አንዳንድ ሰዎች ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በሆሊዉድ የፊልም ኢንዱስትሪ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው አንድ ሰው ያደረገውን ተመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ትላልቅ የፊልም ኩባንያዎች መካከል የአንዱ ምክትል ፕሬዝዳንት እንደመሆኑ መጠን ጊዜውን የሚያሳልፈው በመዝናኛው ዓለም በጣም ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሲሆን መኖሪያውም የናጠጡ ሀብታሞች በሚኖሩበት ሰፈር ውስጥ ነው። ለእረፍት ወደ ካምቦዲያ በሄደበት ጊዜ ፕኖም ፔን በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ራት እየበላ ሳለ አንዲት ልጅ ሳንቲም ለመነችው። እሱም አንድ ዶላርና ለስላሳ መጠጥ ሰጣት። ልጅቷም በጣም ተደሰተች። ይሁንና በቀጣዩ ቀን ምሽት ላይም ልጅቷ እዚያው ስትለምን አገኛት። ይህ ሰው ይህን መሰሉን ችግር ለማስወገድ ዘላቂ እርዳታ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተገነዘበ።
ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ይህ ሰው በመዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ የነበረውን ሥራ ትቶ በካምቦዲያ ያሉ ድሆችን በመርዳት ላይ ሙሉ ትኩረት ለማድረግ ወሰነ። በመሆኑም በካምቦዲያ አዳሪ ትምህርት ቤት ከፈተ። ይሁንና ከስሜት መረበሽ ማምለጥ አልቻለም። በአንድ በኩል እየሠራ ባለው ነገር ደስታና እርካታ ሲሰማው በሌላ በኩል ደግሞ በዕለቱ የሚያጋጥሙት እልባት የሚሹ ችግሮች ከሚያሳድሩበት የተስፋ መቁረጥና የብስጭት ስሜት ጋር ይታገላል።
ከላይ የተጠቀሱት አራቱም ግለሰቦች በሕይወታቸው ውስጥ የሚፈልጉት ነገር ምን እንደሆነ እንደሚያውቁ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁንና ከብዙ ድካም በኋላ ያሰቡት ደረጃ ላይ ሲደርሱ የባዶነት ስሜት ተሰምቷቸዋል። አንተስ ልትደርስበት የምትፈልገው ግብ ምንድን ነው? በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው? በአሁኑ ሕይወትህ የማታ ማታ እንደማትቆጭ እርግጠኛ ነህ?