“እባካችሁ ይህችን ትንሽ ስጦታዬን ተቀበሉኝ”
“እባካችሁ ይህችን ትንሽ ስጦታዬን ተቀበሉኝ”
እነዚህ ቃላት ሩሲያ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ከተጻፈ አንድ ደብዳቤ ላይ የተወሰዱ ናቸው። ቢሮው ከደብዳቤው ጋር ከሱፍ በተሠሩ ካልሲዎች የተሞላ አንድ ትልቅ ካርቶን ደርሶታል።
ስጦታውን የላከችው በምሥራቅ ሩሲያ ጠረፍ አካባቢ ባለ ጉባኤ ውስጥ የምትገኝ ኤልለ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ነች። ይህች የ67 ዓመት አረጋዊት እህት የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት በመስበክ ይሖዋን ከአሥር ዓመት በላይ ስታገለግል ቆይታለች። ነገር ግን ድንገት በደረሰባት የደም መርጋት ሳቢያ ግማሽ አካሏ ሽባ ሆነ። ይሁን እንጂ ኤልለ በፍቅር ተነሳሳታ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለእምነት ባልንጀሮቿ ልብስ ትሠራ የነበረችውን የዶርቃን ምሳሌ ተከትላለች።—የሐዋርያት ሥራ 9:36, 39
ኤልለ በደብዳቤዋ ላይ እንዲህ ብላለች:- “እግሮቼን ማንቀሳቀስ ባልችልም እጆቼን ማንቀሳቅስ እችላለሁ። ስለዚህ ደብዳቤ በመጻፍ እመሠክራለሁ።” አክላም እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “እጆቼን ማንቀሳቀስ እስከቻልኩ ድረስ ጥቂት የሚሞቁ ካልሲዎችን መሥራት እንዳለበኝ ወሰንኩ። እነዚህ ካልሲዎች እንደ ምሥራቅ ሩሲያና ሳይቤሪያ ባሉ ቀዝቃዛ አካባቢዎች የመንግሥት አዳራሾችን ለመገንባት ለሚሄዱ ወንድሞችና እህቶች እንዲሰጥልኝ እፈልጋለሁ።”
ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮቹን አስመልክቶ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 13:35) ኤልለ ያሳየችው እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርትን ማንነት ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት ነው።