በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሌሎችን መንፈስ የምታድስ ነህ?

የሌሎችን መንፈስ የምታድስ ነህ?

የሌሎችን መንፈስ የምታድስ ነህ?

ሊባኖስንና ሶርያን በሚያዋስነው አንቲ-ሊባነን በሚባለው የተራራ ሰንሰለት ደቡባዊ ጫፍ ላይ ከባሕር ወለል በላይ 2,814 ሜትር የሚደርስ አስደናቂ ከፍታ ያለው የአርሞንዔም ተራራ ይገኛል። የተራራው ጫፍ በዓመት ውስጥ ለበርካታ ወራት በበረዶ የሚሸፈን ሲሆን ይህም በምሽት የሚነፍሰው እርጥበት ያዘለ ሞቃት አየር በአናቱ ላይ ሲያልፍ እንዲቀዘቅዝና ጤዛ እንዲፈጥር ምክንያት ይሆናል። ጤዛው ከተራራው በታች ወዳሉት ፈር ወደተባሉት የዛፍ ዓይነቶችና ሌሎች የፍራፍሬ ዛፎች ቁልቁል ይወርዳል። ከዚያም ከዛፎቹ በታች ወደሚገኙት የወይን ተክሎች ይሰርጋል። ለረጅም ወራት በሚዘልቀው የጥንቷ እስራኤል የበጋ ወቅት ለዕፅዋቱ ዋነኛ የውኃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው ሕይወትን የሚያድሰው ይህ ጠል ነበር።

በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተዘመረ አንድ መዝሙር ላይ በይሖዋ አምላኪዎች መካከል የሚታየው መንፈስን የሚያድስ አንድነት ‘በጽዮን ተራራ ላይ በሚወርደው የአርሞንዔም ጠል’ ተመስሏል። (መዝሙር 133:1, 3) የአርሞንዔም ተራራ ለዕጽዋት ሕይወትን የሚያድስ ጠል እንደሚሰጥ ሁሉ እኛም የምናገኛቸውን ሰዎች መንፈስ ልናድስ እንችላለን። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ የሌሎችን መንፈስ በማደስ ረገድ የተወው ምሳሌ

ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረ ሰው ነው። ከእሱ ጋር ጥቂት ጊዜ አብሮ ማሳለፍ እንኳ መንፈስን በእጅጉ የሚያድስ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ወንጌል ጸሐፊው ማርቆስ “[ኢየሱስ] ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው” ብሏል። (ማርቆስ 10:16) በዚህ ሁኔታ የልጆቹ መንፈስ ምንኛ ታድሶ ይሆን!

ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል። ደቀ መዛሙርቱ ባሳየው ትሕትና ልባቸው ተነክቶ መሆን አለበት። ከዚያም ኢየሱስ “እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ” አላቸው። (ዮሐንስ 13:1-17) አዎን፣ እነሱም ቢሆኑ ትሑት መሆን ያስፈልጋቸዋል። ሐዋርያቱ ኢየሱስ ሊያስተምራቸው የፈለገውን ነገር ወዲያውኑ ያልተረዱና ቆየት ብሎም በዚያው ምሽት ከመካከላቸው ታላቅ የሚመስለው ማን እንደሆነ መከራከር የጀመሩ ቢሆንም ኢየሱስ አልተበሳጨባቸውም። ከዚህ ይልቅ በትዕግሥት አስረድቷቸዋል። (ሉቃስ 22:24-27) ሌላው ቀርቶ “[ኢየሱስ] ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም።” እንዲሁም “መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” በእርግጥም ኢየሱስ የሌሎችን መንፈስ በማደስ ረገድ የተወው ምሳሌ ሊኮረጅ የሚገባው ነው።—1 ጴጥሮስ 2:21, 23

ኢየሱስ “ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:29) ከኢየሱስ በቀጥታ መማር ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስብ! በተወለደበት ከተማ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ኢየሱስ በምኩራባቸው ሲያስተምር ካዳመጡ በኋላ “ይህ ሰው ይህን ጥበብና እነዚህን ታምራት የማድረግ ኀይል ከየት አገኘ?” በማለት በመገረም ጠይቀዋል። (ማቴዎስ 13:54) ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹ ዘገባዎችን በማንበብ የሌሎችን መንፈስ ማደስ ስለምንችልበት መንገድ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ኢየሱስ የሚያንጽ ንግግር በመናገርና ሌሎችን የመርዳት ዝንባሌ በመያዝ ረገድ ግሩም ምሳሌ የተወልን እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

የሚያንጽ ንግግር መናገር

አንድን ሕንጻ ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ በጣም ቀላል ነው። ንግግርን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ፍጽምና የጎደለን እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ድክመቶችና ጉድለቶች አሉብን። ንጉሥ ሰሎሞን “ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” ብሏል። (መክብብ 7:20) የአንድን ሰው ጉድለት ለይቶ ማወቅና ጎጂ በሆኑ ቃላት ስሜቱን ማቁሰል ቀላል ነው። (መዝሙር 64:2-4) በሌላ በኩል፣ የሚያንጽ ንግግር መናገር ጥረት ይጠይቃል።

ኢየሱስ አንደበቱን ሌሎችን ለማነጽ ተጠቅሞበታል። የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጅ ለሰዎች ሕይወት የሚያድስ መንፈሳዊ ትምህርት ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 8:1) በተጨማሪም ለደቀ መዛሙርቱ በሰማይ የሚኖረውን አባቱን ማንነት በመግለጥ መንፈሳቸውን አድሶላቸዋል። (ማቴዎስ 11:25-27) ሰዎች ወደ ኢየሱስ መቅረባቸው ምንም አያስደንቅም!

ከዚህ በተቃራኒ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ስለ ሌሎች ፍላጎት ደንታ አልነበራቸውም። ኢየሱስ “በግብዣ ቦታ የከበሬታ ስፍራ፣ በምኵራብም የመጀመሪያውን መቀመጫ መያዝ ይወዳሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:6) እንዲያውም “ሕጉን የማያውቅ ይህ ሕዝብ ግን የተረገመ ነው” በማለት ተራውን ሕዝብ ይንቁ ነበር። (ዮሐንስ 7:49) ይህ አመለካከት የሌሎችን መንፈስ የሚያድስ እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም!

ብዙውን ጊዜ ንግግራችን በውስጣችን ያለውን ነገርና ለሌሎች ያለንን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “መልካም ሰው በልቡ ከሞላው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሞላው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና።” (ሉቃስ 6:45) ታዲያ ንግግራችን የሌሎችን መንፈስ የሚያድስ እንዲሆን ምን ማድረግ እንችላለን?

እንዲህ ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ከመናገራችን በፊት ቆም ብለን በማሰብ ነው። ምሳሌ 15:28 “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” ይላል። የምንናገረውን ነገር ማመዛዘን ረጅም ጊዜ የሚወስድ አይደለም። ከመናገራችን በፊት ለጥቂት ጊዜ ቆም ብለን በማሰብ የምንሰነዝረው ሐሳብ የሌሎችን መንፈስ የሚያድስ መሆን አለመሆኑን ማወቅ እንችላለን። ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን:- ‘ልናገረው ያሰብኩት ነገር ፍቅር የሚንጸባረቅበት ነው? የምናገረው ነገር እውነት ነው ወይስ ሐሜት? “በወቅቱ የተሰጠ [“የተነገረ፣”NW] ቃል” ነው? የሚያዳምጡኝን ሰዎች መንፈስ የሚያድስና የሚያንጽ ነው?’ (ምሳሌ 15:23) የምንናገረው ነገር አዎንታዊ ካልሆነና በዚያን ወቅት መነገር ከሌለበት ያን ሐሳብ ላለመናገር የታሰበበት ጥረት እናድርግ። ልትናገር ያሰብከውን አላስፈላጊ ነገር ከመናገር ተቆጥበህ ዝም ከማለት ይልቅ ሐሳቡን ይበልጥ በሚያንጽና ተገቢ በሆነ ቃል ለምን አትተካውም? ግድ የለሽ ቃል ልክ “እንደ ሰይፍ ይወጋል፤” የሚያንጽ ንግግር ግን “ፈውስን ያመጣል።”—ምሳሌ 12:18

ሌላው አስፈላጊ ነጥብ ደግሞ የእምነት አጋሮቻችንን በይሖዋ ዓይን ውድ እንዲሆኑ ባደረጓቸው ባሕርያት ላይ ማተኮር ነው። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም” ብሏል። (ዮሐንስ 6:44) ይሖዋ የእያንዳንዱን ታማኝ አገልጋዩን ሌላው ቀርቶ አስቸጋሪ ባሕርይ እንዳላቸው የሚሰማንን ወንድሞችና እህቶች እንኳ ሳይቀር መልካም ባሕርያቸውን ይመለከታል። እኛም የእነሱን መልካም ባሕርያት ለመመልከት ከፍተኛ ጥረት ካደረግን ስለ እነሱ አዎንታዊ ነገር ለመናገር የሚያስችል በቂ ምክንያት እናገኛለን።

ሌሎችን መርዳት

ኢየሱስ የተጨቆኑ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ይረዳ ነበር። ሕዝቡ “እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) ይሁንና ኢየሱስ ሰዎቹ ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ ተመልክቶ ብቻ ዝም አላለም፤ ከዚህ ይልቅ ረድቷቸዋል። “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ” የሚል ግብዣ አቅርቦላቸዋል። በተጨማሪም “ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነው” የሚል ዋስትና ሰጥቷቸዋል።—ማቴዎስ 11:28, 30

የምንኖርበት ዘመን “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ብዙ ሰዎች ‘በዚህ ዓለም ጭንቀት’ ዝለዋል። (ማቴዎስ 13:22) ሌሎች ደግሞ የሚያስጨንቁ የግል ችግሮች አሉባቸው። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) ታዲያ የእነዚህን ሰዎች መንፈስ ማደስ የምንችለው እንዴት ነው? ልክ እንደ ክርስቶስ እኛም ሸክማቸው እንዲቀልላቸው በመርዳት ነው።

አንዳንድ ሰዎች ስለ ችግሮቻቸው ለሌሎች በመናገር ሸክማቸውን ማቅለል ይፈልጋሉ። ያዘኑ ሰዎች እርዳታ ፈልገው ወደ እኛ ሲመጡ ጊዜ ዋጅተን በጥሞና እናዳምጣቸዋለን? ሌሎችን በአዘኔታ መንፈስ ማዳመጥ ራስን መግዛት ይጠይቃል። ይህ ደግሞ፣ ምን ምላሽ እንደምንሰጥ ወይም ችግሩን እንዴት መፍታት እንዳለብን ከማሰብ ይልቅ ግለሰቡ የሚናገረውን ነገር በትኩረት ማዳመጥን ይጨምራል። በጥሞና በማዳመጥ፣ ግለሰቡን ዓይን ዓይኑን በመመልከትና አስፈላጊ ሲሆን ፈገግ በማለት አሳቢነታችንን ማሳየት እንችላለን።

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የእምነት አጋሮቻችንን ለማበረታታት የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎች አሉን። ለምሳሌ ያህል፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ከጤንነት ችግሮች ጋር ለሚታገሉ ወንድሞችና እህቶች ትኩረት መስጠት እንችላለን። አንዳንዴ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊትና ካለቀ በኋላ ጥቂት ደቂቃዎችን ወስዶ የሚያበረታቱ ቃላትን መናገር ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ጥናት ላይ ያልተገኙ ካሉ ስልክ ደውለን ደህንነታቸውን መጠየቅና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም እርዳታ መስጠት እንችላለን።—ፊልጵስዩስ 2:4

ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። ከእነሱ ጋር በመተባበርና የሚሰጠንን ማንኛውንም ሥራ በትሕትና በመሥራት ሸክማቸውን ልናቀልላቸው እንችላለን። የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ያሳስበናል:- “ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጉዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም።” (ዕብራውያን 13:17) የፈቃደኝነት መንፈስ በማሳየት ‘በሚገባ የሚያስተዳድሩንን’ ሽማግሌዎች መንፈስ ማደስ እንችላለን።—1 ጢሞቴዎስ 5:17

ሁልጊዜ የሚያበረታቱ ቃላትን መናገርና ጠቃሚ ተግባራትን ማከናወን

ሕይወትን የሚያድስ ጠል የሚፈጠረው ሥፍር ቁጥር ከሌላቸው በቀስታ የሚወርዱ የውኃ ቅንጣቶች ነው። በተመሳሳይም የሌሎችን መንፈስ ማደስ አንድ የሚያስመሰግን ተግባር በመፈጸም ብቻ የሚገኝ ውጤት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁልጊዜ የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት ማንጸባረቅን ይጠይቃል።

ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 12:10) የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ እናድርግ። በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን የሌሎችን መንፈስ የምናድስ እንሁን።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአርሞንዔም ተራራ ላይ የሚወርደው ጠል የዕፅዋትን ሕይወት ያድሳል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአዘኔታ ስሜት የሚያዳምጥ ሰው የሌሎችን መንፈስ ያድሳል