በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚረዱህን ባሕርያት አዳብር

ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚረዱህን ባሕርያት አዳብር

ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚረዱህን ባሕርያት አዳብር

“ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19

1. በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ምን ዓይነት ችሎታዎችና ባሕርያት ማዳበር አስፈልጓቸው ነበር?

 አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስችሏቸውን ችሎታዎችና ባሕርያት ማዳበር ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃምና ሣራ አምላክ ባዘዛቸው መሠረት የበለጸገች ከተማ የነበረችውን ዑርን ለቅቀው የወጡ ሲሆን በድንኳን ውስጥ ለመኖር የሚረዷቸውን ባሕርያትና ችሎታዎች ማዳበርም አስፈልጓቸዋል። (ዕብራውያን 11:8, 9, 15) ኢያሱ እስራኤላውያንን እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለማስገባት ደፋር መሆን፣ በይሖዋ መታመንና የአምላክን ሕግ ማወቅ ነበረበት። (ኢያሱ 1:7-9) ባስልኤልና ኤልያብ ከፍተኛ ችሎታ የነበራቸው ቢሆንም የአምላክ መንፈስ ችሎታቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ እንደረዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ይህም በመገናኛው ድንኳን ግንባታና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ሥራዎች በተካሄዱበት ወቅት ጥሩ ተሳትፎ ለማድረግና ሥራውን በበላይነት ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል።—ዘፀአት 31:1-11

2. ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራ ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ከዚያ በፊት ሰዎች ይህን የመሰለ ተልእኮ ተሰጥቷቸው አያውቅም። ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ የትኞቹን ባሕርያት ማፍራት ያስፈልጋል? እነዚህን ባሕርያት እንዴት ማዳበር እንችላለን?

ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር እንዳለህ አሳይ

3. ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠን ትእዛዝ ምን አጋጣሚ ይከፍትልናል?

3 አንድ ሰው፣ ሌሎችን ቀርቦ ለማነጋገርና እውነተኛውን አምላክ እንዲያመልኩ ለማሳመን ጥረት የሚያደርገው ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ካለው ብቻ ነው። እስራኤላውያን የአምላክን ትእዛዛት በሙሉ ልብ በመታዘዝ፣ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት በማቅረብና ይሖዋን በመዝሙር በማወደስ ለእሱ ፍቅር እንዳላቸው ማሳየት ይችሉ ነበር። (ዘዳግም 10:12, 13፤ 30:19, 20፤ መዝሙር 21:13፤ 96:1, 2፤ 138:5) እኛም ሰዎችን ደቀ መዛሙርት የማድረግ መብት ያገኘን እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ሕግጋት እንጠብቃለን። ይሁንና ከዚህ በተጨማሪ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሌሎች በመናገር ለእሱ ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን። አምላክ ስለሰጠን ተስፋ የሚሰማንን ከልብ የመነጨ አድናቆት የሚያሳዩ ትክክለኛ ቃላትን በመምረጥ በልበ ሙሉነት መናገር ይኖርብናል።—1 ተሰሎንቄ 1:5 NW፤ 1 ጴጥሮስ 3:15

4. ኢየሱስ ሰዎችን ስለ ይሖዋ ማስተማር ያስደስተው የነበረው ለምንድን ነው?

4 ኢየሱስ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ስለነበረው ስለ አምላክ ዓላማ፣ ስለ መንግሥቱ እንዲሁም ስለ እውነተኛው አምልኮ ለሌሎች መናገር በጣም ያስደስተው ነበር። (ሉቃስ 8:1፤ ዮሐንስ 4:23, 24, 31) እንዲያውም ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውን መፈጸም ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) መዝሙራዊው የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት በኢየሱስ ላይ ተፈጽመዋል:- “‘አምላኬ ሆይ፤ ፈቃድህን ላደርግ እሻለሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ።’ በታላቅ ጉባኤ ውስጥ ጽድቅን አበሠርሁ፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ አንተ እንደምታውቀው፣ ከንፈሮቼን አልገጠምሁም።”—መዝሙር 40:8, 9፤ ዕብራውያን 10:7-10

5, 6. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚካፈሉ ሰዎች ሊያዳብሩት የሚገባ ዋነኛ ባሕርይ ምንድን ነው?

5 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር የጀመሩ አዳዲስ ሰዎች ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ በሙሉ ልብ የሚናገሩበት ጊዜ አለ። ይህም የሚያዳምጧቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምሩ በማሳመን ረገድ የተዋጣላቸው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። (ዮሐንስ 1:41) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንድንጠመድ የሚያነሳሳን ዋነኛ ባሕርይ ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። በመሆኑም አዘውትረን የአምላክን ቃል በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ለእሱ ያለንን ፍቅር እናቀጣጥል።—1 ጢሞቴዎስ 4:6, 15፤ ራእይ 2:4

6 ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለይሖዋ ያለው ፍቅር ቀናተኛ አስተማሪ እንዲሆን እንደረዳው ምንም አያጠራጥርም። ይሁንና ውጤታማ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ እንዲሆን ያስቻለው ይህ ብቻ አልነበረም። ታዲያ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የረዳው ሌላው ባሕርይ ምንድን ነው?

ለሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳይ

7, 8. ኢየሱስ ለሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

7 ኢየሱስ ለሰዎች ከልብ ያስብ ነበር። ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ማለትም የአምላክ “ዋና ባለሙያ” ሆኖ በሰማይ ባገለገለባቸው ጊዜያት በሰው ልጆች ደስ ይሰኝ ነበር። (ምሳሌ 8:30, 31) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ በኋላም የርኅራኄ ስሜት ያሳይ የነበረ መሆኑ ወደ እሱ ለመጡት ሰዎች እረፍት አስገኝቶላቸዋል። (ማቴዎስ 11:28-30) ኢየሱስ የይሖዋን ፍቅርና ርኅራኄ አንጸባርቋል፤ ይህም ሰዎች እውነተኛውን አንድ አምላክ እንዲያመልኩ አነሳስቷቸዋል። ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅራዊ አሳቢነት ያሳይና ያሉበት ሁኔታ ያሳስበው ስለነበር ሁሉም ዓይነት ሰዎች እሱ ሲያስተምር ለማዳመጥ ፈቃደኞች ነበሩ።—ሉቃስ 7:36-50፤ 18:15-17፤ 19:1-10

8 አንድ ሰው ኢየሱስን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለበት በጠየቀው ጊዜ ‘ኢየሱስ ተመለከተውና ወደደው።’ (ማርቆስ 10:17-21) መጽሐፍ ቅዱስ በቢታንያ ይኖሩ ስለነበሩ ኢየሱስ ስላስተማራቸው አንዳንድ ሰዎች ሲናገር ‘ኢየሱስ ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር’ ይላል። (ዮሐንስ 11:1, 5) ኢየሱስ ለሰዎች ከልቡ ያስብ ስለነበር የእረፍት ጊዜውን እንኳ መሥዋዕት አድርጎ ያስተምራቸው ነበር። (ማርቆስ 6:30-34) ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው እንዲህ ዓይነቱ ጥልቅ አሳቢነት፣ ሌሎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲሳቡ በማድረግ ረገድ ከማንም በላይ ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል።

9. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ይካፈል የነበረው ጳውሎስ ምን ዓይነት ዝንባሌ ነበረው?

9 ሐዋርያው ጳውሎስም እውነትን ለሰበከላቸው ሰዎች ከልብ ያስብላቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስትናን ለተቀበሉ የተሰሎንቄ ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል:- “[የአምላክን] ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ።” ጳውሎስ በፍቅር ተነሳስቶ ባደረገው ጥረት በተሰሎንቄ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ‘ጣዖታትን ከማምለክ ተመልሰው ሕያው የሆነውን አምላክ ማገልገል’ ጀምረዋል። (1 ተሰሎንቄ 1:9፤ 2:8) እኛም ኢየሱስና ጳውሎስ እንዳደረጉት ለሰዎች እውነተኛ አሳቢነት የምናሳይ ከሆነ ምሥራቹ “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ሰዎችን ልብ ሲነካ ማየት የሚያስገኘውን ደስታ ልናጣጥም እንችላለን።—የሐዋርያት ሥራ 13:48

የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ይኑርህ

10, 11. ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ስንጥር የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ውጤታማ የሆኑ ክርስቲያኖች የራሳቸውን ጥቅም ለመሠዋት ፈቃደኛ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ የሚሰጡት ቁሳዊ ሀብት ለማከማቸት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እንዲያውም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!” ብሏቸዋል። ንግግሩ ደቀ መዛሙርቱን ያስገረማቸው ቢሆንም ኢየሱስ አክሎ እንዲህ አላቸው:- “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው! ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል።” (ማርቆስ 10:23-25) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ይበልጥ ማተኮር እንዲችሉ አኗኗራቸውን ቀላል እንዲያደርጉ መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:22-24, 33) ታዲያ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚረዳን እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ያዘዘውን ሁሉ ማስተማር ብዙ ጥረት ይጠይቃል። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ እንዲሳካለት የሚፈልግ ክርስቲያን፣ ፍላጎት ላሳየ ሰው በየሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ይጥራል። ሙሉ ጊዜ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ አንዳንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች የማግኘት አጋጣሚያቸውን ከፍ ለማድረግ በሰብዓዊ ሥራ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ቀንሰዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች በአካባቢያቸው ለሚኖሩና ከእነሱ የተለየ ጎሳ ላላቸው ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ ሲሉ አዲስ ቋንቋ ተምረዋል። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚካፈሉ ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ በመከሩ ሥራ ላይ ይበልጥ ለመሳተፍ መኖሪያቸውን ትተው ወደ ሌላ አካባቢ ወይም አገር ተዛውረዋል። (ማቴዎስ 9:37, 38) ይህ ሁሉ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። ይሁንና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ውጤታማ ለመሆን ከዚህ የበለጠ ነገር ያስፈልጋል።

ታጋሽ ሁን፤ ሆኖም ጊዜ አታባክን

12, 13. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ትዕግሥት እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚረዳን ሌላው ባሕርይ ትዕግሥት ነው። የምንሰብከው መልእክት ሰዎች አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ የሚጠይቅባቸው ቢሆንም ደቀ መዛሙርት ማድረግ በአብዛኛው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑም በላይ ትዕግሥት ይጠይቃል። (1 ቆሮንቶስ 7:29) ኢየሱስ ወንድሙን ያዕቆብን ታግሶታል። ያዕቆብ ስለ ኢየሱስ የስብከት እንቅስቃሴ በሚገባ ያውቅ የነበረ ይመስላል፤ ሆኖም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ደቀ መዝሙር እንዳይሆን ወደኋላ ያደረገው ነገር ነበር። (ዮሐንስ 7:5) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ያዕቆብ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከሐዋርያት ጋር ለጸሎት እንደተሰበሰበ ስለሚጠቁም፣ ኢየሱስ ከሞተበት ጊዜ አንስቶ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ድረስ ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ ደቀ መዝሙር ሆኗል ብለን መናገር እንችላለን። (የሐዋርያት ሥራ 1:13, 14) ያዕቆብ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት ያደረገ ሲሆን ቆየት ብሎም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከባድ ኃላፊነቶችን ተቀብሏል።—የሐዋርያት ሥራ 15:13፤ 1 ቆሮንቶስ 15:7

13 ገበሬዎች የሚዘሩት ሰብል ለማደግ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ክርስቲያኖች የሚተክሏቸው ነገሮችም በአብዛኛው የሚያድጉት ቀስ ብለው ነው። የአምላክን ቃል መረዳት፣ ለይሖዋ ፍቅር ማዳበርና የክርስቶስ ዓይነት መንፈስ ማንጸባረቅ ጊዜ የሚፈልጉ ነገሮች ናቸው። በመሆኑም ትዕግሥት ያስፈልጋል። ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ። እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቦአል።” (ያዕቆብ 5:7, 8) ያዕቆብ የእምነት አጋሮቹ ‘ጌታ እስኪመጣ ድረስ በትዕግሥት እንዲጠባበቁ’ አሳስቧቸዋል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ አንድ ነገር ሳይረዱ ሲቀሩ በትዕግሥት ያብራራላቸው ወይም ደግሞ በምሳሌ ያስረዳቸው ነበር። (ማቴዎስ 13:10-23፤ ሉቃስ 19:11፤ 21:7፤ የሐዋርያት ሥራ 1:6-8) ጌታ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበት በአሁኑ ወቅትም ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ስንጥር ትዕግሥት ማሳየታችን የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። በዘመናችንም የኢየሱስ ተከታዮች የሚሆኑ ሰዎች በትዕግሥት የሚያስተምራቸው ይፈልጋሉ።—ዮሐንስ 14:9

14. ትዕግሥተኞች ብንሆንም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ጊዜያችንን በጥበብ የምንጠቀመው እንዴት ነው?

14 ይሁንና የቱንም ያህል ታጋሽ ብንሆን የአምላክ ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባስጀመርናቸው በአብዛኞቹ ሰዎች ልብ ውስጥ ፍሬ አያፈራም። (ማቴዎስ 13:18-23) እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ተገቢውን ጥረት ካደረግን በኋላ ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፋችንን በጥበብ በማቆም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚያደንቁ ሌሎች ሰዎችን መፈለግ ይኖርብናል። (መክብብ 3:1, 6) እውነት ነው፣ አድናቆት ያላቸው ሰዎችም እንኳ አመለካከታቸውን፣ ዝንባሌያቸውንና በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች እንዲያስተካክሉ መርዳት ረዘም ያለ ጊዜ ይጠይቅ ይሆናል። በመሆኑም፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ትክክለኛ አመለካከት እንዲያዳብሩ በትዕግሥት እንደረዳቸው ሁሉ እኛም ታጋሽ እንሆናለን።—ማርቆስ 9:33-37፤ 10:35-45

የማስተማር ጥበብ አዳብር

15, 16. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል ባልተወሳሰበ መንገድ ማስተማርና ጥሩ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

15 ለአምላክ ፍቅር ማዳበር፣ ለሰዎች ማሰብ፣ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት እንዲሁም ትዕግሥተኛ መሆን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ውጤታማ እንድንሆን የሚያስችሉን ቁልፍ ነገሮች ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ ነገሮችን ግልጽ በሆነና ባልተወሳሰበ መንገድ ለማስረዳት እንድንችል የማስተማር ጥበብ ማዳበር ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸው ቃላት ውጤታማ የነበሩት ያልተወሳሰቡ ስለሆኑ ነው። ኢየሱስ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ሐሳቦች ሳታስታውስ አትቀርም:- “በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ።” “የተቀደሰ ነገር ለውሾች አትስጡ።” “ጥበብ . . . በሥራዋ ጸደቀች።” “የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ።” (ማቴዎስ 6:20፤ 7:6፤ 11:19፤ 22:21) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ይናገር የነበረው አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ግልጽ በሆነ መንገድ ያስተምርና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ያስተማረውን ነገር በዝርዝር ያብራራ ነበር። የኢየሱስን የማስተማር ዘዴ መኮረጅ የምትችለው እንዴት ነው?

16 ባልተወሳሰበና ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስተማር ቁልፉ ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ነው። አንድ ያልተዘጋጀ አስፋፊ ብዙ ማውራት ይቀናዋል። ስለ አንድ ጉዳይ የሚያውቀውን ነገር ሁሉ በመናገርና ሐሳቡን በማንዛዛት ዋናው ነጥብ እንዲድበሰበስ ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ በተቃራኒ፣ ጥሩ ዝግጅት ያደረገ አንድ አስፋፊ ስለሚያስተምረው ሰው ያስባል፤ በርዕሰ ትምህርቱ ላይ ያሰላስላል፤ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑትን ነጥቦች ብቻ በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 15:28፤ 1 ቆሮንቶስ 2:1, 2) የተማሪውን እውቀት ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ከመሆኑም ባሻገር በጥናቱ ወቅት መጉላት ያለባቸው ነጥቦች የትኞቹ እንደሆኑ ያውቃል። አስፋፊው ስለሚወያዩበት ርዕሰ ጉዳይ ብዙ ትኩረት የሚስቡ ሐሳቦችን ሊያውቅ ይችላል። ሆኖም አንድን ነገር በግልጽ ማስተማር የሚቻለው አላስፈላጊ ሐሳቦችን ከመናገር በመቆጠብ ነው።

17. ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳቦች እንዲያስተውሉ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?

17 በተጨማሪም ኢየሱስ ለሰዎች እውነታውን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ነገሩን ራሳቸው እንዲያመዛዝኑ ይረዳቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ጴጥሮስን “ስምዖን፤ የምድር ነገሥታት ግብር ወይም ቀረጥ የሚቀበሉት ከራሳቸው ልጆች ወይስ ከሌሎች ይመስልሃል?” ሲል ጠይቆት ነበር። (ማቴዎስ 17:25) መጽሐፍ ቅዱስን ማብራራት በጣም የሚያስደስተን በመሆኑ ብዙ ላለመናገር ራሳችንን መግዛት ይኖርብናል። ይህን ማድረጋችን ተማሪው ሐሳቡን እንዲገልጽ ወይም በጥናቱ ወቅት የሚሸፈነውን ነጥብ እንዲያብራራ አጋጣሚ ይሰጠዋል። እርግጥ ነው፣ በሰዎች ላይ የጥያቄ መዓት ማዥጎድጎድ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ በዘዴ፣ ጥሩ ምሳሌዎችን በመጠቀምና የታሰበባቸው ጥያቄዎች በመጠየቅ ጥናቶቻችን በጽሑፎቻችን ላይ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች እንዲያስተውሉ ልንረዳቸው እንችላለን።

18. ‘የማስተማር ጥበብን’ ማዳበር ምንን ይጨምራል?

18 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ማስተማር ጥበብ” ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2 NW፤ ቲቶ 1:9 NW) እንዲህ ያለው የማስተማር ችሎታ አንድ ሰው የተማረውን እንዲያስታውስ ከመርዳት የበለጠ ነገር ማድረግን ይጨምራል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በእውነትና በሐሰት፣ በጥሩና በመጥፎ፣ እንዲሁም ጥበብ በሆነውና ባልሆነው መካከል ያለውን ልዩነት እንዲያስተውል ለመርዳት መጣር ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ስናስተምርና ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርበት ለማድረግ ስንጥር ግለሰቡ አምላክን መታዘዝ ያለበት ለምን እንደሆነ ሊገነዘብ ይችላል።

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት ተካፈል

19. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሁሉም ክርስቲያኖች አስተዋጽኦ የሚያበረክቱት እንዴት ነው?

19 የክርስቲያን ጉባኤ የተቋቋመበት ዓላማ ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ነው። አንድ አዲስ ሰው ደቀ መዝሙር ሲሆን የሚደሰተው መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናው የይሖዋ ምሥክር ብቻ አይደለም። ለምሳሌ፣ አንድን የጠፋ ልጅ ለመፈለግ ብዙ ሰዎች ቢሰማሩ፣ ልጁን ሊያገኝ የሚችለው አንድ ሰው ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ልጁ ተገኝቶ ከቤተሰቡ ጋር ሲቀላቀል በፍለጋው ላይ የተካፈሉት ሁሉ ይደሰታሉ። (ሉቃስ 15:6, 7) በተመሳሳይም ደቀ መዛሙርት ማድረግ የቡድን ሥራ ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚሆኑ ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። አንድ አዲስ ሰው በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት ሲጀምር እያንዳንዱ ክርስቲያን ግለሰቡ ለእውነተኛው አምልኮ ያለው አድናቆት እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (1 ቆሮንቶስ 14:24, 25) ስለሆነም በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ሲገኙ ሁሉም ክርስቲያኖች ይደሰታሉ።

20. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማስተማር የምትፈልግ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

20 በርካታ ታማኝ ክርስቲያኖች ሌሎችን ስለ ይሖዋና ስለ እውነተኛው አምልኮ የማስተማር አጋጣሚ ቢያገኙ ደስ ይላቸዋል። ይሁን እንጂ የቻሉትን ያህል ቢጥሩም ደቀ መዛሙርት የማድረግ አጋጣሚ አላገኙ ይሆናል። አንተም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ለማሳደግ፣ ለሰዎች አሳቢነት ለማሳየት፣ የራስህን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግና ታጋሽ ለመሆን እንዲሁም የማስተማር ጥበብን ለማዳበር ጥረት ማድረግህን ቀጥል። ከሁሉም በላይ እውነትን ለሌሎች ለማስተማር ያለህን ፍላጎት ለይሖዋ በጸሎት ንገረው። (መክብብ 11:1) በይሖዋ አገልግሎት የምታከናውነው ማንኛውም ተግባር፣ አምላክን ለሚያስከብረው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ መገንዘብህ ያጽናናሃል።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ለአምላክ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ የሚካፈሉ ሰዎች ሊያዳብሯቸው የሚገቡ ባሕርያት ምንድን ናቸው?

• ‘የማስተማር ጥበብ’ ምንን ይጨምራል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ሌሎችን ደቀ መዛሙርት በማድረግ ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው ያሳያሉ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ የሚካፈሉ ክርስቲያኖች ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት ያለባቸው ለምንድን ነው?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ የሚካፈሉ ሰዎች ሊያዳብሯቸው የሚገቡ አንዳንድ ባሕርያት ምንድን ናቸው?

[በገጽ 25ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚገኘው ግሩም ውጤት ሁሉንም ክርስቲያኖች ያስደስታቸዋል