በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁ ሰላማውያን እንዲሆኑ አስተምሯቸው

ልጆቻችሁ ሰላማውያን እንዲሆኑ አስተምሯቸው

ልጆቻችሁ ሰላማውያን እንዲሆኑ አስተምሯቸው

የስምንት ዓመቷ ኒኮል ቤተሰቦቿ አካባቢ ቀይረው ወደ ሩቅ ቦታ የሚሄዱ መሆናቸው በደስታ እንድትዋጥ ስላደረጋት ስለ እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ በየጊዜው ለቅርብ ጓደኛዋ ለጋብሪኤል ታጫውታታለች። አንድ ቀን ጋብሪኤል፣ ብትሄድ ባትሄድ ጉዳይዋ እንዳልሆነ በመናገር በድንገት ኒኮል ላይ ትጮኽባታለች። ኒኮል በሁኔታው በጣም በመጎዳቷና በመናደዷ “ጋብሪኤልን ሁለተኛ ዓይኗን ማየት አልፈልግም!” በማለት ለእናቷ ትነግራታለች።

እንደ ኒኮልና ጋብሪኤል ሁሉ ልጆች በመካከላቸው አለመግባባት ሲያጋጥማቸው ብዙውን ጊዜ ወላጆች ጣልቃ ገብተው ማስታረቅ ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ ያለባቸው የተጎዳው ወገን እንዳያዝን ለማባበል ብቻ ሳይሆን ልጆቹ እንዲህ ያሉ አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ለማሠልጠን ጭምር ነው። በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች በተፈጥሯቸው ‘ልጅነት’ የሚያጠቃቸው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው ሊያስከትል ስለሚችለው ጉዳት ምንም ግንዛቤ የላቸውም። (1 ቆሮንቶስ 13:11) በመሆኑም ከቤተሰባቸው አባላትም ይሁን ከሌሎች ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያስችሏቸውን ባሕርያት እንዲያዳብሩ እገዛ ያስፈልጋቸዋል።

ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው ‘ሰላምን እንዲፈልጉና እንዲከተሉ’ አስፈላጊውን ማሠልጠኛ የመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። (1 ጴጥሮስ 3:11) የጥርጣሬ፣ የፍርሃትና የጥላቻ ስሜቶችን ለማሸነፍ በመጣር ደስታ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም ሰላም ፈጣሪ በመሆን የሚገኘው ደስታ ግን ከዚያ የላቀ ነው። ወላጅ ከሆናችሁ ልጆቻችሁ ሰላማዊ እንዲሆኑ እንዴት ማስተማር ትችላላችሁ?

‘የሰላምን አምላክ’ የማስደሰት ፍላጎት እንዲኖራቸው እርዷቸው

ይሖዋ “የሰላም አምላክ” የተባለ ከመሆኑም በላይ ‘ሰላም ሰጪ’ እንደሆነ ተደርጎም ተገልጿል። (ፊልጵስዩስ 4:9፤ ሮሜ 15:33 NW) በመሆኑም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው አምላክን የማስደሰትና ባሕርያቱን የመኮረጅ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመርዳት የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በጥሩ ሁኔታ ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ዮሐንስ የተመለከተውን አንድ አስደናቂ ራእይ በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ እርዷቸው፤ ዮሐንስ በዚህ ራእይ ላይ በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ የመረግድ ዕንቁ የመሰለ ዕጹብ ድንቅ ቀስተ ደመና ተመልክቶ ነበር። a (ራእይ 4:2, 3) ይህ ቀስተ ደመና በይሖዋ ዙሪያ ሰፍኖ የሚገኘውን ሰላምና መረጋጋት እንደሚያመለክት እንዲሁም ለሚታዘዙት ሁሉ እንዲህ ያሉትን በረከቶች እንደሚያፈስላቸው አስረዷቸው።

ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ “የሰላም ልዑል” በተባለው በልጁ በኢየሱስ በኩል መመሪያ ይሰጠናል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ኢየሱስ ከጠብና ከጭቅጭቅ መራቅን በሚመለከት ጠቃሚ ትምህርቶችን አስተምሯል። በመሆኑም እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ከትንንሽ ልጆቻችሁ ጋር አንብባችሁ ተወያዩባቸው። (ማቴዎስ 26:51-56፤ ማርቆስ 9:33-35) በተጨማሪም በአንድ ወቅት “ዐመፀኛ” የነበረው ጳውሎስ፣ በአኗኗሩ ላይ ለውጥ ያደረገበትንና “የጌታም አገልጋይ ሊጣላ አይገባውም፤ ይልቁን ለሰው ሁሉ ገር፣ . . . ትዕግሥተኛም መሆን ይገባዋል” በማለት የጻፈበትን ምክንያት አብራሩላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 1:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24) ልጆቻችሁ ከጠበቃችሁት በላይ አስደሳች ለውጥ ያደርጉ ይሆናል።

ኢቫን፣ የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ በትምህርት ቤት አውቶቡስ ላይ አንድ ልጅ ሰድቦት እንደነበረ ያስታውሳል። በወቅቱ የተሰማውን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በጣም ከመናደዴ የተነሳ ብድሬን ለመመለስ ፈልጌ ነበር! በኋላ ላይ ግን ጥል የሚፈልጉ ልጆችን በሚመለከት ቤት ውስጥ የተማርኩት ትምህርት ትዝ አለኝ። ይሖዋ ‘ለማንም ክፉን በክፉ እንዳልመልስ’ እንዲሁም ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንድኖር’ እንደሚፈልግብኝ አውቃለሁ።” (ሮሜ 12:17, 18) ኢቫን እንደምንም ብሎ ራሱን አረጋግቶ በየዋህነት መንፈስ መልስ በመስጠቱ ጠብ ሊያስነሳ የሚችለውን ሁኔታ መፍታት ችሏል። ይህን ያደረገው የሰላምን አምላክ ማስደሰት ስለፈለገ ነበር።

ሰላማዊ ወላጅ ሁኑ

ቤታችሁ ሰላም የሰፈነበት ነው? ከሆነ የምታደርጉትን በማየት ብቻ ልጆቻችሁ ስለ ሰላም ብዙ ሊማሩ ይችላሉ። ልጆቻችሁ ሰላማውያን እንዲሆኑ አስተምራችሁ ጥሩ ውጤት ማግኘታችሁ በአብዛኛው የተመካው የአምላክንና የክርስቶስን የሰላም መንገድ ለመከተል በምታደርጉት ጥረት ላይ ነው።—ሮሜ 2:21

ረስ እና ሲንዲ የተባሉ ባልና ሚስት ሁለቱን ልጆቻቸውን ሌሎች የሚያናድድ ነገር ሲያደርጉባቸው ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ምላሽ መስጠት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለማሠልጠን ብዙ ጥረት አድርገዋል። ሲንዲ እንዲህ ትላለች:- “እኔና ረስ ከልጆቻችንም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር አለመግባባቶች በሚያጋጥሙን ጊዜ የምናሳየው ባሕርይ እነሱም ተመሳሳይ ሁኔታ ሲገጥማቸው ችግሩን በሚፈቱበት መንገድ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።”

ስህተት በምትሠሩበት ጊዜም እንኳ (መቼም ስህተት የማይሠራ ወላጅ የለም) አጋጣሚውን ለልጆቻችሁ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማስተማር ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ። ስቲቨን “እኔና ባለቤቴ ቴሪ ሦስቱን ልጆቻችንን ገና ነገሩ በደንብ ሳይገባን በቁጣ ገንፍለን የቀጣናቸው ጊዜያት ነበሩ፤ በዚህ ጊዜ ይቅርታ እንጠይቃቸዋለን” በማለት ተናግሯል። ቴሪም አክላ እንዲህ ብላለች:- “ልጆቻችን እኛም ፍጹማን እንዳልሆንና ስህተቶች እንደምንሠራ እንዲያውቁ እናደርጋቸዋለን። ይህ ደግሞ በቤታችን ሰላም እንዲሰፍን ብቻ ሳይሆን ልጆቻችን ሰላምን መከታተል የሚችሉበትን መንገድ እንዲማሩ ረድቷቸዋል።”

ታዲያ ልጆቻችሁ እናንተ እነሱን ከምትይዙበት መንገድ እንዴት ሰላማዊ መሆን እንደሚቻል እየተማሩ ነው? ኢየሱስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” በማለት አሳስቧል። (ማቴዎስ 7:12) ጉድለቶች ቢኖሩባችሁም እንኳ ለልጆቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ እርግጠኞች ሁኑ። ልጆች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መመሪያ ሲሰጣቸው ነው።

ለቁጣ የዘገያችሁ ሁኑ

ምሳሌ 19:11 (የ1980 ትርጉም) “የቍጣን ስሜት መቈጣጠር አስተዋይነት ነው” ይላል። ልጆቻችሁ እንዲህ ያለ ማስተዋል እንዲያዳብሩ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ አባት የሆነው ዴቪድ፣ እሱና ባለቤቱ ማሪያን ጠቃሚ ሆኖ ያገኙትን አንድ መንገድ እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “አንድ ሰው የሚጎዳ ነገር ተናግሯቸው ወይም አድርጎባቸው በሚበሳጩበት ጊዜ ራሳቸውን በግለሰቡ ቦታ አስቀምጠው ሁኔታውን ለማጤን እንዲሞክሩ እንረዳቸዋለን። እንደሚከተሉት ያሉ ቀላል ጥያቄዎችን እንጠይቃቸዋለን:- ‘ግለሰቡ ውሎው ውጥረት የበዛበት ነበር? ቅናት አድሮበት ይሆን? አንድ ሰው አበሳጭቶት ይሆን?’” ማሪያን አክላ እንዲህ ብላለች:- “ይህ ደግሞ ነገሩን እያብሰለሰሉ ከመበሳጨት እንዲሁም ማን ጥፋተኛ እንደሆነና እንዳልሆነ ሙግት ከመግጠም ይልቅ እንዲረጋጉ ያደርጋቸዋል።”

እንደዚህ የመሰሉ ሥልጠናዎች ግሩም የሆኑ ውጤቶችን ሊያስገኙ ይችላሉ። በዚህ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ መጀመሪያ ላይ ተጠቅሳ የነበረችውን ኒኮል እናቷ ሚሼል ከጓደኛዋ ከጋብሪኤል ጋር እንዲታረቁ ከማድረግ ባለፈ መንገድ እንዴት እንደረዳቻት ልብ በል። ሚሼል እንዲህ ትላለች:- “እኔና ኒኮል ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) b የሚለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 14ን አብረን አነበብን። በኋላም ኢየሱስ አንድን ሰው ‘እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት’ ይቅር ማለት አለብን ሲል ምን ማለቱ እንደሆን አብራራሁላት። ኒኮል ስሜቷን ስትገልጽ በጥሞና ካዳመጥኳት በኋላ ጋብሪኤል የቅርብ ጓደኛዋ በጣም ሩቅ ወደሆነ አካባቢ ልትሄድባት በመሆኑ ሊሰማት የሚችለውን የሐዘንና የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንድትረዳላት ለማድረግ ጣርኩ።”—ማቴዎስ 18:21, 22

ኒኮል፣ ጋብሪኤል እንደዚያ እንድትጮኽባት ያደረጋት ምን ሊሆን እንደሚችል ማስተዋልዋ ስሜቷን እንድትረዳ እንዲሁም ስልክ በመደወል ይቅርታ እንድትጠይቅ አነሳስቷታል። ሚሼል እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ኒኮል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለሌሎች ስሜት የምትጠነቀቅና ሰዎች ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ነገሮችን የምትፈጽም ልጅ ሆናለች፤ ይህም ደስታ አስገኝቶላታል።”—ፊልጵስዩስ 2:3, 4

ልጆቻችሁን፣ በሚፈጠሩ ስህተቶችና አለመግባባቶች ከልክ በላይ እንዳይረበሹ እርዷቸው። እንደዚህ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ ለሌሎች በጎ ነገር ሲመኙና አፍቃሪዎች ሲሆኑ በማየት እርካታ እንድታገኙ ያስችላችኋል።—ሮሜ 12:10፤ 1 ቆሮንቶስ 12:25

ይቅር ባይ በመሆን ክብር እንዲያገኙ አበረታቷቸው

ምሳሌ 19:11 “በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው” ይላል። ኢየሱስ እጅግ በተጨነቀበት ጊዜ የይቅር ባይነትን ባሕርይ በማሳየት አባቱን መስሏል። (ሉቃስ 23:34) ልጆችህ የአንተን ይቅር ባይነት ሲመለከቱና ምን ያህል እንደሚያስደስት በግል ሲረዱ ይቅር ባይ መሆን ክብር እንደሆነ ሊማሩ ይችላሉ።

ከሴት አያቱ ጋር በመሆን ሥዕሎችን ከለር መቀባት የሚወደውን የአምስት ዓመቱን ዊሊን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንድ ቀን አያቱ ድንገት ከለር መቀባታቸውን አቁመው ዊሊን ተቆጡትና ትተውት ሄዱ። ዊሊም በሁኔታው አዘነ። የዊሊ አባት የሆነው ሳም እንዲህ ብሏል:- “አያቱ አልዛይመር በተባለ በሽታ ትሠቃያለች። ስለዚህ ችግሩን ለዊሊ ሊገባው በሚችል ሁኔታ አስረዳነው።” ዊሊን በብዙ አጋጣሚዎች ይቅር እንደተባለ ካስታወሱት በኋላ እሱም ለሌሎች ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንዳለበት ገለጹለት። ሳም፣ ዊሊ ከዚያ በኋላ በወሰደው እርምጃ በጣም ተገርሟል። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ትንሹ ልጃችን የ80 ዓመት ወደሆነችው አያቱ ሄዶ በጸጸት ስሜት ሲያናግራትና እጇን ይዞ ወደ ጠረጴዛው ሲወስዳት ስንመለከት እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ምን እንደተሰማን ልትገምቱ ትችላላችሁ!”

ልጆች የሌሎችን ጉድለትና ስህተት ‘ችለው’ ማለፋቸውና ይቅር ማለታቸው በእውነትም ክብር ይሆንላቸዋል። (ቈላስይስ 3:13) ሌላው ቀርቶ ሰዎች ሆን ብለው የሚያበሳጭ ነገር በሚያደርጉባቸው ጊዜም እንኳ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምላሽ መስጠታቸው ኃይል ሊኖረው እንደሚችል አረጋግጡላቸው፤ ምክንያቱም “የሰው መንገድ እግዚአብሔርን ደስ ሲያሰኘው፣ ጠላቶቹ እንኳ አብረውት በሰላም እንዲኖሩ ያደርጋል።”—ምሳሌ 16:7

ልጆቻችሁ ሰላማዊ እንዲሆኑ መርዳታችሁን ቀጥሉ

ወላጆች የአምላክን ቃል ተጠቅመው ‘በሰላማዊ’ ሁኔታ ‘ሰላምን በመዝራት’ ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ ለልጆቻቸው እውነተኛ የበረከት ምንጭ ይሆኑላቸዋል። (ያዕቆብ 3:18) እንዲህ ያሉ ወላጆች ግጭቶችን መፍታት በሚያስችሏቸውና ሰላማዊ ለመሆን በሚያስፈልጓቸው መሣሪያዎች ልጆቻቸውን እያስታጠቋቸው ነው። ይህ ደግሞ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ደስታና እርካታ እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ዳን እና ካቲ፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው ሦስት ልጆች አሏቸው። ዳን እንዲህ ይላል:- “በለጋ ዕድሜ ላይ ሳሉ እነሱን ማሠልጠን ተፈታታኝ የነበረ ቢሆንም ልጆቻችን በመንፈሳዊ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙ መሆናቸው በጣም አስደስቶናል። አሁን ከሌሎች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሲሆን ሰላም የሚያደፈርስ ነገር ሲገጥማቸው ሌሎችን በነፃ ይቅር ይላሉ።” ካቲም አክላ “ሰላም የአምላክ መንፈስ ፍሬ ክፍል በመሆኑ ይህ በተለይ ለእኛ የሚያበረታታ ነው” ብላለች።—ገላትያ 5:22, 23

ምንም እንኳ በልጆች ላይ የሚታየው ለውጥ መጀመሪያ ላይ አዝጋሚ ሊመስል ቢችልም ክርስቲያን ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጆቻችሁ ሰላማዊ እንዲሆኑ ለማስተማር ‘መታከት’ ወይም ‘ተስፋ መቁረጥ’ የለባችሁም። ይህን በምታደርጉበት ጊዜ ‘የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር እንደሚሆን’ እርግጠኞች ሁኑ።—ገላትያ 6:9፤ 2 ቆሮንቶስ 13:11

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! በተባለው መጽሐፍ ገጽ 75 ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው?

ሚዲያ አዌርነስ ኔት ወርክ “በመገናኛ ብዙኃን በሚተላለፍ መዝናኛ ውስጥ የሚታየው ዓመጽ” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ዋናው ገጸ ባሕርይም ሆነ ተቀናቃኙ በተደጋጋሚ ኃይል ሲጠቀሙ የሚያሳዩ ፊልሞች ችግሮችን ለመፍታት ብቸኛው ቁልፍ የኃይል እርምጃ መውሰድ ነው የሚል ሐሳብ ያስተላልፋሉ።” ጥናት ከተደረገባቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ፊልሞችና የሙዚቃ ቪዲዮዎች ውስጥ የኃይል እርምጃ መውሰድ መጥፎ ውጤት እንደሚያስከትል የጠቆሙት 10 በመቶ የሚያህሉት ብቻ ናቸው። ጽሑፉ እንዳለው በተቀሩት ላይ “የኃይል እርምጃ መውሰድ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ተገቢ፣ የተለመደና የማይቀር ነገር እንደሆነ ተደርጎ ቀርቧል።”

ይህ ሁኔታ ቴሌቪዥን በመመልከት ልማዳችሁ ላይ ማስተካከያ የማድረጉን አስፈላጊነት አያስገነዝባችሁም? በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉት መዝናኛዎች ልጆቻችሁ ሰላማውያን እንዲሆኑ የምታደርጉትን ጥረት መና እንዲያስቀርባችሁ አትፍቀዱ።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆቻችሁ ‘የሰላምን አምላክ’ የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርጉ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጎጂ ንግግሮችንና ድርጊቶችን ለማረም አስፈላጊውን ጥረት አድርጉ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆቻችሁ ይቅርታ መጠየቅና ይቅርታ ማድረግን መማር አለባቸው