የይሖዋ ሉዓላዊነትና የአምላክ መንግሥት
የይሖዋ ሉዓላዊነትና የአምላክ መንግሥት
‘ይሖዋ ሆይ፤ ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። ይሖዋ ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው።’—1 ዜና መዋዕል 29:11
1. ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት አለው የምንለው ለምንድን ነው?
“እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቶአል፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።” (መዝሙር 103:19) መዝሙራዊው አገዛዝን በተመለከተ መሠረታዊ የሆነውን ሐቅ በዚህ መንገድ ገልጾታል። ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት አለው።
2. ዳንኤል የይሖዋን መንፈሳዊ ግዛት የገለጸው እንዴት ነበር?
2 እርግጥ ነው፣ አንድ ገዥ ሉዓላዊ ገዥነቱን ለማሳየት እንዲችል ተገዥዎች ሊኖሩት ያስፈልጋል። ይሖዋ፣ በመጀመሪያ አንድያ ልጁን ከዚያም የመላእክት ሠራዊትን ወደ ሕልውና ካመጣ በኋላ በእነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታቱ ላይ መግዛት ጀመረ። (ቈላስይስ 1:15-17) ከብዙ ዘመናት በኋላ ነቢዩ ዳንኤል የይሖዋን አገዛዝ በተመለከተ ራእይ አይቶ ነበር። ዳንኤል እንዲህ ብሏል:- “እኔም ስመለከት፣ ‘ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ጥንታዌ ጥንቱም ተቀመጠ፤ . . . ሺህ ጊዜ ሺሆች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍ በፊቱ ቆመዋል።’” (ዳንኤል 7:9, 10) “ጥንታዌ ጥንቱ” የተባለው ይሖዋ ሕልቆ መሣፍርት ለሌላቸው ዘመናት፣ መንፈሳዊ ልጆቹን ያቀፈው ቤተሰብ ሉዓላዊ ገዥ ሆኖ ቆይቷል፤ በጣም ሰፊና ሥርዓታማ በሆነው በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ያሉት መንፈሳዊ ልጆችም ፈቃዱን የሚፈጽሙ “አገልጋዮቹ” ሆነው ይሠራሉ።—መዝሙር 103:20, 21
3. የይሖዋ ግዛት የሰፋው እንዴት ነው?
3 ውሎ አድሮም ይሖዋ ምድርን ጨምሮ ግዙፍና ውስብስብ የሆነውን አጽናፈ ዓለም በመፍጠር ግዛቱን አሰፋ። (ኢዮብ 38:4, 7) በሥርዓትና ያላንዳች ስህተት የሚንቀሳቀሱትን የሰማይ አካላት ከምድር ሆኖ ለሚመለከታቸው ሰው የሚመራቸው ወይም የሚቆጣጠራቸው አካል የሚያስፈልግ አይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “[ይሖዋ] ስላዘዘ ተፈጥረዋልና፣ . . . ከዘላለም እስከ ዘላለም አጸናቸው፤ የማይሻርም ሕግ ደነገገላቸው።” (መዝሙር 148:5, 6) ይሖዋ ምንጊዜም መንፈሳዊ አካላትን እንዲሁም ግዑዙን ጽንፈ ዓለም በመምራት፣ በመቆጣጠርና በማስተዳደር ሉዓላዊ ገዥነቱን ሲያሳይ ቆይቷል።—ነህምያ 9:6
4. ይሖዋ፣ የሰው ልጆችን የሚገዛው እንዴት ነው?
4 አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ሲፈጥር ደግሞ ሉዓላዊ ገዥነቱን በሌላ መንገድ አሳይቷል። ይሖዋ፣ የሰው ልጆች ዓላማ ያለውና አስደሳች ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ከማቅረቡም በላይ በምድር ያሉትን ፍጥረታት የመግዛት መብት ሰጥቷቸዋል፤ በዚህ መንገድ ሰዎች ከእነሱ በታች በሆኑ ፍጥረታት ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው አድርጓል። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:8, 9) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው አምላክ የሚገዛው ደግነት በተሞላበትና ለተገዥዎቹ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ ከመሆኑም በላይ ተገዥዎቹን ያከብራቸዋል። አዳምና ሔዋን ለይሖዋ ሉዓላዊነት እስከተገዙ ድረስ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ነበራቸው።—ዘፍጥረት 2:15-17
5. ይሖዋ ሉዓላዊ ገዥነቱን የሚያሳይበትን መንገድ እንዴት አድርገህ ትገልጸዋለህ?
5 ታዲያ ይህን ሁሉ ሁኔታ ከተመለከትን በኋላ ምን ብለን መደምደም እንችላለን? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ምንጊዜም ፍጥረታቱን ሁሉ ሲገዛ ቆይቷል። በሁለተኛ ደረጃ፣ አምላክ የሚገዛው ለተገዥዎቹ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ ከመሆኑም በላይ ያከብራቸዋል። በመጨረሻም ለአምላክ አገዛዝ መገዛታችንና አገዛዙን መደገፋችን ዘላለማዊ በረከት ያስገኝልናል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት እንደሚከተለው ብሎ ለመናገር መገፋፋቱ አያስደንቅም:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤ ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤ አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ።”—1 ዜና መዋዕል 29:11
የአምላክ መንግሥት ለምን አስፈለገ?
6. በአምላክ ሉዓላዊነትና በመንግሥቱ መካከል ምን ግንኙነት አለ?
6 የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ኃይሉን የሚጠቀም እስከሆነ ድረስ የአምላክ መንግሥት ለምን አስፈለገ? አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሉዓላዊ ገዥ ሥልጣኑን የሚጠቀመው በተገዥዎቹ ላይ በሾመው ወኪል አማካኝነት ነው። በመሆኑም የአምላክ መንግሥት፣ አምላክ በፍጥረታቱ ላይ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን የሚያሳይበት መንገድ ወይም ፍጡራኑን ለመግዛት የሚጠቀምበት ወኪል ነው።
7. ይሖዋ ሉዓላዊነቱን የሚያሳይበት አዲስ መንገድ ያዘጋጀው ለምን ነበር?
7 ይሖዋ ሉዓላዊነቱን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ነበር፤ አንድ አዲስ ሁኔታ በተፈጠረበት ጊዜም ሉዓላዊነቱን የሚያሳይበት ሌላ አዲስ መንገድ አዘጋጅቷል። ይህንን ያደረገው ዓመጸኛ የሆነ አንድ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ አዳምና ሔዋን በይሖዋ አገዛዝ ላይ እንዲያምጹ ባደረጋቸው ጊዜ ነበር። ይህ ዓመጽ በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነበር። በምን መንገድ? ሰይጣን፣ ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ ብትበላ ‘እንደማትሞት’ ሲነግራት ይሖዋ ሐሰተኛና እምነት የማይጣልበት እንደሆነ በተዘዋዋሪ መናገሩ ነበር። ከዚህም በላይ ሰይጣን፣ ሔዋንን “ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” ብሏታል። እዚህ ላይ ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ችላ ብለው በራሳቸው መንገድ ቢሄዱ የተሻለ እንደሚሆንላቸው ሐሳብ እያቀረበ ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-6) ይህ ደግሞ በአምላክ የመግዛት መብትና በአገዛዙ ትክክለኛነት ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ግድድር ነው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን ያደርግ ይሆን?
8, 9. (ሀ) አንድ ሰብዓዊ ገዥ በግዛቱ ውስጥ ዓመጽ ቢነሳ ምን ያደርጋል? (ለ) ይሖዋ በኤደን ዓመጽ ሲነሳ ምን አደረገ?
8 አንድ ገዥ በግዛቱ ውስጥ ዓመጽ ቢነሳ ምን ያደርጋል? ታሪክ የሚያውቁ ሰዎች እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች የተፈጸሙባቸውን ጊዜያት ያስታውሱ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሉዓላዊ ገዥ፣ ምንም ያህል ደግ ቢሆን ጉዳዩን ችላ ብሎ ከማለፍ ይልቅ ዓመጸኞቹን በክህደት በመወንጀል ፍርድ ይበይንባቸዋል። ከዚያም ገዥው ዓማጽያኑን በቁጥጥር ሥር አውሎ ሰላም እንዲያሰፍን አንድ ግለሰብ ይሾም ይሆናል። በተመሳሳይም ይሖዋ በዓመጸኞቹ ላይ ወዲያውኑ እርምጃ በመውሰድና ፍርድ በማስተላለፍ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠረው አሳይቷል። አዳምና ሔዋን የዘላለም ሕይወት ስጦታ የማይገባቸው እንደሆኑ ከፈረደባቸው በኋላ ከኤደን ገነት አባረራቸው።—ዘፍጥረት 3:16-19, 22-24
9 ይሖዋ፣ በሰይጣን ላይ ፍርድ ሲበይን ሉዓላዊ ገዥነቱን የሚያሳይበትና በግዛቱ ሁሉ ላይ ሰላም የሚያሰፍንበት አዲስ መንገድ እንደሚኖር ገለጸ። አምላክ፣ ለሰይጣን እንዲህ ብሎታል:- “በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:15) በመሆኑም ይሖዋ፣ ሰይጣንንና ግብረ አበሮቹን የሚያጠፋ እንዲሁም አገዛዙ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ‘ዘር’ የማስነሳት ብሎም ለዚህ ዘር ሥልጣን የመስጠት ዓላማ እንዳለው ገልጿል።—መዝሙር 2:7-9፤ 110:1, 2
10. (ሀ) ‘ዘሩ’ ማንን ያመለክታል? (ለ) ጳውሎስ የመጀመሪያውን ትንቢት ፍጻሜ አስመልክቶ ምን ብሏል?
10 ይህ ‘ዘር’ ኢየሱስ ክርስቶስንና ከእሱ ጋር አብረው የሚገዙ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ያመለክታል። አንድ ላይ ሆነው የአምላክን መሲሐዊ መንግሥት አቋቁመዋል። (ዳንኤል 7:13, 14, 27፤ ማቴዎስ 19:28፤ ሉቃስ 12:32፤ 22:28-30) ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ግልጽ የሆነው በአንድ ጊዜ አልነበረም። እንዲያውም የመጀመሪያው ትንቢት የሚፈጸምበት መንገድ ‘ላለፉት ረጅም ዘመናት የተሰወረ ምስጢር [“ቅዱስ ምስጢር፣” NW]’ ሆኖ ነበር። (ሮሜ 16:25, 26) ለበርካታ ዘመናት የእምነት ሰዎች ‘ቅዱሱ ምስጢር’ የሚገለጥበትንና የመጀመሪያው ትንቢት ፍጻሜ አግኝቶ የይሖዋ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበትን ጊዜ ሲጠባበቁ ቆይተዋል።—ሮሜ 8:19-21
‘ቅዱሱ ምስጢር’ ቀስ በቀስ ተገለጠ
11. ይሖዋ፣ ለአብርሃም ምን አሳወቀው?
11 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ይሖዋ ‘የአምላክ መንግሥት ቅዱስ ምስጢር’ ገጽታዎች ቀስ በቀስ እንዲታወቁ አደረገ። (ማርቆስ 4:11 NW) ይሖዋ ይህን ከገለጠላቸው ሰዎች መካከል “የእግዚአብሔር ወዳጅ” የተባለው አብርሃም ይገኝበታል። (ያዕቆብ 2:23) ይሖዋ ለአብርሃም ከእሱ “ታላቅ ሕዝብ” እንደሚገኝ ቃል ገብቶለት ነበር። ቆየት ብሎም “ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ” እንዲሁም “የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” ብሎታል።—ዘፍጥረት 12:2, 3፤ 17:6፤ 22:17, 18
12. ከጥፋት ውኃ በኋላ የሰይጣን ዘር የተገለጠው እንዴት ነበር?
12 በአብርሃም ዘመንም እንኳ የሰው ልጆች ሌሎችን ለመግዛትና የበላይ ለመሆን መሞከር ጀምረው ነበር። ለአብነት ያህል፣ የኖኅ የልጅ ልጅ የነበረውን ናምሩድን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ናምሩድም በምድር ላይ ኀያል ሰው እየሆነ ሄደ። በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ አዳኝ ነበረ።” (ዘፍጥረት 10:8, 9) በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ናምሩድና ሌሎች ራሳቸውን የሾሙ ገዥዎች ሰይጣን የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ነበሩ። እነሱም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው የሰይጣን ዘር ክፍል ሆነዋል።—1 ዮሐንስ 5:19
13. ይሖዋ፣ በያዕቆብ በኩል ምን ትንቢት ተናገረ?
13 ሰይጣን ሰብዓዊ ገዥዎች እንዲኖሩ ለማድረግ ቢጥርም ይሖዋ ምንጊዜም ዓላማውን ያስፈጽማል። ይሖዋ፣ የአብርሃም የልጅ ልጅ በሆነው በያዕቆብ በኩል ዓላማውን እንዲህ በማለት ገልጧል:- “በትረ መንግሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤ የገዥነት ምርኵዝም ከእግሮቹ መካከል። ገዥነት የሚገባው [“ሴሎ፣” የግርጌ ማስታወሻ] እስኪመጣ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል።” (ዘፍጥረት 49:10) “ሴሎ” የሚለው ቃል “ባለቤት የሆነው፤ ባለመብት የሆነው” የሚል ትርጉም አለው። በመሆኑም ይህ ትንቢታዊ ጥቅስ “በትረ መንግሥት” እንዲሁም “የገዥነት ምርኵዝ” ወይም ሉዓላዊነትን ለመቀበልና ‘በሕዝቦች’ ወይም በመላው የሰው ዘር ላይ ለመግዛት ሕጋዊ መብት ያለው አካል እንደሚመጣ ይጠቁማል። ይህ አካል ማን ይሆን?
“ሴሎ እስኪመጣ ድረስ”
14. ይሖዋ ከዳዊት ጋር ምን ቃል ኪዳን ገብቷል?
14 ከይሁዳ ዝርያዎች መካከል ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ንጉሥ እንዲሆን መጀመሪያ የመረጠው እረኛ የነበረውን የእሴይን ልጅ ዳዊትን ነበር። a (1 ሳሙኤል 16:1-13) ዳዊት በተለያየ ጊዜ ኃጢአት የሠራና አምላክን የበደለ ቢሆንም ለይሖዋ ሉዓላዊነት ታማኝ ስለነበር በይሖዋ ፊት ሞገስን አግኝቷል። ይሖዋ በኤደን ገነት የተናገረውን ትንቢት የበለጠ ግልጽ ለማድረግ “በእግርህ እንዲተካ ከአብራክህ የተከፈለ ዘር አስነሣልሃለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ” በማለት ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ይህ ቃል ኪዳን የሚያመለክተው በዳዊት እግር ተተክቶ የነገሠውን ልጁን ሰሎሞንን ብቻ አይደለም። ምክንያቱም ቃል ኪዳኑ አክሎ “እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ” ይላል። ይሖዋ ከዳዊት ጋር የገባው ይህ ቃል ኪዳን፣ ተስፋ የተደረገው የመንግሥት ‘ዘር’ ከጊዜ በኋላ በዳዊት የዘር ሐረግ እንደሚመጣ ግልጽ አደረገ።—2 ሳሙኤል 7:12, 13
15. የይሁዳ መንግሥት ለአምላክ መንግሥት ጥላ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ የሚችለው ለምንድን ነው?
15 ከዳዊት ጀምሮ ሊቀ ካህኑ በቅዱስ ዘይት የሚቀባቸው ነገሥታት ሥርወ መንግሥት ጀመረ። በመሆኑም እነዚህ ነገሥታት የተቀቡ ወይም መሲሖች ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። (1 ሳሙኤል 16:13፤ 2 ሳሙኤል 2:4፤ 5:3፤ 1 ነገሥት 1:39) እነዚህ ነገሥታት በይሖዋ ዙፋን ላይ እንደተቀመጡና በኢየሩሳሌም ለይሖዋ ንጉሥ ሆነው እንደሚገዙ ይገለጽ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 9:8) በዚህ መንገድ የይሁዳ መንግሥት የአምላክን መንግሥት ይወክል ነበር፤ እንዲሁም የይሖዋ ሉዓላዊነት መገለጫ ነበር።
16. የይሁዳ ነገሥታት አገዛዝ መጨረሻው ምን ሆነ?
16 ንጉሡም ሆነ ሕዝቡ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ሲገዙ እሱ ጥበቃ ያደርግላቸው እንዲሁም ይባርካቸው ነበር። በተለይ በሰሎሞን የግዛት ዘመን ተወዳዳሪ የሌለው ሰላምና ብልጽግና ነበር፤ ይህም የሰይጣን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ተወግዶና የይሖዋ ሉዓላዊነት ተረጋግጦ የአምላክ መንግሥት ሲገዛ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር የሚያሳይ ትንቢታዊ ጥላ ነበር። (1 ነገሥት 4:20, 25) የሚያሳዝነው ግን በዳዊት የዘር ሐረግ የተነሱት አብዛኞቹ ነገሥታት ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ባለመኖራቸው ሕዝቡ በጣዖት አምልኮና በሥነ ምግባር ብልግና ተዘፈቁ። በመጨረሻም ይሖዋ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን ይህን መንግሥት እንዲያጠፉት ፈቀደ። ሰይጣን የይሖዋ አገዛዝ ትክክል እንዳልሆነ ለማስመሰል ያደረገው ጥረት በዚህ ወቅት የተሳካ ይመስል ነበር።
17. በዳዊት የዘር ሐረግ የተነሱት ነገሥታት ይገዙበት የነበረው መንግሥት ቢወድቅም ይሖዋ ሉዓላዊ ገዥ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?
17 መጀመሪያ የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ከዚያም በዳዊት የዘር ሐረግ የተነሱት ነገሥታት ይገዙበት የነበረው የይሁዳ መንግሥት መውደቅ ይሖዋ የመግዛት መብት እንዳልነበረው ወይም በአግባቡ መግዛት እንዳልቻለ አያሳይም፤ ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ያሳደረውን ተጽዕኖ እንዲሁም የሰው ልጅ ከአምላክ ርቆ ራሱን መምራቱ ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት የሚጠቁም ነበር። (ምሳሌ 16:25፤ ኤርምያስ 10:23) ይሖዋ በዚህ ጊዜም ቢሆን ሉዓላዊ ገዥ እንደነበር ለማሳየት በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር:- “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ . . . ባድማ! ባድማ! ባድማ አደርጋታለሁ፤ የሚገባው ባለ መብት እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለእርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ።” (ሕዝቅኤል 21:26, 27) ይህ ጥቅስ ተስፋ የተደረገበት ‘ዘር’ ማለትም “የሚገባው ባለ መብት” በዚያን ጊዜ ገና እንዳልመጣ ይጠቁማል።
18. መልአኩ ገብርኤል ለማርያም ምን አላት?
18 እስቲ አሁን ደግሞ በ2 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ የተፈጸመውን ሁኔታ እንመልከት። መልአኩ ገብርኤል፣ በሰሜናዊ ፓለስቲና በገሊላ በምትገኘው በናዝሬት ከተማ ወደምትኖረው ማርያም የተባለች ድንግል ተላከ። መልአኩም እንዲህ አላት:- “እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”—ሉቃስ 1:31-33
19. ምን አስደናቂ ክንውን የሚፈጸምበት ጊዜ ቀርቦ ነበር?
19 በመጨረሻም ‘ቅዱሱ ምስጢር’ የሚታወቅበት ጊዜ ደረሰ። ተስፋ የተደረገበት ‘ዘር’ ዋነኛ ክፍል ሊገለጥ ነው። (ገላትያ 4:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:16) ሰይጣን የዚህን ዘር ተረከዝ ይቀጠቅጣል። ሆኖም ይህ ‘ዘር’ በምላሹ የሰይጣንን ራስ በመቀጥቀጥ እሱንም ሆነ ግብረ አበሮቹን ጠራርጎ ያጠፋቸዋል። ከዚህም በላይ ዘሩ፣ ሰይጣን ያስከተለው ጉዳት በሙሉ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት እንደሚስተካከልና የይሖዋ ሉዓላዊነት እንደሚረጋገጥ ይመሠክራል። (ዕብራውያን 2:14፤ 1 ዮሐንስ 3:8) ኢየሱስ ይህንን የሚፈጽመው እንዴት ነው? ልንከተለው የምንችለው ምን ምሳሌ ትቶልናል? መልሱን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በእስራኤል ላይ እንዲገዛ አምላክ መጀመሪያ የመረጠው ሳኦል ከብንያም ነገድ ነበር።—1 ሳሙኤል 9:15, 16፤ 10:1
ልታብራራ ትችላለህ?
• ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት እንዳለው የሚያሳየው ምንድን ነው?
• ይሖዋ፣ መንግሥት ያቋቋመው ለምንድን ነው?
• ይሖዋ ‘ቅዱሱን ምስጢር’ ቀስ በቀስ የገለጠው እንዴት ነበር?
• በዳዊት የዘር ሐረግ የተነሱት ነገሥታት ይገዙበት የነበረው መንግሥት ቢወድቅም ይሖዋ ሉዓላዊ ገዥ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በአብርሃም በኩል ምን እንደሚመጣ ተናገረ?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዳዊት የዘር ሐረግ የተነሱት ነገሥታት ይገዙበት የነበረው መንግሥት መውደቅ ይሖዋ የመግዛት መብት እንዳልነበረው አያሳይም የምንለው ለምንድን ነው?