ለይሖዋ ቀን ተዘጋጅተሃል?
ለይሖዋ ቀን ተዘጋጅተሃል?
“ታላቁ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ቅርብ ነው፤ ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል።”—ሶፎንያስ 1:14
1-3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ቀን ምን ይላል? (ለ) እኛስ ከፊታችን የሚጠብቀን የትኛው ‘የይሖዋ ቀን’ ነው?
ታላቁ የይሖዋ ቀን የሚለው አገላለጽ የ24 ሰዓት ርዝማኔ ያለውን ጊዜ ሳይሆን ይሖዋ በክፉዎች ላይ መለኮታዊ ፍርዱን የሚያስፈጽምበትን ረዘም ያለ ጊዜ የሚያመለክት ነው። ይህ ቀን የጨለማ፣ የመዓት፣ የቁጣ፣ የጭንቀትና የጥፋት ቀን በመሆኑ አምላክን ለማያገለግሉ ሰዎች አስፈሪ መሆኑ ምንም አያስደንቅም። (ኢሳይያስ 13:9፤ አሞጽ 5:18-20፤ ሶፎንያስ 1:15) የኢዩኤል ትንቢት “ወዮ ለዚያ ቀን፤ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ቀርቦአልና፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ እንደ ጥፋት ይመጣል” ይላል። (ኢዩኤል 1:15) ይሁን እንጂ በዚያ ታላቅ ቀን አምላክ “ልበ ቅኖችን” ያድናቸዋል።—መዝሙር 7:10
2 ‘የይሖዋ ቀን’ የሚለው አገላለጽ አምላክ በተለያዩ ጊዜያት የወሰዳቸውን የፍርድ እርምጃዎች ለማመልከት ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በባቢሎናውያን በጠፋችበት ወቅት በነዋሪዎቿ ላይ የይሖዋ ቀን መጥቶባቸው ነበር። (ሶፎንያስ 1:4-7) በተመሳሳይም አምላክ ልጁን ያልተቀበለውን የአይሁድ ብሔር በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሮማውያን አማካኝነት በማጥፋት ፍርዱን አስፈጽሟል። (ዳንኤል 9:24-27፤ ዮሐንስ 19:15) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ከአሕዛብ ሁሉ ጋር ስለሚዋጋበት’ የይሖዋ ቀን ትንቢት ይናገራል። (ዘካርያስ 14:1-3) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው መልእክት ላይ ይህንን ቀን ከክርስቶስ መገኘት ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። ይህ ጊዜ የጀመረው ኢየሱስ በሰማይ ዙፋን ላይ በተቀመጠበት በ1914 ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:1, 2) በግልጽ የሚታዩት ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት የይሖዋ ቀን በፍጥነት እየቀረበ ነው፤ በመሆኑም በሶፎንያስ 1:14 [NW] ላይ የተመሠረተውና “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል” የሚለው ጥቅስ የ2007 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት ጥቅስ መሆኑ ተስማሚ ነበር።
3 ታላቁ የአምላክ ቀን ስለቀረበ ዝግጁ ሆነህ የምትጠባበቅበት ጊዜ አሁን ነው። ታዲያ ለዚያ ቀን መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆነህ ለመጠባበቅ ልትወስዳቸው የሚገቡ ምን ተጨማሪ እርምጃዎች አሉ?
ዝግጁ ሁን
4. ኢየሱስ ራሱን ያዘጋጀው ለየትኛው ከባድ ፈተና ነበር?
4 ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ ደቀ መዛሙርቱን “ዝግጁ ሁኑ” በማለት መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 24:44) ኢየሱስ ይህን በተናገረበት ወቅት እሱ ራሱ ከፊቱ ለሚጠብቀው ከባድ ፈተና ማለትም ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ ለመሞት ተዘጋጅቶ ነበር። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ለፈተናው ራሱን ካዘጋጀበት መንገድ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
5, 6. (ሀ) ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር ለይሖዋ ቀን እንድንዘጋጅ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅር በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?
5 ኢየሱስ ለይሖዋና እሱ ላወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶች ከልብ የመነጨ ፍቅር ነበረው። ዕብራውያን 1:9 ኢየሱስን አስመልክቶ ሲናገር “ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ በላይ አስቀመጠህ፣ የደስታንም ዘይት ቀባህ” ይላል። ኢየሱስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱ ፍቅር ስለነበረው ለእሱ ያለውን ታማኝነት ጠብቋል። እኛም በተመሳሳይ ለአምላክ ፍቅር ካለን እንዲሁም ካወጣቸው ሕጎች ጋር ተስማምተን የምንኖር ከሆነ ጥበቃ ያደርግልናል። (መዝሙር 31:23) እንዲህ ያለው ፍቅርና ታዛዥነት ለታላቁ የይሖዋ ቀን ዝግጁ እንድንሆን ይረዳናል።
6 ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅር ነበረው። ‘ሕዝቡ እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ ያዘነላቸው’ ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 9:36) በዚህም ምክንያት ምሥራቹን ሰብኮላቸዋል። እኛም የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች እንድንሰብክ የሚገፋፋን እንዲህ ያለው ፍቅር ነው። ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ በትጋት መካፈላችንን እንድንቀጥል ያስችለናል፤ ይህ ደግሞ ለታላቁ የይሖዋ ቀን ዝግጁ እንድንሆን ይረዳናል።—ማቴዎስ 22:37-39
7. የይሖዋን ቀን በምንጠባበቅበት በዚህ ወቅት ደስተኞች እንድንሆን የሚያስችለን ምንድን ነው?
7 ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ይጓጓ ነበር። (መዝሙር 40:8) እኛም እንዲህ የሚሰማን ከሆነ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ ደስታ እናገኛለን። ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም በልግስና እንሰጣለን፤ ይህ ደግሞ እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) አዎን፣ የይሖዋ ‘ደስታ ብርታታችን ነው።’ ይህም ደስታ ለታላቁ የአምላክ ቀን ይበልጥ ዝግጁ እንድንሆን ያስችለናል።—ነህምያ 8:10
8. በጸሎት አማካኝነት ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
8 ኢየሱስ ወደ አምላክ ልባዊ ጸሎት ማቅረቡ ለሚያጋጥመው የእምነት ፈተና ዝግጁ እንዲሆን ረድቶታል። ክርስቶስ ዮሐንስ ባጠመቀው ወቅት ይጸልይ ነበር። ሐዋርያቱን ከመምረጡ በፊትም ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12-16) ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ምሽት ላይ ያቀረበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት ሲያነብ ልቡ የማይነካ ማን ነው? (ማርቆስ 14:32-42፤ ዮሐንስ 17:1-26) አንተስ እንደ ኢየሱስ የጸሎት ሰው ነህ? አዘውትረህ ወደ ይሖዋ ጸልይ፣ ረጅም ጸሎት የመጸለይ ልማድ ይኑርህ፣ የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለማግኘት ጣር እንዲሁም አመራሩን እንዳገኘህ ሲሰማህ ወዲያውኑ ተግባራዊ አድርግ። ታላቁ የአምላክ ቀን በፍጥነት እየቀረበ ባለበት በዚህ የሚያስጨንቅ ጊዜ በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከመቼውም ጊዜ የበለጠ በጸሎት ወደ ይሖዋ ከመቅረብ ወደኋላ አትበል።—ያዕቆብ 4:8
9. ስለ ይሖዋ ስም መቀደስ ማሰባችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
9 በተጨማሪም ኢየሱስ የይሖዋ ታላቅ ስም እንዲቀደስ የነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ከፊቱ ለሚጠብቀው ፈተና ዝግጁ እንዲሆን ረድቶታል። እንዲያውም ተከታዮቹ ወደ አምላክ በሚያቀርቡት ጸሎት ውስጥ “ስምህ ይቀደስ” የሚለውን ሐሳብ ማካተት እንደሚኖርባቸው አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) እኛም የይሖዋ ስም እንዲቀደስ ከልብ የምንፈልግ ከሆነ በስሙ ላይ ነቀፌታ የሚያመጣ ምንም ነገር ላለማድረግ ጥረት እናደርጋለን። ይህ ደግሞ ለታላቁ የይሖዋ ቀን ይበልጥ ዝግጁ እንድንሆን ያስችለናል።
አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይኖርብህ ይሆን?
10. ራሳችንን መመርመራችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
10 የይሖዋ ቀን ነገ ቢመጣ ከጥፋቱ ልትድን እንደምትችል ይሰማሃል? እያንዳንዳችን በድርጊታችን ወይም በዝንባሌያችን ላይ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገን እንደሆነ ለማወቅ ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። የሰው ሕይወት አጭርና ምንም ዋስትና የሌለው በመሆኑ ሁላችንም በየቀኑ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መኖር ያስፈልገናል። (መክብብ 9:11, 12፤ ያዕቆብ 4:13-15) ከዚህ በመነሳት በሕይወታችን ውስጥ ትኩረት የሚሹ አንዳንድ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።
11. የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን በተመለከተ ምን ግብ አለህ?
11 ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባው አንዱ ነጥብ ‘ታማኙ ባሪያ’ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድናነብ የሚሰጠን ምክር ነው። (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በዓመት አንድ ጊዜ አንብበህ ለመጨረስ ግብ ማውጣት ትችላለህ። ያነበብከውን የምታሰላስልበት ጊዜም ይኑርህ። በየቀኑ አራት የሚያህሉ ምዕራፎችን ብታነብ መጽሐፍ ቅዱስ ያሉትን 1,189 ምዕራፎች በአንድ ዓመት ውስጥ አንብበህ መጨረስ ትችላለህ። እያንዳንዱ የእስራኤል ንጉሥ የይሖዋን ሕግ “በሕይወቱ ዘመን ሁሉ” እንዲያነብ ይጠበቅበት ነበር። ኢያሱም ተመሳሳይ ነገር እንዳደረገ ግልጽ ነው። (ዘዳግም 17:14-20፤ ኢያሱ 1:7, 8) በጉባኤ ውስጥ ያሉ መንፈሳዊ እረኞች ‘ትክክለኛውን ትምህርት’ ለማስተላለፍ ስለሚረዳቸው የአምላክን ቃል በየቀኑ ማንበባቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ቲቶ 2:1
12. የይሖዋ ቀን መቅረቡ ምን እንድታደርግ ሊገፋፋህ ይገባል?
12 የይሖዋ ቀን መቅረቡ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ እንድትገኝና በተቻለህ መጠን ተሳትፎ እንድታደርግ ሊገፋፋህ ይገባል። (ዕብራውያን 10:24, 25) እንዲህ ማድረግህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ እንደመሆንህ መጠን የመስበክ ችሎታህን ያሻሽልልሃል። ይህ ደግሞ ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ ሰዎችን ፈልጎ ለማግኘትና ለመርዳት ያስችልሃል። (የሐዋርያት ሥራ 13:48) ከዚህም በላይ አረጋውያንን እንደ መርዳትና ወጣቶችን እንደ ማበረታታት ባሉ ሌሎች የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ላይ የምታደርገውን ተሳትፎ መጨመር ትችል ይሆናል። እንዲህ ማድረግህ እርካታ እንደሚያስገኝልህ ምንም ጥርጥር የለውም!
ከሌሎች ጋር ያለህ ግንኙነት
13. አዲሱን ሰው መልበስን በተመለከተ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?
13 የይሖዋ ቀን በጣም እየቀረበ እንደመሆኑ መጠን “እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” ለመልበስ የበለጠ ጥረት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን? (ኤፌሶን 4:20-24) አምላካዊ ባሕርያትን እያዳበርክ ስትሄድ ሌሎች ‘በመንፈስ እየኖርክ’ እንዲሁም የመንፈስን ፍሬ እያፈራህ መሆኑን ማስተዋላቸው አይቀርም። (ገላትያ 5:16, 22-25) አንተም ሆንክ ቤተሰብህ አዲሱን ሰው ለመልበስ ያደረጋችሁትን ጥረት የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን መጥቀስ ትችላለህ? (ቈላስይስ 3:9, 10) ለምሳሌ ያህል፣ በሰዎች ዘንድ የምትታወቀው ለእምነት አጋሮችህም ሆነ ለሌሎች በምታደርገው ደግነት ነው? (ገላትያ 6:10) ቅዱሳን መጻሕፍትን አዘውትረህ ማጥናትህ የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆነህ እንድትጠብቅ የሚያስችሉህን አምላካዊ ባሕርያት እንድታዳብር ይረዳሃል።
14. አንድ ሰው ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማዳበር በሚያደርገው ጥረት መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይ ያለበት ለምንድን ነው?
14 በትንሽ በትልቁ የምትናደድ ብትሆንና ራስህን የመግዛት ባሕርይ ይበልጥ ማዳበር እንዳለብህ ቢሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ራስን መግዛት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በውስጥህ የሚያፈራው ፍሬ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ከገለጸው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንገድ አንተም መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልይ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ . . . እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”—ሉቃስ 11:9-13
15. በአንተና በአንድ የእምነት ባልንጀራህ መካከል አለመግባባት ቢፈጠር ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
15 በአንተና በአንድ የእምነት ባልንጀራህ መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል እንበል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ የጉባኤውን ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ ስትል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። (መዝሙር 133:1-3) በማቴዎስ 5:23, 24 ወይም በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ አድርግ። ቅር እንደተሰኘህ ፀሐይ እንድትገባብህ ከመፍቀድ ይልቅ ሁኔታውን በፍጥነት ለማስተካከል ጣር። አለመግባባቱን ለመፍታት ብዙውን ጊዜ የሚያስፈልገው ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን ብቻ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ “እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ” በማለት ጽፏል።—ኤፌሶን 4:25, 26, 32
16. የትዳር ጓደኛሞች በምን ረገድ ርኅራኄ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል?
16 የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ርኅራኄ ማሳየታቸውና ይቅር ባይ መሆናቸው አስፈላጊ ነው። ከትዳር ጓደኛህ ጋር ባለህ ግንኙነት ይበልጥ አፍቃሪና ርኅሩኅ መሆን እንዳለብህ ከተሰማህ በአምላክና በቃሉ በመታገዝ እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት አድርግ። በ1 ቆሮንቶስ 7:1-5 ላይ በሚገኘው ምክር መሠረት ግንኙነታችሁን ለማሻሻልና ለትዳር ጓደኛህ ምንጊዜም ታማኝ ሆነህ ለመኖር በበኩልህ ማድረግ የምትችለው ነገር ይኖር ይሆን? ባልም ሆነ ሚስት ‘ርኅራኄ’ እንዲያሳዩ ከሚጠበቅባቸው አጋጣሚዎች መካከል አንዱ ይህ እንደሆነ ግልጽ ነው።
17. አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ከሠራ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል?
17 አንድ ከባድ ኃጢአት ብትሠራ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በተቻለህ ፍጥነት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ጥረት አድርግ። የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ ከመፈለግ ወደኋላ አትበል። አብረውህ መጸለያቸውና የሚሰጡህ ምክር መንፈሳዊ ጤንነትህ እንዲመለስልህ ይረዳሃል። (ያዕቆብ 5:13-16) በሠራኸው ኃጢአት እንደተጸጸትህ በሚያሳይ መንገድ ወደ ይሖዋ ጸልይ። እንዲህ አለማድረግህ ሁልጊዜ የበደለኛነት ስሜት እንዲሰማህ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሕሊናህ ይረብሽሃል። ዳዊት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር፤ ሆኖም ኃጢአቱን ለይሖዋ ከተናዘዘ በኋላ ከፍተኛ እፎይታ አግኝቷል! እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መተላለፉ ይቅር የተባለለት፣ ኀጢአቱም የተሸፈነለት፣ እንዴት ቡሩክ ነው! እግዚአብሔር ኀጢአቱን የማይቈጥርበት፣ በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው፣ እርሱ ቡሩክ ነው።” (መዝሙር 32:1-5) ይሖዋ ለሠሩት ኃጢአት ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን ይቅር ይላል።—መዝሙር 103:8-14፤ ምሳሌ 28:13
የዓለም ክፍል አለመሆን
18. ለዓለም ምን አመለካከት ሊኖርህ ይገባል?
18 በሰማይ የሚኖረው አባታችን ቃል የገባልንን አስደናቂ አዲስ ዓለም በጉጉት እንደምትጠባበቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ ከአምላክ ለራቀውና የክፋት ጎዳና ለሚከተለው ዓለም ምን አመለካከት አለህ? “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን አልነበረውም። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30) ዲያብሎስም ሆነ እሱ የሚገዛው ዓለም በአንተ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው እንደማትፈልግ ግልጽ ነው። በመሆኑም “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ” የሚለውን የሐዋርያው ዮሐንስ ምክር ተግባራዊ አድርግ። ይህን ምክር መከተልህ የጥበብ እርምጃ ነው፤ ምክንያቱም “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:15-17
19. ክርስቲያን ወጣቶች ማበረታቻ የሚሰጣቸው ምን ዓይነት ግብ እንዲያወጡ ነው?
19 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ‘ከዓለም ርኩሰት ራሳቸውን እንዲጠብቁ’ እየረዳችኋቸው ነው? (ያዕቆብ 1:27) ሰይጣን ልክ እንደ አንድ ዓሣ አጥማጅ ልጆቻችሁን ማጥመድ ይፈልጋል። ልጆቻችሁ የሰይጣን ዓለም ክፍል እንዲሆኑ ለማድረግ ታስበው የተቋቋሙ የተለያዩ ክበቦችና ድርጅቶች አሉ። ይሁንና የይሖዋ አገልጋዮች ቀድሞውንም ቢሆን በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት የሚተርፈው ብቸኛ ድርጅት አባል ናቸው። በመሆኑም ክርስቲያን ወጣቶች ‘ለጌታ ሥራ እንዲተጉ’ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው አምላክን የሚያስከብር አስደሳችና አርኪ ሕይወት እንዲመሩ ብሎም ለይሖዋ ቀን ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ግብ እንዲያወጡ መርዳት ያስፈልጋቸዋል።
ከታላቁ የይሖዋ ቀን ባሻገር ተመልከት
20. የዘላለም ሕይወት ተስፋ እውን እንዲሆንልን ማድረግ የሚገባን ለምንድን ነው?
20 የዘላለም ሕይወት ተስፋ እውን ከሆነልህ የይሖዋን ቀን በተረጋጋ ልብ መጠበቅ ትችላለህ። (ይሁዳ 20, 21 NW) በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ አለህ፤ በዚያ ገነት ውስጥ የወጣትነት ጉልበትህ ይታደሳል፤ በተጨማሪም የምትፈልጋቸው ግቦች ላይ ለመድረስ የሚያስችል በቂ ጊዜ የሚኖርህ ሲሆን ስለ ይሖዋ የምትማርበት ሰፊ አጋጣሚም ታገኛለህ። በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጆች ስለ አምላክ የሚያውቁት በጣም ጥቂት ቢሆንም ወደፊት ለዘላለም ስለ እሱ መማር ትችላለህ። (ኢዮብ 26:14) እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል!
21, 22. ከሞት የሚነሱ ሰዎች ስለ ምን ነገሮች ያጫውቱናል? እኛስ ምን እናስተምራቸዋለን?
21 በገነት ውስጥ ከሞት የሚነሱ ሰዎች እነሱ በኖሩበት ዘመን ስለተከናወኑ አንዳንድ ነገሮች በዝርዝር ይነግሩናል። ሔኖክ አምላክን ለማይፈሩ ሰዎች የይሖዋን መልእክት ለማወጅ ያስቻለውን ድፍረት እንዴት እንዳገኘ ይነግረናል። (ይሁዳ 14, 15) ኖኅ መርከቡን የመገንባቱ ሥራ ምን ይመስል እንደነበር እንደሚነግረን ምንም ጥርጥር የለውም። አብርሃምና ሣራ በዑር የነበራቸውን የተመቻቸ ኑሮ ትተው በድንኳን መኖር ሲጀምሩ ምን ተሰምቷቸው እንደነበር ያጫውቱናል። አስቴር ደግሞ ሕዝቧን ከጥፋት ለማዳን እንዲሁም ሐማ በሕዝቡ ላይ የጠነሰሰውን ሴራ ለማክሸፍ ስላደረገቻቸው ነገሮች በዝርዝር ትነግረናለች። (አስቴር 7:1-6) ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ስላሳለፋቸው ሦስት ቀናት ሲነግረንና መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ሲያጠምቅ የተሰማውን ስሜት ሲያጫውተን በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። (ሉቃስ 3:21, 22፤ 7:28) በእርግጥም ወደፊት በዝርዝር የምናውቃቸው በርካታ አስደናቂ ነገሮች ይኖራሉ!
22 በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ ከሞት የሚነሱ ሰዎች ‘የአምላክን እውቀት እንዲያገኙ’ የመርዳት አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል። (ምሳሌ 2:1-6) በዛሬው ጊዜ ሰዎች የይሖዋ አምላክን እውቀት አግኝተው ተግባራዊ ሲያደርጉት መመልከት እንዴት ያስደስታል! ወደፊት ደግሞ ይሖዋ ከበርካታ ዓመታት በፊት የኖሩ ሰዎችን ለማስተማር የምታደርገውን ጥረት ሲባርክልህና እነሱም የተማሩትን በአድናቆት ተግባራዊ ሲያደርጉ ስትመለከት ምን ያህል እንደምትደሰት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ!
23. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?
23 የይሖዋ ሕዝቦች በመሆናችን ያገኘነውን በረከት ቆጥረን ልንዘልቀው አንችልም። (መዝሙር 40:5) በተለይ ደግሞ ከአምላክ ላገኘናቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች አመስጋኞች ነን። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ታላቁን የይሖዋን ቀን እየተጠባበቅን ለአምላክ በሙሉ ልባችን ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባችንን እንቀጥል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ‘የይሖዋ ቀን’ ምንድን ነው?
• የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆነህ መጠባበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
• ታላቁ የአምላክ ቀን እጅግ በቀረበበት በዚህ ጊዜ ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልገናል?
• የይሖዋ ቀን ካለፈ በኋላ በጉጉት የምትጠብቃቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ራሱን ለፈተና ዝግጁ አድርጓል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሞት የሚነሱ ሰዎች የይሖዋን እውቀት እንዲያገኙ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!