በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ርኅሩኆች” ሁኑ

“ርኅሩኆች” ሁኑ

“ርኅሩኆች” ሁኑ

የሰው ልጆች የዚህን ዘመን ያህል ከረሃብ፣ ከበሽታ፣ ከድህነት፣ ከወንጀል፣ ከእርስ በርስ ግጭትና ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ትግል የገጠሙበትና ከርኅራኄ የመነጨ እርዳታ የሚሹበት ወቅት ኖሮ አያውቅም። ርኅራኄ፣ የሌሎችን ሥቃይ ወይም መከራ መረዳትንና ችግሩን ለማቃለል መፈለግን ያመለክታል። ፍንትው ብላ የወጣች ፀሐይ ደስ የሚል ሙቀት እንደምትሰጥ ሁሉ ርኅራኄም የተጨነቀን ነፍስ ሊያረጋጋ፣ ሥቃዩን ሊያቀልለትና ስሜቱ የተደቆሰን ሰው መንፈስ ሊያድስ ይችላል።

በተግባራችንም ሆነ በምንናገራቸው ቃላት ማለትም ለሌሎች አሳቢነት በማሳየትና በሚፈልጉን ጊዜ አብረናቸው በመሆን ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን። ይህን የምናደርገው ለቤተሰባችን አባላት፣ ለጓደኞቻችንና ለምናውቃቸው ሰዎች ብቻ መሆን የለበትም። ለማናውቃቸው ሰዎችም ጭምር ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ላይ “የሚወዷችሁን ብቻ የምትወዱ ከሆነ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ?” በማለት ጠይቋል። ርኅሩኅ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ አክሎም “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:46, 47፤ 7:12

ወርቃማው ሕግ በመባል የሚታወቀውን ይህን ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታገኘዋለህ። ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀ መመሪያ የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ቅዱሳን መጻሕፍት፣ በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ ሰዎችን የመርዳት ግዴታ እንዳለብን በተደጋጋሚ ጊዜያት ይገልጻሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤትና የእኛም ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ዋነኛ ምሳሌ እንደሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ “[አምላክ] አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች መብት ይሟገታል። ለመጻተኞችም ስለሚያስብ ምግብና ልብስ ይሰጣቸዋል” የሚል እናነባለን። (ዘዳግም 10:18 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ይሖዋ አምላክ “ለተበደሉት የሚፈርድ፣ ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ” እንደሆነ ተገልጿል። (መዝሙር 146:7) ይሖዋ የተቸገሩ ስደተኞችን በተመለከተ “መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት” በማለት ደንግጓል።—ዘሌዋውያን 19:34

ይሁን እንጂ ርኅራኄ ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ በቈላስይስ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት ጽፎላቸዋል:- “አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ . . . የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል። . . . የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን . . . ልበሱ።”—ቈላስይስ 3:9, 10, 12

በመሆኑም ርኅራኄን ማዳበር ጥረት ይጠይቃል። ርኅራኄ፣ ክርስቲያኖች “አዲሱን ሰው” በመልበስ እንዲያዳብሯቸው ከሚጠበቅባቸው ባሕርያት አንዱ ነው። ጳውሎስ የኖረው ጭካኔ በሞላባት የጥንቷ ሮም ውስጥ ነበር። ይህ ሐዋርያ የእምነት አጋሮቹ በባሕርያቸው ላይ ጉልህ ለውጥ አድርገው ከበፊቱ ይበልጥ አዛኞችና ርኅሩኆች እንዲሆኑ አበረታቷቸዋል።

ርኅራኄ ያለው ኃይል

ርኅራኄ የሚያሳዩ ሰዎች ደካማ እንደሆኑና በቀላሉ እንደሚጎዱ ተደርገው ይታያሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ትክክል ነው?

በጭራሽ! እውነተኛ ርኅራኄ እንድናሳይ የሚገፋፋን የፍቅር ተምሳሌት ከሆነው አምላክ የሚመነጭ ጥልቅ ፍቅር ነው። “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” (1 ዮሐንስ 4:16) ይሖዋ “የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3) እዚህ ላይ “ርኅራኄ” ተብሎ የተገለጸው ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “ሐዘኔታ ማሳየት፣ ችግር ለደረሰባቸው መራራት” ማለት ነው። ሌላው ቀርቶ ይሖዋ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነው”!—ሉቃስ 6:35

ፈጣሪያችን እኛም እንደ ርኅራኄ ያሉ ሰናይ ባሕርያትን እንድናሳይ ይፈልግብናል። ሚክያስ 6:8 እንዲህ ይላል:- “ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ . . . አይደለምን?” ምሳሌ 19:22 ደግሞ “ሰው የሚመኘው ጽኑ ፍቅር” ወይም ፍቅራዊ ደግነት እንደሆነ ይናገራል። የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስም “አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ” በማለት ለተከታዮቹ ተመሳሳይ ምክር ሰጥቷል።—ሉቃስ 6:36

ርኅራኄ የተትረፈረፈ በረከት ስለሚያስገኝ ርኅሩኅ እንድሆን የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን። “ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል” የሚለው በምሳሌ 11:17 ላይ የሚገኘው ጥቅስ እውነት መሆኑን ብዙ ጊዜ እንመለከታለን። ችግር ላይ ለወደቀ ሰው ርኅራኄ ስናሳይ አምላክ ያደረግነውን ነገር ለእሱ እንደተደረገ ውለታ ይቆጥረዋል። አገልጋዮቹ ለሚያከናውኑት ማንኛውም የርኅራኄ ድርጊት ውለታ መመለስ እንዳለበት ይሰማዋል። ንጉሥ ሰሎሞን “ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል” በማለት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ጽፏል። (ምሳሌ 19:17) ጳውሎስም “ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ” በማለት ጽፏል።—ኤፌሶን 6:8

ርኅራኄ ሰላም እንዲኖር የማድረግ፣ ግጭትን ወይም አለመግባባትን ደግሞ የማስቀረት ኃይል አለው። አለመግባባትን ለማስወገድ ከመርዳቱም በላይ ይቅርታ ለማድረግ መንገድ ይከፍታል። አለመግባባት የሚፈጠረው ብዙውን ጊዜ ሐሳባችንን ወይም ስሜታችንን እንደምንፈልገው አድርገን መግለጽ ባለመቻላችን ወይም ድርጊታችን የተሳሳተ ትርጉም ስለተሰጠው ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ርኅራኄ፣ የተፈጠረውን አለመግባባት ለማስወገድና ሰላም እንዲኖር ለማድረግ ይረዳል። በርኅሩኅነቱ የሚታወቅን ሰው ይቅር ማለት ቀላል ነው። ርኅራኄ፣ ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሰጠውን “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳናል።—ቈላስይስ 3:13

ርኅራኄ—ሐዘኔታ በተግባር ሲገለጽ

ከዚህም በላይ ርኅራኄ፣ ጭንቀትን የማቅለል ኃይል አለው። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ርኅራኄ ለተጨነቁ ሰዎች ሐዘኔታ እንድናሳይና መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች ችግራቸውን እንድንረዳላቸው ያደርገናል። ርኅራኄ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች መራራትንና እነሱን ለመርዳት ጠቃሚ እርምጃ መውሰድን ያጠቃልላል።

ክርስቲያኖች የሌሎችን ችግር በመረዳት ኢየሱስን መምሰል ይችላሉ። ኢየሱስ ሌሎችን በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ ለመርዳት ጊዜ አጥቶ አያውቅም። ሰዎች ተቸግረው ከተመለከተ በርኅራኄ ተነሳስቶ እነሱን ለመርዳት ይጥር ነበር።

ኢየሱስ በመንፈሳዊ ሁኔታ ድሃ የሆኑ ሰዎች ሲያይ ምን እንደተሰማው ተመልከት:- “ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) እዚህ ላይ “አዘነላቸው” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “አንድን ሰው አንጀቱ እንዲላወስ የሚያደርገውን ስሜት” እንደሚያመለክት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ተናግረዋል። እንዲያውም ይህ ቃል በግሪክኛ ቋንቋ የርኅራኄን ስሜት ለመግለጽ ከሚያገለግሉት ኃይለኛ ቃላት አንዱ እንደሆነ ይነገራል።

በተመሳሳይም ርኅሩኅ ክርስቲያኖች፣ ሌሎች ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ችግር ሲደርስባቸው እነሱን ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆች . . . ሁኑ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:8) ለምሳሌ ያህል፣ ችግረኛ የሆነ አንድ የክርስቲያኖች ቤተሰብ አባላት በጤና ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ባስፈለጋቸው ጊዜ በሄዱበት አካባቢ የነበሩ የእምነት አጋሮቻቸው ለስድስት ወር ያህል ኪራይ ሳይከፍሉ የሚኖሩበት ቤት ሰጧቸው። ባልየው እንዲህ ይላል:- “በየቀኑ እየመጡ ስለ ደህንነታችን ይጠይቁን ነበር፤ የሚሰጡን ማበረታቻ እንግድነት እንዳይሰማን አድርጎናል።”

እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ የማያውቋቸው ሰዎች ስለሚያስፈልጋቸው ነገርም ያስባሉ። ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን የማያውቋቸውን ሰዎች ለማገልገል በደስታ ይጠቀሙበታል። በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ከዚያ በፊት ጨርሶ የማያውቋቸውን ሰዎች የረዱት ፈቃደኛ ሠራተኞች የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።

ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው የክርስቲያን ጉባኤ ርኅራኄና ፍቅራዊ ደግነት የሰፈነበት ነው። ፍቅር፣ የጉባኤው አባላት ሌሎችን ማገልገል የሚችሉበትን መንገድ እንዲፈልጉ ያነሳሳቸዋል። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወላጅ የሌላቸው ልጆችና መበለቶች የተለያዩ የግል ችግሮች ስላሉባቸው አሳቢነት እንድታሳዩአቸውና ችግራቸውን እንድትረዱላቸው ይፈልጉ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉት የጉባኤያችሁ አባላት ድህነትን፣ የቤት ችግርን ወይም ሌሎች የግል ችግሮቻቸውን መቋቋም እንዲሁም ከሕክምና ወጪ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን የአቅም ውስንነት ማሸነፍ እንዲችሉ ልትረዷቸው ትችላላችሁ?

በግሪክ የሚኖሩ የአንድ ባልና ሚስትን ሁኔታ እንመልከት። ባልየው በጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ሕክምና ያስፈልገው ነበር። እሱና ባለቤቱ ብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወሰዱ። እነዚህ ክርስቲያኖች ኑሯቸውን የሚመሩት የብርቱካን ምርታቸው ተሰብስቦ በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ነበር። ታዲያ እነሱ ሆስፒታል ሳሉ የብርቱካን ምርቱን ማን ይሰበስብላቸዋል? በአካባቢያቸው የሚገኘው ጉባኤ ይህን አደረገላቸው። የጉባኤው አባላት ብርቱካኑን ለቅመው በመሸጥ በችግር ላይ የወደቁት ባልና ሚስት ገቢ እንዲያገኙ ከማድረጋቸውም በላይ ከጭንቀት እንዲገላገሉ ረድተዋቸዋል።

ርኅራኄ በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ርኅሩኅ የሆኑ ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ የተጨነቁ ሰዎች በዋነኝነት የሚፈልጉት በደግነት ቤታቸው ሄዶ የሚጠይቃቸውና ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጣቸው፣ ችግራቸውን የሚረዳላቸው እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ የሚሰጣቸው ሰው እንደሆነ ይገነዘባሉ።—ሮሜ 12:15

ርኅራኄ የሰፈነበት ማኅበረሰብ

ዓለም አቀፉ የክርስቲያን ጉባኤ፣ ርኅራኄና ደግነት የሚታይበት እንዲሁም ሰላምና ማጽናኛ የሚገኝበት ሥፍራ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ርኅራኄ ሰዎችን እንደሚስብ ጭካኔ ደግሞ እንደሚያሸሽ ይገነዘባሉ። በመሆኑም የሰማዩን አባታቸውን ለመምሰል ሲሉ ተግባራዊ በሆኑ መንገዶች ‘ርኅራኄ’ ለማሳየት ይጥራሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያናዊ ማኅበረሰባቸው ውስጥ የሰፈነውን ርኅራኄ፣ ፍቅርና አሳቢነት እንድታጣጥም ሞቅ ባለ ስሜት ይጋብዙሃል። ማኅበረሰባቸውን አስደሳችና ማራኪ ሆኖ እንደምታገኘው እርግጠኞች ናቸው።—ሮሜ 15:7

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ፣ የቈላስይስ ክርስቲያኖች ርኅራኄን እንዲለብሱ ጽፎላቸዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሰዎች ተቸግረው ሲመለከት በርኅራኄ ተነሳስቶ እነሱን ለመርዳት ይጥር ነበር