“ውድ የሆነው ስጦታህ”
“ውድ የሆነው ስጦታህ”
እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው a የተባለውን መጽሐፍ በሚመለከት ይህን አስተያየት የሰጡት የቀድሞ የቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ግለሰቡ ይህን መጽሐፍ ያገኙት አንድ ጎረቤታቸው ለጥየቃ ቤታቸው በሄደበት ወቅት ነበር። ከጊዜ በኋላ የሚከተለውን የአድናቆት ደብዳቤ ጽፈዋል:- “ቤቴ ድረስ መጥተህ ስለጠየቅኸኝ በእጅጉ ተደስቻለሁ፤ ይበልጥ የማረከኝ ግን ‘በታላቁ ሰው’ ላይ ብቻ የሚያተኩረው ውድ የሆነው ስጦታህ ነው።”
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መጽሐፉን ከመረመሩ በኋላ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል:- “ሰዎች የወንጌልን መልእክት ለመስማት ይበልጥ ፍላጎት ቢያሳድሩና ኢየሱስ የሰጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ቢያደርጉ ኖሮ ዛሬ ያለው ዓለም ፈጽሞ የተለየ ገጽታ በኖረው ነበር። ይህ ቢሆን ኖሮ የጸጥታው ምክር ቤት ባላስፈለገ እንዲሁም የአሸባሪዎች ጥቃትና ዓመጽ በዓለም ላይ ቦታ ባልኖራቸው ነበር።” ምንም እንኳ ግለሰቡ ይህ ሐሳብ የሕልም እንጀራ እንደሆነ ቢሰማቸውም ጎረቤታቸው ላደረገው ነገር ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል።
ደብዳቤው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ሕልመኛ አይደላችሁም፤ ወይም ደግሞ የወደፊቱ ጊዜ ምንም ተስፋ የለውም የሚል አፍራሽ አመለካከት ያላችሁም አይደላችሁም። ከዚህ ይልቅ የሰው ልጅ ጥረት ካደረገ የሰዎችም ሆነ ነገሮች ያሉበት ሁኔታ ይሻሻላል የሚል እምነት ካላቸው ሰዎች የምትመደቡ ናችሁ።”
የይሖዋ ምሥክሮች የተሻለ ዓለም ሊመጣ የሚችለው በሰዎች ጥረት ሳይሆን አምላክ በሚወስደው እርምጃ እንደሆነ ያምናሉ። እንዲሁም ታላቁን ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል ይጥራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ ቤትህ መጥተው አነጋግረውህ ያውቃሉ? እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠውን ታላቅ ሰው በሚመለከት ከእነሱ ጋር ብትነጋገር በውይይቱ ልትደሰት እንደምትችል እናምናለን። የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር የማረካቸውን መጽሐፍ ለአንተም ቢሰጡህ ደስ ይላቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።