በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ጸንታችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ የሚያደርግላችሁን ማዳን እዩ’

‘ጸንታችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ የሚያደርግላችሁን ማዳን እዩ’

‘ጸንታችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ የሚያደርግላችሁን ማዳን እዩ’

“እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ከእኔ ጋር ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” —መዝሙር 118:6

1. የሰው ዘር በቅርቡ ምን ያጋጥመዋል?

 በቅርቡ የሰው ዘር እስከ ዛሬ አይቶት የማያውቅ እጅግ አስከፊ የሆነ መከራ ያጋጥመዋል። ኢየሱስ በዘመናችን የሚከሰተውን ይህን መከራ አስመልክቶ ትንቢት ሲናገር ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለው የሌለ፣ ታላቅ መከራ ይሆናል። ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልተረፈ ነበረ፤ ስለ ተመረጡት ሲባል ግን እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ።”—ማቴዎስ 24:21, 22

2. ታላቁ መከራ እስካሁን እንዳይጀምር ያደረገው ምንድን ነው?

2 በሰዎች የማይታዩት መላእክት ይህ ታላቅ መከራ እንዳይጀምር አራቱን የምድር ነፋሳት አግደው ይዘዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በሰጠው ራእይ ላይ ይህ የሆነበትን ምክንያት ተመልክቷል። አረጋዊው ሐዋርያ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማእዘኖች ቆመው አየሁ፤ እነርሱም . . . አራቱን የምድር ነፋሶች ያዙ። ከዚያም የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከምሥራቅ ሲመጣ አየሁ፤ እርሱም . . . አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ እንዲህ አላቸው፤ ‘በአምላካችን አገልጋዮች ግንባር ላይ ማኅተም እስከምናደርግባቸው ድረስ ምድርን ወይም ባሕርን፣ ወይም ዛፎችን አትጒዱ።’”—ራእይ 7:1-3

3. በታላቁ መከራ መጀመሪያ ላይ ምን ይፈጸማል?

3 በተቀቡት ‘የአምላክ አገልጋዮች’ ላይ የመጨረሻ ማኅተም የማድረጉ ሂደት ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ነው። አራቱ መላእክት የጥፋት ነፋሳቱን ለመልቀቅ ተዘጋጅተዋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በመጀመሪያ የሚከሰተው ነገር ምንድን ነው? አንድ መልአክ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን፣ እንዲህ ባለ ኀይል ትወረወራለች፤ ተመልሳም አትገኝም” በማለት መልስ ሰጥቷል። (ራእይ 18:21) ይህ ሲፈጸም ማለትም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ሲጠፋ በሰማይ እንዴት ያለ ደስታ ይሆናል!—ራእይ 19:1, 2

4. ወደፊት እንደሚፈጸሙ የምንጠብቃቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

4 የምድር ብሔራት ሁሉ ኃይላቸውን አስተባብረው በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ይነሳሉ። እነዚህ ብሔራት ታማኝ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የሚያደርጉት ጥረት ይሳካላቸዋል? ሁኔታው ሲታይ የሚሳካላቸው ሊመስል ይችላል። ሆኖም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን የተሰለፈው የሰማይ ሠራዊት እነዚህን ሰብዓዊ ኃይሎች ድምጥማጣቸውን ያጠፋል። (ራእይ 19:19-21) በመጨረሻም ዲያብሎስና መላእክቱ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ወደማያደርጉበት ጥልቅ ውስጥ ይጣላሉ። ለአንድ ሺህ ዓመት ስለሚታሰሩ ከዚያ በኋላ የሰው ልጆችን ማሳሳት አይችሉም። ከጥፋቱ ለሚተርፉት እጅግ ብዙ ሰዎች ይህ እንዴት ያለ ታላቅ እፎይታ ያስገኝላቸዋል!—ራእይ 7:9, 10, 14፤ 20:1-3

5. ለይሖዋ ታማኝ የሚሆኑ ሰዎች ደስታ የሚያስገኝ ምን አጋጣሚ ይኖራቸዋል?

5 እነዚህን አስደናቂና አስፈሪ ክስተቶች የምንመለከትበት ጊዜ ቅርብ ነው። ይሖዋ እነዚህን ሁሉ እርምጃዎች የሚወስደው የመግዛት መብቱን ማለትም ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ ነው። ለይሖዋ ታማኝ ከሆንና ጽኑ አቋማችንን በመጠበቅ ሉዓላዊነቱን ከደገፍን ለስሙ መቀደስና ለዓላማው መሳካት የበኩላችንን ድርሻ የማበርከት አጋጣሚ እናገኛለን። ይህ ደግሞ ወደር የሌለው ደስታ ያስገኝልናል!

6. ወደፊት ከሚያጋጥሙን ነገሮች አንጻር የትኛውን ታሪክ እንመረምራለን?

6 እነዚህ ታላላቅ ክስተቶች ለሚፈጸሙበት ጊዜ ተዘጋጅተናል? በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ እምነት አለን? ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜና የተሻለ ነው ብሎ ባሰበው መንገድ ሊረዳን እንደሚችል እንተማመናለን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ የጻፈላቸውን ሐሳብ ማስታወሳችን ጥሩ ነው። ጳውሎስ “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” ብሏቸው ነበር። (ሮሜ 15:4) ትምህርት፣ ማጽናኛና ተስፋ እንድናገኝ ከተጻፉልን ነገሮች መካከል ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጻውያን ከባድ የጭቆና ቀንበር ነጻ እንዳወጣቸው የሚናገረው ታሪክ ይገኝበታል። ይሖዋ እስራኤላውያንን ባዳነበት ወቅት የተከናወኑትን አስደናቂ ክስተቶች በጥልቀት መመርመራችን ታላቁ መከራ በፍጥነት እየቀረበ ባለበት በዚህ ጊዜ ትልቅ ማበረታቻ ይሆንልናል።

ይሖዋ ሕዝቡን አዳነ

7. በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ግብጽ ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር?

7 ጊዜው 1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። ይሖዋ ቀደም ሲል በግብጻውያን ላይ ዘጠኝ መቅሰፍቶችን አምጥቷል። ከዘጠነኛው መቅሰፍት በኋላ ፈርዖን “ከፊቴ ጥፋ! ስማ! ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ” በማለት ሙሴን አባረረው። ሙሴም “እንዳልከው ይሁን! እኔም ዳግመኛ ከፊትህ አልደርስም” በማለት መለሰለት።—ዘፀአት 10:28, 29

8. እስራኤላውያን ከጥፋቱ ለመዳን የሚያስችል ምን መመሪያ ተሰጣቸው? መመሪያውን መከተላቸውስ ምን ውጤት አስገኘላቸው?

8 ይሖዋ በፈርዖንና በግብጻውያን ላይ አንድ የመጨረሻ መቅሰፍት እንደሚያመጣ ለሙሴ ነገረው። በአቢብ (ኒሳን) ወር 14ኛ ቀን ላይ የእያንዳንዱ ግብጻዊና የእንስሶቻቸው በኩር እንደሚገደል ገለጸለት። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን አምላክ በሙሴ በኩል የሰጣቸውን መመሪያ በጥንቃቄ በመከተል ሕይወታቸውን ማትረፍ ይችላሉ። እስራኤላውያን የቤታቸውን መቃንና ጉበን በበግ ጠቦት ደም መቀባት እንዲሁም ከቤታቸው ሳይወጡ መቆየት ይጠበቅባቸው ነበር። ታዲያ በዚያ ሌሊት ምን ተፈጸመ? ሙሴ ‘እኩለ ሌሊት ላይ እግዚአብሔር በግብፅ ምድር የነበረውን በኵር ሁሉ ቀሠፈ’ በማለት ተናግሯል። በዚህ ጊዜ ፈርዖን አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ተነሡ . . . ከሕዝቤ መካከል ውጡ! ሂዱ፤ በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን አምልኩ” አላቸው። ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ እስራኤላውያን ቁጥሩ በውል ከማይታወቅ “ድብልቅ ሕዝብ” ጋር በመሆን ወዲያውኑ ግብጽን ለቅቀው ወጡ።—ዘፀአት 12:1-7, 29, 31, 37, 38

9. አምላክ፣ እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ የመራቸው በየትኛው አቅጣጫ ነበር? ለምንስ?

9 ለእስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመሄድ አቋራጩ መንገድ በሜድትራኒያን ባሕር በኩል አድርገው በፍልስጥኤማውያን ምድር መጓዝ ነበር። ሆኖም ይህ ጠላቶቻቸው የሚኖሩበት አካባቢ ነው። በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡን አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ እንዳይገቡ ለማድረግ ሲል ቀይ ባሕር አካባቢ ወደሚገኘው ምድረ በዳ መራቸው። በጉዞው ላይ ያለው ሕዝብ በሚሊዮን የሚቆጠር ቢሆንም የሚጓዘው በተደራጀ ሁኔታ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእስራኤል ልጆች የጦርነት ዓይነት አሰላለፍ ይዘው ከግብጽ ምድር እንደወጡ’ ይናገራል።—ዘፀአት 13:17, 18 NW

‘ይሖዋ የሚያደርግላችሁን ማዳን እዩ’

10. አምላክ እስራኤላውያን በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ የነገራቸው ለምንድን ነው?

10 ከዚህ በኋላ ያልጠበቁት ትእዛዝ ተሰጣቸው። ይሖዋ ሙሴን “እስራኤላውያን ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው፤ በበኣልዛፎንም አንጻር በባሕሩ አጠገብ ይስፈሩ” አለው። እስራኤላውያን ይህንን መመሪያ ተከትለው ሲጓዙ በተራሮችና በቀይ ባሕር መካከል በሚገኝ ምንም ማምለጫ የሌለው በሚመስል ቦታ ላይ ደረሱ። ይሁንና ይሖዋ እንዲህ ያደረገው ያለ ምክንያት አልነበረም። ሙሴን እንዲህ አለው:- “የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] መሆኔን ያውቃሉ።”—ዘፀአት 14:1-4

11. (ሀ) ፈርዖን ምን እርምጃ ወሰደ? በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ምን ተሰማቸው? (ለ) ሙሴ ለእስራኤላውያን ምን መልስ ሰጣቸው?

11 ፈርዖን እስራኤላውያን ግብጽን ለቅቀው እንዲወጡ መፍቀዱ ስህተት እንደሆነ ስለተሰማው 600 ምርጥ የጦር ሠረገሎችን ይዞ ተከተላቸው። እስራኤላውያን የግብጽን ሠራዊት ከሩቅ ሲመለከቱ በፍርሃት ርደው “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን?” በማለት በሙሴ ላይ ጮኹ። ሙሴ ግን ይሖዋ እንደሚያድናቸው በመተማመን እንዲህ አላቸው:- “አትፍሩ። ጸንታችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርግላችሁን ማዳን እዩ። . . . ይሖዋ ራሱ ለእናንተ ይዋጋል፤ እናንተም ዝም ብላችሁ ትመለከታላችሁ።”—ዘፀአት 14:5-14 NW

12. ይሖዋ ሕዝቡን ያዳነው እንዴት ነው?

12 ሙሴ እንደተናገረው ይሖዋ በመላእክት ተጠቅሞ ለእስራኤላውያን ይዋጋላቸዋል። አንድ የይሖዋ መልአክ እስራኤላውያንን ሲመራ የነበረው የደመና ዓምድ በተአምራዊ ሁኔታ ወደኋላቸው እንዲመጣ አደረገ። ይህ ዓምድ ግብጻውያኑ ጨለማ እንዲሆንባቸው ሲያደርግ ለእስራኤላውያን ደግሞ ብርሃን እንዲሆንላቸው አድርጓል። (ዘፀአት 13:21, 22፤ 14:19, 20) ሙሴ አምላክ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ። ታሪኩ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እግዚአብሔር ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ . . . እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ አለፉ።” ግብጻውያን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ፤ ይሁን እንጂ ከሕዝቡ ጎን የነበረው ይሖዋ ግብጻውያን ግራ እንዲጋቡ አደረጋቸው። ከዚያም ሙሴን “ውሃው ግብፃውያንን ሠረገሎቻቸውንና ፈረሰኞቻቸውን ተመልሶ እንዲሸፍናቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ” አለው። በዚህ መንገድ የፈርዖን ሠራዊት አንድም ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ጠፋ!—ዘፀአት 14:21-28፤ መዝሙር 136:15

ይሖዋ እስራኤላውያንን ካዳነበት መንገድ የምናገኘው ትምህርት

13. እስራኤላውያን ከጥፋት ከዳኑ በኋላ ምን አደረጉ?

13 እስራኤላውያን ተአምራዊ በሆነ መንገድ መዳናቸው ምን ስሜት አሳድሮባቸዋል? ሙሴና እስራኤላውያን በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ “ከፍ ከፍ ብሎ ከብሮአልና፣ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ . . . እግዚአብሔር፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል” በማለት ይሖዋን በመዝሙር አወድሰውታል! (ዘፀአት 15:1, 18) አዎን፣ መጀመሪያ የታያቸው ነገር ይሖዋን ማወደስ ነበር። በዚህ ሁኔታ የይሖዋ ሉዓላዊነት ተረጋገጠ።

14. (ሀ) እስራኤላውያን ያጋጠማቸው ሁኔታ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? (ለ) የ2008 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው?

14 ከእነዚህ አስገራሚ ክስተቶች ምን ትምህርት፣ ማጽናኛና ተስፋ እናገኛለን? ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ፈተና ማስወገድ እንደሚችል እንገነዘባለን። ችግሮቹ ምንም ይሁኑ ምን ማስወገድ ይችላል። ይሖዋ ኃይለኛውን የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ቀይ ባሕር እንዲከፈል ስላደረገ ባሕሩ እስራኤላውያን እንዳይሻገሩ እንቅፋት ሊሆንባቸው አልቻለም። በተጨማሪም ይሖዋ ቀይ ባሕር ለፈርዖን ሠራዊት መቀበሪያው እንዲሆን ማድረግ ችሏል። በዚህ ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን እኛም እንደ መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንድንል ይገፋፋናል። (መዝሙር 118:6) ከዚህም በላይ በሮሜ 8:31 ላይ የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት ማጽናኛ ይሆኑናል። ጥቅሱ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?” ይላል። በእርግጥም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ ቃላት በይሖዋ እንድንተማመን ያደርጉናል! እንዲሁም በውስጣችን ሊሰማን የሚችለው ፍርሃትና ጥርጣሬ ተወግዶ ልባችን በተስፋ እንዲሞላ ያስችሉናል። ስለሆነም የ2008 የዓመት ጥቅስ “ጸንታችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ . . . የሚያደርግላችሁን ማዳን እዩ” የሚል መሆኑ በጣም ተስማሚ ነው!—ዘፀአት 14:13 NW

15. እስራኤላውያን ከግብጽ ነጻ በወጡበት ወቅት ታዛዥ መሆናቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነበር? ዛሬስ ታዛዥነት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

15 እስራኤላውያን ከግብጽ ነጻ ስለመውጣታቸው ከሚናገረው ታሪክ ምን ተጨማሪ ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ይሖዋ እንድናደርግ የሚፈልገው ነገር ምንም ይሁን ምን መታዘዝ እንዳለብን እንማራለን። እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል ለማክበር ስለሚያደርጉት ዝግጅት የተሰጣቸውን ዝርዝር መመሪያ ታዘዋል። ኒሳን 14 ሌሊት ከቤታቸው አልወጡም። በመጨረሻ ከግብጽ የወጡትም በተሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት ‘የጦርነት ዓይነት አሰላለፍ’ ተከትለው ነበር። (ዘፀአት 13:18 NW) እኛም ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው! (ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም) ከኋላችን የሚሰማውን “ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል፣ . . . ‘መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ’” የሚለውን የአምላክ ቃል በጥሞና ማዳመጥ ይኖርብናል። (ኢሳይያስ 30:21) ታላቁ መከራ ወደሚጀምርበት ጊዜ ይበልጥ እየተቃረብን ስንሄድ ዝርዝር መመሪያዎች ሊሰጡን ይችላሉ። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ጉዟችን አስተማማኝ መሆኑ የተመካው ከሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር ቦታችንን ይዘን እኩል በመሄዳችን ላይ ነው።

16. ይሖዋ እስራኤላውያንን ነጻ ለማውጣት ነገሮችን አቅጣጫ ካስያዘበት መንገድ ምን እንማራለን?

16 ይሖዋ እስራኤላውያንን በተራሮችና በቀይ ባሕር መካከል ወደሚገኝ አደገኛ ቦታ መርቷቸው እንደነበር አስታውስ። ሁኔታው ሲታይ ትክክለኛ አካሄድ አይመስልም ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ያደረገው ያለ ምክንያት አልነበረም፤ ይህ ሁኔታ ለእሱ ክብር ለሕዝቡ ደግሞ መዳንን አስገኝቷል። በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ድርጅታዊ አሠራሮች ግልጽ አይሆኑልን ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ ታማኝ በሆነው ድርጅቱ በኩል በሚሰጠን መመሪያ እንድንተማመን የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንዳንድ ጊዜ ጠላቶቻችን የተሳካላቸው ይመስል ይሆናል። ነገሮችን የማስተዋል ችሎታችን ውስን ስለሆነ ስለ ጉዳዩ የተሟላ ግንዛቤ ላይኖረን ይችላል። ቢሆንም ይሖዋ ጥንት ለእስራኤላውያን እንዳደረገው ሁሉ በትክክለኛው ጊዜ ነገሮችን አቅጣጫ የማስያዝ ችሎታ አለው።—ምሳሌ 3:5

በይሖዋ ታመኑ

17. አምላክ በሚሰጠን አመራር ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

17 እስራኤላውያን በቀን የደመና ዓምድ በሌሊት ደግሞ የእሳት ዓምድ እንደሚመራቸው ሲገነዘቡ ምን ያህል የመተማመን ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል ገምት! የእውነተኛው ‘አምላክ መልአክ’ በጉዟቸው እየመራቸው እንደነበር ግልጽ ነው። (ዘፀአት 13:21, 22፤ 14:19) ዛሬም ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚመራ፣ እንደሚጠብቅና እንደሚያድን መተማመን እንችላለን። ‘[ይሖዋ] ታማኞቹን አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል’ በሚለው ቃል ላይ እምነት መጣል እንችላለን። (መዝሙር 37:28) መላእክት በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች እየረዱ እንዳሉ በፍጹም አንርሳ። በእነሱ እርዳታ ‘ጸንተን መቆምና ይሖዋ የሚያደርግልንን ማዳን ማየት’ እንችላለን።—ዘፀአት 14:13 NW

18. “የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ” መልበስ ያለብን ለምንድን ነው?

18 ሁላችንም በእውነት መንገድ ላይ ‘ጸንተን እንድንቆም’ የሚያስችለን ምንድን ነው? ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የጠቀሰውን መንፈሳዊ የጦር ዕቃ መልበሳችን ነው። ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ” በማለት የሰጠውን ምክር ልብ እንበል። ይህን የጦር ዕቃ ሙሉ በሙሉ ለብሰናል? በመጪዎቹ ወራት ሁላችንም እያንዳንዱን መንፈሳዊ የጦር ዕቃ በተገቢው ሁኔታ መልበሳችንን ለማረጋገጥ ራሳችንን መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ጠላታችን ሰይጣን ዲያብሎስ ድክመታችንን ስለሚያውቅ ሳናስበው ሊያጠምደን ወይም በደካማ ጎናችን ሊያጠቃን ይሞክራል። ከክፉ መንፈሳዊ ኃይላት ጋር ውጊያ አለብን። ቢሆንም ይሖዋ በሚሰጠን ብርታት ውጊያውን በአሸናፊነት መወጣት እንችላለን!—ኤፌሶን 6:11-18፤ ምሳሌ 27:11

19. ከጸናን ምን ልዩ መብት እናገኛለን?

19 ኢየሱስ ተከታዮቹን “ጸንታችሁም በመቆም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 21:19) የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ፈተና በታማኝነት ከሚቋቋሙትና በአምላክ ጸጋ አማካኝነት ‘ጸንተው በመቆም ይሖዋ የሚያደርግላቸውን ማዳን ለማየት’ ከሚታደሉት ሰዎች መካከል ለመሆን ያብቃን!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በቅርቡ ምን አስደናቂ ክስተቶች ይፈጸማሉ?

• ይሖዋ በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት የማዳን ኃይሉን ያሳየው እንዴት ነው?

• ወደፊት ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የ2008 የዓመት ጥቅስ “ጸንታችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ . . . የሚያደርግላችሁን ማዳን እዩ” የሚል ነው። —ዘፀአት 14:13 NW

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል”

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈርዖን ግትር መሆኑ በግብጽ ላይ ጥፋት አስከትሏል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን ይሖዋ ያዘዛቸውን በሙሉ በመፈጸማቸው ከጥፋት ተርፈዋል