በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወታቸው ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርገዋል​—አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ?

ሕይወታቸው ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርገዋል​—አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ?

ሕይወታቸው ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርገዋል​—አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ?

ማርክ ካናዳ ውስጥ የሚኖር ወንድም ሲሆን ለጠፈር ምርምር ድርጅቶች የሚያገለግሉ የተራቀቁ መሣሪያዎችን በሚያመርት ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። ይህ ወንድም ግማሽ ቀን እየሠራ የዘወትር አቅኚ ሆኖ ያገለግል ነበር። አንድ ቀን አለቃው ከፍተኛ ደሞዝ የሚያስገኝ የሥራ እድገት ሊሰጠው እንዳሰበ ይገልጽለታል። ሥራውን ከተቀበለ ሙሉ ቀን መሥራት ይጠበቅበታል። ማርክ ምን አደረገ?

ኤሚ በፊሊፒንስ የምትኖር እህት ስትሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ወደ ማጠናቀቁ ገደማ ላይ የዘወትር አቅኚ ሆና ታገለግል ነበር። ከዚያ በኋላ የሙሉ ቀን ሥራ እንድትሠራ ግብዣ ቀረበላት። ሥራው ጠቀም ያለ ክፍያ የሚያስገኝ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜዋን የሚወስድባት ነበር። ኤሚ ምን ውሳኔ አድርጋ ይሆን?

ማርክና ኤሚ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያደረጉ ሲሆን ምርጫቸው ያስከተለው ውጤት በጥንቷ ቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች የተሰጠው ምክር ጥበብ ያዘለ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በዚህ ዓለም የሚጠቀሙም [ሙሉ በሙሉ] እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ’ በማለት ጽፏል።—1 ቆሮ. 7:29-31

ዓለምን ተጠቀምበት፤ ግን ሙሉ በሙሉ አይሁን

ማርክና ኤሚ ውሳኔያቸው ምን ውጤት እንዳስከተለባቸው ከማየታችን በፊት፣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ የተጠቀመበት “ዓለም” (ወይም በግሪክኛው ኮስሞስ) የሚለው ቃል ምን ትርጉም እንዳለው በአጭሩ እንመልከት። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ የተጠቀሰው ኮስሞስ የሚለው ቃል የምንኖርበትን የዓለም ሥርዓት ማለትም ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ በአጠቃላይ የሚያመለክት ሲሆን ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያስፈልጉንን እንደ መጠለያ፣ ምግብና ልብስ ያሉ ነገሮችም ይጨምራል። * እንደነዚህ የመሰሉትን የዕለት ተዕለት ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት አብዛኞቻችን ሥራ መያዝ ያስፈልገናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን በማቅረብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታችንን ለመወጣት ዓለምን ከመጠቀም ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም። (1 ጢሞ. 5:8) ያም ሆኖ ግን ‘ዓለም እንደሚያልፍ’ እንገነዘባለን። (1 ዮሐ. 2:17) በመሆኑም ዓለምን “ሙሉ በሙሉ” ሳይሆን የሚያስፈልገንን ያህል ብቻ እንጠቀምበታለን።—1 ቆሮ. 7:31 NW

በርካታ ወንድሞችና እህቶች በዓለም አጠቃቀማችን ላይ የተቻለንን ያህል ገደብ እንድናበጅ በሚናገረው በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተገፋፍተው ያሉበትን ሁኔታ እንደገና መርምረዋል፣ በሥራ የሚያሳልፉትን ጊዜ ቀንሰዋል እንዲሁም አኗኗራቸውን ቀላል አድርገዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ከቤተሰባቸው ጋርም ሆነ በይሖዋ አገልግሎት የሚያሳልፉት ተጨማሪ ጊዜ ስላስገኘላቸው ብዙም ሳይቆይ እርምጃው ሕይወታቸው ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን እንዳደረገላቸው ተገንዝበዋል። ከዚህም በላይ አኗኗራቸውን ቀላል ማድረጋቸው በዓለም ላይ ብዙም እንዳይተማመኑ፤ በአንጻሩ ደግሞ በይሖዋ ላይ ያላቸው ትምክህት እየጨመረ እንዲሄድ አድርጓቸዋል። አንተስ ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም አኗኗርህን ቀላል ማድረግ ትችላለህ?—ማቴ. 6:19-24, 33

“ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንደቀረብን ይሰማናል”

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ማርክ ዓለምን ሙሉ በሙሉ እንዳንጠቀም የተሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተል የቀረበለትን ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ የሥራ እድገት ሳይቀበል ቀረ። ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ማርክ አዲሱን ሥራ እንዲቀበል ለማግባባት አለቃው ከበፊቱ የበለጠ ደሞዝ እንደሚያገኝ ነገረው። ማርክ “ይህ ፈተና ነበር፤ ሆኖም በድጋሚ ግብዣውን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳልሆን ቀረሁ” በማለት ተናግሯል። ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲገልጽ የሚከተለውን ብሏል:- “እኔና ባለቤቴ ፓውላ በተቻለን መጠን ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ለማድረግ ፈልገን ነበር። በመሆኑም አኗኗራችንን ቀላል ለማድረግ ወሰንን። ግባችን ላይ ለመድረስ የሚያስችለንን ጥበብ እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ ጸለይንና እሱን በስፋት ማገልገል የምንጀምርበትን ቁርጥ ያለ ጊዜ ወሰንን።”

ፓውላ እንዲህ በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች:- “በአንድ ሆስፒታል ውስጥ በጸሐፊነት በሳምንት ሦስት ቀን እሠራ የነበረ ሲሆን ጥሩ ደሞዝም አገኝ ነበር። በተጨማሪም የዘወትር አቅኚ ሆኜ አገለግል ነበር። ይሁን እንጂ እኔም እንደ ማርክ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄጄ ይሖዋን የማገልገል ፍላጎት ነበረኝ። ሆኖም የሥራ መልቀቂያ ሳስገባ አለቃዬ ለዋና ጸሐፊነት አዲስ ክፍት የሥራ መደብ እንዳለና ለዚያ ብቁ እንደሆንኩ ነገረችኝ። በሆስፒታሉ ውስጥ በጸሐፊነት ሥራ የመጨረሻውን ከፍተኛ ክፍያ የሚያስገኘው ይህ ቦታ ነበር፤ ሆኖም ለመልቀቅ ያደረግሁትን ውሳኔ አልቀየርኩም። ለዚህ የሥራ መደብ ማመልከት ያልፈለግሁበትን ምክንያት ለአለቃዬ ስነግራት እንዲህ ያለ እምነት በማሳየቴ አደነቀችኝ።”

ብዙም ሳይቆይ ማርክና ፓውላ ካናዳ ውስጥ በአንድ ገለልተኛ አካባቢ በሚገኝ ትንሽ ጉባኤ ውስጥ በልዩ አቅኚነት እንዲያገለግሉ ተመደቡ። ወደዚያ በመሄዳቸው ምን ውጤት አገኙ? ማርክ እንዲህ ይላል:- “የዕድሜዬን ግማሽ ለሚጠጉ ዓመታት የቆየሁበትን አስተማማኝ ሥራዬን በለቀቅሁ ጊዜ ፍርሃት አድሮብኝ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ አገልግሎታችንን ባርኮልናል። መንፈሳዊ ስጦታ ለሌሎች ማካፈል መቻላችን ከፍተኛ የሆነ የደስታ ስሜት አስገኝቶልናል። በተጨማሪም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ትዳራችን ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን ረድቶናል። ጭውውታችን ሁሉ በጣም ጠቃሚ በሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኗል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንደቀረብን ይሰማናል።” (ሥራ 20:35) ፓውላም አክላ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ሥራህንና የሞቀ ቤትህን ትተህ ስትሄድ በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት መጣል አለብህ። እኛም ያደረግነው ይህንን ሲሆን ይሖዋም ባርኮናል። በአዲሱ ጉባኤያችን ውስጥ ያሉት ውድ ወንድሞችና እህቶች ተወዳጅና ተፈላጊ እንደሆንን እንዲሰማን አድርገውናል። ቀደም ሲል በሥራ ቦታ አጠፋው የነበረውን ጉልበት አሁን ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት እጠቀምበታለሁ። እንዲህ ባለ ሥራ ላይ በመሰማራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

‘ሀብታም ብሆንም ደስተኛ አልነበርኩም’

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሚ ያደረገችው ውሳኔ ከማርክ የተለየ ነበር። ጠቀም ያለ ክፍያ የሚያስገኝ የሙሉ ቀን ሥራ እንድትሠራ የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። ኤሚ እንዲህ ትላለች:- “በመጀመሪያው ዓመት በአገልግሎት ላይ በንቃት መካፈሌን ቀጥዬ ነበር፤ ሆኖም ከጊዜ በኋላ መንግሥቱን ከማስቀደም ይልቅ የሥራ እድገት ለማግኘት የበለጠ ትኩረት መስጠት እንደጀመርኩ ተረዳሁ። በሥራዬ እድገት እንዳገኝ የሚያስችሉ አጓጊ ግብዣዎች በየጊዜው ይቀርቡልኝ ስለነበር እኔም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መድከም ጀመርኩ። በሥራ ቦታ ያለኝ ኃላፊነት እየጨመረ ሲሄድ በአገልግሎት የማሳልፈው ጊዜ እየቀነሰ መጣ። በመጨረሻ በስብከቱ ሥራ ላይ መካፈሌን ከናካቴው አቆምኩ።”

ኤሚ ያንን ጊዜ ወደኋላ መለስ ብላ በማስታወስ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ከገንዘብ አኳያ ሲታይ ሀብታም ነበርኩ። ብዙ እጓዝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ያገኘሁት የኃላፊነት ቦታ ከፍተኛ ከበሬታ አስገኝቶልኛል፤ ሆኖም ደስተኛ አልነበርኩም። ገንዝብ ቢኖረኝም በርካታ ችግሮች ነበሩብኝ። ችግሩ ምን እንደሆነ ለማወቅ እፈልግ ነበር። በመጨረሻም በዚህ ዓለም ውስጥ ሥራን ሳሳድድ ‘የእምነትን መንገድ ስቼ ልሄድ’ ምንም እንዳልቀረኝ ተገነዘብኩ። ልክ የአምላክ ቃል እንዳለው በተከተልኩት አካሄድ ምክንያት ራሴን ‘ለብዙ ሥቃይ’ ዳርጌ ነበር።”—1 ጢሞ. 6:10

ታዲያ ኤሚ ምን አደረገች? እንዲህ ትላለች:- “መንፈሳዊ ጤንነቴን መልሼ ማግኘት እንድችል ሽማግሌዎች እንዲረዱኝ የጠየቅኋቸው ሲሆን በስብሰባዎችም ላይ መገኘት ጀመርኩ። በስብሰባ ላይ በተገኘሁበት ጊዜ አንድ መዝሙር ሲዘመር ማልቀስ ጀመርኩ። ቀደም ሲል አቅኚ ሆኜ በመከሩ ሥራ በተካፈልኩባቸው አምስት ዓመታት ከቁሳዊ ነገሮች አንጻር ደሃ የነበርኩ ቢሆንም ምን ያህል ደስተኛ እንደነበርኩ ትዝ አለኝ። ከዚያ በኋላ መንግሥቱን ማስቀደም እንጂ ገንዘብ በማሳደድ ጊዜዬን በከንቱ ማጥፋት እንደማይኖርብኝ ተረዳሁ። ደሞዜ ተቀንሶ ግማሽ የሚያህለው ብቻ የሚከፈለኝ ቢሆንም እንኳ ከደረጃዬ ዝቅ ብዬ ለመሥራት ጥያቄ በማቅረብ በስብከቱ ሥራ እንደገና መካፈል ጀመርኩ።” ኤሚ በደስታ እንዲህ ትላለች:- “ለጥቂት ዓመታት አቅኚ ሆኜ የማገልገል አስደሳች መብት አግኝቼ ነበር። በአሁኑ ወቅት፣ አብዛኛውን ጊዜዬን ለዓለም በመሥራት ሳጠፋ አግኝቼው የማላውቀው ከፍተኛ ደስታ አለኝ።”

አንተስ ሁኔታዎችህን ማስተካከልና አኗኗርህን ቀላል ማድረግ ትችላለህ? ያለህን ጊዜ የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማስቀደም የምትጠቀምበት ከሆነ አንተም ሕይወትህ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ታደርጋለህ።—ምሳሌ 10:22

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2፣ ገጽ 1207-1208⁠ን ተመልከት።

[ገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሁኔታዎችህን ማስተካከልና አኗኗርህን ቀላል ማድረግ ትችላለህ?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ገና ከአሁኑ ወድጄዋለሁ!”

ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ዴቪድ እንደ ሚስቱና ልጆቹ እሱም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ለመጀመር ይመኝ ነበር። በሚሠራበት ድርጅት ውስጥ የግማሽ ቀን ሥራ በማግኘቱ የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ለውጡ ሕይወቱ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጎለት ይሆን? ከተወሰኑ ወራት በኋላ ዴቪድ ለአንድ ጓደኛው እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር:- “ከቤተሰብ ጋር በመሆን በይሖዋ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከመካፈል ይበልጥ የሚያረካ ሌላ ነገር የለም። የአቅኚነት አገልግሎትን እስክለምደው ድረስ የተወሰነ ጊዜ ይወስድብኛል ብዬ አስቤ ነበር፤ ሆኖም ገና ከአሁኑ ወድጄዋለሁ! በእጅጉ መንፈስን የሚያድስ ነው።”

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርክ እና ፓውላ በአገልግሎት ላይ