በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ለመፈጸም ትኩረት ስጥ’

‘በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ለመፈጸም ትኩረት ስጥ’

‘በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ለመፈጸም ትኩረት ስጥ’

“በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ከፍጻሜ እንድታደርስ ለአገልግሎቱ ትኩረት መስጠትህን ቀጥል።”—ቈላ. 4:17 NW

1, 2. ክርስቲያኖች ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ምን ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል?

በአካባቢያችን ከሚኖሩት ሰዎች ጋር በተያያዘ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎብናል። እነዚህ ሰዎች “ከታላቁ መከራ” በሕይወት መትረፋቸው የተመካው አሁን በሚያደርጉት ውሳኔ ላይ ነው። (ራእይ 7:14) የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ “ወደ ሞት የሚነዱትን ታደጋቸው፤ እየተጐተቱ ለእርድ የሚሄዱትን አድናቸው” በማለት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ጽፏል። እንዴት የሚያስገርም አባባል ነው! ሰዎች ከፊታቸው ስለተቀመጠላቸው ምርጫ እንድንነግራቸው የተጣለብንን ኃላፊነት አለመወጣት በደም ዕዳ ተጠያቂ ያደርገናል። ይኸው የምሳሌ መጽሐፍ ክፍል በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “አንተም፣ ‘ስለዚህ ነገር ምንም አላውቅም’ ብትል፣ ልብን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን? ሕይወትህን የሚጠብቃት እርሱ አያውቅምን? ለእያንዳንዱስ እንደ ሥራው መጠን አይከፍለውምን?” በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የይሖዋ አገልጋዮች፣ ሰዎች ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን አደገኛ ሁኔታ ‘አላወቅንም’ ማለት አይችሉም።—ምሳሌ 24:11, 12

2 ይሖዋ ለሕይወት ትልቅ ዋጋ ይሰጣል። አገልጋዮቹም በተቻላቸው መጠን የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል። እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት አድን መልእክት ማወጅ አለበት። የተጣለብን ኃላፊነት አደጋ መምጣቱን ሲመለከት ማስጠንቀቂያ ከሚሰጥ ጕበኛ ጋር ይመሳሰላል። የመጥፋት አደጋ ባጠላባቸው ሰዎች የደም ዕዳ መጠየቅ አንፈልግም። (ሕዝ. 33:1-7) በመሆኑም ‘ቃሉን ከመስበክ’ ወደኋላ አለማለታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—2 ጢሞቴዎስ 4:1, 2, 5ን አንብብ።

3. በዚህና በቀጣዮቹ ሁለት የጥናት ርዕሶች ውስጥ የትኞቹ ነጥቦች ይብራራሉ?

3 ይህ ርዕስ ሕይወት አድን ለሆነው አገልግሎትህ መሰናክል ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን እንዴት መወጣት እንደምትችልና ብዙ ሰዎችን መርዳት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። በቀጣዩ የጥናት ርዕስ ውስጥ ደግሞ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች የማስተማር ጥበብ ማዳበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። ሦስተኛው የጥናት ርዕስ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ያገኟቸውን አንዳንድ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች ይዟል። ይሁን እንጂ እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች ከመመርመራችን በፊት፣ ጊዜያችን ይህን ያህል አስጨናቂ የሆነበትን ምክንያት ማየታችን ጠቃሚ ነው።

ብዙዎች ብሩሕ ተስፋ የሌላቸው ለምንድን ነው?

4, 5. የሰው ዘር በምን ሁኔታ ውስጥ ይገኛል? ብዙዎችስ ምን ይሰማቸዋል?

4 በዓለም ላይ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች የምንኖረው በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ መሆኑንና መጨረሻው በጣም መቅረቡን ያሳያሉ። የሰው ልጆች፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ‘የመጨረሻው ዘመን’ ምልክቶች እንደሆኑ በጠቀሷቸው ክስተቶች ምክንያት እየተሠቃዩ ነው። ጦርነትን፣ የምግብ እጥረትንና የምድር መንቀጥቀጥን ጨምሮ ‘የምጥ [ጣር] መጀመሪያ’ ተብለው የተጠቀሱት ሌሎች ችግሮች የሰው ልጆችን ለችግርና ለሥቃይ ዳርገዋቸዋል። ሕገወጥነት፣ ራስ ወዳድነትና አምላክን አለመፍራት በሁሉም ቦታ የሚታዩ ባሕርያት ናቸው። ያለንበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ለመመራት ለሚጥሩ ሰዎች እንኳ ‘አስጨናቂ’ ሆኖባቸዋል።—ማቴ. 24:3, 6-8, 12፤ 2 ጢሞ. 3:1-5

5 ይሁንና አብዛኛው የሰው ዘር በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉት ሁኔታዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው አያውቅም። በዚህም ምክንያት ብዙዎች ስለ ራሳቸውም ሆነ ስለ ቤተሰባቸው ደህንነት ይጨነቃሉ። የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ወይም በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ሌሎች አሳዛኝ ሁኔታዎች ብዙዎችን ለሐዘን ዳርገዋቸዋል። ብዙ ሰዎች እነዚህ ችግሮች የሚደርሱባቸው ለምን እንደሆነ ባለማወቃቸውና መፍትሔው የሚገኘው ከየት እንደሆነ ባለመገንዘባቸው ብሩሕ ተስፋ አይታያቸውም።—ኤፌ. 2:12

6. “ታላቂቱ ባቢሎን” ተከታዮቿን መርዳት ያልቻለችው ለምንድን ነው?

6 የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው “ታላቂቱ ባቢሎን” ለሰው ዘር ምንም ማጽናኛ መስጠት አልቻለችም። እንዲያውም “በዝሙቷ የወይን ጠጅ” አማካኝነት ብዙዎች በመንፈሳዊ ግራ እንዲጋቡ አድርጋለች። ከዚህም በላይ የሐሰት ሃይማኖት እንደ አንዲት አመንዝራ ሴት ‘የምድርን ነገሥታት’ እያታለለችና እየተቆጣጠረቻቸው ነው፤ ይህንንም የምታደርገው በሐሰት መሠረተ ትምህርቶቿና በመናፍስታዊ ድርጊቶቿ በመጠቀም አብዛኛው የሰው ዘር ለፖለቲካዊ መሪዎች ያለማንገራገር እንዲገዛ በማድረግ ነው። የሐሰት ሃይማኖት አብዛኛውን የሰው ዘር መቆጣጠርና ተሰሚነት ማግኘት ብትችልም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመቀበል ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።—ራእይ 17:1, 2, 5፤ 18:23

7. የአብዛኛው የሰው ዘር የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው? ይሁን እንጂ አንዳንዶችን መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ አብዛኛው የሰው ዘር ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ ላይ እየተጓዘ መሆኑን ተናግሯል። (ማቴ. 7:13, 14) አንዳንዶች በዚህ ሰፊ መንገድ ላይ የሚጓዙት የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ሆን ብለው ባለመታዘዝ ሲሆን አብዛኞቹ ግን ተታልለው ወይም የሃይማኖት መሪዎቻቸው ይሖዋ በእርግጥ ከእነሱ ምን እንደሚፈልግ ስላላስተማሯቸው ነው። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶች አኗኗራቸውን መለወጥ የሚያስፈልጋቸው ለምን እንደሆነ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ቢቀርብላቸው እርምጃ ለመውሰድ ሊነሳሱ ይችላሉ። ይሁንና ታላቂቱ ባቢሎንን የሙጥኝ የሚሉና የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ለመቀበል ፈቃደኛ የማይሆኑ ሰዎች “ከታላቁ መከራ” አይተርፉም።—ራእይ 7:14

ሳታሰልሱ ስበኩ

8, 9. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ተቃውሞ በደረሰባቸው ጊዜ ምን አደረጉ? ለምንስ?

8 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ የመንግሥቱን ምሥራች እንደሚሰብኩና ሌሎችን ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርጉ ተናግሯል። (ማቴ. 28:19, 20) ስለሆነም እውነተኛ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ ላይ መካፈላቸው ለአምላክ ታማኝ መሆናቸውን የሚያሳዩበት መንገድና እምነታቸው የሚጠብቅባቸው መሠረታዊ ብቃት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በመሆኑም በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ተቃውሞ ቢገጥማቸውም እንኳ ከመስበክ ወደኋላ አላሉም። ይሖዋ ኃይል እንደሚሰጣቸው በመተማመን ‘ቃሉን በፍጹም ድፍረት መናገር’ እንዲችሉ ጸልየዋል። በምላሹም ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞሉ አደረገ፤ እነሱም የአምላክን ቃል በድፍረት ተናገሩ።—ሥራ 4:18, 29, 31

9 ተቃውሞው እየተባባሰ ሲመጣ የኢየሱስ ተከታዮች ምሥራቹን ከመስበክ ወደኋላ ብለዋል? በፍጹም። የሐዋርያት ስብከት ያስቆጣቸው የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ሐዋርያቱን አሰሯቸው፣ አስፈራሯቸው እንዲሁም ገረፏቸው። ሆኖም ሐዋርያቱ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን [ያለማሰለስ] ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም።” ‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ መታዘዝ’ እንዳለባቸው በሚገባ ተረድተው ነበር።—ሥራ 5:28, 29, 40-42

10. በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? ሆኖም ጥሩ ምግባር ማሳየታቸው ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

10 በዛሬው ጊዜ የሚኖሩት አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች በስብከታቸው ምክንያት ድብደባና እስር አልደረሰባቸውም። ይሁንና ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች ለማለት ይቻላል አንድ ዓይነት ፈተናና ችግር ይደርስባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናህ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የሌለውን ወይም ለየት ብለህ እንድትታይ የሚያደርግህን አካሄድ እንድትከተል ያነሳሳህ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመረኮዙ ውሳኔዎች በማድረግህ የሥራ ባልደረቦችህ፣ የትምህርት ቤት ጓደኞችህ አሊያም ጎረቤቶችህ ከሰው የማትገጥም እንደሆንክ አድርገው ያስቡ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ይህ ሁኔታ ወደኋላ እንድትል ሊያደርግህ አይገባም። ዓለም በመንፈሳዊ ጨለማ ተውጧል። ክርስቲያኖች ግን “እንደ ከዋክብት [ማብራት]” ይኖርባቸዋል። (ፊልጵ. 2:15) ቅን ልብ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች መልካም ሥራህን ተመልክተው ሊያደንቁና ይሖዋን ለማክበር ሊነሳሱ ይችላሉ።—ማቴዎስ 5:16ን አንብብ።

11. (ሀ) አንዳንዶች ለስብከቱ ሥራ ምን ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ዓይነት ተቃውሞ ገጥሞታል? ምንስ ምላሽ ሰጠ?

11 የመንግሥቱን መልእክት ያለማሰለስ ለመስበክ ድፍረት ያስፈልገናል። አንዳንድ ሰዎች ሌላው ቀርቶ ዘመዶችህም እንኳ ሊያፌዙብህ ወይም በሌሎች መንገዶች ተስፋ ሊያስቆርጡህ ይሞክሩ ይሆናል። (ማቴ. 10:36) ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን በታማኝነት በመፈጸሙ ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜያት ተደብድቧል። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ ተቃውሞ ሲያጋጥመው ምን እንዳደረገ ተመልከት። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መከራ ተቀብለን ተንገላታን፤ ነገር ግን ብርቱ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን።” (1 ተሰ. 2:2) ጳውሎስ ከተያዘ፣ ልብሱ ተገፎ በበትር ከተደበደበና ወደ ወህኒ ከተጣለ በኋላ የምሥራቹን መስበኩን መቀጠል ተፈታታኝ ሆኖበት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (ሥራ 16:19-24) ታዲያ መስበኩን እንዲቀጥል ድፍረት የሰጠው ምንድን ነው? አምላክ የሰጠውን የስብከት ተልእኮ ለመወጣት የነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ነው።—1 ቆሮ. 9:16

12, 13. አንዳንዶች ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? ችግሮቹን መቋቋም የቻሉትስ እንዴት ነው?

12 ሰዎች እምብዛም ቤታቸው በማይገኙበት ወይም ለመንግሥቱ መልእክት ግድየለሽ በሆኑበት ክልል ውስጥ በቅንዓት ማገልገላችንን መቀጠል ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ምን ማድረግ እንችላለን? መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የበለጠ ደፋር መሆን ይኖርብን ይሆናል። ፕሮግራማችንን ማስተካከል ወይም ብዙ ሰዎች በምናገኝበት ቦታ ምሥራቹን ለመስበክ ጥረት ማድረግ ሊጠይቅብን ይችላል።—ከዮሐንስ 4:7-15፤ ከሐዋርያት ሥራ 16:13፤ 17:17 ጋር አወዳድር።

13 ብዙዎች መታገል የሚኖርባቸው ሌሎች ፈተናዎች ደግሞ የዕድሜ መግፋትና የጤንነት ችግር ናቸው። እነዚህ ችግሮች በስብከቱ ሥራ የሚፈልጉትን ያህል እንዳይካፈሉ እንቅፋት ይሆኑባቸዋል። አንተም ያለህበት ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ ያለብህን የአቅም ገደብ ይረዳል፤ እንዲሁም በምታደርገው ነገር ይደሰታል። (2 ቆሮንቶስ 8:12ን አንብብ።) ያጋጠመህ ችግር ተቃውሞም ይሁን የሰዎች ግድየለሽነት ወይም ጤና ማጣት፣ ምሥራቹን ለሌሎች ለማወጅ አቅምህ የፈቀደውን ያህል አድርግ።—ምሳሌ 3:27፤ ከማርቆስ 12:41-44 ጋር አወዳድር።

‘ለአገልግሎትህ ትኩረት ስጥ’

14. ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ምን ምሳሌ ትቷል? ምንስ ምክር ሰጥቷል?

14 ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን በቁም ነገር ይመለከት የነበረ ሲሆን የእምነት አጋሮቹንም እንዲሁ እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል። (ሥራ 20:20, 21፤ 1 ቆሮ. 11:1) በተለይ ጳውሎስ ካበረታታቸው ክርስቲያኖች መካከል በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ አርክጳ የተባለ ሰው ይገኝበታል። ጳውሎስ ለቈላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “አርክጳን ‘በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ከፍጻሜ እንድታደርስ ለአገልግሎቱ ትኩረት መስጠትህን ቀጥል’ በሉት” ብሏል። (ቈላ. 4:17 NW) ስለ አርክጳ ማንነትም ሆነ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኝ እንደነበር የምናውቀው ነገር የለም። ሆኖም ይህ ሰው የመስበክ ኃላፊነት ተቀብሏል። አንተም ራስህን የወሰንክ ክርስቲያን ከሆንክ ምሥራቹን የመስበክ ኃላፊነት ተቀብለሃል። ታዲያ አገልግሎትህን ለመፈጸም ትኩረት ትሰጣለህ?

15. ራስን መወሰን ምንን ይጨምራል? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

15 ከመጠመቃችን በፊት ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ ራሳችንን ለይሖዋ ወስነናል። በሌላ አነጋገር የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። በመሆኑም ራሳችንን እንደሚከተለው በማለት መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘በእርግጥ በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የአምላክን ፈቃድ መፈጸም ነው?’ ለቤተሰባችን የሚያስፈልጋቸውን ማቅረብን የመሰሉ ይሖዋ እንድንወጣቸው የሚፈልግብን የተለያዩ ኃላፊነቶች ይኖሩብን ይሆናል። (1 ጢሞ. 5:8) ይሁንና የቀረውን ጊዜያችንንና ኃይላችንን የምናውለው ለምን ነገሮች ነው? በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ምንድን ነው?—2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን አንብብ።

16, 17. ወጣት የሆኑ ወይም በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ክርስቲያኖች ምን አጋጣሚዎች አሏቸው?

16 ትምህርትህን ያጠናቀቅህ ወይም ለማጠናቀቅ የተቃረብክ ራስህን የወሰንክ ወጣት ክርስቲያን ነህ? በዚህ ወቅት ከባድ የቤተሰብ ኃላፊነት አይኖርብህ ይሆናል። ታዲያ በሕይወትህ ምን ለማድረግ አቅደሃል? የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የገባኸውን ቃል በተሻለ ሁኔታ መፈጸም የምትችለው ምን ዓይነት ውሳኔ ብታደርግ ነው? በርካታ ክርስቲያኖች አቅኚ ሆነው ለማገልገል ሁኔታቸውን አመቻችተዋል። ይህም ታላቅ ደስታና እርካታ አስገኝቶላቸዋል።—መዝ. 110:3፤ መክ. 12:1

17 ምናልባትም ብዙ ኃላፊነት የሌለብህና የሙሉ ጊዜ ሰብዓዊ ሥራ የምትሠራ ጎልማሳ ልትሆን ትችላለህ። ፕሮግራምህ በፈቀደልህ መጠን በጉባኤ እንቅስቃሴዎች መካፈል እንደሚያስደስትህ ጥርጥር የለውም። ይሁንና የበለጠ ደስታ ለማግኘት ትፈልጋለህ? በአገልግሎት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ስለ ማስፋት አስበህ ታውቃለህ? (መዝ. 34:8፤ ምሳሌ 10:22) በአንዳንድ ክልሎች ሕይወት አድን የሆነውን የእውነት መልእክት ለእያንዳንዱ ሰው ለማዳረስ ገና መሠራት ያለበት ብዙ ሥራ አለ። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደህ ለማገልገል በአኗኗርህ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችላለህ?—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8ን አንብብ።

18. አንድ ወጣት ባልና ሚስት ምን ማስተካከያ አደረጉ? ይህስ ምን ውጤት አስገኘላቸው?

18 ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩትን የኬቨንን እና የኤለናን ሁኔታ ተመልከት። * በአካባቢያቸው ያሉ ወጣት የሆኑ አዲስ ተጋቢዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ቤት መግዛት እንደሚያስፈልጋቸው ተሰማቸው። ሁለቱም ሙሉ ቀን ስለሚሠሩ የተደላደለ ኑሮ መምራት ይችላሉ። ይሁንና ሥራቸውና በቤት ውስጥ የሚያከናውኗቸው ነገሮች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ስለሚወስዱ ለመስክ አገልግሎት የሚያውሉት በቂ ጊዜ አልነበራቸውም። አብዛኛውን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚያጠፉት ቁሳዊ ንብረቶቻቸውን በመንከባከብ እንደሆነ ተገነዘቡ። ይሁን እንጂ ደስተኛ የሆኑ አንድ አቅኚ ባልና ሚስት የሚመሩትን ቀላል ኑሮ ሲመለከቱ እነሱም በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ በሚሰጧቸው ነገሮች ረገድ ማስተካከያ ለማድረግ ወሰኑ። የይሖዋን መመሪያ በጸሎት ከጠየቁ በኋላ ቤታቸውን ሸጠው አፓርታማ ውስጥ መኖር ጀመሩ። ኤለና በሰብዓዊ ሥራ ላይ የምታሳልፈውን ሰዓት ቀንሳ አቅኚ ሆነች። ኬቨንም ባለቤቱ በአገልግሎት የምታገኛቸውን የሚያስደስቱ ተሞክሮዎች ሲመለከት የሙሉ ጊዜ ሥራውን ትቶ አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ አገር ተዛወሩ። ኬቨን እንዲህ ብሏል:- “ሁልጊዜም በትዳራችን ደስተኞች ነበርን። ይሁንና መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ስንጣጣር ደስታችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጨመረ።”—ማቴዎስ 6:19-22ን አንብብ።

19, 20. ምሥራቹን መስበክ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች ሁሉ የላቀ የሆነው ለምንድን ነው?

19 ምሥራቹን መስበክ፣ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች ሁሉ የላቀ ሥራ ነው። (ራእይ 14:6, 7) ይህ ሥራ ለይሖዋ ስም መቀደስ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (ማቴ. 6:9) በየዓመቱ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚቀበሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው ከመሻሻሉም ባሻገር ለመዳን የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተዋል። ሆኖም “ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ?” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ጠይቋል። (ሮሜ 10:14, 15) እውነትም ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አገልግሎትህን ለመፈጸም የምትችለውን ያህል ለማድረግ ለምን ቁርጥ ውሳኔ አታደርግም?

20 ሰዎች ያለንበትን ዘመን አሳሳቢነትና የሚያደርጓቸው ውሳኔዎች የሚያስከትሏቸውን ውጤቶች እንዲያስተውሉ መርዳት የምትችልበት ሌላው መንገድ የማስተማር ችሎታህን በማሻሻል ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 ስማቸው ተቀይሯል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ክርስቲያኖች ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ምን ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል?

• በአገልግሎታችን ላይ የሚያጋጥሙንን መሰናክሎች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

• የተቀበልነውን አገልግሎት መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተቃውሞ እያለ ለመስበክ ድፍረት ያስፈልጋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉ ሰዎች በአብዛኛው በቤታቸው የማይገኙ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?