በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው

“ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው

“ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው

“የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ።”—ሥራ 13:48 NW

1, 2. የጥንት ክርስቲያኖች ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች በምድር ዙሪያ እንደሚሰበክ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ምን ጥረት አድርገዋል?

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ የጥንት ክርስቲያኖች ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች በምድር ዙሪያ እንደሚሰበክ የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ምን ጥረት እንዳደረጉ የሚተርክ አስደናቂ ዘገባ ይዟል። (ማቴ. 24:14) ቀናተኞቹ ሰባኪዎች ከእነሱ በኋላ ክርስትናን ለተቀበሉት ሰዎች አርዓያ ሆነውላቸዋል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በኢየሩሳሌም ባከናወኑት ቅንዓት የተሞላበት አገልግሎት ምክንያት ‘ብዙ ካህናትን’ ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ወደነበረው ጉባኤ ጎርፈዋል።—ሥራ 2:41፤ 4:4፤ 6:7

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ሚስዮናውያን ብዙዎች ክርስትናን እንዲቀበሉ ረድተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ሄዶ በሰበከበት ወቅት ብዙ ሕዝብ አዳምጦታል። (ሥራ 8:5-8) ጳውሎስ ከተለያዩ የጉዞ ጓደኞቹ ጋር ሆኖ በቆጵሮስ፣ በትንሿ እስያ፣ በመቄዶንያ፣ በግሪክና በጣሊያን በመዘዋወር ክርስትናን ሰብኳል። በሰበከባቸው ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ በርካታ አይሁድና ግሪካውያን አማኞች ሆነዋል። (ሥራ 14:1፤ 16:5፤ 17:4) ቲቶ ደግሞ በቀርጤስ ሰብኳል። (ቲቶ 1:5) ጴጥሮስ በባቢሎን ያገለግል የነበረ ሲሆን የመጀመሪያ መልእክቱን በጻፈበት ማለትም ከ62-64 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የክርስቲያኖች የስብከት እንቅስቃሴ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ በሰፊው ይታወቅ ነበር። (1 ጴጥ. 1:1፤ 5:13) እነዚያ ጊዜያት እንዴት የሚያስደስቱ ነበሩ! በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በከፍተኛ ቅንዓት ከመስበካቸው የተነሳ ጠላቶቻቸው ‘ዓለሙን ሁሉ እንዳናወጡ’ ተናግረዋል።—ሥራ 17:6 NW፤ 28:22

3. በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በሚያከናውኑት የስብከት እንቅስቃሴ ምን ውጤት እየተገኘ ነው? ይህስ ምን ስሜት ይፈጥርብሃል?

3 በዘመናችንም የክርስቲያን ጉባኤ አስደናቂ እድገት እያሳየ ነው። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓመታዊ ሪፖርት ስታነብና በዓለም ዙሪያ እየተገኘ ያለውን እድገት ስትመለከት አትበረታታም? በ2007 የአገልግሎት ዓመት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ከስድስት ሚሊዮን በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራታቸውን ማወቅህ አላስደሰተህም? ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ዓመት፣ ወደ አሥር ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ መገኘታቸው፣ እነዚህ ሰዎች ለምሥራቹ የተወሰነ ፍላጎት እንዳላቸው የሚጠቁም ነው። ይህም ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ እንዳለ ያሳያል።

4. ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ በመስጠት ላይ የሚገኙት እነማን ናቸው?

4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ” ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥሩ ምላሽ እየሰጡ ነው። (ሥራ 13:48 NW) ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ወደ ድርጅቱ እየሳባቸው ነው። (ሐጌ 2:7ን አንብብ።) በዚህ የመሰብሰብ ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ መካፈል እንድንችል ለአገልግሎታችን ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

ያለአድልዎ ስበኩ

5. የይሖዋን ሞገስ የሚያገኙት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

5 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “[አምላክ] ለማንም እንደማያዳላ . . . ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ” እንደሚቀበላቸው ተረድተው ነበር። (ሥራ 10:34, 35) አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረቱ የተመካው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባለው እምነት ነው። (ዮሐ. 3:16, 36) በተጨማሪም ይሖዋ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል።”—1 ጢሞ. 2:3, 4

6. የመንግሥቱ ሰባኪዎች ምን ማድረግ የለባቸውም? ለምንስ?

6 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የሰዎችን ዘር፣ አለባበስና ቁመና፣ ሃይማኖት፣ እንዲሁም ሰዎቹ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ወይም ሌሎች ነገሮችን ተመልክተው ምሥራቹን አይቀበሉም ብለው አስቀድመው መፍረዳቸው ስህተት ነው። እስቲ ቆም ብለህ አስብ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነገረህ ሰው አድልዎ ባለማሳየቱ አመስጋኝ አይደለህም? ታዲያ አንተስ ሕይወቱን ሊያድንለት የሚችለውን መልእክት ለሚያዳምጥህ ለማንኛውም ሰው ከመናገር ወደኋላ ማለት ይኖርብሃል?—ማቴዎስ 7:12ን አንብብ።

7. በምንሰብክላቸው ሰዎች ላይ መፍረድ የሌለብን ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ ኢየሱስን ፈራጅ አድርጎ ሾሞታል፤ በመሆኑም እኛ በማንኛውም ሰው ላይ የመፍረድ ሥልጣን የለንም። ይህ መሆኑ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ከኢየሱስ በተቃራኒ እኛ ሰዎች የምንፈርደው ‘ዓይናችን ባየውና ጆሯችን በሰማው’ ነገር ላይ ተመርኩዘን ነው። ኢየሱስ ግን የሰዎችን ልብና ውስጣዊ ሐሳብ ማንበብ ይችላል።—ኢሳ. 11:1-5፤ 2 ጢሞ. 4:1

8, 9. (ሀ) ሳውል ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ምን ዓይነት ሰው ነበር? (ለ) ከሐዋርያው ጳውሎስ ተሞክሮ ምን እንማራለን?

8 ሁሉም ዓይነት ሰዎች ማለት ይቻላል የይሖዋ አገልጋዮች መሆን ችለዋል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በኋላ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው የጠርሴሱ ሳውል ነው። ሳውል ፈሪሳዊና ክርስቲያኖችን ክፉኛ ይቃወም የነበረ ሰው ነው። ጳውሎስ ክርስቲያኖች እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች አይደሉም ብሎ በቅንነት ያስብ የነበረ መሆኑ የክርስቲያን ጉባኤን እንዲያሳድድ አነሳስቶታል። (ገላ. 1:13) ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ጳውሎስ ክርስቲያን ይሆናል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሳውል ልቡ ጥሩ እንደሆነ ስለተመለከተ ልዩ ተልእኮ እንዲፈጽም መረጠው። በዚህም ምክንያት ሳውል በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤ ውስጥ ከነበሩት ቀናተኛና ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል።

9 የሐዋርያው ጳውሎስ ተሞክሮ ምን ያስተምረናል? በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ የምንሰብከውን መልእክት ክፉኛ የሚቃወሙ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ይሁንና ከእነዚህ ሰዎች መካከል እውነተኛ ክርስትናን የሚቀበል ያለ በማይመስልበት ጊዜም እንኳ ተስፋ ቆርጠን ከእነሱ ጋር መወያየታችንን አናቆምም። አንዳንድ ጊዜ፣ በጭራሽ ፍላጎት የለውም ብለን ያሰብነው ሰው የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ ይሆናል። የእኛ ተልእኮ ምሥራቹን ለሰዎች ሁሉ ያለማሰለስ መስበክ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 5:42ን አንብብ።

ያለማሰለስ የሚሰብኩ በረከት ያጭዳሉ

10. የሚያስፈሩ ለሚመስሉ ሰዎች ከመስበክ ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው? በክልላችሁ የተገኘ ተሞክሮ ካለ ተናገር።

10 ውጫዊ መልክ አሳሳች ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ኢግናስዮ * በደቡብ አሜሪካ በሚገኝ አንድ አገር በእስር ቤት ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። ኢግናስዮ ዓመጸኛ በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይፈራ ነበር። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ነገሮችን ሠርተው የሚሸጡ እስረኞች፣ ዕዳቸውን ያልከፈሉ እስረኞችን እያስፈራራ ገንዘባቸውን እንዲቀበልላቸው ይልኩት ነበር። ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ እያደገ ሲሄድና የተማረውን በሥራ ላይ ማዋል ሲጀምር ዓመጸኝነቱን ትቶ ሰላማዊ ሰው ሆነ። ከዚያ በኋላ እስረኞቹ ገንዘባቸውን እንዲሰበስብላቸው ኢግናስዮን መላካቸውን አቆሙ። ኢግናስዮ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና የአምላክ መንፈስ በባሕርይው ላይ ለውጥ እንዲያደርግ ስለረዳው በጣም ደስተኛ ነው። በተጨማሪም እሱን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ጥረት ያደረጉት አስፋፊዎች አድልዎ ባለማሳየታቸው አመስጋኝ ነው።

11. ሰዎችን ተመላልሰን የምንጠይቀው ለምንድን ነው?

11 የምሥራቹን የነገርናቸውን ሰዎች ተመላልሰን የምንጠይቅበት አንዱ ምክንያት፣ ያሉበት ሁኔታ ወይም አመለካከታቸው ሊለወጥ ስለሚችል ነው፤ ደግሞም ይለወጣል። አንዳንዶች ለመጨረሻ ጊዜ ካነጋገርናቸው በኋላ በከባድ በሽታ ተይዘው፣ ከሥራ ተፈናቅለው ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት አጥተው ሊሆን ይችላል። (መክብብ 9:11ን አንብብ።) በዓለም ላይ የሚከሰቱ ሁኔታዎች ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በቁም ነገር እንዲያስቡ ይገፋፏቸው ይሆናል። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች ከዚህ ቀደም ለመልእክቱ ግድየለሽ፣ ሌላው ቀርቶ ተቃዋሚ የነበረን ሰው እንኳ በጎ ምላሽ እንዲሰጥ ሊያደርጉት ይችላሉ። በመሆኑም ምቹ በሆኑ አጋጣሚዎች ሁሉ ለሌሎች ከመስበክ ወደኋላ ማለት የለብንም።

12. ለምንሰብክላቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?

12 ሰዎችን በአንድ ወገን መፈረጅና መፍረድ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ይመስላል። ይሁንና ይሖዋ ሰዎችን የሚመለከተው በግለሰብ ደረጃ ነው። እያንዳንዱ ሰው ያሉትን ጥሩ ባሕርያት ይመለከታል። (1 ሳሙኤል 16:7ን አንብብ።) እኛም በምናገለግልበት ጊዜ እንዲህ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል። በርካታ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ለምንሰብክላቸው ሰዎች ሁሉ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ጥሩ ውጤት ያስገኛል።

13, 14. (ሀ) አንዲት አቅኚ በአገልግሎት ስላገኘቻት ሴት የተሳሳተ አመለካከት የነበራት ለምንድን ነው? (ለ) ከዚህ ተሞክሮ ምን እንማራለን?

13 ሳንድራ የተባለች አንዲት አቅኚ በካሪቢያን ደሴት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ሩት የምትባል ሴት አገኘች። ሩት የካርኒቫል በዓላት አፍቃሪ ስትሆን የአገሪቱ የካርኒቫል ንግሥት በመባል ሁለት ጊዜ ተሸልማለች። ሩት ሳንድራ ለነገረቻት መልእክት ጥሩ ፍላጎት በማሳየቷ መጽሐፍ ቅዱስ ልታስጠናት ተስማሙ። ሳንድራ ሁኔታውን በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “ወደ ሳሎኗ ስገባ ሩት የካርኒቫል ልብሷን ለብሳ የተነሳችውን ትልቅ ፎቶና የተቀበለቻቸውን ሽልማቶች ተመለከትኩ። በመሆኑም እንደ እሷ ያለ ታዋቂና የካርኒቫል አፍቃሪ የሆነ ሰው ለእውነት ፍላጎት ሊኖረው አይችልም የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። በመሆኑም ተመላልሶ መጠየቅ ማድረጌን አቆምኩ።”

14 ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ሩት ወደ መንግሥት አዳራሽ መጣች። ከዚያም ስብሰባው ሲያልቅ ሳንድራን “ልታስጠኚኝ መምጣትሽን ያቆምሽው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀቻት። ሳንድራም ይቅርታ ጠይቃ ጥናቱን ለመቀጠል ቀጠሮ ያዘች። ሩት ፈጣን እድገት ያደረገች ሲሆን በካርኒቫል ልብሶች የተነሳቻቸውን ፎቶዎች ከተሰቀሉበት አወረደች። ከዚያም በሁሉም የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ላይ መካፈል ጀመረች፤ እንዲሁም ራሷን ለይሖዋ ወስና ተጠመቀች። ሳንድራ መጀመሪያ ላይ ስለ ሩት ያሰበችው ስህተት መሆኑን እንደተገነዘበች ጥርጥር የለውም።

15, 16. (ሀ) አንዲት አስፋፊ ለዘመዷ መመሥከሯ ምን ውጤት አስገኝቶላታል? (ለ) አንድ ዘመድህ ያለበት ሁኔታ ወይም አኗኗሩ እንዳትመሠክርለት ሊያግድህ የማይገባው ለምንድን ነው?

15 ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ባይመስሏቸውም እንኳ ለማያምኑ የቤተሰብ አባሎቻቸው የመሰከሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረውን የእህት ጆይስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ ተመልከት። የእህቷ ባል የነበረ ሰው ከአሥራዎቹ ዕድሜው ጀምሮ በተደጋጋሚ እስር ቤት ይገባ ነበር። ጆይስ እንዲህ ትላለች:- “በሌብነቱ ይታወቅ እንዲሁም አደገኛ ዕፆች ይወስድና ብዙ መጥፎ ነገሮችን ያደርግ ስለነበር ሰዎች ሕይወቱ ከንቱ እንደሆነ ይናገሩ ነበር። እኔ ግን ሁኔታው ተስፋ ያለው ባይመስልም ለ37 ዓመት ያህል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነገርኩት።” በመጨረሻ ይህ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረ ሲሆን በሕይወቱ ውስጥ አስደናቂ ለውጦችን አደረገ። በእርግጥም ጆይስ ዘመዷን ለመርዳት በትዕግሥት መጣሯ በእጅጉ ክሷታል። የጆይስ አማች በቅርቡ በካሊፎርኒያ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በ50 ዓመት ዕድሜው ተጠምቋል። ጆይስ “በደስታ አነባሁ። በእሱ ተስፋ ባለመቁረጤ በጣም ተደስቻለሁ!” ብላለች።

16 አንዳንድ ዘመዶችህ ያሉበትን ሁኔታ ወይም አኗኗራቸውን ስትመለከት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለእነሱ ለመንገር ታመነታ ይሆናል። ጆይስ ግን ለአማቿ ከመናገር ወደኋላ አላለችም። ደግሞስ በሌላ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ማን ሊያውቅ ይችላል? ምናልባትም ይህ ሰው እውነትን በቅንነት የሚፈልግ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም እውነትን የሚያገኝበትን አጋጣሚ አትንፈገው።—ምሳሌ 3:27ን አንብብ።

መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የሚረዳ ውጤታማ መሣሪያ

17, 18. (ሀ) ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ሪፖርቶች ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ጠቃሚ መሣሪያ መሆኑን የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) አንተስ ይህን መጽሐፍ በመጠቀም ምን የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች አግኝተሃል?

17 ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን እንዲረዱ በማስቻል ረገድ ጥሩ ውጤት እያስገኘ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ፔኒ የተባለች አቅኚ ይህን መጽሐፍ በመጠቀም የተለያዩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረች። ከእነዚህ መካከል አጥባቂ ሃይማኖተኞች የሆኑ ሁለት አረጋውያን ይገኙበታል። ፔኒ እነዚህ አረጋውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የቀረቡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ሲመለከቱ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መገመት ቸግሯት ነበር። ይሁንና እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ትምህርቱ የቀረበበት መንገድ ግልጽ፣ ምክንያታዊና ያልተንዛዛ በመሆኑ ሳይከራከሩ ወይም ሳይበሳጩ የሚማሩት ነገር እውነት መሆኑን አምነው ተቀብለዋል።”

18 በብሪታንያ የምትኖር ፓት የተባለች አስፋፊ ከእስያ የመጣች አንዲት ስደተኛን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረች። ይህች ሴት ከአገሯ ለመሰደድ የተገደደችው ባሏና ወንዶች ልጆቿ በአማጽያን ወታደሮች ከተወሰዱ በኋላ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አይታቸው አታውቅም። አማጽያኑ እሷንም ሊገድሏት ይዝቱባት ነበር፤ ቤቷን አቃጥለውባታል እንዲሁም ብዙ ሆነው ደፍረዋታል። የደረሰባት መከራ ሕይወቷ ባዶ እንደሆነ እንዲሰማት ስላደረጋት በተደጋጋሚ ጊዜ ራሷን ለማጥፋት አስባ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷ ተስፋ ፈነጠቀላት። ፓት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ለመረዳት ቀላል የሆኑ ማብራሪያዎችና ምሳሌዎች አስደናቂ ለውጥ እንድታደርግ ረዷት።” ይህች ሴት ፈጣን እድገት በማድረግ ያልተጠመቀች አስፋፊ ሆናለች። እንዲሁም በሚቀጥለው ትልቅ ስብሰባ ላይ መጠመቅ እንደምትፈልግ ገልጻለች። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ እንዲረዱና እንዲያደንቁ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ ደስታ ያስገኛል!

“በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት”

19. የስብከቱ ሥራ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠን ተልእኮ ይበልጥ አጣዳፊ እየሆነ ይሄዳል። በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ለምንሰብከው መልእክት በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው። ይሁንና “ታላቁ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቀን ቅርብ ነው።” ይህም በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ‘እየተጐተቱ ለእርድ እየሄዱ መሆናቸውን’ ያስገነዝበናል።—ሶፎ. 1:14፤ ምሳሌ 24:11

20. የእያንዳንዳችን ቁርጥ ውሳኔ ምን መሆን ይኖርበታል?

20 እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች አሁንም ቢሆን ልንረዳቸው እንችላለን። ይሁንና እንዲህ ማድረግ እንድንችል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ‘ስለ ክርስቶስ ይኸውም ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን የቀጠሉትን’ ክርስቲያኖች ምሳሌ መኮረጅ ይኖርብናል። (ሥራ 5:42 NW) ስደት እያለም በስብከቱ ሥራ በመጽናት፣ ‘ለማስተማር ጥበብህ’ ትኩረት በመስጠትና ለሁሉም ሰዎች ያለአድልዎ በመስበክ የጥንት ክርስቲያኖችን ምሳሌ ተከተል! “በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት”፤ በዚህ ከጸናን የይሖዋን ሞገስ ስለምናገኝ የተትረፈረፈ በረከት እናጭዳለን።—2 ጢሞ. 4:2፤ ገላትያ 6:9ን አንብብ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ለምሥራቹ በጎ ምላሽ በመስጠት ላይ የሚገኙት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

• የምንሰብክላቸው ሰዎች ስለሚሰጡት ምላሽ አስቀድመን መፍረድ የሌለብን ለምንድን ነው?

• ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ምን ውጤት እያስገኘ ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሺዎች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በጎ ምላሽ እየሰጡ ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወት መለወጡ ምን ያስተምረናል?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች ሰዎች የሚሰጡትን ምላሽ በተመለከተ አስቀድመው አይፈርዱም