ክርስቲያኖች እንደ ስንዴ ሲበጠሩ
ክርስቲያኖች እንደ ስንዴ ሲበጠሩ
ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱን “እነሆ፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ” በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር። (ሉቃስ 22:31) እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?
እንደሚታወቀው የስንዴ መከር የመሰብሰብ ሥራ ብዙ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። በመጀመሪያ ገበሬዎች ያጨዱትን ስንዴ ከማሳ ወደ አውድማ ይወስዳሉ። ከዚያም አውድማ ላይ አድርገው በዱላ በመምታት ወይም በላዩ ላይ ከብቶችን በመንዳት ይወቁታል። ይህ ዘዴ ፍሬው ከገለባው እንዲለያይ ለማድረግ ይረዳል። በመቀጠልም ገበሬዎቹ የተወቃውን እህል በመንሽ ወደ ላይ በመበተን ለነፋስ ይሰጡታል። በዚህ ጊዜ ነፋሱ እብቁን ገለል ሲያደርገው ስንዴው አውድማው ላይ ይቀራል። በመጨረሻም አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማስወገድ ስንዴው በደንብ ይበጠራል።
ኢየሱስ እንዳለው ሰይጣን በዚያ ዘመን በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ያልተቋረጠ ጥቃት ሰንዝሮባቸዋል፤ ዛሬም በእኛ ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ይፈጽማል። (ኤፌ. 6:11) ይህ ሲባል ግን በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥመንን እያንዳንዱን አስቸጋሪ ነገር የሚያመጣብን ሰይጣን ነው ማለት አይደለም። (መክ. 9:11 NW) ይሁንና ሰይጣን ጽኑ አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ ማንኛውንም አጋጣሚ ከመጠቀም ወደኋላ አይልም። ለምሳሌ፣ በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሕይወት እንድንመራ፣ ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ እንድንመርጥ ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው የጾታ ድርጊት እንድንፈጽም ሊፈትነን ይችላል። እንዲሁም አብረውን የሚማሩ ሰዎችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችንን ወይም የማያምኑ ዘመዶቻችንን ተጠቅሞ ከትምህርትም ሆነ ከሥራ ጋር በተያያዘ ይህ ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች በሙሉ እንድናሳድድ ብርቱ ግፊት ሊያደርግብን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ሰይጣን ለአምላክ ያለንን ጽኑ አቋም እንድናላላ ለማድረግ ስደት ሊያስነሳብን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሰይጣን እኛን ለማበጠር የሚጠቀምባቸው ሌሎች ብዙ መንገዶች አሉ።
ይህን ኃይለኛ ጠላት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ሰይጣን ከእኛ የበለጠ ኃይል ስላለው በራሳችን ኃይል ልንቋቋመው አንችልም። ሆኖም ይሖዋ ከሰይጣን እጅግ የላቀ ኃይል እንዳለው እናውቃለን። በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት ካለን፣ ለመጽናት የሚያስችል ጥበብና ድፍረት እንዲሰጠን ከልብ የምንጸልይ ከሆነና በመመሪያዎቹ ሙሉ በሙሉ የምንታመን ከሆነ ሰይጣንን መቋቋም እንድንችል ያበረታናል።—መዝ. 25:4, 5
ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ፣ በሰይጣን የተንኮል ዘዴዎች ከመታለል እንድንጠበቅ ‘መልካሙን ከክፉው ለመለየት’ የሚረዳን ችሎታ ያስፈልገናል። (ዕብ. 5:13, 14) ይሖዋ ይህን ችሎታ እንድናዳብር ይረዳናል። ከዚያም ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ትክክለኛውን ጎዳና የሙጥኝ ብለን መቀጠል ያስፈልገናል። የይሖዋን መመሪያ ከተከተልን ትክክል የሆነውን ለማድረግ በወሰድነው ቁርጥ አቋም እንድንጸና ምንጊዜም ይደግፈናል።—ኤፌ. 6:10
ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥረን ይሞክር ይሆናል፤ ነገር ግን በይሖዋ ኃይል በመታገዝ በእምነት ጸንተን ልንቃወመው እንችላለን። (1 ጴጥ. 5:9) አዎን፣ የይሖዋ ቃል “ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ያዕ. 4:7