በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማቴዎስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የማቴዎስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የማቴዎስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚናገረውን አስደሳች ዘገባ የጻፈው የመጀመሪያው ሰው ማቴዎስ ነው። ማቴዎስ የኢየሱስ ክርስቶስ የቅርብ ወዳጅ ሲሆን በአንድ ወቅት ቀረጥ ሰብሳቢ ነበር። በመጀመሪያ በዕብራይስጥ የተጻፈውና በኋላም ወደ ግሪክኛ የተተረጎመው የማቴዎስ ወንጌል ተጽፎ ያለቀው በ41 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። ይህ መጽሐፍ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ከግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር በማገናኘት ረገድ እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

ልብ የሚነኩና ጠቃሚ ሐሳቦችን የያዘው የማቴዎስ ወንጌል በቅድሚያ የተጻፈው ለአይሁዳውያን ሲሆን የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። ይህ ወንጌል ለያዘው መልእክት ትኩረት መስጠታችን በእውነተኛው አምላክ፣ እሱ በሰጣቸው ተስፋዎችና በልጁ ላይ ያለንን እምነት ያጠነክርልናል።—ዕብ. 4:12

“መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች”

(ማቴ. 1:1 እስከ 20:34)

ማቴዎስ በዋነኝነት ያተኮረው በአምላክ መንግሥትና በኢየሱስ ትምህርቶች ላይ ነበር፤ ይህ ደግሞ የጊዜ ቅደም ተከተሉን በጠበቀ መልኩ እንዳይጽፍ አድርጎታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የተራራውን ስብከት የሰጠው ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ዓመታት አጋማሽ ላይ ቢሆንም ይህ ስብከት በመጽሐፉ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው መጀመሪያ አካባቢ ነው።

ኢየሱስ በገሊላ ባገለገለበት ወቅት ተአምራትን ፈጽሟል፣ ለ12ቱ ሐዋርያት አገልግሎትን የሚመለከቱ መመሪያዎችን ሰጥቷል፣ ፈሪሳውያንን አውግዟል እንዲሁም ስለ መንግሥቱ የሚገልጹ የተለያዩ ምሳሌዎችን ተናግሯል። ከዚያ ከገሊላ ተነስቶ “ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደ።” (ማቴ. 19:1) በመንገድ ላይ ሳለ ኢየሱስ ‘ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፣ በዚያም የሰው ልጅ ሞት ይፈረድበታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሣል’ በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው።—ማቴ. 20:18, 19

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

3:16—ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ‘ሰማይ የተከፈተው’ በምን መንገድ ነው? ይህ አባባል ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ያሳለፈውን ሕይወት ማስታወሱን የሚጠቁም ሳይሆን አይቀርም።

5:21, 22 [NW]—በቁጣ ገንፍሎ መናገር ንዴትን አምቆ ለረጅም ጊዜ ከመያዝ የበለጠ ከባድ ኃጢአት ነው? ኢየሱስ፣ አንድ ሰው ወንድሙን ተቀይሞ ንዴቱን ለረጅም ጊዜ አምቆ መያዙ ከባድ ኃጢአት እንደሚሆንበት ተናግሯል። ይሁን እንጂ በቁጣ ገንፍሎ ግለሰቡን የሚያንቋሽሽ ቃል መናገሩ ከዚያ የከፋ ይሆንበታል፤ እንዲህ ያለው ሰው በአካባቢ ሸንጎ ሳይሆን በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠያቂ ይሆናል።

5:48—‘የሰማዩ አባታችን ፍጹም እንደሆነ ሁሉ እኛም ፍጹም መሆን’ እንችላለን? አዎን፣ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ፍጹም መሆን እንችላለን። ኢየሱስ እዚህ ላይ እየተናገረ የነበረው ስለ ፍቅር ሲሆን አድማጮቹ ፍቅርን ልክ እንደ አምላክ ፍጹም በሆነ ወይም በተሟላ መንገድ እንዲያሳዩ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 5:43-47) ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ጠላቶቻቸውንም ጭምር በመውደድ ነው።

7:16—የእውነተኛው ሃይማኖት መለያ ምልክት የሆኑት ‘ፍሬዎች’ ምንድን ናቸው? እነዚህ ፍሬዎች ባሕርያችንን ብቻ ሳይሆን የምናምንባቸውን ነገሮች ማለትም በጥብቅ የምንከተላቸውን ትምህርቶች ይጨምራሉ።

10:34-38—በቤተሰብ መካከል ለሚፈጠረው መከፋፈል መንስኤው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው መልእክት ነው? በፍጹም። በቤተሰብ መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆነው አማኝ ያልሆኑት የቤተሰቡ አባላት የሚኖራቸው አመለካከት ነው። እነዚህ ሰዎች ክርስትናን ላለመቀበል ወይም ለመቃወም ይመርጡ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ በቤተሰብ ውስጥ መከፋፈልን ይፈጥራል።—ሉቃስ 12:51-53

11:2-6—ዮሐንስ፣ አምላክ ከተናገረው ነገር በመነሳት ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ካረጋገጠ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው” እሱ መሆኑን የጠየቀው ለምንድን ነው? ዮሐንስ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ከራሱ ከኢየሱስ ማረጋገጫ ማግኘት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ዮሐንስ መንግሥታዊ ሥልጣን ይዞ በመምጣት አይሁዳውያን የተገባላቸውን ተስፋ የሚፈጽም “ሌላ” ሰው መኖሩን ለማወቅ ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ የሰጠው መልስ እሱን የሚተካ ሌላ አካል እንደሌለ ያረጋግጣል።

19:28—ፍርድ የሚሰጣቸው ‘አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች’ የሚያመለክቱት ማንን ነው? እነዚህ ነገዶች 12ቱን የመንፈሳዊ እስራኤል ነገዶች የሚያመለክቱ አይደሉም። (ገላ. 6:16፤ ራእይ 7:4-8) ኢየሱስ ይህን እየነገራቸው የነበሩት ሐዋርያት የመንፈሳዊ እስራኤል ክፍል ይሆናሉ እንጂ በዚህ ቡድን አባላት ላይ የሚፈርዱ አይሆኑም። ኢየሱስ እነሱን ‘በመንግሥቱ ላይ እንደሚሾማቸው’ ቃል የገባላቸው ሲሆን ወደፊት ደግሞ ‘ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት’ ይሆናሉ። (ሉቃስ 22:28-30፤ ራእይ 5:10) እነዚህ የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ‘በዓለም ላይ ይፈርዳሉ።’ (1 ቆሮ. 6:2) በመሆኑም በሰማይ ዙፋን ላይ እንደሚቀመጡ የተነገረላቸው ቅቡዓን ፍርድ የሚሰጧቸው ‘አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች’፣ ነገሥታትም ሆነ ካህናት ያልሆነውን መላውን የሰው ዘር የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው፤ እነዚህም ጥንት በስርየት ቀን ከነበሩት ከ12ቱ ነገዶች ጋር ይመሳሰላሉ።—ዘሌ. ምዕ. 16

ምን ትምህርት እናገኛለን?

4:1-10:- በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ሰይጣን በሰዎች ውስጥ ያለ የክፋት ባሕርይ ሳይሆን እውን አካል እንደሆነ ያሳያል። እኛን ለመፈተን ‘የሥጋ ምኞትን፣ የዐይን አምሮትንና የኑሮ ትምክሕትን’ ይጠቀማል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን ለአምላክ ታማኝ እንድንሆን ይረዳናል።—1 ዮሐ. 2:16

5:1 እስከ 7:29:- በመንፈሳዊ ድሆች መሆናችን ሊታወቀን ይገባል። ሰላማዊ ሁን። ሥነ ምግባር ከጎደለው አስተሳሰብ ራቅ። ቃልህን ጠብቅ። ስትጸልይ ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ስጥ። በአምላክ ዘንድ ባለጠጋ ለመሆን ጣር። የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ አስቀድም። በሌሎች ላይ አትፍረድ። የአምላክን ፈቃድ አድርግ። በተራራው ስብከት ላይ የተሰጡት ትምህርቶች ምንኛ ጠቃሚ ናቸው!

9:37, 38:- ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በመካፈል የመከሩ ጌታ “ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ” ካቀረብነው ልመና ጋር የሚስማማ ተግባር ማከናወን ይኖርብናል።—ማቴ. 28:19, 20

10:32, 33:- ስለ እምነታችን ለመናገር ፈጽሞ መፍራት አይኖርብንም።

13:51, 52:- የመንግሥቱን እውነቶች በትክክል መረዳት ይህን ውድ ሀብት ለሌሎች የማካፈል ኃላፊነት ያስከትላል።

14:12, 13, 23:- ትኩረታችን ሳይከፋፈል ማሰላሰል እንድንችል ብቻችንን መሆናችን አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ አለ።—ማር. 6:46፤ ሉቃስ 6:12

17:20:- መንፈሳዊ እድገታችንን የሚገቱ እንደ ተራራ ያሉ ፈተናዎችን ለማሸነፍና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም እምነት ያስፈልገናል። በይሖዋና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለንን እምነት ለመገንባትና ለማጠናከር ቸልተኞች መሆን አይኖርብንም።—ማር. 11:23፤ ሉቃስ 17:6

18:1-4፤ 20:20-28:- የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ፍጹም አለመሆናቸውና ለሥልጣን ትልቅ ቦታ በሚሰጥ ሃይማኖት ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ከሌሎች ልቀው ለመታየት ከልክ በላይ እንዲጨነቁ አድርጓቸዋል። ራሳችንን ከኃጢአት ዝንባሌ ለመጠበቅም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ላገኘናቸው መብቶችና ኃላፊነቶች ተገቢውን አመለካከት ለመያዝ ትሕትናን ማዳበር ይኖርብናል።

‘የሰው ልጅ አልፎ ይሰጣል’

(ማቴ. 21:1 እስከ 28:20)

ኢየሱስ ኒሳን 9, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ‘በአህያ ላይ ተቀምጦ’ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። (ማቴ. 21:5) በሚቀጥለው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በዚያ ይነግዱ የነበሩ ሰዎችን አባረረ። ኒሳን 11 በቤተ መቅደስ አስተማረ፣ የኦሪት ሕግ መምህራንንና ፈሪሳውያንን አወገዘ፤ ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ ‘የመምጣቱና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ’ ምን እንደሆነ ነገራቸው። (ማቴ. 24:3) በማግስቱም ለደቀ መዛሙርቱ “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል” አላቸው።—ማቴ. 26:1, 2

ዕለቱ ኒሳን 14 ነበር። ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ ካቋቋመ በኋላ ይሁዳ አሳልፎ ሰጠው፤ ከዚያም ለፍርድ ቀረበ። በመጨረሻም ተሰቀለ። በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሳ። ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለተከታዮቹ “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው።—ማቴ. 28:19

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

22:3, 4, 9—ሰዎች ወደ ሠርጉ ግብዣ እንዲመጡ ሦስቱ ጥሪዎች የቀረቡት መቼ ነበር? የሙሽራውን ክፍል ለመሰብሰብ የመጀመሪያው ጥሪ የቀረበው ኢየሱስና ተከታዮቹ የስብከት ሥራቸውን በጀመሩበት በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። ይህ ጥሪ እስከ 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ ቀጥሏል። ሁለተኛው ጥሪ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ከወረደበት ጊዜ አንስቶ እስከ 36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ ቀጥሏል። ሁለቱም ጥሪዎች የቀረቡት ለአይሁዳውያን፣ ወደ ይሁዲነት ለተለወጡና ለሳምራውያን ብቻ ነበር። ሦስተኛው ጥሪ ግን በየአውራ ጎዳናው ለሚገኙ ሰዎች ማለትም ላልተገረዙ አሕዛብ የቀረበ ነበር። ይህ ጥሪ የጀመረው ሮማዊው የጦር አዛዥ ቆርኔሌዎስ ክርስትናን በተቀበለበት በ36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲሆን ጥሪው እስከ ዘመናችንም ቀጥሏል።

23:15—በፈሪሳውያን አማካኝነት ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠ ሰው ከራሳቸው ከፈሪሳውያን “በእጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ” የሚሆነው ለምንድን ነው? በፈሪሳውያን አማካኝነት ወደ አይሁድ እምነት ከተለወጡት መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ከባድ ኃጢአት ይፈጽሙ የነበሩ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ጽንፈኛ ወደሆኑት ወደ ፈሪሳውያን በመለወጥ ከተወገዙት መምህራኖቻቸው የበለጠ ጽንፈኛ ሆነው ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች አይሁዳዊ ከሆኑት ፈሪሳውያን የበለጠ “የገሃነም ልጅ” የሚሆኑት በዚህ ምክንያት ነው።

27:3-5—ይሁዳ የተጸጸተው ለምን ነበር? የይሁዳ ጸጸት እውነተኛ ንስሐ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ የለም። የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ኃጢአቱን የተናዘዘው ለካህናት አለቆችና ለሽማግሌዎች ነበር። ይሁዳ ‘ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት’ በመፈጸሙ ምክንያት የበደለኝነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት አሠቃይቶት ነበር። (1 ዮሐ. 5:16) የተጸጸተው ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ስለነበር ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

21:28-31:- ይሖዋ የእሱን ፈቃድ እንድንፈጽም ይጠብቅብናል። ለምሳሌ ያህል መንግሥቱን በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት መካፈል ይኖርብናል።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20

22:37-39:- ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት አምላክ እሱን ከሚያመልኩ ሰዎች የሚጠብቀውን ነገር ጠቅለል አድርገው ያስቀምጡልናል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመከሩ ሥራ በቅንዓት እየተካፈልክ ነው?

[ምንጭ]

© 2003 BiblePlaces.com

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማቴዎስ በዋነኝነት ያተኮረው በአምላክ መንግሥት ላይ ነው