በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ መንገድ ሂድ

በይሖዋ መንገድ ሂድ

በይሖዋ መንገድ ሂድ

“ይሖዋን የሚፈሩ ሁሉ፣ በመንገዱም የሚሄዱ ደስተኞች ናቸው።”—መዝ. 128:1 NW

1, 2. አንድ ሰው እውነተኛ ደስታ ማግኘት ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

ሁሉም ሰው ደስተኛ መሆን ይፈልጋል። ይሁንና ደስተኛ ለመሆን መፈለግም ሆነ ደስታን ለማግኘት መጣር፣ ደስተኛ ከመሆን የተለዩ መሆናቸውን ሳትስማማበት አትቀርም።

2 ይሁን እንጂ፣ አንድ ሰው እውነተኛ ደስታ ማግኘት ይችላል። መዝሙር 128:1 (NW) “ይሖዋን የሚፈሩ ሁሉ፣ በመንገዱም የሚሄዱ ደስተኞች ናቸው” ይላል። ይሖዋን የምናመልክና ፈቃዱን በመፈጸም በመንገዱ የምንሄድ ከሆነ ደስተኞች መሆን እንችላለን። ይህ በምግባራችንና በባሕርያችን ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?

እምነት የሚጣልብህ ሰው መሆንህን አስመሥክር

3. እምነት የሚጣልበት ሰው መሆን ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

3 ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች ልክ እንደ እሱ እምነት የሚጣልባቸው ናቸው። ይሖዋ ለጥንት እስራኤላውያን የገባውን ቃል አንድም ሳያስቀር ፈጽሞላቸዋል። (1ነገ. 8:56) ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነው ቃል በሕይወታችን ከምንገባው ከማንኛውም ቃል ሁሉ ይልቅ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። አዘውትረን መጸለያችን ይህን ቃላችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። ልክ እንደ መዝሙራዊው ዳዊት “አምላክ ሆይ፤ ስእለቴን ሰምተሃልና፤ . . . ለስምህ ዘወትር ውዳሴ አቀርባለሁ፤ ስእለቴንም በየጊዜው እፈጽማለሁ [“እፈጽም ዘንድ፣” የ1954 ትርጉም]” በማለት መጸለይ እንችላለን። (መዝ. 61:5, 8፤ መክ. 5:4-6) የአምላክ ወዳጅ መሆን ከፈለግን እምነት የሚጣልብን ሰዎች መሆን ይኖርብናል።—መዝ. 15:1, 4

4. ዮፍታሔ ለይሖዋ የገባውን ስእለት ለመፈጸም እሱም ሆነ ሴት ልጁ ምን አደረጉ?

4 እስራኤላውያን በመሳፍንት ይተዳደሩ በነበሩበት ወቅት፣ ዮፍታሔ ይሖዋ በአሞናውያን ላይ ድል እንዲቀዳጅ ከረዳው ከጦርነት ሲመለስ በመጀመሪያ ሊቀበለው የሚወጣውን ሰው ‘እንደሚቃጠል መሥዋዕት’ አድርጎ ለማቅረብ ተሳለ። ወደ ቤት ሲመለስ በመጀመሪያ ልትቀበለው የወጣችው አንድ ልጁ ነበረች። ዮፍታሔና ትዳር ያልመሠረተችው ልጁ በይሖዋ በመታመን ስእለቱን ፈጽመዋል። በእስራኤላውያን ዘንድ ጋብቻም ሆነ ልጅ መውለድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች ቢሆኑም የዮፍታሔ ልጅ ሳታገባ ለመኖር ፈቃደኛ ሆናለች። ይህም ሕይወቷን በሙሉ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት አስገኝቶላታል።—መሳ. 11:28-40

5. ሐና እምነት የሚጣልባት ሴት መሆኗን ያስመሠከረችው እንዴት ነው?

5 ፈሪሃ አምላክ የነበራት ሐና እምነት የሚጣልባት ሴት መሆኗን አስመሥክራለች። ሐና ከባሏ ከሕልቃና እና ከጣውንቷ ከፍናና ጋር በተራራማው የኤፍሬም አገር ትኖር ነበር። ፍናና ብዙ ልጆች በመውለዷ በተለይ ቤተሰቡ ወደ ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ወቅት፣ መካን በነበረችው በሐና ላይ ትሳለቅባት ነበር። በአንድ ወቅት ሐና ወንድ ልጅ ከወለደች ለይሖዋ እንደምትሰጠው ስእለት ተሳለች። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳሙኤል ብላ ጠራችው። ልጁ ጡት በጣለ ጊዜ ሐና “በሕይወት ዘመኑ ሁሉ” ይሖዋን እንዲያገለግል ሴሎ ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ወሰደችው። (1 ሳሙ. 1:11) ሐና ወደፊት ሌሎች ልጆች እንደምትወልድ ባታውቅም ስእለቷን ፈጽማለች።—1 ሳሙ. 2:20, 21

6. ቲኪቆስ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑ የታየው እንዴት ነው?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ቲኪቆስ የተባለ ክርስቲያን እምነት የሚጣልበትና “ታማኝ አገልጋይ” ነበር። (ቈላ. 4:7) ቲኪቆስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ከግሪክ ተነስቶ በመቄዶንያ በኩል ወደ ትንሿ እስያ፣ ከዚያም ምናልባት ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ አብሮት ነበር። (ሥራ 20:2-4) በይሁዳ ይኖሩ ለነበሩት ችግር የደረሰባቸው ክርስቲያኖች የተሰበሰበውን ስጦታ በማድረስ ቲቶን የረዳው ‘ወንድም’ እሱ ሳይሆን አይቀርም። (2 ቆሮ. 8:18, 19፤ 12:18) ጳውሎስ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበት ወቅት፣ እምነት የሚጣልበት ቲኪቆስ በኤፌሶንና በቈላስይስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ደብዳቤዎችን እንዲያደርስለት ልኮታል። (ኤፌ. 6:21, 22፤ ቈላ. 4:8, 9) ጳውሎስ በሮም ለሁለተኛ ጊዜ ሲታሰር ቲኪቆስን ወደ ኤፌሶን ልኮታል። (2 ጢሞ. 4:12) እኛም እምነት የሚጣልብን ሰዎች ከሆን በይሖዋ አገልግሎት ግሩም መብቶችን እናገኛለን።

7, 8. ዳዊትና ዮናታን የልብ ጓደኛሞች ነበሩ ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

7 አምላክ እምነት የሚጣልብን ወዳጅ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (ምሳሌ 17:17) የንጉሥ ሳኦል ልጅ የሆነው ዮናታን የዳዊት ወዳጅ ነበር። ዮናታን፣ ዳዊት ጎልያድን መግደሉን ሲሰማ ምን እንደተሰማው መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቈራኘች፤ እንደራሱም አድርጎ ወደደው” ይላል። (1 ሳሙ. 18:1, 3) ሌላው ቀርቶ ዮናታን፣ ሳኦል ዳዊትን ሊገድለው እንደሚፈልግ ባወቀ ጊዜ ሁኔታውን በመንገር አስጠንቅቆታል። ዳዊት ከሸሸ በኋላ ዮናታን ከዳዊት ጋር በመገናኘት ቃል ኪዳን አድርጓል። ዮናታን ለሳኦል ስለ ዳዊት መናገሩ ሕይወቱን ሊያሳጣው የነበረ ቢሆንም ሁለቱ ጓደኛሞች በድጋሚ ተገናኝተው ወዳጅነታቸውን አድሰዋል። (1 ሳሙ. 20:24-41) ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት ወቅትም ዮናታን ዳዊትን ‘በአምላክ ስም’ አበረታቶታል።—1 ሳሙ. 23:16-18

8 ዮናታን ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገ ውጊያ ላይ ሕይወቱ አለፈ። (1 ሳሙ. 31:6) በዚህ ወቅት ዳዊት እንዲህ የሚል የሐዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ:- “ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ አዘንሁ፤ አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤ ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ፤ ከሴት ፍቅርም ይልቅ ግሩም ነበር።” (2 ሳሙ. 1:26) ዳዊትና ዮናታን እጅግ የሚዋደዱ የልብ ጓደኛሞች ነበሩ።

ምንጊዜም ‘ትሑት’ ሁን

9. በመሳፍንት ምዕራፍ 9 ላይ ያለው ምሳሌ የትሕትናን አስፈላጊነት የሚያሳየው እንዴት ነው?

9 የአምላክ ወዳጅ ለመሆን ከፈለግን ‘ትሑት’ መሆን አለብን። (1 ጴጥ. 3:8፤ መዝ. 138:6) በመሳፍንት ምዕራፍ 9 ላይ የትሕትናን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ምሳሌ ይገኛል። የጌዴዎን ልጅ የሆነው ኢዮአታም “ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ” ብሏል። በዚህ ምሳሌ ላይ የወይራ ዛፍና በለስ እንዲሁም የወይን ተክል ተጠቅሰዋል። እነዚህ ተክሎች ወንድሞቻቸው በሆኑት በእስራኤላውያን ላይ ለመንገሥ ያልፈለጉትን ብቃት ያላቸው ሰዎች ያመለክታሉ። ከማገዶነት ያለፈ ፋይዳ የሌለው የእሾህ ቍጥቋጦ ግን ኩራተኛውን ንጉሥ አቤሜሌክን ያመለክታል። አቤሜሌክ ሌሎችን የመጨቆን ፍላጎት የነበረው ነፍሰ ገዳይ ሰው ነበር። አቤሜሌክ ‘እስራኤልን ሦስት ዓመት የገዛ’ ቢሆንም ያለ ዕድሜው ሞቷል። (መሳ. 9:8-15, 22, 50-54) በእርግጥም ‘ትሑት’ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው!

10. ሄሮድስ ‘ለአምላክ ክብር ባለመስጠቱ’ ከደረሰበት አስከፊ ሁኔታ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሁዳን ይገዛ በነበረው በኩሩው ንጉሥ በሄሮድስ አግሪጳ እና በጢሮስና በሲዶና ነዋሪዎች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። እነዚህ ሰዎች ከንጉሡ ጋር እርቅ ለመፍጠር ፈለጉ። በአንድ ወቅት ሄሮድስ ንግግር ሲያቀርብ ሕዝቡ “ይህስ የአምላክ ድምፅ እንጂ የሰው አይደለም!” ብለው ጮኹ። ሄሮድስ ይህን መሰሉን ውዳሴ በመቀበሉና ‘ለአምላክ ክብር ሳይሰጥ’ በመቅረቱ በይሖዋ መልአክ ተመትቶ በአስከፊ ሁኔታ ሞተ። (ሥራ 12:20-23) እኛስ፣ ንግግር በማቅረብ አሊያም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ረገድ የተሳካልን ነን? ከሆነ ይህን ችሎታ የሰጠንን አምላክ ልናመሰግነው ይገባል።—1 ቆሮ. 4:6, 7፤ ያዕ. 4:6

ብርቱና ደፋር ሁን

11, 12. የሔኖክ ታሪክ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ድፍረትና ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው የሚያሳየው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ በትሕትና በመንገዱ የምንሄድ ከሆነ ድፍረትና ብርታት ይሰጠናል። (ዘዳ. 31:6-8, 23) ከአዳም ጀምሮ ሲቆጠር ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ በዘመኑ ከነበሩት ክፉ ሰዎች በተቃራኒ ቀናውን መንገድ በመከተል ከአምላክ ጋር በድፍረት ሄዷል። (ዘፍ. 5:21-24) በሔኖክ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ዓመጸኞችና ተሳዳቢዎች ነበሩ። በመሆኑም ይሖዋ ሔኖክ ጠንካራ የፍርድ መልእክት እንዲነግራቸው ብርታት ሰጥቶታል። (ይሁዳ 14, 15ን አንብብ።) የአምላክን የፍርድ መልእክት ለማወጅ የሚያስችል ድፍረት አለህ?

12 ይሖዋ፣ በኖኅ ዘመን ታላቅ የውኃ ጥፋት በማምጣት በወቅቱ በነበረው ከአምላክ የራቀ ዓለም ላይ ፍርዱን አስፈጽሟል። ይሁንና ሔኖክ የተናገረው ትንቢት ለእኛም ማበረታቻ ይዞልናል። እልፍ አእላፋት የሆኑት የአምላክ ቅዱሳን መላእክት በቅርቡ በዘመናችን ያለውን ከአምላክ የራቀ ዓለም ያጠፋሉ። (ራእይ 16:14-16፤ 19:11-16) ይሖዋ ጸሎታችንን በመስማት ስለ ፍርድ መልእክቱም ሆነ በመንግሥቱ ግዛት ሥር ስለሚኖሩት በረከቶች የሚገልጸውን ምሥራች ለመስበክ የሚያስችል ድፍረት ይሰጠናል።

13. አምላክ የገጠመንን የሚያስጨንቅ ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ድፍረትና ጥንካሬ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

13 የሚደርሱብንን አስጨናቂ ችግሮች ለመቋቋም አምላክ የሚሰጠው ድፍረትና ብርታት ያስፈልገናል። ዔሳው ሁለት ኬጢያውያን ሴቶችን በማግባቱ ምክንያት “[የወላጆቹ] የይስሐቅና የርብቃ ልብ ያዝን ነበር።” እንዲያውም ርብቃ እንዲህ ስትል በምሬት ተናግራለች:- “ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ [ልጃችን] ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ።” (ዘፍ. 26:34, 35፤ 27:46) ይስሐቅም ይሖዋን ከሚያመልኩ ሰዎች መካከል ሚስት እንዲፈልግ ያዕቆብን ወደ ሌላ ቦታ በመላክ ተገቢ እርምጃ ወስዷል። ይስሐቅና ርብቃ፣ ዔሳው ያደረገውን ነገር መለወጥ ባይችሉም አምላክ ለእሱ ታማኝ ሆነው ለመኖር የሚያስችላቸውን ጥበብ፣ ድፍረትና ብርታት ሰጥቷቸዋል። እርዳታ ስንፈልግ ወደ ይሖዋ በጸሎት የምንቀርብ ከሆነ ለእኛም ተመሳሳይ ነገር ያደርግልናል።—መዝ. 118:5

14. አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ልጃገረድ ድፍረት ያሳየችው እንዴት ነው?

14 ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ፣ አንዲት ትንሽ እስራኤላዊት ልጃገረድ በወራሪ ጦር ተማርካ ተወሰደችና ንዕማን በሚባል የሶርያ ሠራዊት አለቃ ቤት ታገለግል ጀመር። ይህ ሰው በለምጽ ተይዞ ነበር። አምላክ በነቢዩ ኤልሳዕ በኩል ስላደረገው ተአምር የሰማችው ይህች ልጅ ወደ ንዕማን ሚስት በድፍረት በመቅረብ ‘ጌታዬ በእስራኤል ወዳለው የይሖዋ ነቢይ ቢሄድ ከለምጹ ይፈውሰው ነበር’ አለቻት። ንዕማንም ወደ እስራኤል በመሄድ ከለምጹ በተአምር ተፈወሰ። (2 ነገ. 5:1-3) ይህቺ ትንሽ ልጅ፣ ይሖዋ ድፍረት እንደሚሰጣቸው በማመን ለአስተማሪዎቻቸው፣ አብረዋቸው ለሚማሩ ልጆችና ለሌሎች ሰዎች ለሚመሠክሩ በዘመናችን ላሉ ወጣቶች ግሩም ምሳሌ ትሆናለች!

15. የአክዓብ ቤት አዛዥ የነበረው አብድዩ ምን የድፍረት እርምጃ ወስዷል?

15 አምላክ የሚሰጠን ድፍረት የሚደርስብንን ስደት በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። በነቢዩ ኤልያስ ዘመን ይኖር የነበረው የንጉሥ አክዓብ ቤት አዛዥ የሆነው አብድዩ ያጋጠመውን ሁኔታ ተመልከት። ንግሥት ኤልዛቤል የአምላክ ነቢያት እንዲገደሉ ባዘዘች ጊዜ አብድዩ መቶውን ነቢያት ወስዶ ‘አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ ውስጥ ሸሸጋቸው።’ (1 ነገ. 18:13፤ 19:18) አብድዩ ለይሖዋ ነቢያት እንዳደረገው አንተስ በስደት ላይ ያሉ የእምነት ባልደረቦችህን በድፍረት ትረዳቸዋለህ?

16, 17. አርስጥሮኮስና ጋይዮስ ለደረሰባቸው ስደት ምን ምላሽ ሰጡ?

16 ስደት ሲደርሰብን ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሮሜ 8:35-39) የጳውሎስ የሥራ ባልደረባ የሆኑት አርስጥሮኮስና ጋይዮስ በኤፌሶን የቲያትር ማሳያ ስፍራ ተሰብስበው ከነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር። ተቃውሞውን ያነሳሳው ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ ሲሆን እሱና በተመሳሳይ ሙያ ይተዳደሩ የነበሩ ሌሎች ሰዎች የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች ከብር እየሠሩ ይሸጡ ነበር። ይሁንና የጳውሎስን ስብከት የሰሙ በርካታ የከተማይቱ ነዋሪዎች የጣዖት አምልኮን በመተዋቸው ብዙ ትርፍ ያስገኝላቸው የነበረው ንግድ ስጋት ላይ ወደቀ። ረብሸኞቹ አርስጥሮኮስንና ጋይዮስን እየጎተቱ ወደ ቲያትር ማሳያ ስፍራው ከወሰዷቸው በኋላ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር። አርስጥሮኮስና ጋይዮስ በዚያ እንደሚሞቱ ሳይሰማቸው አልቀረም። ይሁንና የከተማይቱ ዋና ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኘው።—ሥራ 19:23-41

17 እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢገጥምህ ከዚያ በኋላ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ላለመግባት የአገልግሎት እንቅስቃሴህን ትቀንሳለህ? አርስጥሮኮስና ጋይዮስ በጣም ፈርተው እንደነበር የሚጠቁም ነገር የለም። አርስጥሮኮስ የተሰሎንቄ ሰው እንደመሆኑ መጠን ምሥራቹን መስበክ ስደት ሊያስከትል እንደሚችል ያውቃል። ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ጳውሎስ በተሰሎንቄ ሲሰብክ ሁከት ተፈጥሮ ነበር። (ሥራ 17:5፤ 20:4) አርስጥሮኮስና ጋይዮስ በይሖዋ መንገድ በመሄዳቸው፣ አምላክ የደረሰባቸውን ስደት ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬና ድፍረት ሰጥቷቸዋል።

ሌሎችን የሚጠቅመውን አስብ

18. ጵርስቅላና አቂላ ‘ሌሎችን የሚጠቅመውን ይመለከቱ’ የነበረው እንዴት ነው?

18 በአሁኑ ጊዜ ስደት እየደረሰብንም ይሁን አይሁን የእምነት አጋሮቻችን ያሉበት ሁኔታ ሊያሳስበን ይገባል። ጵርስቅላና አቂላ ‘ሌሎችን የሚጠቅመውን ይመለከቱ’ ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:4ን አንብብ።) የብር አንጥረኛው ድሜጥሮስ በኤፌሶን ሁከት ባስነሳበት ወቅት ጳውሎስ ያረፈው ምሳሌ በሆኑት በእነዚህ ባልና ሚስት ቤት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ሁኔታ ጵርስቅላና አቂላ ለጳውሎስ ሲሉ ‘ሕይወታቸውን ለአደጋ እንዲሰጡ’ ሳያነሳሳቸው አልቀረም። (ሮሜ 16:3, 4፤ 2 ቆሮ. 1:8) በዛሬው ጊዜም፣ በስደት ውስጥ ላሉ ወንድሞቻችን ያለን የአሳቢነት ስሜት “እንደ እባብ ብልኆች” እንድንሆን ያደርገናል። (ማቴ. 10:16-18) ሥራችንን በጥንቃቄ የምንፈጽም ከመሆኑም ሌላ የወንድሞቻችንን ስምም ሆነ ሌሎች መረጃዎችን ለአሳዳጆች አሳልፈን አንሰጥም።

19. ዶርቃ ለሌሎች ሰዎች ምን መልካም ነገሮችን አድርጋለች?

19 ለሌሎች ጥቅም የምናስብ መሆናችንን የምናሳይባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች መሠረታዊ የሆነ ነገር እንደቸገራቸው ስንመለከት የጎደላቸውን በማሟላት ልንረዳቸው እንችል ይሆናል። (ኤፌ. 4:28፤ ያዕ. 2:14-17) በአንደኛው መቶ ዘመን በነበረው የኢዮጴ ጉባኤ ውስጥ በለጋስነቷ የምትታወቅ ዶርቃ የተባለች አንዲት ሴት ነበረች። (የሐዋርያት ሥራ 9:36-42ን አንብብ።) ዶርቃ ችግረኛ ለሆኑ መበለቶች ልብስ መስፋትን ጨምሮ ‘ዘወትር በትጋት በጎ ነገር ታደርግና ድኾችን ትረዳ’ ነበር። በ36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ስትሞት ብዙዎቹ መበለቶች እጅግ አዘኑ። ይሁንና አምላክ በሐዋርያው ጴጥሮስ አማካኝነት ዶርቃን ከሞት አስነሳት። ዶርቃ ቀሪውን ሕይወቷን ምሥራቹን በደስታ በመስበክና ለሌሎች መልካም በማድረግ እንዳሳለፈች ጥርጥር የለውም። በዛሬው ጊዜም የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ዶርቃን የመሰሉ እህቶች በመካከላችን መኖራቸው እጅግ ያስደስታል!

20, 21. (ሀ) ማበረታቻ መስጠት ሌሎችን የሚጠቅመውን ከማሰብ ጋር ምን ግንኙነት አለው? (ለ) ሌሎችን ለማበረታታት ምን ማድረግ ትችላለህ?

20 ሌሎችን በማበረታታት እንደምናስብላቸው እናሳያለን። (ሮሜ 1:11, 12) የጳውሎስ የሥራ ባልደረባ የሆነው ሲላስ ለሌሎች የብርታት ምንጭ ነበር። ስለ ግርዘት የተነሳው ጥያቄ በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ በኢየሩሳሌም የነበረው የበላይ አካል በተለያዩ ቦታዎች ይገኙ ለነበሩት ክርስቲያኖች ደብዳቤ የሚያደርሱ ተወካዮችን ልኮ ነበር። ሲላስ፣ ይሁዳ፣ በርናባስና ጳውሎስ ወደ አንጾኪያ ተላኩ። በዚያም ሲላስና ይሁዳ “ወንድሞችን ብዙ ንግግር በማድረግ መከሯቸው፤ አበረቷቸውም።”—ሥራ 15:32

21 ከጊዜ በኋላ ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ ታሰሩ፤ ሆኖም የመሬት መናወጥ በመነሳቱ ሳቢያ ነፃ ወጡ። ጳውሎስና ሲላስ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ለወህኒ ቤቱ ጠባቂ መመሥከራቸውና እሱም ሆነ ቤተሰቡ አማኞች መሆናቸው እጅግ አስደስቷቸው መሆን አለበት! ሲላስና ጳውሎስ ከተማውን ለቀው ከመሄዳቸው በፊት ወንድሞችን አበረታቷቸው። (ሥራ 16:12, 40) አንተም፣ ጳውሎስና ሲላስ እንዳደረጉት ሁሉ በስብሰባዎች ላይ በምትሰጠው ሐሳብ፣ በንግግርህና ቅንዓት በተሞላበት አገልግሎትህ ሌሎችን ለማበረታታት ተጣጣር። ሌሎችን ‘የሚያበረታታ ቃል እንዳለህ’ ከተሰማህ ፈጽሞ ‘ከመናገር’ ወደኋላ አትበል።—ሥራ 13:15 NW

በይሖዋ መንገድ መሄድህን ቀጥል

22, 23. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈሩት ዘገባዎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

22 ‘የብርታት ሁሉ ምንጭ የሆነው [ይሖዋ] አምላክ’ በቃሉ ውስጥ እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎች ተመዝግበው እንዲቆዩልን ስላደረገ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (2 ቆሮ. 1:3ባይንግተን) ከእነዚህ ተሞክሮዎች ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግና የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንዲመራን መፍቀድ ይኖርብናል።—ገላ. 5:22-25

23 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ማሰላሰላችን አምላካዊ ባሕርያትን እንድናፈራ ይረዳናል። ‘ጥበብን፣ ዕውቀትንና ደስታን ከሚሰጠን’ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናክርልናል። (መክ. 2:26) ይህ ደግሞ አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ያስደስተዋል። (ምሳሌ 27:11) በይሖዋ መንገድ መጓዛችንን በመቀጠል የአምላክን ልብ ደስ ለማሰኘት ያደረግነውን ውሳኔ እስከ መጨረሻው አጽንተን እንያዝ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• እምነት የሚጣልብህ ሰው መሆንህን ማስመሥከር የምትችለው እንዴት ነው?

• ‘ትሑት’ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

• የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ደፋሮች እንድንሆን የሚረዱን እንዴት ነው?

• ለሌሎች ጥቅም እንደምናስብ በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮፍታሔ የገባውን ስእለት መፈጸም ቀላል ባይሆንም እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች የነበሩት ዮፍታሔና ሴት ልጁ ስእለቱን ፈጽመዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እናንት ወጣቶች፣ ከእስራኤላዊቷ ልጃገረድ ምን ትማራላችሁ?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዶርቃ፣ የእምነት ባልንጀሮቿ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማሟላት የረዳቻቸው እንዴት ነው?