በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እስራኤላውያን ከፈጸሙት ስሕተት ትምህርት ማግኘት

እስራኤላውያን ከፈጸሙት ስሕተት ትምህርት ማግኘት

እስራኤላውያን ከፈጸሙት ስሕተት ትምህርት ማግኘት

እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ ይሖዋ ከእነሱ ምን እንደሚጠብቅባቸው ያውቁ ነበር። አምላክ በሙሴ በኩል እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር:- “የምድሪቱን ነዋሪዎች በሙሉ ከፊታችሁ አሳዳችሁ አስወጧቸው፤ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩ ጣዖቶቻቸውን በሙሉ አጥፉ፤ እንዲሁም በኰረብታ ላይ የተሠሩትን መስገጃዎቻቸውን ሁሉ አፈራርሱ።”—ዘኍ. 33:52

እስራኤላውያን ከምድሪቱ ነዋሪዎች ጋር ምንም ዓይነት የሰላም ስምምነት መፍጠርም ሆነ በጋብቻ መተሳሰር አይገባቸውም ነበር። (ዘዳ. 7:2, 3) እንዲያውም የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች “ከምትሄድበት አገር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ አለዚያ በመካከልህ ወጥመድ ይሆኑብሃል” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። (ዘፀ. 34:12) ያም ሆኖ እስራኤላውያን አምላክን ባለመታዘዝ ወጥመድ ውስጥ ገቡ። ለውድቀት የዳረጋቸው ምንድን ነው? ከእነሱ ታሪክ ማስጠንቀቂያ የሚሆነን ምን ትምህርት እናገኛለን?—1 ቆሮ. 10:11

ወዳጅነት መመሥረታቸው ወደ ጣዖት አምልኮ መርቷቸዋል

እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር በያዙበት ጊዜ ነዋሪዎቹን በቀላሉ ድል ማድረግ ችለው ነበር። ይሁን እንጂ የእስራኤል ልጆች የአምላክን ትእዛዝ በተሟላ ሁኔታ ሳይፈጽሙ ቀርተዋል። ጠላቶቻቸውን ከምድሪቱ አላስወጧቸውም። (መሳ. 1:1 እስከ 2:10) ከዚህ ይልቅ፣ ‘ከሰባቱ የአሕዛብ’ ብሔራት ጋር ተቀላቅለው መኖር የጀመሩ ሲሆን ከነዋሪዎቹ ጋር ዘወትር መገናኘታቸው ወዳጅነት ወደ መመሥረት መራቸው። (ዘዳ. 7:1) ይህ ሁኔታ በእስራኤላውያን ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ። እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔር አምላካቸውንም ረሱ፤ የበኣልንና የአስታሮትን አማልክት አመለኩ።” (መሳ. 3:5-7) እስራኤላውያን ከምድሪቱ ነዋሪዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረታቸው ከእነሱ ጋር በጋብቻ ወደ መቆራኘትና ጣኦቶቻቸውን ወደ ማምለክ መርቷቸዋል። አንዴ የጋብቻ ዝምድና ከመሠረቱ በኋላ፣ ጣኦት አምላኪ የሆኑትን ሕዝቦች ከምድሪቱ እንዲያስወጡ የተሰጣቸውን ትእዛዝ መፈጸም አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ግልጽ ነው። እውነተኛው አምልኮ ተበከለ፤ እንዲሁም እስራኤላውያን የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀመሩ።

የተስፋይቱ ምድር ነዋሪዎች የእስራኤላውያን ጠላቶች ከነበሩበት ጊዜ ይልቅ ወዳጆቻቸው በሆኑበት ወቅት ያስከተሉባቸው መንፈሳዊ ጉዳት ይበልጣል። እስራኤላውያን ሃይማኖታቸው እንዲበከል ያደረገው ሌላ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችል ተመልከት።

በእርሻና በበኣል አምልኮ መካከል ያለው ዝምድና

እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ መኖራቸውን ትተው አብዛኞቹ በእርሻ ሥራ መተዳደር ጀመሩ። የእርሻ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት መንገድ ቀደም ሲል በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ይጠቀሙበት ከነበረው ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና እስራኤላውያን የኮረጁት የከነዓናውያንን የእርሻ ዘዴ ብቻ አልነበረም። ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር መቀራረባቸው ሰዎቹ ከእርሻ ጋር በተያያዘ የነበራቸውን አምልኮ ጭምር ወደ መከተል መርቷቸዋል።

ከነዓናውያን ምድሪቱን ፍሬያማ ያደርጋሉ ብለው የሚያምኑባቸውን በርካታ የበኣል አማልክት ያመልኩ ነበር። እስራኤላውያን ምድሪቱን ከማልማትና ሰብል ከመሰብሰብ በተጨማሪ፣ ያገኙትን የተትረፈረፈ ምርት የሰጧቸው የከነዓናውያን አማልክት እንደሆኑ በማሰብ ቀስ በቀስ እነሱን ማምለክ ጀመሩ። በመሆኑም በርካታ እስራኤላውያን ይሖዋን እናመልካለን ቢሉም እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የክህደት አካሄድ እየተከተሉ ነበር።

ለዘመናችን የሚሆን ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ

እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተስፋይቱ ምድር ነዋሪዎች ጋር ሲገናኙ በበዓል አምልኮም ሆነ አምልኮው በሚያካትታቸው አጸያፊ ድርጊቶች የመካፈል ፍላጎት እንዳልነበራቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከእነሱ ጋር የመሠረቱት ቅርርብ እነዚህን ነገሮች ወደመፈጸም መርቷቸዋል። እኛስ የወዳጅነት ስሜት ከሚያሳዩን ሆኖም እምነታችንን ከማይጋሩ እንዲሁም የምንመራበትን የሥነ ምግባር መሥፈርትና መሠረታዊ ሥርዓት ከማይከተሉ ሰዎች ጋር መቀራረባችን እንዲህ ያለ አስከፊ መዘዝ ሊያስከትልብን እንደሚችል መጠበቅ አይኖርብንም? እርግጥ ነው፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ ሌላው ቀርቶ በቤታችን እንኳ የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ሰዎች ጋር በተወሰነ መጠን መቀራረባችን የግድ ሊሆን ይችላል። ይሁንና የእስራኤላውያን ታሪክ እንደሚያሳየው እምነታችንን ከማይጋሩ ሰዎች ጋር ለመወዳጀት መፈለግ በራስ ላይ ችግር መጋበዝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” በማለት ይህ የማይታበል ሐቅ መሆኑን ይገልጻል።—1 ቆሮ. 15:33

በዛሬው ጊዜም እስራኤላውያን ያጋጠሟቸው ዓይነት በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይገጥሙናል። በዘመናችን ያለው ኅብረተሰብ እንደ አምላክ የሚያያቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ መካከል ገንዘብ፣ የመዝናኛው ዓለም ኮከቦች፣ ታዋቂ ስፖርተኞች፣ የፖለቲካ ሥርዓቶች፣ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎችና ሌላው ቀርቶ የቤተሰብ አባላት ይገኙበታል። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዱ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ ይችላል። ይሖዋን ከማይወዱ ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት ለመንፈሳዊ ውድቀት ይዳርጋል።

ልቅ የሆነ የጾታ ብልግና እስራኤላውያንን የማረካቸውና ያሳታቸው የበዓል አምልኮ ዋነኛ ክፍል ነበር። ዛሬም ከአምላክ ሕዝቦች መካከል አንዳንዶቹ ከዚህ ጋር በሚመሳሰሉ ወጥመዶች ተይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ብቻውን ሆኖ ኢንተርኔት የሚመለከት ከፍተኛ የማወቅ ጉጉት ያለው ወይም ጥንቁቅ ያልሆነ አንድ ሰው፣ ጥቂት የኮምፒውተር ቁልፎችን በመጫን ብቻ ንጹሕ ሕሊናውን የሚያቆሽሹ ነገሮችን ሊመለከት ይችላል። አንድ ክርስቲያን በኢንተርኔት አማካኝነት የብልግና ሥዕሎችን በመመልከት ወጥመድ ውስጥ ቢወድቅ ምንኛ ያሳዝናል!

ማሳሰቢያዎቹን የሚጠብቁ የተባረኩ ናቸው’

በጓደኛ ምርጫ ረገድ ይሖዋን ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ የምናደርገው ውሳኔ ለግላችን የተተወ ነው። (ዘዳ. 30:19, 20) በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን የተገባ ነው:- ‘የዕረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው ከእነማን ጋር ነው? እነዚህ ሰዎች የአምላክን ሕግጋት የሚመለከቱት እንዴት ነው? ምን ዓይነት ሥነ ምግባር አላቸው? ይሖዋን ያመልካሉ? ከእነሱ ጋር መሆኔ የተሻልኩ ክርስቲያን እንድሆን ያበረታታኛል?’

መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም [“በይሖዋም፣” NW] ሕግ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው። ምስክርነቱን [“ማሳሰቢያዎቹን፣” NW] የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት የተባረኩ ናቸው።” (መዝ. 119:1, 2) በእርግጥም ይሖዋን “የሚፈሩ ሁሉ፣ በመንገዱም የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው።” (መዝ. 128:1) ወዳጆቻችንን ስንመርጥ እስራኤላውያን ከፈጸሟቸው ስሕተቶች ትምህርት እንውሰድ፤ እንዲሁም ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ታዛዥ እንሁን።—ምሳሌ 13:20

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋን ከማይወዱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ወደ ጣዖት አምልኮ ሊመራን ይችላል