በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማርቆስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የማርቆስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የማርቆስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የማርቆስ ወንጌል ከአራቱ ወንጌሎች በጣም አጭሩ ሲሆን የጻፈው ዮሐንስ ማርቆስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተና ትንሣኤ ካገኘ ከ30 ዓመታት ገደማ በኋላ የተጻፈው ይህ ወንጌል ኢየሱስ ምድር ላይ ባገለገለበት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ በርካታ አስደናቂ ክንውኖችን አጠር አጠር አድርጎ ይዘግባል።

አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች በተለይም ለሮማውያን እንደተጻፈ የሚገመተው የማርቆስ ወንጌል፣ ኢየሱስን ታላቅ የስብከት ዘመቻ ያካሄደና ተአምር ሠሪ የሆነ የአምላክ ልጅ አድርጎ ይገልጸዋል። መጽሐፉ ይበልጥ የሚያተኩረው በኢየሱስ ትምህርቶች ላይ ሳይሆን ባከናወናቸው ነገሮች ላይ ነው። ለማርቆስ ወንጌል ትኩረት መስጠታችን በመሲሑ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን ከመሆኑም ባሻገር የአምላክን መልእክት በቅንዓት በማወጅ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን እንድንወጣ ይገፋፋናል።—ዕብ. 4:12

በገሊላ የተከናወነው ታላቅ አገልግሎት

(ማርቆስ 1:1 እስከ 9:50)

ማርቆስ በመጀመሪያዎቹ 14 ቁጥሮች ላይ መጥምቁ ዮሐንስ ስላደረገው እንቅስቃሴና ኢየሱስ በምድረ በዳ ስላሳለፋቸው 40 ቀናት ከገለጸ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ስላከናወነው አገልግሎት የሚገልጸውን አስደናቂ ዘገባ መተረክ ጀመረ። ማርቆስ “ወዲያው” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ መጠቀሙ የጥድፊያ ስሜት እንደነበረው ያሳያል።—ማር. 1:12, 28

ኢየሱስ ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በገሊላ ሦስት የስብከት ዘመቻዎችን አድርጓል። ማርቆስ አብዛኛውን ዘገባውን ያሰፈረው በጊዜ ቅደም ተከተል ነው። የተራራውን ስብከት ጨምሮ ኢየሱስ ያቀረባቸው ሌሎች በርካታ ረጃጅም ንግግሮች በመጽሐፉ ውስጥ አልተካተቱም።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:15 [NW]—ተፈጸመ የተባለው “የተወሰነው ጊዜ” ምን የሚደረግበት ነው? እዚህ ላይ ኢየሱስ አገልግሎት እንዲጀምር የተወሰነው ጊዜ መድረሱን መግለጹ ነበር። ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ስለታጨ የአምላክ መንግሥት ቀርቦ ነበር። ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ለስብከት ሥራው በጎ ምላሽ መስጠትና የአምላክን ሞገስ የሚያስገኝላቸውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

1:44፤ 3:12፤ 7:36—ኢየሱስ፣ ሰዎች የሚያደርጋቸውን ተአምራት ለሌሎች እንዳይናገሩ የፈለገው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ይህን ያደረገው ሰዎች የተጋነኑና የተዛቡ ወሬዎችን ሰምተው አንድ መደምደሚያ ላይ ከሚደርሱ ይልቅ እሱ ክርስቶስ መሆኑን ራሳቸው እንዲያረጋግጡና በማስረጃዎች ላይ ተመሥርተው የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ስለፈለገ ነው። (ኢሳ. 42:1-4፤ ማቴ. 8:4፤ 9:30፤ 12:15-21፤ 16:20፤ ሉቃስ 5:14) ኢየሱስ በጌርሴኖን የሚኖረውን ርኩስ መንፈስ አድሮበት የነበረውን ሰው በፈወሰ ጊዜ ግን ከዚህ የተለየ ነገር አድርጓል። ኢየሱስ ሰውየው ወደ ቤቱ ሄዶ የተደረገለትን ነገር ለዘመዶቹ እንዲናገር አዝዞታል። በጌርሴኖን አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ኢየሱስ አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድ ስለጠየቁት ከእነሱ ጋር የመገናኘቱ አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነበር። በመሆኑም በጎ ነገር የተደረገለት ሰው በዚያ አካባቢ መኖሩና ስለ ኢየሱስ ምሥክርነት መስጠቱ የአሳማዎቹን ማለቅ በተመለከተ መጥፎ ወሬ እንዳይዛመት ይረዳል።—ማር. 5:1-20፤ ሉቃስ 8:26-39

2:28—ኢየሱስ “የሰንበት ጌታ” የተባለው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው” ሲል ጽፏል። (ዕብ. 10:1) በሕጉ ላይ እንደተገለጸው ሰንበት የሚውለው ከስድስት የሥራ ቀን በኋላ ነው። ኢየሱስ ደግሞ በሰንበት ቀን በርካታ ተአምራትን አከናውኗል። ይህ ሁኔታ ጨቋኝ የሆነው የሰይጣን አገዛዝ ከተወገደ በኋላ በሚኖረው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሰው ዘር ለሚያገኘው እረፍትም ሆነ ሌላ በረከት ጥላ ነው። በመሆኑም የዚህ መንግሥት ንጉሥ “የሰንበት ጌታ” ነው።—ማቴ. 12:8፤ ሉቃስ 6:5

3:5፤ 7:34፤ 8:12—ማርቆስ፣ ኢየሱስ የተሰማውን ስሜት እንዴት ሊያውቅ ቻለ? ማርቆስ ከ12ቱ ሐዋርያትም ሆነ ከኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች መካከል አንዱ አልነበረም። ጥንታዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ማርቆስ አብዛኞቹን ሐሳቦች ያገኘው የቅርብ ጓደኛው ከነበረው ከሐዋርያው ጴጥሮስ ነው።—1 ጴጥ. 5:13

6:51, 52—ደቀ መዛሙርቱ ‘እንጀራውን’ በሚመለከት ሳያስተውሉት የቀሩት ነገር ምንድን ነው? ከጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ኢየሱስ ሴቶችንና ልጆችን ሳይጨምር በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣ ብቻ 5,000 ወንዶችን መግቧል። ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ይሖዋ አምላክ፣ ለኢየሱስ ተአምራትን ለማከናወን የሚያስችል ከፍተኛ ኃይል እንደሰጠው ማስተዋል ነበረባቸው። (ማር. 6:41-44) ኢየሱስ የተሰጠው ኃይል ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ቢያስተውሉ ኖሮ በባሕር ላይ ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ ሲራመድ ከመጠን በላይ ባልተገረሙ ነበር።

8:22-26—ኢየሱስ ማየት የተሳነውን ሰው በአንድ ጊዜ ያልፈወሰው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ይህን ያደረገው ለሰውየው በማሰብ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ለረዥም ጊዜ ብርሃን ሳያይ የኖረውን ሰው ቀስ በቀስ መፈወሱ ሰውየው በአንድ ጊዜ ለከፍተኛ የፀሐይ ብርሃን እንዳይጋለጥ ረድቶታል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

2:18፤ 7:11፤ 12:18፤ 13:3:- ማርቆስ አይሁዳውያን ላልሆኑ አንባቢያን እንግዳ ሊሆኑ የሚችሉ ልማዶችን፣ ቃላትን፣ ትምህርቶችንና ቦታዎችን የጠቀሰ ሲሆን ለእነዚህም አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ፈሪሳውያን ‘እንደሚጾሙ’፣ ቁርባን ደግሞ “መባ” ማለትም ለአምላክ የሚቀርብ ስጦታ እንደሆነ፣ ሰዱቃውያን “የሙታን ትንሣኤ የለም” እንደሚሉ እንዲሁም ‘ቤተ መቅደሱ በደብረ ዘይት ተራራ ትይዩ’ እንደሚገኝ ግልጽ አድርጓል። የመሲሑ የዘር ሐረግ በጣም የሚያስፈልገው ለአይሁዳውያን በመሆኑ በወንጌሉ ውስጥ ሳያካትተው ቀርቷል። ይህ ሁኔታ ለእኛም ምሳሌ ይሆነናል። በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስንካፈልም ይሁን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ንግግር ስንሰጥ የአድማጮቻችንን ማንነት ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን።

3:21:- ኢየሱስ ዘመዶቹ አማኞች ስላልነበሩ በእምነታቸው ምክንያት ከቤተሰባቸው አባላት ተቃውሞ ወይም ፌዝ የሚደርስባቸውን ሰዎች ስሜት ይረዳል።

3:31-35:- ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኗል፤ ‘ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም’ ደግሞ እናቱ ሆናለች። (ገላ. 4:26) ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢየሱስ ከሥጋዊ ዘመዶቹ የበለጠ የሚቀርበውም ሆነ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለደቀ መዛሙርቱ ነበር። ይህም በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያውን እንድንሰጥ ያስተምረናል።—ማቴ. 12:46-50፤ ሉቃስ 8:19-21

8:32-34:- ሌሎች የሚያደርጉልንን የተሳሳተ ደግነት ለመገንዘብም ሆነ ለመቃወም ፈጣኖች መሆን ይኖርብናል። አንድ የክርስቶስ ተከታይ ‘ራሱን ለመካድ’ ዝግጁ መሆን እንዲሁም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸውን ምኞቶችና ግቦች ከማሳደድ መቆጠብ አለበት። የራሱን የመከራ እንጨት ለመሸከምም ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል። ይህም ሲባል ክርስቲያን በመሆኑ ምክንያት ሥቃይ፣ ውርደት ወይም ስደት ሌላው ቀርቶ ሞትም እንኳ ቢደርስበት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለበት። በተጨማሪም ኢየሱስ ከተከተለው የሕይወት ጎዳና ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር እሱን ‘በየዕለቱ መከተል’ አለበት። የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ልክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማዳበርንና ይህን መንፈስ ይዞ መቀጠልን ይጠይቃል።—ማቴ. 16:21-25፤ ሉቃስ 9:22, 23

9:24:- ስለ እምነታችን ለሌሎች ለመናገርም ሆነ እምነት እንዲጨመርልን ለመለመን ማፈር የለብንም።—ሉቃስ 17:5

የመጨረሻው ወር

(ማርቆስ 10:1 እስከ 16:8)

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ32 መጨረሻ ገደማ ኢየሱስ “ወደ ይሁዳ አገርና በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው አካባቢ” መጣ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ወደ እሱ ተሰበሰበ። (ማር. 10:1) በዚያ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከሰበከ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም አቀና።

ኒሳን 8 ኢየሱስ በቢታንያ ነበር። በማዕድ ተቀምጦ እያለ አንዲት ሴት መጥታ በራሱ ላይ ሽቶ አፈሰሰችበት። ኢየሱስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስከ ትንሣኤው ድረስ የተከናወኑት ነገሮች የተጻፉት በጊዜ ቅደም ተከተላቸው ነው።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

10:17, 18—ኢየሱስ “ቸር [“ጥሩ፣” NW] መምህር” በማለት የጠራውን ሰው ያረመው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ይህን የሽንገላ አጠራር ባለመቀበል ክብር የሚገባው ይሖዋ መሆኑን የጠቆመ ከመሆኑም በላይ የጥሩ ነገሮች ሁሉ ምንጭ እውነተኛው አምላክ መሆኑን አመልክቷል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ አንድ መሠረታዊ እውነት ማስገንዘብ ፈልጎ ነበር። ይኸውም ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር በሚመለከት መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው የሁሉ ነገሮች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ብቻ እንደሆነ ገልጿል።—ማቴ. 19:16, 17፤ ሉቃስ 18:18, 19

14:25—ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ “በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ ይህን ሲል በሰማይ ቃል በቃል ወይን ጠጅ አለ ማለቱ አልነበረም። ደስታ አንዳንድ ጊዜ በወይን ጠጅ ይመሰል ስለነበር ኢየሱስ በትንሣኤ ከሚነሱት ቅቡዓን ተከታዮቹ ጋር አብሮ መሆን የሚያስገኝለትን ደስታ መጥቀሱ ነበር።—መዝ. 104:15፤ ማቴ. 26:29

14:51, 52—‘ዕራቁቱን የሸሸው’ ወጣት ማን ነው? ይህን ሁኔታ የጠቀሰው ማርቆስ ብቻ ስለሆነ ዕራቁቱን የሸሸው እሱ ራሱ ነው ብለን መደምደማችን ምክንያታዊ ነው።

15:34—ኢየሱስ “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ማለቱ እምነት አንሶት እንደነበር ያሳያል? በጭራሽ። ምንም እንኳ ኢየሱስ እንዲህ ያለበትን ምክንያት በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም እነዚህ ቃላት ይሖዋ የልጁ ታማኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈተን ሲል የሚያደርግለትን ጥበቃ ማንሳቱን ኢየሱስ እንደተገነዘበ የሚጠቁሙ ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ኢየሱስ ይህን ያለው መዝሙር 22:1 ላይ እሱን አስመልክቶ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ሊሆን ይችላል።—ማቴ. 27:46

ምን ትምህርት እናገኛለን?

10:6-9:- አምላክ የትዳር ጓደኛሞች ዕድሜ ልክ አብረው እንዲኖሩ ዓላማው ነበር። በመሆኑም ባልና ሚስቶች በትዳራቸው ውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸው ለመፋታት ከመጣደፍ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል።—ማቴ. 19:4-6

12:41-44:- ድሃዋ መበለት እውነተኛውን አምልኮ በገንዘብ በመደገፍ ረገድ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ምሳሌ ትታልናለች።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ይህ ሰው የተደረገለትን ነገር ለዘመዶቹ እንዲናገር ያዘዘው ለምንድን ነው?