በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታላቁን ሚስዮናዊ ምሳሌ ተከተሉ

የታላቁን ሚስዮናዊ ምሳሌ ተከተሉ

የታላቁን ሚስዮናዊ ምሳሌ ተከተሉ

“እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ።”—1 ቆሮ. 11:1

1. የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ መከተል ያለብን ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ የታላቁን ሚስዮናዊ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ተከትሏል። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ቆሮ. 11:1) ኢየሱስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ በትሕትና ረገድ ትምህርት ከሰጣቸው በኋላ “እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 13:12-15) በዛሬው ጊዜ ያለን ክርስቲያኖችም በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን እንዲሁም በምናሳየው ባሕርይ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ መከተል አለብን።—1 ጴጥ. 2:21

2. በበላይ አካሉ የተሾምክ ሚስዮናዊ ባትሆንም ምን ዓይነት መንፈስ ማዳበር ትችላለህ?

2 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ሚስዮናዊ የሚባለው ወንጌላዊ ሆኖ የሚላክና ለሌሎች ሰዎች ምሥራች የሚያውጅ ሰው ነው። በዚህ ረገድ ጳውሎስ ትኩረት የሚስቡ አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስቷል። (ሮሜ 10:11-15ን አንብብ።) ሐዋርያው፣ “ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ?” በማለት እንደጠየቀ ልብ በል። ከዚያም ከኢሳይያስ ትንቢት በመጥቀስ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ብሏል። (ኢሳ. 52:7) ምንም እንኳ በሚስዮናዊነት እንድታገለግል ተሹመህ ወደ ሌላ አገር ባትላክም እንደ ኢየሱስ ቀናተኛ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ በመሆን የወንጌላዊነትን መንፈስ ማዳበር ትችላለህ። ባለፈው ዓመት 6,957,852 የሚያህሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በ236 አገሮች ‘የወንጌል ሰባኪነቱን ተግባር’ አከናውነዋል።—2 ጢሞ. 4:5

“እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል”

3, 4. ኢየሱስ በሰማይ ትቶት የመጣው ነገር ምንድን ነው? እኛስ የእሱ ተከታዮች ለመሆን ምን ማድረግ አለብን?

3 ኢየሱስ በምድር የተሰጠውን ሥራ ለመፈጸም በሰማይ የነበረውን ሕይወትና ክብሩን በመተው “የባሪያን መልክ ይዞ . . . ራሱን ባዶ አደረገ።” (ፊልጵ. 2:7) የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል የምናደርገው ማንኛውም ነገር ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ ካደረገው ጋር ሊወዳደር አይችልም። ይሁን እንጂ በሰይጣን ዓለም ውስጥ የነበሩንን ነገሮች በቁጭት መለስ ብለን ባለመመልከት የእሱ ተከታዮች በመሆን መጽናት እንችላለን።—1 ዮሐ. 5:19

4 በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን “እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል” ብሎት ነበር። (ማቴ. 19:27) ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ እንድርያስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን እንዲከተሉት ግብዣ ሲያቀርብላቸው መረባቸውን ትተው ወዲያው ተከተሉት። ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን ትተው አገልግሎቱን ዋነኛ ተግባራቸው አደረጉት። የሉቃስ የወንጌል ዘገባ እንደሚገልጸው፣ ጴጥሮስ “እነሆ፤ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” ብሎታል። (ሉቃስ 18:28) አብዛኞቻችን ኢየሱስን ለመከተል ስንል “ያለንን ሁሉ” መተው አላስፈለገንም። ይሁን እንጂ የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆንና ይሖዋን በሙሉ ልባችን ለማገልገል ‘ራሳችንን መካድ’ አስፈልጎናል። (ማቴ. 16:24) እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰዳችን የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶልናል። (ማቴዎስ 19:29ን አንብብ።) የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል የወንጌላዊነት መንፈስ የምናንጸባርቅ ከሆነ በተለይ ደግሞ አንድ ሰው ወደ አምላክና ውድ ወደሆነው ልጁ እንዲቀርብ በመርዳት ረገድ አነስተኛ አስተዋጽኦ እንኳ ካበረከትን ደስተኞች እንሆናለን።

5. በሌላ አገር የሚኖሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲማሩ ምን እርምጃ ለመውሰድ ሊነሳሱ እንደሚችሉ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

5 የወርቅ ማዕድን በማውጣት ሥራ ላይ የተሰማራ ቫልሚር የተባለ ብራዚላዊ በማዕከላዊ ሱሪናም ይኖር ነበር። ይህ ሰው የአልኮል ሱሰኛ ከመሆኑም በላይ በሥነ ምግባር የተበላሸ ሕይወት ይመራ ነበር። በአንድ ወቅት፣ ከተማ ውስጥ እያለ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑት ጀመር። ቫልሚር በየቀኑ ያጠና የነበረ ሲሆን በሕይወቱ ውስጥ በርካታ ለውጦችን አደረገ፤ ብዙም ሳይቆይ ራሱን ወስኖ ተጠመቀ። ሥራው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር እንደሚያስቸግረው ሲመለከት አትራፊ የሆነውን ሥራውን ተወ፤ ከዚያም ቤተሰቡ መንፈሳዊ ሀብት እንዲያገኝ ለመርዳት ሲል ወደ ብራዚል ተመለሰ። እንደ ቫልሚር ሁሉ በሌላ አገር የሚኖሩ በርካታ ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲማሩ ዘመዶቻቸውንና ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ሲሉ በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ያላቸውን ሥራ ትተው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ። እንደነዚህ ያሉት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እውነተኛ የወንጌላዊነት መንፈስ እያሳዩ ነው።

6. የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመሄድ ሁኔታችን የማይፈቅድልን ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?

6 በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ሄደው ለማገልገል ችለዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ከአገራቸው ውጭ ሄደው ያገለግላሉ። እያንዳንዳችን እንዲህ ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ አንችል ይሆናል፤ ያም ሆኖ ምንጊዜም በአገልግሎት የአቅማችንን ያህል በመሥራት የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን።

ይሖዋ አስፈላጊውን ሥልጠና ይሰጣል

7. የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን የማገልገል ችሎታቸውን ለማሻሻል የሚፈልጉ ሰዎችን ለማሠልጠን የሚረዱ የትኞቹ ትምህርት ቤቶች አሉ?

7 ኢየሱስ ከአባቱ ሥልጠና እንዳገኘ ሁሉ እኛም በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ ካዘጋጀልን ሥልጠና ተጠቃሚዎች መሆን እንችላለን። ኢየሱስ ራሱ “በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 6:45፤ ኢሳ. 54:13) በዛሬው ጊዜ ብቁ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንድንሆን ለመርዳት ሲባል የተዘጋጁ ትምህርት ቤቶች አሉ። ሁላችንም በጉባኤያችን በሚሰጠው በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንደተጠቀምን ምንም ጥርጥር የለውም። አቅኚዎች፣ በአቅኚዎች የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመካፈል መብት አላቸው። ለረጅም ዓመታት በዚህ የአገልግሎት መስክ ሲካፈሉ የቆዩ በርካታ አቅኚዎች በትምህርት ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ የመካፈል መብት አግኝተዋል። ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ደግሞ የማስተማር ችሎታቸውን ለማሻሻልና የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ይበልጥ በተሻለ መንገድ ለማገልገል እንዲችሉ በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ተካፍለዋል። በርካታ ያላገቡ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ ሌሎችን መርዳት እንዲችሉ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ሥልጠና አግኝተዋል። እንዲሁም በውጭ አገር ሚስዮናዊ ሆነው የሚያገለግሉት በርካታ ወንድሞችና እህቶች በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሠልጥነዋል።

8. አንዳንድ ወንድሞች ይሖዋ ከሚሰጠው ሥልጠና ለመጠቀም ሲሉ ምን መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ሆነዋል?

8 በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ለመካፈል ሲሉ ማስተካከያዎችን አድርገዋል። ዩጉ የተባለ ወንድም በካናዳ በሚካሄደው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል ሲል አሠሪውን ፈቃድ ጠየቀ፤ ሆኖም አሠሪው ስላልፈቀደለት ዩጉ ሥራውን ለቀቀ። ዩጉ ስላደረገው ውሳኔ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ፈጽሞ አልቆጭም፤ እንዲያውም ፈቃድ ቢሰጠኝ ኖሮ መሥሪያ ቤቱ ውለታ እንደዋለልኝ በመቁጠር ከድርጅቱ ምንጊዜም እንዳልለቅ ይጠበቅብኝ ነበር። አሁን ግን ይሖዋ የሚሰጠኝን ማንኛውም የአገልግሎት መብት ለመቀበል ሁኔታዬ የተመቻቸ ነው።” ብዙዎች አምላክ ከሚሰጠው ማሠልጠኛ ለመጠቀም ሲሉ በአንድ ወቅት ከፍ አድርገው ይመለከቱት የነበረውን ነገር መሥዋዕት አድርገዋል።—ሉቃስ 5:28

9. ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርትና ትጋት የተሞላበት ጥረት ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

9 ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርትና ትጋት የተሞላበት ጥረት ሰዎች አስገራሚ ለውጥ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) በጓቲማላ የሚኖረውን የሳውሎን ሁኔታ እንመልከት። ሳውሎ ሲወለድ ጀምሮ የተወሰነ የአእምሮ ችግር ነበረበት፤ ከአስተማሪዎቹ አንዷ ለእናቱ፣ ልጁ ማንበብ እንዲችል ልታስገድደው ብትሞክር እሱን ከማስጨነቅ ሌላ የሚፈይደው ነገር ስለማይኖር እንዲህ ማድረግ እንደሌለባት ነገረቻት። በመሆኑም ሳውሎ ማንበብ ሳይችል ከትምህርት ቤት ወጣ። ያም ሆኖ ግን አንድ የይሖዋ ምሥክር፣ ማንበብና መጻፍ መማር (እንግሊዝኛ) በተባለው ብሮሹር በመጠቀም ሳውሎን ማንበብ አስተማረው። ከጊዜ በኋላ ሳውሎ እድገት አድርጎ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ ክፍል ማቅረብ ጀመረ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሳውሎ እናት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል የልጇን አስተማሪ አገኘቻት። አስተማሪዋም ሳውሎ ማንበብ እንደቻለ ስትሰማ በቀጣዩ ሳምንት ሳውሎን ይዛው እንድትመጣ እናቱን ጠየቀቻት። በቀጣዩ ሳምንት አስተማሪዋ ሳውሎን ስታገኘው “ምንድን ነው የምታስተምረኝ?” አለችው። ሳውሎም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ አንድ አንቀጽ ያነብላት ጀመር። አስተማሪዋም “እኔ አላምንም፤ እያስተማርከኝ እኮ ነው!” በማለት ከተናገረች በኋላ እንባዋን መቆጣጠር አቅቷት ሳውሎን አቀፈችው።

የሰዎችን ልብ የሚነካ ትምህርት

10. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር የሚረዳ ምን ግሩም መሣሪያ ተዘጋጅቶልናል?

10 የኢየሱስ ትምህርት፣ ይሖዋ በቀጥታ ባስተማረውና በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው መመሪያ ላይ የተመሠረተ ነበር። (ሉቃስ 4:16-21፤ ዮሐ. 8:28) እኛም የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ በማድረግና በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተመሥርተን በማስተማር የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። በመሆኑም የሁላችንም ንግግርም ሆነ አስተሳሰብ ተመሳሳይ ነው፤ ይህ ደግሞ ለአንድነታችን አስተዋጽኦ ያደርጋል። (1 ቆሮ. 1:10) “ታማኝና ልባም ባሪያ” በምናስተምረው ትምህርት አንድነት እንዲኖረንና የወንጌላዊነት ሥራችንን ለማከናወን እንድንችል የሚረዱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ስለሚያዘጋጅልን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም፤ 28:19, 20) ከእነዚህ ጽሑፎች አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በ179 ቋንቋዎች ይገኛል።

11. በኢትዮጵያ የምትገኝ አንዲት እህት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ያጋጠማትን ተቃውሞ የተቋቋመችው እንዴት ነው?

11 የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ በመጠቀም ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናት የተቃዋሚዎችን ልብ እንኳ ሊለውጥ ይችላል። በኢትዮጵያ የምትገኘው ሉላ የተባለች አቅኚ በአንድ ወቅት አንዲትን ሴት መጽሐፍ ቅዱስን እያስጠናች እያለ የጥናቷ ዘመድ በድንገት በሩን በርግዳ በመግባት ማጥናት እንደሌለባቸው ተናገረች። ሉላም፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 15 ላይ በሚገኘው ስለ ሐሰት ገንዘብ በሚገልጸው ምሳሌ በመጠቀም የጥናቷን ዘመድ በእርጋታ አነጋገረቻት። በዚህ ጊዜ ሴትየዋ የተረጋጋች ሲሆን ጥናታቸውን እንዲቀጥሉም ፈቀደችላት። እንዲያውም በቀጣዩ ጥናታቸው ላይ የተገኘች ሲሆን ገንዘብ ከፍላም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንደምትፈልግ ገለጸች! ብዙም ሳይቆይ በሳምንት ሦስት ጊዜ ማጥናት የጀመረች ከመሆኑም በላይ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አደረገች።

12. ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ማስተማር እንደሚችሉ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናገር።

12 ልጆችም ቢሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ሌሎችን መርዳት ይችላሉ። በሃዋይ የሚገኘው የ11 ዓመቱ ኪአኑ ትምህርት ቤት ሆኖ ይህንን መጽሐፍ ሲያነብ አብሮት የሚማር ልጅ “በዓላትን የማታከብረው ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው። ኪአኑ፣ በመጽሐፉ ተጨማሪ ክፍል ላይ ከሚገኘው “በዓላትን ማክበር ይኖርብናል?” ከሚለው ርዕስ መልሱን በቀጥታ አነበበለት። ከዚያም የመጽሐፉን ርዕስ ማውጫ በማሳየት የልጁን ትኩረት የሚስበው የትኛው ትምህርት እንደሆነ ጠየቀው። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። የይሖዋ ምሥክሮች ባለፈው የአገልግሎት ዓመት 6,561,426 የሚያህሉ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኑ ሲሆን አብዛኞቹም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ተጠቅመዋል። አንተስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጠናት በዚህ መጽሐፍ እየተጠቀምክ ነው?

13. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው በምን መንገድ ነው?

13 የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅሞ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማስጠናት የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በኖርዌይ የሚገኙ ልዩ አቅኚ የሆኑ ባልና ሚስት ከዛምቢያ ከመጣ አንድ ቤተሰብ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። ከዛምቢያ የመጡት ባልና ሚስት ሦስት ሴቶች ልጆች ስላሏቸው ሌላ ልጅ መውለድ አይፈልጉም ነበር። በመሆኑም ሴትየዋ ስታረግዝ ጽንሱን ለማስወረድ ወሰኑ። ስለ ጉዳዩ ከሐኪም ጋር ከመነጋገራቸው ከጥቂት ቀናት በፊት “አምላክ ለሕይወት ያለው ዓይነት አመለካከት አለህ?” የሚለውን ምዕራፍ አጠኑ። ባልና ሚስቱ በምዕራፉ ውስጥ ያለው በማሕፀን ውስጥ የሚገኝን ጽንስ የሚያሳይ ሥዕል ልባቸውን ስለነካው ላለማስወረድ ወሰኑ። ይህ ቤተሰብ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን የቀጠለ ሲሆን ልጃቸው ከተወለደም በኋላ በአስጠኛቸው ስም ሰየሙት።

14. ከምናስተምረው ትምህርት ጋር በሚስማማ መልኩ መኖር ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

14 ከኢየሱስ የማስተማር ዘዴዎች መካከል ጎላ ብሎ የሚታየው አንዱ ገጽታ ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖሩ ነው። በዚህ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉትን የይሖዋ ምሥክሮችን መልካም ምግባር ብዙ ሰዎች ያደንቃሉ። በኒው ዚላንድ የሚገኝ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ ሰው ከመኪናው ውስጥ ቦርሳው ተሰረቀ። ይህንን ሁኔታ ለፖሊስ ሲያሳውቅ ፖሊሱ “ንብረትህ ሊመለስልህ የሚችለው የይሖዋ ምሥክሮች ካገኙት ብቻ ነው” አለው። አንዲት ጋዜጣ የምታደርስ የይሖዋ ምሥክር ቦርሳውን አገኘችውና ለሰውየው ነገረችው። የቦርሳው ባለቤት፣ ይህች እህት ቦርሳውን እንዳገኘችው ሲያውቅ ወደ ቤቷ ሄደ። ሰውየው በጣም የሚፈልገውን መረጃ በማግኘቱ በጣም ተደሰተ። እህትም “የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ንብረትህን መልሼልሃለሁ” አለችው። ነጋዴው፣ የዚያን ዕለት ጠዋት ፖሊሱ የነገረውን በማስታወስ በጣም ተደነቀ። ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው እውነተኛ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ትምህርቶች መሠረት የሚኖሩ ከመሆኑም በላይ የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ።—ዕብ. 13:18

ለሰዎች ባለን አመለካከት ረገድ ኢየሱስን መምሰል

15, 16. ሰዎች በምንሰብከው መልእክት እንዲሳቡ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ ለሰዎች የነበረው አመለካከት ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ ያደርጋቸው ነበር። ለአብነት ያህል፣ ፍቅሩና ትሕትናው ተራ የሆኑ ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ አድርጓል። ወደ እሱ ለሚመጡት ሰዎች ርኅራኄ ያሳያቸው ከመሆኑም በላይ በደግነት አጽናንቷቸዋል፤ ብዙዎችንም ፈውሷል። (ማርቆስ 2:1-5ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ እኛ ተአምር ማድረግ አንችልም፤ ሆኖም ሰዎችን ወደ እውነት የሚስቧቸውን እንደ ፍቅር፣ ትሕትና እንዲሁም ርኅራኄ ያሉትን ባሕርያት ማሳየት እንችላለን።

16 ታሪዋ የተባለች ልዩ አቅኚ በደቡብ ፓስፊክ ርቀው ከሚገኙት የኪሪባቲ ደሴቶች በአንዱ ላይ የሚኖሩትን ቢሬ የተባሉ አረጋዊ ቤት ባንኳኳችበት ወቅት ያጋጠማት ሁኔታ ርኅራኄ ማሳየት የሚያስገኘውን ውጤት ያጎላል። እኚህ አረጋዊ ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ቢናገሩም ታሪዋ የተወሰነ የአካላቸውን ክፍል ማንቀሳቀስ እንደማይችሉ ስትመለከት አዘነችላቸው። “አምላክ ለታመሙ ሰዎችና ለአረጋውያን ምን ተስፋ እንደሰጠ ሰምተው ያውቃሉ?” ብላ ጠየቀቻቸው። ከዚያም በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የሚገኝ ጥቅስ አነበበችላቸው። (ኢሳይያስ 35:5, 6ን አንብብ።) አረጋዊው በሰሙት ነገር በመደነቅ እንዲህ ብለዋል:- “ለብዙ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ያነበብኩ ከመሆኔም በላይ የሃይማኖቴ አባል የሆነ ሚስዮናዊ እየመጣ ይጠይቀኛል፤ ሆኖም ይህን ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይቼው አላውቅም።” ቢሬ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመሩ ሲሆን ጥሩ መንፈሳዊ እድገትም አደረጉ። እኚህ አረጋዊ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ቢኖርባቸውም በአሁኑ ጊዜ ተጠምቀው በመላው የደሴቲቱ ክፍል ምሥራቹን ለመስበክ በእግራቸው መጓዝ የቻሉ ሲሆን ቅድሚያውን ወስደው አንድን ገለልተኛ ቡድን ይረዳሉ።

የክርስቶስን ምሳሌ መከተላችሁን ቀጥሉ

17, 18. (ሀ) ውጤታማ ወንጌላዊ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) አገልግሎታቸውን በቁም ነገር የሚመለከቱ ሰዎች ምን ያገኛሉ?

17 በአገልግሎቱ የተገኙ በርካታ አስደሳች ተሞክሮዎች እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ ያሳያቸውን ባሕርያት ካዳበርንና እነዚህን ባሕርያት በሕይወታችን ውስጥ የምናንጸባርቅ ከሆነ እኛም ውጤታማ ወንጌላውያን መሆን እንችላለን። እንግዲያው ቀናተኛ ወንጌላውያን በመሆን የክርስቶስን ምሳሌ መከተላችን እንዴት የተገባ ነው!

18 አንዳንዶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሲሆኑ ጴጥሮስ “ታዲያ ምን እናገኝ ይሆን?” በማለት ጠይቆ ነበር። ኢየሱስም እንዲህ በማለት መለሰለት:- “ስለ ስሜ ብሎ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን፣ ልጆችን ወይም ዕርሻን የሚተው ሁሉ መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።” (ማቴ. 19:27-29) እኛም የታላቁን ሚስዮናዊ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ መከተላችንን ከቀጠልን የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት በሕይወታችን ሲፈጸም እንመለከታለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋ ወንጌላዊ እንድንሆን የሚያሠለጥነን እንዴት ነው?

• የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ በአገልግሎታችን ውጤታማ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

• ለሰዎች ባለን አመለካከት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ እንድርያስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን እንዲከተሉት ሲጠራቸው ወዲያውኑ ተከትለውታል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት” እንደተባለው መጽሐፍ ያሉ ጽሑፎች በማስተማር ሥራችን አንድነት እንዲኖረን ይረዱናል