በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎችን የምትመለከቱት በይሖዋ ዓይን ነው?

ሌሎችን የምትመለከቱት በይሖዋ ዓይን ነው?

ሌሎችን የምትመለከቱት በይሖዋ ዓይን ነው?

“በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው።” —1 ቆሮ. 12:25

1. ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንፈሳዊው ገነት ስትገባ ምን ተሰምቶህ ነበር?

በክፋት ከተሞላው ከዚህ ዓለም ወጥተን ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መሰብሰብ ስንጀምር በመካከላቸው ያለውን የሞቀ ፍቅርና አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩትን አሳቢነት በመመልከታችን ተደስተን ነበር። እነዚህ ሰዎች በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ካሉት አስቸጋሪ፣ በጥላቻ የተሞሉና ጠበኛ የሆኑ ሰዎች ምንኛ የተለዩ ናቸው! ሰላም ወደሰፈነበትና አንድነት ያላቸው ሰዎች ወደሚገኙበት መንፈሳዊ ገነት መጥተናል።—ኢሳ. 48:17, 18፤ 60:18፤ 65:25

2. (ሀ) ለሌሎች ባለን አመለካከት ላይ ምን ነገር ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል? (ለ) እኛስ በዚህ ረገድ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

2 ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ካለብን አለፍጽምና የተነሳ ለወንድሞቻችን የተሳሳተ አመለካከት ማዳበር ልንጀምር እንችላለን። ፍጹማን አለመሆናችን ወንድሞቻችን ባሏቸው ግሩም የሆኑ መንፈሳዊ ባሕርያት ላይ ከማተኮር ይልቅ ስህተቶቻቸውን አጋነን እንድንመለከት ሊያደርገን ይችላል። በአጭር አነጋገር፣ ወንድሞቻችንን በይሖዋ ዓይን መመልከት እንዳለብን እንድንዘነጋ ያደርገናል። እንዲህ ያለ ችግር ካለብን ራሳችንን መመርመርና አስተሳሰባችንን ከይሖዋ አመለካከት ጋር ማስማማት ይኖርብናል።—ዘፀ. 33:13

ይሖዋ ወንድሞቻችንን የሚመለከታቸው እንዴት ነው?

3. መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያን ጉባኤን ከምን ጋር ያመሳስለዋል?

3 በ1 ቆሮንቶስ 12:2-26 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ “ብዙ ብልቶች” ካሉት አንድ አካል ጋር አመሳስሎታል። አንዱ የአካል ክፍል ከሌላው እንደሚለይ ሁሉ የጉባኤው አባላትም በባሕርያቸውም ሆነ በችሎታቸው ይለያያሉ። ያም ሆኖ ይሖዋ ሁሉንም የጉባኤ አባላት የተቀበላቸው ከመሆኑም በላይ እያንዳንዳቸውን ይወዳቸዋል እንዲሁም ያደንቃቸዋል። ጳውሎስም የጉባኤው አባላት “እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ” መክሯል። የሌሎች ባሕርይ ከእኛ ስለሚለይ ይህን ማድረጉ ቀላል ላይሆን ይችላል።

4. ለወንድሞቻችን ባለን አመለካከት ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

4 በወንድሞቻችን ድክመቶች ላይ የማተኮር ዝንባሌ ይኖረን ይሆናል። እንዲህ ያለ ዝንባሌ መያዝ በአንድ ሥዕል የተወሰነ ክፍል ላይ ብቻ የማተኮር ያህል ነው። ይሖዋ ግን ሥዕሉን ሙሉ በሙሉ ይመለከተዋል። ምናልባትም እኛ በአንድ ግለሰብ ጉድለት ላይ ማተኮር ይቀናን ይሆናል፤ ይሖዋ ግን ግለሰቡ ያሉትን ግሩም ባሕርያት ጨምሮ አጠቃላይ ማንነቱን ይመለከታል። ይሖዋን ለመምሰል ይበልጥ በጣርን መጠን በጉባኤ ውስጥ ፍቅርና አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ እናደርጋለን።—ኤፌ. 4:1-3፤ 5:1, 2

5. በሌሎች ላይ መፍረድ ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ብዙውን ጊዜ በሌሎች ላይ የመፍረድ ዝንባሌ እንዳላቸው ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። በመሆኑም “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ መፍረድ ተዉ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ማቴ. 7:1 NW) እዚህ ላይ ኢየሱስ “አትፍረዱ” ሳይሆን “መፍረድ ተዉ” እንዳለ ልብ በል። ኢየሱስ ከአድማጮቹ መካከል ብዙዎቹ ሌሎችን የመንቀፍ ልማድ እንደተጠናወታቸው ያውቅ ነበር። እኛስ እንዲህ ያለ ልማድ ይኖረን ይሆን? ሌሎችን የመንቀፍ ልማድ ካለን በእኛም ላይ ስለሚያስፈርድብን ይህን ዝንባሌ ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። ደግሞስ ይሖዋ በኃላፊነት ባስቀመጠው ሰው ላይ የምንፈርደው ወይም ይህ ሰው የጉባኤው አባል መሆን የለበትም ብለን የምንወስነው እኛ ማን ነን? አንድ ወንድም የተወሰኑ ድክመቶች ይኖሩበት ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ እስከተቀበለው ድረስ እኛ ይህን ለማድረግ እምቢተኛ መሆናችን ተገቢ ነው? (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚመራና ማስተካከያ መደረግ ካለበት እሱ በወሰነው ጊዜ እርምጃ እንደሚወስድ በእርግጥ እምነት አለን?ሮሜ 14:1-4ን አንብብ።

6. ይሖዋ አገልጋዮቹን እንዴት ይመለከታቸዋል?

6 ይሖዋ እያንዳንዱ ክርስቲያን በአዲሱ ዓለም ውስጥ ፍጽምና ደረጃ ላይ ሲደርስ ምን ዓይነት ሰው ሊሆን እንደሚችል የማወቅ አስደናቂ ችሎታ አለው። በተጨማሪም ያደረጉትን መንፈሳዊ እድገት ያውቃል። በመሆኑም በድክመቶቻቸው ላይ አያተኩርም። መዝሙር 103:12 “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ” ይላል። እኛም ለዚህ እጅግ አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል!—መዝ. 130:3

7. ይሖዋ ለዳዊት ከነበረው አመለካከት ምን እንማራለን?

7 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በአንድ ሰው መልካም ጎን ላይ ትኩረት የማድረግ አስደናቂ ችሎታ እንዳለው የሚጠቁሙ ሐሳቦችን ይዟል። አምላክ ዳዊትን አስመልክቶ ሲናገር ‘ባሪያዬ ዳዊት፣ በፊቴ መልካም ነገር በማድረግ ብቻ ትእዛዜን ጠብቋል፣ በፍጹም ልቡም ተከትሎኛል’ ብሏል። (1 ነገ. 14:8) እርግጥ ነው፣ ዳዊት ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት እንዳሉ እናውቃለን። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ዳዊት ልቡ ቅን መሆኑን ያውቅ ስለነበረ በመልካም ባሕርያቱ ላይ አተኩሯል።—1 ዜና 29:17

ወንድሞቻችሁን በይሖዋ ዓይን ተመልከቱ

8, 9. (ሀ) ይሖዋን መምሰል የምንችለው በምን መንገድ ነው? (ለ) ይህን እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል? ከዚህስ ምን እንማራለን?

8 ይሖዋ የሰዎችን ልብ ማንበብ የሚችል ሲሆን እኛ ግን እንዲህ የማድረግ ችሎታ የለንም። ይህ ብቻ እንኳ በሌሎች ላይ ላለመፍረድ በቂ ምክንያት ይሆነናል። ሰዎች አንድን ነገር እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸውን ውስጣዊ ስሜት ሙሉ በሙሉ አናውቅም። ስለዚህ ከጊዜ በኋላ በሚወገደው በሰዎች አለፍጽምና ላይ ትኩረት ባለማድረግ ይሖዋን ለመምሰል መጣር ይገባናል። በዚህ ረገድ ይሖዋን ለመኮረጅ ግብ ማውጣትህ ጥሩ አይመስልህም? እንዲህ ማድረጋችን ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል።—ኤፌ. 4:23, 24

9 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አሸንዳው የወላለቀ፣ መስኮቶቹ የተሰባበሩና ጣሪያው የሚያንጠባጥብ አንድ ያረጀ ቤት አለ እንበል። ይህን ቤት የሚመለከቱ በርካታ ሰዎች ‘ቤቱ ሲያዩት ደስ ስለማይል መፍረስ አለበት’ ብለው ሊደመድሙ ይችላሉ። ይሁንና ከዚህ ፍጹም የተለየ አመለካከት ያለው አንድ ሰው ቤቱን ያየው ይሆናል። ይህ ሰው ላይ ላዩን ከሚታዩት ችግሮች አልፎ በመመልከት ቤቱ ጠንካራ ተደርጎ የተሠራ እንደሆነና ሊጠገን እንደሚችል ይገነዘብ ይሆናል። በመሆኑም ይህ ሰው ቤቱን ገዝቶ አንዳንድ የጥገና ሥራዎችን በማካሄድ ላይ ላዩን የሚታዩትን ችግሮች ሊያስወግድና ማራኪ ሊያደርገው ይችላል። ከዚያም በቤቱ አቅራቢያ የሚያልፉ ሰዎች ‘እንዴት የሚያምር ቤት ነው’ ይሉ ይሆናል። እኛስ ቤቱን ለመጠገን ብርቱ ጥረት እንዳደረገው ሰው መሆን እንችላለን? ላይ ላዩን በሚታዩት የወንድሞቻችን ጉድለቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ያሏቸውን መልካም ባሕርያት መመልከትና ተጨማሪ መንፈሳዊ እድገት ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገንዘብ እንችል ይሆን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እኛም ልክ እንደ ይሖዋ ወንድሞቻችንን ባላቸው መንፈሳዊ ውበት እንወዳቸዋለን።ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።

10. በፊልጵስዩስ 2:3, 4 ላይ ያለው ምክር ምን እንድናደርግ ይረዳናል?

10 ሐዋርያው ጳውሎስ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን የሚረዱ አንዳንድ ምክሮችን ሰጥቶናል። ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል አበረታቷቸዋል:- “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።” (ፊልጵ. 2:3, 4) ትሕትና ለሌሎች ተገቢ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። በተጨማሪም ለሌሎች አሳቢነት ማሳየታችንና መልካም ጎናቸውን ማየታችን ይሖዋ ለእነሱ ያለው ዓይነት አመለካከት መያዝ እንድንችል ይረዳናል።

11. በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ ምን ሁኔታ ይታያል?

11 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ዙሪያ እየታየ ያለው ለውጥ ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዲዘዋወሩ ምክንያት ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ከተሞች ውስጥ ከተለያየ አካባቢ የመጡ ሰዎች ይኖራሉ። እኛ ወዳለንበት አካባቢ ከመጡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመቀበል አብረውን ይሖዋን ማምለክ ጀምረዋል። እነዚህ ሰዎች “ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋ” የተውጣጡ ናቸው። (ራእይ 7:9) በመሆኑም በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ሰዎች ይገኛሉ።

12. አንዳችን ለሌላው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? አንዳንድ ጊዜ ተገቢ አመለካከት መያዝ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

12 በመሆኑም በጉባኤያችን ውስጥ አንዳችን ለሌላው ተገቢ አመለካከት እንዲኖረን ጥረት ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል። ይህ ደግሞ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለወንድሞቻችሁ ቅን [“ግብዝነት የሌለበት፣” የ1954 ትርጉም] ፍቅር ይኑራችሁ” እንዲሁም ‘እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ’ በማለት የሰጠውን ምክር በቁም ነገር እንድንመለከት ያደርገናል። (1 ጴጥ. 1:22) ከተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ ሰዎች እውነተኛ ፍቅር ማዳበር ከባድ ሊሆን ይችላል። የእምነት አጋሮቻችን ያላቸው ባሕል፣ የትምህርትና የኑሮ ደረጃ እንዲሁም ዘር ከእኛ የተለየ ሊሆን ይችላል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል የአንዳንዶቹን አስተሳሰብ ወይም ነገሮችን የሚያዩበትን መንገድ መረዳት አስቸጋሪ ሆኖብሃል? እነሱም ስለ አንተ እንደዚሁ ሊሰማቸው ይችላል። ያም ሆኖ ሁላችንም “ለመላው የወንድማማች ኅብረት ፍቅር ይኑራችሁ” የሚል ትእዛዝ ተሰጥቶናል።—1 ጴጥ. 2:17 NW

13. በአስተሳሰባችን ላይ ምን ዓይነት ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል?

13 ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ለማስፋት በአስተሳሰባችን ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 6:12, 13ን አንብብ።) “ለሌሎች ጭፍን ጥላቻ የለኝም። ግን . . . ” በማለት አንድ ዓይነት ብሔር ያላቸው ሰዎች ተለይተው ይታወቁበታል ብለህ የምታስበውን መጥፎ ባሕርይ ትጠቅሳለህ? እንዲህ ብለን መናገራችን በውስጣችን ጭፍን ጥላቻ እንዳለና ይህን ባሕርይ ማስወገድ እንዳለብን ይጠቁማል። ምናልባትም ራሳችንን ‘ከእኔ የተለየ ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር ለመቀራረብ ሁልጊዜ ጥረት አደርጋለሁ?’ ብለን መጠየቅ እንችላለን። በዚህ መንገድ ራሳችንን መመርመራችን በዓለም ዙሪያ ላሉት ወንድሞቻችን ባለን ፍቅርና አክብሮት ረገድ አንዳንድ ማሻሻያዎችን እንድናደርግ ይረዳናል። 

14, 15. (ሀ) ለሌሎች ሰዎች ያላቸውን አመለካከት ያስተካከሉ ሰዎችን ምሳሌ ጥቀስ። (ለ) እነሱን መምሰል የምንችለውስ እንዴት ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ አመለካከታቸውን በማስተካከል ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ይጠቅሳል፤ ከእነዚህ መካከል ሐዋርያው ጴጥሮስ አንዱ ነው። ጴጥሮስ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን ወደ አሕዛብ ቤት አይገባም ነበር። በመሆኑም ያልተገረዘ አሕዛብ ወደነበረው ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት እንዲሄድ ሲነገረው ምን ተሰምቶት እንደሚሆን ገምት! ይሁንና ጴጥሮስ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የክርስቲያን ጉባኤ አባል እንዲሆኑ የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ስለተረዳ በአመለካከቱ ላይ ማስተካከያ አድርጓል። (ሥራ 10:9-35) በኋላ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው ሳውልም ቢሆን በውስጡ ያለውን ጭፍን ጥላቻ ማስወገድ አስፈልጎት ነበር። ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ካለው ከፍተኛ ጥላቻ የተነሳ ‘ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ያሳድድና ለማጥፋት ይጥር እንደነበር’ ሳይሸሽግ ተናግሯል። ያም ሆኖ ጌታ ኢየሱስ ማስተካከያ እንዲያደርግ ሲነግረው ከፍተኛ ለውጦችን ያደረገ ከመሆኑም በላይ በፊት ሲያሳድዳቸው ከነበሩት ክርስቲያኖች ሳይቀር መመሪያዎችን ተቀብሏል።—ገላ. 1:13-20

15 እኛም በይሖዋ መንፈስ እርዳታ በአመለካከታችን ላይ ለውጥ ማድረግ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም። በውስጣችን ትንሽም ቢሆን ሰዎችን በጭፍን የመጥላት ዝንባሌ እንዳለ ከተረዳን ከሥሩ ነቅለን ለማውጣትና “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ” መትጋት ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:3-6) መጽሐፍ ቅዱስ ‘በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን እንድንለብስ’ ያበረታታል።—ቈላ. 3:14

በአገልግሎታችን ይሖዋን መምሰል

16. ሰዎችን በተመለከተ የአምላክ ዓላማ ምንድን ነው?

16 ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ “ለማንም አያደላም” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 2:11) ይሖዋ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲያመልኩት ዓላማው ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4ን አንብብ።) ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ‘ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የዘላለም ወንጌል’ እንዲሰበክ ዝግጅት አድርጓል። (ራእይ 14:6) ኢየሱስ ‘እርሻው ዓለም እንደሆነ’ ተናግሯል። (ማቴ. 13:38) ይህ ለአንተም ሆነ ለቅርብ ዘመዶችህ ምን ትርጉም አለው?

17. ሁሉንም ዓይነት ሰዎች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

17 የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ለማካፈል ሁላችንም ራቅ ወዳሉ ቦታዎች መሄድ አንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ መልእክቱን በአካባቢያችን ለሚኖሩ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለመጡ ሰዎች ማዳረስ እንችላለን። በተደጋጋሚ ጊዜ ለሰበክንላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለመመሥከር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ንቁዎች ነን? ምሥራቹ በሚገባ ላልደረሳቸው ሰዎች የመስበክ ግብ ለምን አታወጣም?—ሮሜ 15:20, 21

18. ኢየሱስ ለሰዎች ምን ዓይነት አሳቢነት አሳይቷል?

18 ኢየሱስ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች የመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ይሰብክ የነበረው በተወሰነ አካባቢ ብቻ አልነበረም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ኢየሱስ ‘በከተሞችና በመንደሮች [ሁሉ] ይዞር’ እንደነበር ይነግረናል። በዚያም ‘ሕዝቡን ባየ ጊዜ ያዘነላቸው’ ከመሆኑም ሌላ እነሱን መርዳት አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።—ማቴ. 9:35-37

19, 20. ይሖዋና ኢየሱስ ለሁሉም ሰዎች ያላቸው ዓይነት የአሳቢነት መንፈስ እንዳለን የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

19 እኛስ ተመሳሳይ ዝንባሌ እንዳለን ልናሳይ የምንችልባቸው መንገዶች ይኖሩ ይሆን? አንዳንዶች በክልላቸው ውስጥ በሚገኙ ብዙም ባልተሠራባቸው አካባቢዎች ለመስበክ ጥረት ያደርጋሉ። ይህም በንግድ ቦታዎች፣ በመናፈሻዎች፣ በአውቶቡስ ፌርማታዎች ወይም በቀላሉ ሊገባባቸው በማይችሉ የመኖሪያ ሕንፃዎች አካባቢ መስበክን ይጨምር ይሆናል። ሌሎች ደግሞ በአካባቢያቸው መኖር የጀመሩ አሊያም ከዚህ ቀደም እምብዛም ምሥክርነቱ ያልደረሳቸውን ከእነሱ የተለየ ጎሳ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት ሲሉ አዲስ ቋንቋ ለመማር ይጥራሉ። እነዚህን ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሰላም ማለታችን እንኳ ስለ ደኅንነታቸው እንደምናስብ እንዲረዱ ሊያደርጋቸው ይችላል። ያለንበት ሁኔታ አዲስ ቋንቋ ለመማር የሚያመች ካልሆነ እንዲህ ለማድረግ የሚጥሩትን ማበረታታት እንችል ይሆን? ከአገራቸው ውጪ ለሚገኙ ሰዎች ለመስበክ ጥረት የሚያደርጉ ወንድሞችና እህቶችን መንቀፍ አሊያም እንዲህ ለማድረግ በተነሳሱበት ዓላማ ላይ ጥያቄ ማንሳት አንፈልግም። ሁሉም ሰው በይሖዋ ዓይን ውድ ነው፤ እኛም ተመሳሳይ አመለካከት እንዲኖረን እንፈልጋለን።—ቈላ. 3:10, 11

20 ሰዎችን በይሖዋ ዓይን መመልከት ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን ላገኘናቸው ሰዎች ሁሉ መስበክን ይጨምራል። አንዳንዶች ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ንጽሕናቸውን የማይጠብቁ አሊያም ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር እንደሚመሩ በግልጽ የሚታይ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ደግነት የጎደለው ድርጊት ቢፈጽሙብንም እንኳ ይህ ስለ ብሔራቸው ወይም ስለ ጎሳቸው የተዛባ አመለካከት እንዲኖረን ምክንያት ሊሆን አይገባም። አንዳንዶች ጳውሎስን ያንገላቱት ቢሆንም፣ እሱ ግን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ብሔር ላላቸው ሰዎች ከመስበክ ወደኋላ አላለም። (ሥራ 14:5-7, 19-22) ጳውሎስ አንዳንድ ግለሰቦች ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡ እምነት ነበረው።

21. ሌሎችን በይሖዋ ዓይን መመልከት ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

21 በአገልግሎታችን ከምናገኛቸው ሰዎች፣ በጉባኤያችን ካሉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም በዓለም አቀፉ የወንድማማች ኅብረት ውስጥ ካሉት የእምነት አጋሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ተገቢውን አመለካከት ወይም የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ አስፈላጊ መሆኑ አሁን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግልጽ ሆኖልናል። የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ባንጸባረቅን መጠን ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። ከዚህም ባሻገር ሌሎች፣ ‘የእጁ ሥራ ለሆኑት ሁሉ’ ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳየውንና ‘የማያዳላውን’ አምላክ ይሖዋን እንዲወዱ ልንረዳቸው እንችላለን።—ኢዮብ 34:19

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ለወንድሞቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን አይገባም?

• ለወንድሞቻችን ባለን አመለካከት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

• ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ኅብረት ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• በአገልግሎት ረገድ ይሖዋ ለሰዎች ያለው አመለካከት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተለየ ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር ይበልጥ መተዋወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምሥራቹን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ የሚረዱህ አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?