በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሚዛናዊነት በሚንጸባረቅበት መንገድ እሺ ባዮች ሁኑ

ሚዛናዊነት በሚንጸባረቅበት መንገድ እሺ ባዮች ሁኑ

ሚዛናዊነት በሚንጸባረቅበት መንገድ እሺ ባዮች ሁኑ

“ገሮች . . . እንዲሆኑ አሳስባቸው።”—ቲቶ 3:1, 2 የ1954 ትርጉም

1, 2. ቅዱሳን መጻሕፍት ገር ስለመሆን ምን ይላሉ? ገር መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባታችን ይሖዋ በጥበቡ ተወዳዳሪ የለውም። እኛም የእሱ ፍጥረታት እንደመሆናችን መጠን በሕይወታችን ውስጥ የምንጠቀምባቸውን መመሪያዎች ለማግኘት ወደ እሱ ዘወር እንላለን። (መዝ. 48:14) ክርስቲያን ደቀ መዝሙር የሆነው ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ [“ገር፣” የ1954 ትርጉም] . . . ናት።”—ያዕ. 3:17

2 ሐዋርያው ጳውሎስም “ገርነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚል ምክር ሰጥቷል። * (ፊልጵ. 4:5) ክርስቶስ ኢየሱስ፣ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እና ጌታ ነው። (ኤፌ. 5:23) ሁላችንም ለክርስቶስ መመሪያ መገዛታችንና ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ እሺ ባዮች መሆናችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

3, 4. (ሀ) እሺ ባዮች በመሆን የምናገኛቸውን ጥቅሞች በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ቀጥለን የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

3 ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ገሮች ወይም እሺ ባዮች ለመሆን ፈቃደኞች ስንሆን እንጠቀማለን። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት:- በብሪታንያ የሽብርተኝነት ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሆነ የተጠረጠሩ ሰዎች ከተደረሰባቸው በኋላ፣ አብዛኞቹ መንገደኞች ቀደም ሲል ወደ አውሮፕላን ይዘው እንዲገቡ ይፈቀድላቸው የነበሩ ነገሮችን እንዳያስገቡ የሚከለክለውን ሕግ ለመታዘዝ ፈቃደኞች ነበሩ። በተመሳሳይም መኪና ስናሽከረክር፣ ለምሳሌ አደባባይ ላይ ስንሆን ሁሉም ሰው አደጋ ሳያጋጥመው መጓዝ እንዲችልና የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር ለሌሎች አሽከርካሪዎች ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን እንገነዘባለን።

4 ለአብዛኞቻችን እሺ ባዮች መሆን ቀላል አይደለም። ይህንን ባሕርይ ለማዳበር እንድንችል ከዚህ ባሕርይ ጋር ስለተያያዙ ሦስት ነጥቦች ይኸውም ስለ ውስጣዊ ግፊታችንና ለሥልጣን ስላለን አመለካከት እንዲሁም እሺ ባዮች መሆን ያለብን እስከ ምን ድረስ እንደሆነ እየተመለከትን እንሄዳለን።

እሺ ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

5. በሙሴ ሕግ ሥር አንድ ባሪያ ከጌታው ጋር መኖሩን እንዲቀጥል የሚገፋፋው ምን ሊሆን ይችላል?

5 ከክርስትና ዘመን በፊት የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ፣ እሺ ባይ እንድንሆን ወይም እንድንገዛ ሊገፋፋን የሚገባውን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያጎላል። በሙሴ ሕግ ሥር፣ ባሪያዎች የነበሩ ዕብራውያን በባርነት ማገልገል በጀመሩ በሰባተኛው ዓመት ወይም በኢዮቤልዩ ዓመት (ከሁለቱ ቀድሞ በደረሰው ጊዜ ማለት ነው) ነፃ ይወጡ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ባሪያ በባርነት ለመቀጠል ሊመርጥ ይችላል። (ዘፀአት 21:5, 6ን አንብብ።) ባሪያው እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያደርግ የሚገፋፋው ምን ሊሆን ይችላል? ይህ ባሪያ አሳቢ በሆነው ጌታው ሥር በባርነት መኖሩን እንዲቀጥል የሚገፋፋው ፍቅር ነው።

6. ፍቅር፣ እሺ ባዮች እንድንሆን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

6 በተመሳሳይም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሕይወታችንን ለእሱ እንድንወስንና ከውሳኔያችን ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንኖር ይገፋፋናል። (ሮሜ 14:7, 8) ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐ. 5:3) ይህ ዓይነቱ ፍቅር ራስ ወዳድ አይደለም። (1 ቆሮ. 13:4, 5) ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነትም ለሰዎች ያለን ፍቅር እሺ ባዮች እንድንሆንና ከራሳችን ይልቅ የእነሱን ፍላጎት እንድናስቀድም ይገፋፋናል። ራስ ወዳድ ከመሆን ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ከግምት እናስገባለን።—ፊልጵ. 2:2, 3

7. እሺ ባዮች መሆን ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ምን ሚና ይጫወታል?

7 በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን ሌሎችን ማሰናከል የለብንም። (ኤፌ. 4:29) በእርግጥም ፍቅር፣ የተለያየ አስተዳደግና ባሕል ያላቸው ሰዎች እድገት አድርገው የይሖዋ አገልጋዮች እንዳይሆኑ እንቅፋት የሚሆንባቸው ምንም ነገር እንዳናደርግ ይገፋፋናል። ይህም አብዛኛውን ጊዜ እሺ ባዮች መሆንን ይጠይቅብናል። ለአብነት ያህል፣ መኳኳያዎችን የመጠቀምና ስቶኪንግ የማድረግ ልማድ ያላቸው ሚስዮናውያን እህቶች እንዲህ ማድረጋቸው ሥነ ምግባራዊ አቋማቸው አጠያያቂ እንዲሆን በሚያደርግበትና ሌሎችን በሚያሰናክልበት አካባቢ በእነዚህ ነገሮች መጠቀም አለብን የሚል ግትር አቋም አይዙም።—1 ቆሮ. 10:31-33

8. ለአምላክ ያለን ፍቅር ራሳችንን ‘ከሁሉ እንደምናንስ’ አድርገን እንድንቆጥር የሚረዳን እንዴት ነው?

8 ለይሖዋ ያለን ፍቅር ኩራትን እንድናስወግድ ይረዳናል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በተከራከሩ ጊዜ ኢየሱስ፣ አንድ ትንሽ ልጅ አቁሞ እንዲህ አላቸው:- “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።” (ሉቃስ 9:48፤ ማር. 9:36) በግለሰብ ደረጃ ‘ከሁሉ እንደምናንስ’ አድርገን ራሳችንን መቁጠር ሊከብደን ይችላል። የወረስነው አለፍጽምና እንዲሁም የኩራት ዝንባሌ ከፍ ብለን ለመታየት እንድንፈልግ ይገፋፋን ይሆናል፤ በሌላ በኩል ግን ትሕትና እሺ ባዮች በመሆን ሌሎችን ከራሳችን እንድናስበልጥ ይረዳናል።—ሮሜ 12:10

9. እሺ ባዮች ለመሆን የእነማንን ሥልጣን መቀበል አለብን?

9 እሺ ባዮች ለመሆን አምላክ የሾማቸውን ሰዎች ሥልጣን መቀበል አለብን። ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነውን የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት ይቀበላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይህን በግልጽ ነግሯቸዋል:- “ነገር ግን ይህን እንድታውቁ እወዳለሁ፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው።”—1 ቆሮ. 11:3

10. እሺ ባዮች በመሆን ለይሖዋ ሥልጣን መገዛታችን ምን ያሳያል?

10 እሺ ባዮች በመሆን ለአምላክ ሥልጣን መገዛታችን እሱ አፍቃሪ አባታችን እንደሆነ አድርገን እንደምንተማመንበት ያሳያል። ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚፈጸሙትን ነገሮች በሙሉ ስለሚያውቅ የሚገባንን ሽልማት ሊሰጠን ይችላል። ይህን ማወቃችን ደግሞ ሌሎች አክብሮት በጎደለው መንገድ ሲይዙን ወይም በጣም ተቆጥተው ንዴታቸውን ሲገልጹ መብቴ ካልተከበረ ብለን ግትር አቋም እንዳንይዝ ይረዳናል። ጳውሎስ “ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” በማለት ጽፏል። አክሎም የሚከተለውን መመሪያ በመስጠት ይህንን ምክር አጠናክሮታል:- “ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቁጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።”—ሮሜ 12:18, 19

11. ለክርስቶስ የራስነት ሥልጣን እንደምንገዛ እንዴት ማሳየት እንችላለን?

11 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አምላክ የሾማቸውን ወንድሞች ማክበር አለብን። በራእይ ምዕራፍ 1 ላይ ክርስቶስ ኢየሱስ በቀኝ እጁ የጉባኤውን “ከዋክብት” እንደያዘ ተገልጿል። (ራእይ 1:16, 20) በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ “ከዋክብት” በጉባኤዎች ውስጥ ያሉትን የሽማግሌዎች አካላት ወይም የበላይ ተመልካቾች ያመለክታሉ። እነዚህ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች ለክርስቶስ አመራር የሚገዙ ከመሆኑም በላይ ኢየሱስ ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት ረገድ የተወውን የደግነት ምሳሌ ይኮርጃሉ። ሁሉም የጉባኤው አባላት ኢየሱስ፣ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያዘጋጅ ለሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ይገዛሉ። (ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም) በዛሬው ጊዜም በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የቀረበልንን ትምህርት ለማጥናትና በተግባር ለማዋል ፈቃደኛ መሆናችን በግለሰብ ደረጃ ለክርስቶስ ራስነት እንደምንገዛ የሚያሳይ ሲሆን ይህ ደግሞ ሰላምና አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ሮሜ 14:13, 19

እሺ ባዮች መሆን ያለብን እስከ ምን ድረስ ነው?

12. እሺ ባይ የማንሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ የምንለው ለምንድን ነው?

12 እሺ ባዮች መሆን ሲባል ግን እምነታችንን እናላላለን ወይም አምላክ የሰጠንን መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ እንላለን ማለት አይደለም። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች፣ በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ሲያዟቸው ምን አቋም ወሰዱ? ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” በማለት በድፍረት ተናግረዋል። (ሥራ 4:18-20፤ 5:28, 29) ዛሬም የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ምሥራቹን መስበካችንን እንድናቆም ሊያስገድዱን ቢሞክሩ፣ ሥራችንን በዘዴ ለማከናወን ሁኔታዎችን እናስተካክላለን እንጂ መስበካችንን አናቆምም። ከቤት ወደ ቤት እንዳንሰብክ እገዳ ቢጣልብንም እንኳ የቤቱን ባለቤቶች ማግኘት የምንችልባቸውን ሌሎች መንገዶች በመፈለግ አምላክ የሰጠንን ተልእኮ በታዛዥነት መወጣታችንን እንቀጥላለን። በተመሳሳይም ‘በሥልጣን ያሉት ሹማምንት’ ስብሰባዎቻችንን ቢያግዱ በትናንሽ ቡድኖች ሆነን በጥበብ እንሰበሰባለን።—ሮሜ 13:1፤ ዕብ. 10:24, 25

13. ኢየሱስ ለባለ ሥልጣናት ስለ መገዛት ምን ብሏል?

13 ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ለባለ ሥልጣናት የመገዛትን አስፈላጊነት ሲያጎላ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው። አንድ ሰው [“አንድ ባለ ሥልጣን፣” NW] አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ።” (ማቴ. 5:40, 41) * እኛም ለሌሎች ያለን አሳቢነትና እነሱን ለመርዳት ያለን ፍላጎት በምሳሌያዊ አነጋገር ዕጥፉን መንገድ እንድንሄድ ይገፋፋናል።—1 ቆሮ. 13:5፤ ቲቶ 3:1, 2

14. እሺ ባይ መሆናችን ከከሃዲዎች ጋር እንድንተባበር ሊያደርገን የማይገባው ለምንድን ነው?

14 ይሁን እንጂ እሺ ባዮች ለመሆን ያለን ፍላጎት ከከሃዲዎች ጋር በመሆን አቋማችንን እንድናላላ ሊያደርገን ፈጽሞ አይገባም። በዚህ ረገድ ግልጽና ጥብቅ አቋም መያዛችን እውነት እንዳይበረዝና የጉባኤው አንድነት እንዳይናጋ ያደርጋል። ጳውሎስ ‘ሐሰተኛ ወንድሞችን’ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለእነዚህ ሰዎች ለአንድ አፍታ እንኳ አልተገዛንላቸውም [“እሺ ብለን አልተገዛንላቸውም፣” NW]፤ ይኸውም፣ የወንጌል እውነት ከእናንተ ጋር ጸንቶ እንዲኖር ነው።” (ገላ. 2:4, 5) በጉባኤ ውስጥ ክህደት ብቅ ቢል እንኳ ለአምላክ ያደሩ ክርስቲያኖች ትክክል የሆነውን ነገር አጥብቀው መደገፋቸውን ይቀጥላሉ።

የበላይ ተመልካቾች እሺ ባዮች መሆን አለባቸው

15. ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ስብሰባ በሚያደርጉበት ጊዜ እሺ ባዮች መሆን የሚችሉት በምን መንገድ ነው?

15 የበላይ ተመልካቾች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚሾሙ ወንድሞች ከሚጠበቁባቸው ብቃቶች አንዱ እሺ ባይ መሆን ነው። ጳውሎስ፣ “ኤጲስ ቆጶስ . . . ገር” ወይም እሺ ባይ ሊሆን እንደሚገባው ጽፏል። (1 ጢሞ. 3:2, 3 የ1954 ትርጉም) በተለይ የተሾሙ ወንዶች በጉባኤ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በሚሰበሰቡበት ጊዜ ይህን ባሕርይ ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት እያንዳንዱ ሽማግሌ ሐሳቡን በግልጽ መናገር ይችላል፤ ይህ ሲባል ግን ሁሉም ሽማግሌዎች የግድ ሐሳብ መስጠት አለባቸው ማለት አይደለም። አንድ ሽማግሌ፣ በውይይቱ ወቅት ሌሎቹ የተሾሙ ወንድሞች ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሲጠቅሱ በሚያዳምጥበት ጊዜ መጀመሪያ ላይ የነበረውን አመለካከት ሊለውጥ ይችላል። በዚህ ጊዜ አንድ የጎለመሰ ሽማግሌ፣ የሌሎችን አመለካከት ለመቀበል አሻፈረኝ በማለት እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ግትር አቋም ከመያዝ ይልቅ እሺ ባይ በመሆን የሌሎችን ሐሳብ ይቀበላል። ሽማግሌዎቹ ውይይታቸውን ሲጀምሩ እርስ በርስ የሚቃረኑ ሐሳቦች ይኖሯቸው ይሆናል፤ ሆኖም ትሑትና እሺ ባይ የሆኑ የበላይ ተመልካቾች በጉዳዩ ላይ መጸለያቸው አንድ ሐሳብ እንዲኖራቸው ያደርጋል።—1 ቆሮ. 1:10፤ ኤፌሶን 4:1-3ን አንብብ።

16. አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ምን ዓይነት መንፈስ ሊያንጸባርቅ ይገባል?

16 አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ቲኦክራሲያዊ ሥርዓትን ለማክበር መጣር አለበት። ለመንጋው እረኛ ሆኖ በሚያገለግልበት ጊዜም እንኳ የእሺ ባይነት መንፈስ ሊያንጸባርቅ የሚገባው ሲሆን ይህም ለሌሎች አሳቢነትና ደግነት እንዲያሳይ ይረዳዋል። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን።”—1 ጴጥ. 5:2

17. ሁሉም የጉባኤው አባላት ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ የእሺ ባይነት መንፈስ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

17 በዕድሜ የገፉ የጉባኤው አባላት፣ ወጣቶች የሚያበረክቱትን ጠቃሚ እርዳታ ሊያደንቁ እንዲሁም እነዚህን ወጣቶች በአክብሮት ሊይዟቸው ይገባል። ወጣቶችም፣ ይሖዋን በማገልገል የበርካታ ዓመታት ልምድ ያካበቱትን አረጋውያን ያከብሯቸዋል። (1 ጢሞ. 5:1, 2) ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ሊሰጧቸው የሚችሉ ብቃት ያላቸው ወንዶችን ለማግኘት የሚጥሩ ሲሆን እነዚህን ወንድሞችም የአምላክን መንጋ እንዲንከባከቡ ያሠለጥኗቸዋል። (2 ጢሞ. 2:1, 2) እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ልብ ሊለው ይገባል:- “ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጕዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም።”—ዕብ. 13:17

በቤተሰብ ውስጥ እሺ ባይ መሆን

18. በቤተሰብ ውስጥ የእሺ ባይነት መንፈስ ማሳየት ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

18 የእሺ ባይነት መንፈስ በቤተሰብ ውስጥም ሊንጸባረቅ ይገባል። (ቈላስይስ 3:18-21ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ያለውን ድርሻ ይገልጻል። አባት፣ የሚስቱ ራስ ከመሆኑም በላይ ልጆቹን በመምራት ረገድ ዋነኛ ኃላፊነት የተሰጠው ለእሱ ነው። ሚስት፣ የባሏን ሥልጣን መቀበል አለባት፤ ልጆችም ታዛዥ ለመሆን መጣር ያለባቸው ሲሆን ይህም ጌታን ደስ ያሰኘዋል። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ተገቢና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እሺ ባይ በመሆን ለቤተሰቡ አንድነትና ሰላም አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ነጥብ ለመረዳት የሚያስችሉ አንዳንድ ምሳሌዎች ይዟል።

19, 20. (ሀ) እሺ ባይ በመሆን ረገድ የዔሊንና የይሖዋን ምሳሌ አወዳድር። (ለ) ወላጆች ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ትምህርቶች ማግኘት ይችላሉ?

19 ሳሙኤል፣ ገና ታናሽ ብላቴና እያለ ዔሊ በእስራኤል ውስጥ ካህን ሆኖ ያገለግል ነበር። የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ግን ‘ይሖዋን የማይፈሩ ምናምንቴዎች ነበሩ።’ ዔሊ፣ ልጆቹ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸማቸውን ጨምሮ ስለሚሠሩት ክፉ ድርጊት ሰምቶ ነበር። ታዲያ ምን አደረገ? ዔሊ፣ ልጆቹ ኃጢአት የፈጸሙት በይሖዋ ላይ ከሆነ ማንም ሊማልድላቸው እንደማይችል ነገራቸው። ሆኖም ዔሊ ለልጆቹ እርማትም ሆነ ተግሣጽ አልሰጣቸውም። በዚህም የተነሳ የዔሊ ልጆች በመጥፎ ድርጊታቸው የቀጠሉበት ሲሆን በመጨረሻም ይሖዋ ሞት እንደሚገባቸው ወሰነ። ዔሊ የልጆቹን መሞት ሲሰማ እሱም ሞተ። መጨረሻቸው እንዴት የሚያሳዝን ነው! በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ዔሊ፣ ልጆቹ በክፉ ድርጊታቸው እንዲቀጥሉ በመፍቀድ ተገቢ ያልሆነ የእሺ ባይነት መንፈስ ማሳየቱ ትክክል አልነበረም።—1 ሳሙ. 2:12-17, 22-25, 34, 35፤ 4:17, 18

20 ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ይሖዋ፣ መላእክት ከሆኑት ልጆቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት እንመልከት። ነቢዩ ሚክያስ፣ ይሖዋ ከመላእክቱ ጋር ስላደረገው ስብሰባ አስደናቂ ራእይ ተመልክቶ ነበር። ይሖዋ፣ ከመላእክቱ መካከል ንጉሥ አክዓብን አታልሎ ይህ ክፉ ንጉሥ እንዲወድቅ ማድረግ የሚችል ማን እንደሆነ ጠየቀ። ከዚያም መንፈሳዊ ልጆቹ ያቀረቧቸውን የተለያዩ ሐሳቦች አዳመጠ። አንድ መልአክ፣ አክዓብን ማታለል እንደሚችል ሲናገር ይሖዋም ይህን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ጠየቀው። ይሖዋ፣ መልአኩ በሰጠው መልስ ስለረካ ያሰበውን እንዲፈጽም ላከው። (1 ነገ. 22:19-23) ሰብዓዊ ቤተሰቦችም እሺ ባይ በመሆን ረገድ ከዚህ ዘገባ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። አንድ ክርስቲያን ባልና አባት፣ የሚስቱን እንዲሁም የልጆቹን ሐሳብና አስተያየት ግምት ውስጥ ማስገባቱ ተገቢ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሚስቶችና ልጆች ሐሳባቸውን ወይም የሚፈልጉትን ነገር ከገለጹ በኋላ ቅዱሳን መጻሕፍት የመወሰን መብት የሰጡት አካል የሚያወጣውን መመሪያ በማክበር ረገድ እሺ ባዮች መሆን አለባቸው።

21. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

21 ይሖዋ፣ እሺ ባዮች እንድንሆን ለሚሰጠን ፍቅርና ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ማሳሰቢያዎች ምንኛ አመስጋኞች ነን! (መዝ. 119:99) ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እሺ ባዮች መሆን በትዳር ውስጥ ደስታ ለማግኘት አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት ቃል በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በአብዛኛው ‘ገርነት’ ተብሎ ተተርጉሟል። ሆኖም አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “[ቃሉ] አንድ ሰው መብቱን ለመተው እንዲሁም ለሌሎች አሳቢነትና ደግነት ለማሳየት ፈቃደኛ መሆኑን የሚያጠቃልል ሐሳብ ይዟል።” በመሆኑም ይህ ቃል፣ እሺ ባይ እና ምክንያታዊ መሆንን እንዲሁም መብቴ ካልተከበረ ብሎ ድርቅ ከማለት መቆጠብን ወይም ሕጉ ላይ የሠፈረውን ብቻ ይዞ ሙጭጭ አለማለትን ያመለክታል። ገርነት፣ በሥልጣን ላይ ላሉት መገዛትንም ይጨምራል።

^ አን.13 በየካቲት 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 23-26 ላይ የወጣውን “አንድ ባለ ሥልጣን አንድ ነገር እንድታደርግ ቢያስገድድህስ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• እሺ ባይ መሆን ምን መልካም ውጤት ያስገኛል?

• የበላይ ተመልካቾች የእሺ ባይነት መንፈስ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

• በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ እሺ ባይ መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች፣ ሌሎችን በደግነት በመያዝ ረገድ የክርስቶስን ምሳሌ ይከተላሉ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጉባኤ ሽማግሌዎች ስብሰባ በሚያደርጉበት ጊዜ በጉዳዩ ላይ መጸለያቸውና እሺ ባዮች መሆናቸው አንድ ሐሳብ እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ ያደርጋል