በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትዳራችሁ ተደሰቱ

በትዳራችሁ ተደሰቱ

በትዳራችሁ ተደሰቱ

“ቤት በጥበብ ይሠራል፤ በማስተዋልም ይጸናል።”—ምሳሌ 24:3

1. አምላክ፣ ከመጀመሪያው ሰው ጋር በተያያዘ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ የወሰደው እንዴት ነበር?

ጥበበኛ የሆነው በሰማይ የሚኖረው አባታችን ለእኛ የሚበጀንን ያውቃል። ለአብነት ያህል፣ አምላክ ዓላማው እንዲፈጸም በዔድን ገነት ውስጥ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም” እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። በዚህ የአምላክ ዓላማ ውስጥ ከተካተቱት ነገሮች ዋነኛው ደግሞ ባልና ሚስት ልጆች ወልደው ‘ምድርን እንዲሞሉ’ ነበር።—ዘፍ. 1:28፤ 2:18

2. ይሖዋ ለሰው ልጆች ጥቅም ሲል ምን ዝግጅት አድርጓል?

2 ይሖዋ፣ ለአዳም “የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” አለ። ከዚያም የመጀመሪያውን ሰው ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው ካደረገ በኋላ ፍጹም ከሆነው የአዳም አካል አንዲት የጎድን አጥንት ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራት። ይሖዋ፣ ሔዋን የተባለችውን ይህችን ፍጹም ሴት ወደ አዳም ሲያመጣት አዳም እንዲህ አለ:- “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።” በእርግጥም ሔዋን ለአዳም ተስማሚ ረዳት ነበረች። ሁለቱም የየራሳቸው ልዩ ባሕርያት ቢኖሯቸውም በአምላክ አምሳል የተፈጠሩ ፍጹም ሰዎች ነበሩ። በዚህ መንገድ ይሖዋ የመጀመሪያውን ጋብቻ የመሠረተ ሲሆን አዳምና ሔዋንም እርስ በርስ ለመረዳዳትና ለመደጋገፍ የሚያስችላቸውን ይህን መለኮታዊ ዝግጅት መቀበል አልከበዳቸውም።—ዘፍ. 1:27፤ 2:21-23

3. ብዙዎች የአምላክ ስጦታ የሆነውን ጋብቻን እንዴት ይመለከቱታል? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

3 የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የዓመጸኝነት መንፈስ ተስፋፍቷል። ሆኖም ይህ ዓይነቱ መንፈስ ያስከተላቸው ችግሮች መንስኤ አምላክ አይደለም። በርካታ ሰዎች የአምላክ ስጦታ የሆነውን ጋብቻ ጊዜ እንዳለፈበት እንዲሁም የብስጭት ወይም የግጭት መንስኤ እንደሆነ አድርገው በመቁጠር ያቃልሉታል። ትዳር የሚመሠርቱ ብዙ ሰዎች መፋታታቸው የተለመደ ነገር ሆኗል። ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅር አያሳዩአቸው ይሆናል፤ ከዚህም በላይ ባልና ሚስት በመካከላቸው ግጭት በሚነሳበት ጊዜ ሁኔታዎችን ለራሳቸው በሚመች መንገድ ለማስኬድ ሲሉ በልጆቻቸው ይጠቀሙ ይሆናል። በርካታ ወላጆች በቤታቸው ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲኖር ለማድረግ ሲሉ እንኳ እሺ ባዮች ለመሆን ፈቃደኞች አይደሉም። (2 ጢሞ. 3:3) ታዲያ በዚህ አስጨናቂ ዘመን በትዳር ውስጥ ደስታን ጠብቆ መኖር የሚቻለው እንዴት ነው? እሺ ባይ መሆንና ለይሖዋ መመሪያ ሙሉ በሙሉ መገዛት ትዳር እንዳይፈርስ የሚረዳው እንዴት ነው? በዘመናችን በትዳራቸው ደስተኛ ከሆኑ ሰዎች ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?

ለይሖዋ መመሪያ ሙሉ በሙሉ መገዛት

4. (ሀ) ጳውሎስ ስለ ትዳር ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) ታዛዥ የሆኑ ክርስቲያኖች የጳውሎስን መመሪያ የሚከተሉት እንዴት ነው?

4 ክርስቲያን የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች እንደገና ለማግባት ከመረጡ “በጌታ” ብቻ እንዲያገቡ በመንፈስ አነሳሽነት ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 7:39) ይህ ደግሞ ቀደም ሲል የአይሁድ ሃይማኖት ተከታይ ለነበሩ ክርስቲያኖች አዲስ ሐሳብ አልነበረም። አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ፣ በአካባቢያቸው ከነበሩት አረማዊ ብሔራት ጋር ‘እንዳይጋቡ’ በግልጽ የሚከለክል ነበር። ይሖዋ ይህንን መለኮታዊ መመሪያ ችላ ማለት የሚያስከትለውን አደጋ ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- ‘[እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች] እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ያደርጓቸዋል፤ ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላይህ ነዶ፣ ፈጥኖ ያጠፋሃል።’ (ዘዳ. 7:3, 4) የትዳር ጓደኛ በመምረጥ ረገድ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ካሉት አገልጋዮቹ ምን ይጠብቃል? አንድ የአምላክ አገልጋይ የትዳር ጓደኛ እንዲሆነው የሚመርጠው ሰው “በጌታ” ብቻ መሆን እንደሚገባው ግልጽ ነው፤ ይህም ሲባል ራሱን ለአምላክ ወስኖ የተጠመቀ የአምላክ አገልጋይ ሊሆን ይገባል ማለት ነው። የትዳር ጓደኛን በመምረጥ ረገድ ለይሖዋ መመሪያ ሙሉ በሙሉ መገዛት የጥበብ አካሄድ ነው።

5. ይሖዋ የጋብቻን ቃለ መሐላ እንዴት ይመለከተዋል? የተጋቡ ሰዎችስ የገቡትን ቃል እንዴት ሊመለከቱት ይገባል?

5 የጋብቻ ቃለ መሐላ በአምላክ ዓይን ቅዱስ ነው። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ፣ ስለ መጀመሪያው ጋብቻ ሲናገር “እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው” ብሏል። (ማቴ. 19:6) መዝሙራዊው፣ ስእለት ወይም ቃለ መሐላ ምን ያህል ክብደት ሊሰጠው እንደሚገባ ሲያሳስብ “ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት አቅርብ፤ ለልዑልም ስእለትህን ስጥ” ብሏል። (መዝ. 50:14) የተጋቡ ሰዎች በትዳራቸው ውስጥ ከፍተኛ ደስታ ሊያገኙ ቢችሉም በሠርጋቸው ዕለት የገቡትን ቃል አክብደው ሊመለከቱትና ኃላፊነት የሚያስከትል መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል።—ዘዳ. 23:21

6. ከዮፍታሔ ምሳሌ ምን መማር እንችላለን?

6 በ12ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በእስራኤል መስፍን የነበረውን የዮፍታሔን ሁኔታ እንመልከት። ለይሖዋ እንዲህ በማለት ተስሎ ነበር:- “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፣ አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።” ዮፍታሔ፣ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ሲመለስ ልትቀበለው የወጣችው አንድ ልጁ መሆኗን ሲመለከት ስእለቱን ለማፍረስ አስቦ ይሆን? በፍጹም። “ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለእግዚአብሔር ተስያለሁ” በማለት ተናግሯል። (መሳ. 11:30, 31, 35) ዮፍታሔ ለይሖዋ የተሳለውን ስእለት መፈጸሙ ወራሽ የሚሆነው ዘር እንዳይኖረው የሚያደርግ ቢሆንም ቃሉን ጠብቋል። የዮፍታሔ ስእለት ከጋብቻ ቃለ መሐላ የተለየ ቢሆንም ስእለቱን መፈጸሙ፣ ክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች የገቡትን ቃለ መሐላ መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው።

ትዳር የተሳካ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?

7. አዲስ ተጋቢዎች ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?

7 በርካታ ባለትዳሮች በመጠናናት ስላሳለፉት ጊዜ አስደሳች ትዝታ አላቸው። የወደፊት የትዳር ጓደኛቸውን ማወቅ እንዴት አስደሳች ነበር! አብረው ብዙ ጊዜ ማሳለፋቸው ይበልጥ እንዲቀራረቡ አድርጓቸው ነበር። ይሁን እንጂ ለተወሰነ ጊዜ ከተጠናኑ በኋላ የተጋቡትም ሆኑ የትዳር ጓደኛቸውን ሌሎች ሰዎች የመረጡላቸው ባልና ሚስት፣ ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ማስተካከያዎች ማድረግ አስፈልጓቸዋል። አንድ ባል እንዲህ ይላል:- “በትዳራችን መጀመሪያ ላይ የነበረን ዋናው ችግር የነጠላነት ሕይወታችን ማብቃቱን አለመገንዘባችን ነበር። ከጓደኞቻችንና ከቤተሰቦቻችን ጋር ካለን ወዳጅነት ይልቅ በመካከላችን ላለው ግንኙነት ቅድሚያ መስጠት ለተወሰነ ጊዜ አስቸግሮን ነበር።” በትዳር ውስጥ 30 ዓመታት ያሳለፈ አንድ ባል ደግሞ በትዳሩ መጀመሪያ ላይ፣ ሚዛኑን ለመጠበቅ “ስለ ሁለት ሰዎች ማሰብ” እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። አንድን ግብዣ ከመቀበሉ ወይም አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ከመግባቱ በፊት ሚስቱን አማክሮ የሁለቱንም ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ያደርጋል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እሺ ባይ መሆን ጠቃሚ ነው።—ምሳሌ 13:10

8, 9. (ሀ) በግልጽ መወያየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የሌሎችን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ጠቃሚ የሚሆነው በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ነው? ለምንስ?

8 አንዳንድ ጊዜ የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች በጋብቻ ይጣመራሉ። በተለይ በዚህ ጊዜ በግልጽ መወያየት አስፈላጊ ነው። ሰዎች ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መንገድ የተለያየ ነው። የትዳር ጓደኞቻችሁ ከዘመዶቻቸው ጋር እንዴት እንደሚያወሩ መመልከት እነሱን ይበልጥ ለመረዳት ያስችላችኋል። አንዳንድ ጊዜ የአንድን ሰው ሐሳብ ለማወቅ የሚያስችለው የሚናገረው ነገር ሳይሆን የተናገረበት መንገድ ነው። ግለሰቡ ከሚናገርበት መንገድ ብዙ ለማወቅ እንችላለን። (ምሳሌ 16:24፤ ቈላ. 4:6) በመሆኑም በትዳር ውስጥ ደስታ ለማግኘት አስተዋይ መሆን አስፈላጊ ነው።—ምሳሌ 24:3ን አንብብ።

9 ብዙዎች፣ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችንና መዝናኛዎችን በመምረጥ ረገድ የሌላውን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ከመጋባታችሁ በፊት የትዳር ጓደኛችሁ በስፖርት ወይም በሌሎች መዝናኛዎች ጊዜ ያሳልፍ ይሆናል። ታዲያ አሁን አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልግ ይሆን? (1 ጢሞ. 4:8) ከዘመድ አዝማድ ጋር ስለምታሳልፉት ጊዜም ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። ባልና ሚስት መንፈሳዊ ነገሮችንና ሌሎች ተግባሮችን አብረው ለማከናወን ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው።—ማቴ. 6:33

10. ለይሖዋ መመሪያ መገዛት በወላጆችና ባገቡ ልጆች መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

10 አንድ ወንድ ሲያገባ አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ሚስትም እንዲህ ልታደርግ ይገባል። (ዘፍጥረት 2:24ን አንብብ።) ያም ቢሆን ግን አባትንና እናትን ስለማክበር የተሰጠውን መለኮታዊ መመሪያ አንድ ሰው ካገባም በኋላ ተግባራዊ ሊያደርገው ይገባል። በመሆኑም አንድ ወንድና ሴት ከተጋቡ በኋላም ከወላጆቻቸውና ከአማቾቻቸው ጋር የተወሰነ ጊዜ ያሳልፉ ይሆናል። በትዳር ውስጥ 25 ዓመታት ያሳለፈ አንድ ባል እንዲህ ይላል:- “አንዳንድ ጊዜ የትዳር ጓደኛህን እንዲሁም የአንተንም ሆነ የእሷን ወላጆች ብሎም ወንድሞችና እህቶች ምኞትና ፍላጎት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማሟላት አስቸጋሪ ነው። በዚህ ጊዜ ከሁሉ የተሻለውን አካሄድ ለመወሰን ዘፍጥረት 2:24 ጠቅሞኛል። ለሌሎች የቤተሰቤ አባላት ታማኝ መሆንና ከእነርሱ ጋር በተያያዘ ያሉብኝን ኃላፊነቶች መወጣት ቢኖርብኝም ከሁሉ በላይ ቅድሚያ ልሰጠው የሚገባው ለትዳር ጓደኛዬ ያለኝ ታማኝነት እንደሆነ ይህ ጥቅስ አስገንዝቦኛል።” ለይሖዋ መመሪያ የሚገዙ ክርስቲያን ወላጆችም፣ ትዳር የመሠረቱ ልጆቻቸው የራሳቸው ቤተሰብ እንዳላቸውና ይህን ቤተሰብ የመምራቱ ዋና ኃላፊነት የባል እንደሆነ ይገነዘባሉ።

11, 12. የቤተሰብ ጥናትና ጸሎት ለባለትዳሮች ጠቃሚ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

11 ጥሩ የቤተሰብ ጥናት ልማድ አስፈላጊ ነው። የበርካታ ክርስቲያን ቤተሰቦች ተሞክሮ ይህንን ሐቅ ያረጋግጣል። እንዲህ ያለውን የጥናት ፕሮግራም መጀመርም ሆነ ፕሮግራሙን ዘወትር መከተል ቀላል ላይሆን ይችላል። አንድ የቤተሰብ ራስ እንዲህ ብሏል:- “ወደኋላ ተመልሰን ነገሮችን ማስተካከል ብንችል ኖሮ ትዳር ከመሠረትንበት ጊዜ አንስቶ ሁልጊዜ ጥሩ የቤተሰብ ጥናት ፕሮግራም እንዲኖረን አደርግ ነበር።” አክሎም “እኔና ባለቤቴ አብረን በምናጠናበት ወቅት ያገኘናቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ዕንቁዎች ባለቤቴ በደስታ ስትገልጽ መመልከት ታላቅ ስጦታ ነው” ብሏል።

12 አብሮ መጸለይም ትዳር የተሳካ እንዲሆን ይረዳል። (ሮሜ 12:12) ባልና ሚስት በይሖዋ አምልኮ አንድነት ሲኖራቸው ከአምላክ ጋር የሚኖራቸው የጠበቀ ግንኙነት ትዳራቸውን ያጠናክረዋል። (ያዕ. 4:8) አንድ ክርስቲያን ባል እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ስህተት ስንሠራ ወዲያው ይቅርታ መጠየቅና አብረን በምንጸልይበት ጊዜ ይህንን ስህተት መጥቀስ፣ ቀላል በሆነ ጉዳይም እንኳ የትዳር ጓደኛችንን በማበሳጨታችን ልባዊ ሐዘን እንደተሰማን የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው።”—ኤፌ. 6:18

በትዳር ውስጥ እሺ ባይ መሆን

13. ጳውሎስ በትዳር ውስጥ ስለሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ምን ምክር ሰጥቷል?

13 ያገቡ ክርስቲያኖች ዛሬ ባለው በጾታ ስሜት ያበደ ዓለም ውስጥ የተለመዱ ከሆኑት የትዳር ጓደኛሞችን ግንኙነት ከሚያዋርዱ ድርጊቶች መራቅ ይኖርባቸዋል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጳውሎስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ሁሉ ያድርግላት፤ ሚስትም እንዲሁ ለባሏ የሚገባውን ሁሉ ታድርግለት። ሚስት አካሏ የራስዋ ብቻ አይደለም፤ የባሏም ነው፤ እንዲሁም ባል አካሉ የራሱ ብቻ አይደለም፣ የሚስቱም ነው።” ጳውሎስ አክሎም የሚከተለውን ግልጽ መመሪያ ሰጥቷል:- “በጸሎት ለመትጋት ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር፣ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ።” ሐዋርያው እንዲህ ያለበትን ምክንያት ሲገልጽ “ራሳችሁን ባለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደ ገና አብራችሁ ሁኑ” ብሏል። (1 ቆሮ. 7:3-5) ጳውሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ ጸሎትን መጥቀሱ አንድ ክርስቲያን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ያጎላል። ሆኖም ክርስቲያን የሆኑ ባሎችና ሚስቶች ሁሉ ለትዳር ጓደኛቸው አካላዊና ስሜታዊ ፍላጎቶች አሳቢ መሆን እንዳለባቸውም ግልጽ አድርጓል።

14. በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉት መመሪያዎች በጋብቻ ውስጥ ከሚፈጸመው የጾታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ባልና ሚስት በግልጽ መነጋገር ያለባቸው ከመሆኑም በላይ በጾታ ግንኙነት ረገድ አሳቢነት አለማሳየት ወደ ችግር ሊመራቸው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4ን አንብብ፤ ከማቴዎስ 7:12 ጋር አወዳድር።) ይህ እውነት መሆኑ በሃይማኖት በተከፋፈሉ አንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ታይቷል። አለመግባባቶች ቢፈጠሩ እንኳ ክርስቲያን የሆነው ወገን መልካም ባሕርይ በማሳየት፣ ደግ በመሆን እንዲሁም የትብብር መንፈስ በማንጸባረቅ ብዙውን ጊዜ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ማድረግ ይችላል። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2ን አንብብ።) አንድ ባልና ሚስት ለይሖዋና ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸው ፍቅር እንዲሁም እሺ ባይ መሆናቸው በዚህ ረገድ ይረዳቸዋል።

15. መከባበር፣ ትዳርን አስደሳች በማድረግ ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?

15 ደግ የሆነ ባል በሌሎች ጉዳዮች ረገድም ሚስቱን በአክብሮት ይይዛታል። ለአብነት ያህል፣ በጥቃቅን ጉዳዮችም እንኳ ስሜቷን ግምት ውስጥ ያስገባል። በትዳር ውስጥ 47 ዓመታት ያሳለፈ አንድ ባል “በዚህ ረገድ አሁንም እየተማርኩ ነው” በማለት ተናግሯል። ክርስቲያን ሚስቶችም ባሎቻቸውን በጥልቅ እንዲያከብሩ ተመክረዋል። (ኤፌ. 5:33) ስለ ባሎቻቸው አሉታዊ ነገሮችን የሚያወሩ እንዲሁም በሰዎች ፊት የባሎቻቸውን ስህተት የሚናገሩ ሚስቶች ለባሎቻቸው አክብሮት የላቸውም። ምሳሌ 14:1 “ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ ተላላ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች” ይላል።

ለዲያብሎስ ስፍራ አትስጡት

16. ባልና ሚስት ኤፌሶን 4:26, 27⁠ን በትዳራቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

16 “ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤ በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት።” (ኤፌ. 4:26, 27) ይህን ጥቅስ በሥራ ላይ ስናውለው በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መፍታት ወይም ማስወገድ እንችላለን። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች:- “በመካከላችን አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ፣ ለረጅም ሰዓታት መነጋገር የሚያስፈልገን ቢሆንም እንኳ ሳንነጋገር የቀረንበትን ጊዜ ትዝ አይለኝም።” ይህች እህትና ባለቤቷ ከተጋቡበት ጊዜ ጀምሮ ልዩነቶቻቸውን ሳይፈቱ ላለማደር ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር። እህት እንዲህ ብላለች:- “ችግሩ ምንም ይሁን ምን ይቅር ለመባባልና ጉዳዩን ለመርሳት እንጂ ችግሩን ለቀጣዩ ቀን ላለማሳደር ወስነን ነበር።” በዚህ መንገድ ‘ለዲያብሎስ ስፍራ አልሰጡትም።’

17. ባለትዳሮች፣ በትዳር ጓደኛ ረገድ ጥበብ የጎደለው ምርጫ እንዳደረጉ ቢሰማቸው ምን ሊረዳቸው ይችላል?

17 ይሁን እንጂ በትዳር ጓደኛ ረገድ ጥበብ የጎደለው ምርጫ እንዳደረጋችሁ ቢሰማችሁስ? ትዳራችሁ የሌሎችን ያህል ፍቅር የሞላበት እንዳልሆነ ይሰማችሁ ይሆናል። ያም ቢሆን፣ ፈጣሪ ስለ ጋብቻ ጥምረት ያለውን አመለካከት ማስታወሳችሁ ይረዳችኋል። ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት መክሯቸዋል:- “ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች ሁሉ ላይ ይፈርዳል።” (ዕብ. 13:4) ከዚህም በላይ “በሦስት የተገመደ ገመድም ቶሎ አይበጠስም” የሚለው ጥቅስ ልብ ሊባል ይገባል። (መክ. 4:12) ባልና ሚስት የይሖዋ ስም መቀደስ የሚያሳስባቸው ከሆነ የጋብቻ ጥምረታቸውም ሆነ ከአምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና ይጠናከራል። የትዳር ጓደኛሞች ጋብቻቸው የተሳካ እንዲሆን ጥረት ማድረጋቸው የጋብቻ መሥራች የሆነውን ይሖዋን እንደሚያስከብረው በመገንዘብ ጠንክረው መሥራት አለባቸው።—1 ጴጥ. 3:11

18. ትዳርን በተመለከተ ስለምን ነገር እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?

18 ክርስቲያኖች በትዳራቸው ደስታ ማግኘት እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ደስታ ለማግኘት ግን ጥረት ማድረግ እንዲሁም እንደ እሺ ባይነትና ለይሖዋ መመሪያ ሙሉ በሙሉ መገዛት የመሳሰሉትን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ማሳየት ይኖርባቸዋል። በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ጥንዶች ይህ ሊሆን እንደሚችል ማስረጃ ይሆናሉ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በትዳር ውስጥ ደስታ ማግኘት እንደሚቻል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

• ትዳር የተሳካ እንዲሆን ምን ሊረዳ ይችላል?

• የትዳር ጓደኛሞች የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር አለባቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባልና ሚስት አንድን ግብዣ ከመቀበላቸው ወይም ቀጠሮ ከመያዛቸው በፊት መነጋገራቸው ጥበብ ነው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አለመግባባቶችን ሳታሳድሩ በመፍታት ‘ለዲያብሎስ ስፍራ ላለመስጠት’ ጥረት አድርጉ