በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ለእርዳታ የምናሰማውን ጩኸት ይሰማል

ይሖዋ ለእርዳታ የምናሰማውን ጩኸት ይሰማል

ይሖዋ ለእርዳታ የምናሰማውን ጩኸት ይሰማል

“የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው።”—መዝ. 34:15

1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ፣ በርካታ ሰዎች ምን ይሰማቸዋል? (ለ) ይህስ እምብዛም የማያስደንቀን ለምንድን ነው?

የሚያስጨንቅ ሁኔታ ገጥሞሃል? ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰብህ አንተ ብቻ አይደለህም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ መኖር የሚያስከትልባቸውን ጫና ለመቋቋም በየዕለቱ ትግል ያደርጋሉ። ይህ ለአንዳንዶች ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸዋል። እነዚህ ሰዎች እንደሚከተለው ሲል እንደጻፈው እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ይሰማቸዋል:- “እጅግ ዝያለሁ፤ ፈጽሞም ደቅቄአለሁ፤ ከልቤም መታወክ የተነሣ እጮኻለሁ። ልቤ በኀይል ይመታል፤ ጕልበት ከድቶኛል፤ የዐይኔም ብርሃን ጠፍቶአል።”—መዝ. 38:8, 10

2 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሕይወት በተለያዩ ችግሮች የተሞላ መሆኑ ያን ያህል አያስደንቀንም። እነዚህ ችግሮች ደግሞ የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመው “የምጥ ጣር” ተብሎ የተገለጸው ምልክት ክፍል መሆናቸውን እናውቃለን። (ማር. 13:8፤ ማቴ. 24:3) “የምጥ ጣር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አስጨናቂ ሁኔታዎችን ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም ይህ ሐረግ በዚህ ‘አስጨናቂ’ ጊዜ ውስጥ ሰዎች እየደረሰባቸው ያለው ጭንቀት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚያሳይ ተስማሚ መግለጫ ነው።—2 ጢሞ. 3:1

ይሖዋ ጭንቀታችንን ይረዳልናል

3. የአምላክ ሕዝቦች ምን ነገር ይገነዘባሉ?

3 የይሖዋ ሕዝቦች፣ አስጨናቂ ሁኔታ ሊገጥማቸው አልፎ ተርፎም የከፋ ችግር ሊደርስባቸው እንደሚችል በሚገባ ይገነዘባሉ። በሁሉም የሰው ልጆች ላይ ከሚደርሰው መከራ በተጨማሪ የአምላክ አገልጋዮች በመሆናችን እምነታችንን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳው ‘ጠላታችን ዲያብሎስ’ ጥቃት ይሰነዝርብናል። (1 ጴጥ. 5:8) በመሆኑም “ስድብ ልቤን ጐድቶታል፤ ተስፋዬም ተሟጦአል፤ አስተዛዛኝ ፈለግሁ፤ አላገኘሁምም፤ አጽናኝም ፈለግሁ፤ አንድም አልነበረም” በማለት እንደተናገረው እንደ ዳዊት ሊሰማን ይችላል።—መዝ. 69:20

4. ጭንቀት ሲሰማን ምን ሊያጽናናን ይችላል?

4 ይሁንና ዳዊት እንዲህ ሲል ምንም ዓይነት ተስፋ እንደሌለው መናገሩ ነበር? በፍጹም! መዝሙራዊው የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ልብ በል:- “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ችግረኞችን ይሰማልና፤ በእስራት ያለውንም ሕዝቡን አይንቅም።” (መዝ. 69:33) አንዳንድ ጊዜ ያለብን ጭንቀት እስረኛ እንዳደረገን ያህል ሆኖ ይሰማናል። ሌሎች ያለንበትን ሁኔታ በትክክል እንዳልተረዱልን ሆኖ ሊሰማን ይችላል፤ ወይም ደግሞ በእርግጥም ጭንቀታችንን አልተረዱልን ይሆናል። ይሁን እንጂ ልክ እንደ ዳዊት ይሖዋ የሚሰማንን ጭንቀት ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳልን ማወቃችን ያጽናናናል።—መዝ. 34:15

5. ንጉሥ ሰሎሞን ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?

5 የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ለይሖዋ በተወሰነበት ወቅት አምላክ ጭንቀታችንን እንደሚረዳልን ጎላ አድርጎ ገልጿል። (2 ዜና መዋዕል 6:29-31ን አንብብ።) ሰሎሞን፣ ልቡ ቅን የሆነ ሰው ‘ጭንቀቱንና ሕመሙን’ አስመልክቶ የሚያቀርበውን ጸሎት እንዲሰማ ይሖዋን ተማጽኗል። አምላክ እንደነዚህ ያሉ የተጨነቁ ሰዎች ለሚያቀርቡት ጸሎት ምን ምላሽ ይሰጣል? ሰሎሞን፣ አምላክ ጸሎታቸውን መስማት ብቻ ሳይሆን እነሱን ለመርዳት እርምጃ እንደሚወስድ ያለውን እምነት ገልጿል። ይህን መሰሉ የመተማመን ስሜት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ ‘የሰውን ልብ ያውቃል።’

6. ጭንቀትን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ የምንለውስ ለምንድን ነው?

6 እኛም በተመሳሳይ የሚሰማንን ‘ጭንቀትና ሕመም’ አስመልክተን ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን። ይሖዋ ጭንቀታችንን እንደሚረዳልንና እንደሚያስብልን ማወቃችን ሊያጽናናን ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” በማለት ይህ እውነት መሆኑን አረጋግጧል። (1 ጴጥ. 5:7) ይሖዋ የእኛ ሁኔታ ያሳስበዋል። ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ይሖዋ ለሰዎች ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት ጎላ አድርጎ ገልጿል:- “በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ [“አባታችሁ ሳያውቅ፣” NW] ምድር ላይ አትወድቅም። የራስ ጠጒራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው። ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው።”—ማቴ. 10:29-31

ይሖዋ በሚሰጠው እርዳታ ታመን

7. ምን እርዳታ እንደምናገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል?

7 ጭንቀት ሲያጋጥመን፣ ይሖዋ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ ከመሆኑም ሌላ ችሎታውም እንዳለው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣ በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው” ይላል። (መዝ. 34:15-18፤ 46:1) አምላክ የሚረዳን እንዴት ነው? አንደኛ ቆሮንቶስ 10:13 ምን እንደሚል ተመልከት:- “በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።” ይሖዋ ሁኔታዎቹ እንዲስተካከሉ በማድረግ ጭንቀታችንን ሊያስወግድልን ወይም ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል። በዚያም ሆነ በዚህ ይሖዋ ይረዳናል።

8. አምላክ ከሚሰጠው እርዳታ ተጠቃሚዎች ለመሆን ምን ማድረግ አለብን?

8 ይሖዋ ከሚሰጠው እርዳታ ተጠቃሚዎች ለመሆን ምን ማድረግ አለብን? “የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” የሚል ምክር ተሰጥቶናል። ይህም ሲባል የሚያሳስበንንና የሚያስጨንቀንን ሁሉ ለይሖዋ በኃላፊነት እንሰጠዋለን ማለት ነው። ከዚያም መጨነቃችንን ለማቆም ጥረት ማድረግና ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን በመተማመን እሱን በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል። (ማቴ. 6:25-32) እንዲህ ያለው የመተማመን ስሜት ትሕትና ማሳየትንና በራሳችን ኃይል ወይም ጥበብ ከመታመን መራቅን ይጠይቃል። ራሳችንን በትሕትና ‘ከአምላክ ብርቱ እጅ በታች’ ዝቅ በማድረግ ቦታችንን እንደምናውቅ እናሳያለን። (1 ጴጥሮስ 5:6ን አንብብ።) ይህ ደግሞ አምላክ እንዲሆን የፈቀደው ምንም ይሁን ምን ሁኔታውን መቋቋም እንድንችል ይረዳናል። ካለብን ጭንቀት ወዲያውኑ ለመገላገል ከፍተኛ ፍላጎት ይኖረን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ እኛን ለመርዳት መቼና እንዴት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት እንደሚያውቅ እናምናለን።—መዝ. 54:7፤ ኢሳ. 41:10

9. ዳዊት በይሖዋ ላይ የጣለው ሸክም ምንድን ነው?

9 ዳዊት በመዝሙር 55:22 ላይ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም” እንዳለ አስታውስ። ዳዊት ይህን በጻፈበት ወቅት በጣም ተጨንቆ ነበር። (መዝ. 55:4) ዳዊት መዝሙሩን የጻፈው ልጁ አቤሴሎም ንግሥናውን ለመቀማት ባሴረበት ወቅት ነበር። በጊዜው የዳዊት ታማኝ አማካሪ የነበረው አኪጦፌልም በሴራው ተባብሯል። በመሆኑም ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን ከኢየሩሳሌም መሸሽ ግድ ሆኖበት ነበር። (2 ሳሙ. 15:12-14) ዳዊት በዚህ አስጨናቂ ጊዜም እንኳ በአምላክ ይታመን የነበረ ሲሆን ሁኔታው ተስፋ አላስቆረጠውም።

10. የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

10 ልክ እንደ ዳዊት እኛም ያስጨነቀን ነገር ምንም ይሁን ምን በጸሎት ወደ ይሖዋ መቅረባችን እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠንን ምክር እስቲ እንመልከት። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።) እንዲህ ያለው ከልብ የመነጨ ጸሎት ምን ያስገኝልናል? ‘ከማስተዋል በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም፣ ልባችንንና አሳባችንን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።’

11. ‘የአምላክ ሰላም’ ልባችንንና የማሰብ ችሎታችንን የሚጠብቅልን እንዴት ነው?

11 ጸሎት፣ ያለህበት አስጨናቂ ሁኔታ እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል? ሊለውጠው ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን እኛ ባሰብነው መንገድ ብቻ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባናል። ያም ሆኖ ጸሎት ከልክ በላይ በመጨነቅ ሚዛናችንን እንዳንስት ይረዳናል። አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲገጥሙን ‘የአምላክ ሰላም’ እንድንረጋጋ ያደርገናል። ልክ አንድን ከተማ ከጠላት ጥቃት እንደሚጠብቁ ወታደሮች ‘የአምላክ ሰላምም’ ልባችንንና የማሰብ ችሎታችንን ይጠብቅልናል። በተጨማሪም ያደረብንን የጥርጣሬ መንፈስ፣ ፍርሃትና አሉታዊ አስተሳሰብ እንድናስወግድ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ተቻኩለን ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንዳንወስድ ይጠብቀናል።—መዝ. 145:18

12. አንድ ሰው የእእምሮ ሰላም ሊኖረው የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

12 የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች እያሉብንም የአእምሮ ሰላም ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? በተወሰነ መጠን አሁን ካለንበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል አንድ ምሳሌ ተመልከት። አንድ ሠራተኛ አስቸጋሪ የሆነ አለቃ ይኖረው ይሆናል። ይሁን እንጂ ሠራተኛው ደግና ምክንያታዊ ለሆነው የድርጅቱ ባለቤት ስሜቱን የመግለጽ አጋጣሚ አገኘ። ባለቤቱም ሠራተኛው ያለበትን ችግር እንደተረዳለትና አለቃውም በቅርቡ ከቦታው እንደሚነሳ ገለጸለት። በዚህ ጊዜ ሠራተኛው ምን ይሰማዋል? ይህ ሠራተኛ የድርጅቱ ባለቤት በሰጠው ቃል ላይ እምነት ማሳደሩና በአለቃው ላይ ምን እንደሚደርስበት ማወቁ ለጊዜው አንዳንድ ችግሮችን መቋቋም እንዳለበት ቢገነዘብም በሥራው ለመቀጠል ያደረገውን ውሳኔ ይበልጥ ያጠናክርለታል። በተመሳሳይም ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ እንደሚረዳልንና በቅርቡ ‘የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ እንደሚጣል’ እናውቃለን። (ዮሐ. 12:31) ይህ እንዴት የሚያጽናና ነው!

13. ወደ ይሖዋ ከመጸለይ በተጨማሪ ምን ማድረግ አለብን?

13 ታዲያ ችግራችንን ለይሖዋ በጸሎት መንገራችን ብቻ በቂ ነው? አይደለም። ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግም ይጠበቅብናል። ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉ ሰዎችን ወደ ቤቱ በላከ ጊዜ ዳዊት እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “አምላክ ሆይ፤ ከጠላቶቼ እጅ አድነኝ፤ ሊያጠቁኝ ከሚነሡብኝም ጠብቀኝ። ከክፉ አድራጊዎች ታደገኝ፤ ደም ከተጠሙ ሰዎችም አድነኝ።” (መዝ. 59:1, 2) ዳዊት ጸሎት ከማቅረቡም በተጨማሪ የሚስቱን ምክር በመስማት ሸሽቶ አምልጧል። (1 ሳሙ. 19:11, 12) እኛም በተመሳሳይ፣ የገጠመንን አስጨናቂ ችግር ለመቋቋም አሊያም ያለንበትን ሁኔታ ለማሻሻል የሚረዳንን ጥበብ እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን።—ያዕ. 1:5

ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

14. አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

14 የሚያስጨንቁን ነገሮች ወዲያውኑ አይወገዱልን ይሆናል። እንዲያውም ሁኔታው ለተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ይችላል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ ከሆነ ችግራችንን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ችግሮች እየደረሱብን ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን መቀጠላችን ለእሱ ፍቅር እንዳለን ማሳየታችን መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። (ሥራ 14:22) ሰይጣን ኢዮብን እንደሚከተለው በማለት እንደከሰሰው አትዘንጋ:- “ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን? በእርሱና በቤተ ሰቦቹ፣ ባለው ንብረትስ ሁሉ ዙሪያ ዐጥር ሠርተህለት የለምን? የበጎቹና የላሞቹ መንጋ ምድርን ሁሉ እስኪሞሉ ድረስ የእጁን ሥራ ባርከህለታል። እስቲ፣ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ንካበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።” (ኢዮብ 1:9-11) ኢዮብ በታማኝነት በመጽናት የሰይጣን ክስ መሠረተ ቢስ መሆኑን አረጋግጧል። እኛም የገጠመንን አስጨናቂ ሁኔታ በጽናት በመቋቋም ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን ማጋለጥ እንችላለን። በታማኝነት መጽናታችን ተስፋችን እንዲሁም በይሖዋ ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር ያደርጋል።—ያዕ. 1:4

15. ብርታት ሊሰጡን የሚችሉ ምን ምሳሌዎች አሉን?

15 በሁለተኛ ደረጃ፣ ‘በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችን ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ’ አስታውስ። (1 ጴጥ. 5:9) አዎን፣ ‘በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰብህም።’ (1 ቆሮ. 10:13) በመሆኑም በራስህ ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በሌሎች የሕይወት ተሞክሮ ላይ በማሰላሰል ጥንካሬና ድፍረት ማግኘት ትችላለህ። (1 ተሰ. 1:5-7፤ ዕብ. 12:1) የገጠማቸውን ፈተና በታማኝነት መወጣት የቻሉ በቅርብ የምታውቃቸው ክርስቲያኖች በተዉት ምሳሌ ላይ ጊዜ ወስደህ አሰላስል። አንተ የደረሰብህን ዓይነት ችግር ገጥሟቸው ስለነበሩ ሰዎች የሚያወሱ በጽሑፎች ላይ የወጡ ተሞክሮዎችን ለማንበብ ጥረት አድርገሃል? እንዲህ ማድረግህ ብርታት ይሰጥሃል።

16. የተለያዩ ችግሮች ሲደርሱብን አምላክ ብርታት የሚሰጠን እንዴት ነው?

16 ሦስተኛ፣ ይሖዋ “የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” መሆኑን አትዘንጋ። “እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ [“በመከራ ሁሉ፣” የ1954 ትርጉም] ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።” (2 ቆሮ. 1:3, 4) ይህም አምላክ አሁን በገጠመን ችግር ብቻ ሳይሆን “በመከራችን ሁሉ” ከጎናችን ቆሞ ብርታትና ድጋፍ የሚሰጠን ያህል ነው። ይህ ደግሞ “በመከራ ሁሉ ያሉትን” ለማጽናናት ያስችለናል። ጳውሎስ ይህ እውነት መሆኑን ከራሱ የሕይወት ተሞክሮ ተገንዝቧል።—2 ቆሮ. 4:8, 9፤ 11:23-27

17. መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

17 አራተኛ፣ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅም ለመምከር ይጠቅማል፤ ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።” (2 ጢሞ. 3:16, 17 NW) የአምላክ ቃል ‘ለመልካም ሥራ የታጠቅንና ብቁ’ እንድንሆን ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚገጥሙንን አስጨናቂ ሁኔታዎች እንድንቋቋምም ይረዳናል። ‘በሚገባ የታጠቅን’ እና ‘ሙሉ በሙሉ ብቁ’ እንድንሆን ያስችለናል። ይህ ጥቅስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ‘በሚገባ የታጠቀ’ የሚለው ሐረግ ቃል በቃል ሲተረጎም ‘በሚገባ የተዘጋጀ’ ማለት ነው። ይህ ሐረግ በጥንት ዘመን ለጉዞ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ የጫነን ጀልባ ወይም መሥራት ያለበትን ነገር በተገቢው ሁኔታ ለማከናወን አቅም ያለውን ማሽን ለማመልከት ያገለግል ነበር። በተመሳሳይም ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ማንኛውንም ዓይነት ችግር ለመወጣት እንድንችል የሚያስፈልገንን ሁሉ በመስጠት ያስታጥቀናል። በመሆኑም “አምላክ ከፈቀደ የመጣውን ነገር ሁሉ በእሱ እርዳታ መቋቋም እችላለሁ” እንላለን።

ጭንቀት ከሚያስከትሉብን ነገሮች ሁሉ ነፃ መውጣት

18. በታማኝነት ለመጽናት የሚረዳን በምን ነገር ላይ ትኩረት ማድረጋችን ነው?

18 አምስተኛ፣ ይሖዋ የሰው ልጆችን በቅርቡ ከየትኛውም ዓይነት ጭንቀት ነፃ እንደሚያወጣቸው በሚገልጸው ተስፋ ላይ ምንጊዜም ትኩረት አድርግ። (መዝ. 34:19፤ 37:9-11፤ 2 ጴጥ. 2:9) አምላክ እኛን ለማዳን የሚወስደው እርምጃ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ሲያገኝ፣ የሰው ልጆች አሁን ካሉባቸው ችግሮች ነፃ ከመውጣት የበለጠ ነገር ያገኛሉ። ተስፋቸው ከኢየሱስ ጋር በሰማይ መሆንም ይሁን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚም ይከፈትላቸዋል።

19. መጽናት የሚቻለው እንዴት ነው?

19 እስከዚያው ድረስ ግን ይህ ክፉ ሥርዓት የሚያመጣቸውን አስጨናቂ ሁኔታዎች ችለን መኖራችን ግድ ነው። እነዚህ ችግሮች የማይኖሩበትን ጊዜ እንናፍቃለን! (መዝ. 55:6-8) በታማኝነት መጽናታችን የዲያብሎስን ሐሰተኝነት የሚያጋልጥ መሆኑን አንዘንጋ። ጸሎትና ዓለም አቀፉ የክርስቲያን ወንድማማች ኅብረት ብርታት የሚሰጠን ሲሆን ወንድሞቻችን ተመሳሳይ መከራ እንደሚደርስባቸው ማስታወሳችንም ይጠቅመናል። የአምላክን ቃል በጥሩ ሁኔታ በመጠቀም በሚገባ የታጠቅህና ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆነህ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያደርግልህ ያለህ እምነት እንዲቀንስ ፈጽሞ አትፍቀድ። ‘የአምላክ ዐይኖች ወደ ጻድቃን መሆናቸውንና ጆሮዎቹም ጩኸታቸውን’ እንደሚያዳምጡ አትዘንጋ።—መዝ. 34:15

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ዳዊት አስጨናቂ ሁኔታ በገጠመው ጊዜ ምን ተሰምቶት ነበር?

• ንጉሥ ሰሎሞን ምን ትምክህት እንዳለው ገልጿል?

• ይሖዋ የፈቀደውን ለመቀበል እንድንችል ምን ይረዳናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰሎሞን፣ ይሖዋ የተጨነቁ ሕዝቦቹን እንደሚረዳቸው እርግጠኛ ነበር

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት በጸሎት አማካኝነት ሸክሙን ሁሉ በይሖዋ ላይ የጣለ ሲሆን ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃም ወስዷል