በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?

ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?

ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?

‘አምላክን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ።’—መክ. 12:13

1, 2. የመክብብን መጽሐፍ በመመርመር ምን ጥቅም ልናገኝ እንችላለን?

ሁሉም ነገር የተሟላለት የሚመስል አንድ ሰው በአእምሮህ ለመሳል ሞክር። ግለሰቡ በምድር ላይ ካሉት እጅግ ባለጸጋ ሰዎች አንዱ ከመሆኑም በላይ የታወቀ የአገር መሪ እንዲሁም በዘመኑ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ጥበበኛ ነበር። ይህ ሰው እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቢኖሩትም ‘ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ በአእምሮው ይመላለስ ነበር።

2 የዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት ገደማ እንዲህ ያለ ሰው በምድር ላይ ይኖር ነበር። ይህ ግለሰብ ሰሎሞን የሚባል ሲሆን እርካታ ለማግኘት ስላደረገው ጥረትም በመክብብ መጽሐፍ ላይ ተገልጿል። (መክ. 1:13) ከሰሎሞን ተሞክሮ ብዙ የምንማረው ነገር አለ። በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ሐሳብ እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

‘ነፋስን መከተል’

3. ሕይወታችንን በተመለከተ ሁላችንም የትኛውን እውነታ መቀበል አለብን?

3 ሰሎሞን፣ አምላክ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ውብ ነገሮችን በምድር ላይ እንደፈጠረ ገልጿል፤ እነዚህን ቀልብ የሚስቡና ሕልቆ መሳፍርት የሌላቸው አስደናቂ ነገሮች መቼም ቢሆን አይተን አንጠግባቸውም። ሆኖም ሕይወታችን በጣም አጭር በመሆኑ ስለ አምላክ ፍጥረታት የምናደርገውን ምርምር ገና ሳንጀምረው ሕይወታችን ያበቃል። (መክ. 3:11፤ 8:17) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ዕድሜያችን አጭር ከመሆኑም በላይ በፍጥነት ያልፋል። (ኢዮብ 14:1, 2፤ መክ. 6:12) ይህ እውነታ ሕይወታችንን በጥበብ እንድጠቀምበት ሊገፋፋን ይገባል። ይሁን እንጂ የሰይጣን ዓለም የተሳሳተ አካሄድ እንድንከተል ተጽዕኖ ሊያደርግብን ስለሚችል ሕይወታችንን በጥበብ መምራት ቀላል አይደለም።

4. (ሀ) “ከንቱ” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? (ለ) ብዙዎች በሕይወታቸው ውስጥ የሚከታተሏቸውን የትኞቹን ግቦች እንመለከታለን?

4 ሰሎሞን ሕይወታችንን ጥበብ በጎደለው መንገድ መምራት ያለውን አደጋ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ “ከንቱ” የሚለውን ቃል በመክብብ መጽሐፍ ውስጥ ከ30 ጊዜ በላይ ተጠቅሞበታል። “ከንቱ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ባዶ፣ ፍሬ ቢስ፣ ትርጉም የለሽ፣ ዋጋ ቢስ የሆነ ወይም ዘላቂ ጥቅም የሌለው ነገርን ያመለክታል። (መክ. 1:2, 3) አንዳንድ ጊዜ ሰሎሞን “ከንቱ” የሚለውን ቃል ‘ነፋስን ከመከተል’ ጋር በማመሳሰል ተጠቅሞበታል። (መክ. 1:14፤ 2:11) ነፋስን ለመጨበጥ መሞከር ከንቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። እንዲህ ለማድረግ የሚሞክር ሰው ባዶ እጁን ይቀራል። ከንቱ ግቦችን መከታተልም እንዲሁ ለብስጭት ይዳርጋል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕይወት በጣም አጭር በመሆኑ ባዶ እጃችንን እንድንቀር የሚያደርጉ ግቦችን በመከታተል ሕይወታችንን ማባከኑ ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው። እንዲህ ዓይነት ስህተት እንዳንፈጽም ሰሎሞን ብዙዎች በሕይወታቸው ውስጥ ስለሚከታተሏቸው ግቦች የጠቀሳቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት። በመጀመሪያ ተድላና ሀብት ማሳደድን እናያለን። ከዚያም አምላክን ስለሚያስደስት ሥራ እንመረምራለን።

ተድላን ማሳደድ ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል?

5. ሰሎሞን እርካታ ለማግኘት የሞከረው ከየትኞቹ ነገሮች ነበር?

5 በዛሬው ጊዜ እንደሚገኙ ብዙ ሰዎች ሁሉ ሰሎሞንም ተድላን በማሳደድ እርካታ ለማግኘት ሞክሮ ነበር። “ለልቤም ምድራዊ ደስታን አልነፈግሁትም” ብሏል። (መክ. 2:10) ሰሎሞን ደስታ ለማግኘት የሞከረው ከየትኞቹ ነገሮች ነበር? በመክብብ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተገለጸው ከልኩ ሳያልፍ ‘ራሱን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት’ እንዲሁም አካባቢውን በማሳመር፣ የቤተ መንግሥት ንድፎችን በማውጣት፣ ሙዚቃ በማዳመጥና የሚጣፍጡ ምግቦችን በመመገብ ራሱን ለማስደሰት ሞክሮ ነበር።

6. (ሀ) በሕይወት ውስጥ አስደሳች ነገሮችን ማከናወን ስህተት አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በመዝናኛ ረገድ ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

6 መጽሐፍ ቅዱስ ከጓደኞቻችን ጋር አስደሳች ጊዜ ማሳለፍን ያወግዛል? በፍጹም! ለምሳሌ ሰሎሞን በሥራ የደከመ ሰውነትን ለማሳረፍ ዘና ብሎ ጥሩ ምግብ መመገብ የአምላክ ስጦታ እንደሆነ ገልጿል። (መክብብ 2:24⁠ን እና 3:12, 13ን አንብብ።) ከዚህም በላይ ይሖዋ ራሱ፣ ወጣቶችን ኃላፊነት እንደሚሰማቸው በሚያሳይ መንገድ ‘ደስ እንዲላቸውና ልባቸው ደስ እንዲያሰኛቸው’ አበረታቷቸዋል። (መክ. 11:9) ሁላችንም እረፍትና መዝናኛ ያስፈልገናል። (ከማርቆስ 6:31 ጋር አወዳድር።) ያም ሆኖ ግን የሕይወታችን ዋና ዓላማ መዝናኛ ሊሆን አይገባም። መዝናኛ ከምግብ በኋላ እንደሚበላ ጣፋጭ እንጂ እንደ ዋና ምግብ መታየት አይኖርበትም። ጣፋጭ ነገሮችን የቱንም ያህል ብትወድ ሌላ ነገር የማትበላ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ነገሮች እንደሚሰለቹህና ሰውነትህ በቂ ምግብ እንደማያገኝ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም ሰሎሞን ተድላን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት ‘ነፋስን እንደ መከተል’ መሆኑን ተገንዝቧል።—መክ. 2:10, 11

7. በመዝናኛ ምርጫችን ረገድ ጠንቃቆች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

7 ከዚህም በላይ ጤናማ ያልሆኑ መዝናኛዎች አሉ። እንዲያውም ብዙዎቹ መዝናኛዎች በጣም ጎጂ ናቸው፤ ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሹብንና ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር እንድንፈጽም ሊያደርጉን ይችላሉ። ‘ለመዝናናት’ ሲሉ ዕፅ በመውሰድ፣ የአልኮል መጠጥ ያለ ልክ በመጠጣት ወይም ቁማር በመጫወት ከባድ ችግር ውስጥ የሚገቡ ስንቶች ናቸው? ልባችን ወይም ዓይናችን ጎጂ የሆኑ ነገሮችን እንድናደርግ እንዲገፋፉን ከፈቀድን ድርጊታችን የሚያስከትለውን መዘዝ ማጨዳችን እንደማይቀር ይሖዋ በደግነት አስጠንቅቆናል።—ገላ. 6:7

8. ሕይወታችንን መለስ ብለን መመርመራችን ጥበብ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

8 በተጨማሪም ለተድላ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዳናደርግ እንቅፋት ይሆንብናል። ዕድሜያችን በቶሎ እንደሚያልፍ መዘንጋት የለብንም፤ እንዲሁም በዚህ አጭር ሕይወታችን ሁልጊዜ ጤነኞች እንደምንሆንና ችግሮች እንደማይገጥሙን እርግጠኞች መሆን እንደማንችል አንርሳ። ሰሎሞን፣ ‘ወደ ደስታ ቤት’ ከመሄድ ይልቅ በቀብር ሥነ ሥርዓት (በተለይም ታማኝ በነበረ ክርስቲያን ወንድም ወይም እህት ቀብር) ላይ መገኘት ትልቅ ጥቅም እንዳለው የተናገረው ለዚህ ነው። (መክብብ 7:2, 4ን አንብብ።) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የቀብር ንግግሩን ስናዳምጥና ሕይወቱ ስላለፈው ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የሕይወት ታሪክ ስናስብ የራሳችንን አካሄድ ለመመርመር እንነሳሳ ይሆናል። ይህን ማድረጋችን እኛም ቀሪውን ሕይወታችንን በጥበብ ለመጠቀም ግቦቻችንን ማስተካከል እንዳለብን እንድናስብ ይገፋፋን ይሆናል።—መክ. 12:1

ቁሳዊ ንብረት እርካታ ሊያስገኝልን ይችላል?

9. ሰሎሞን ሀብት ማካበትን በተመለከተ ምን ተገንዝቦ ነበር?

9 ሰሎሞን የመክብብን መጽሐፍ በጻፈበት ጊዜ በምድር ላይ ከነበሩት እጅግ ባለጸጋ ሰዎች አንዱ ነበር። (2 ዜና 9:22) የፈለገውን ሁሉ ለማግኘት የሚያስችል ሀብት ነበረው። “ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም” በማለት ጽፏል። (መክ. 2:10) ያም ሆኖ ግን ቁሳዊ ንብረት በራሱ እርካታ እንደማያስገኝ ተገንዝቧል። በመሆኑም “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል።—መክ. 5:10

10. እውነተኛ እርካታና ብልጽግና የሚያስገኘው ምንድን ነው?

10 ቁሳዊ ሀብት አላፊ ቢሆንም በጣም ማራኪ ሊሆን ይችላል። በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተካሄደ ጥናት ላይ ከአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛ ግባቸው “በጣም ሀብታም መሆን” እንደሆነ ገልጸዋል። ታዲያ እዚህ ግባቸው ላይ ቢደርሱ እንኳ እውነተኛ ደስታ ያገኙ ይሆን? እንዲህ ማለት አይቻልም። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ቦታ መስጠቱ ደስታና እርካታ ለማግኘት እንቅፋት እንደሚሆንበት ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ሰሎሞንም ከረጅም ዘመን በፊት ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሶ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ለራሴም ብርንና ወርቅን፣ የነገሥታትና የአውራጃዎችን ሀብት አካበትሁ፤ . . . ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር።” * (መክ. 2:8, 11) ከዚህ በተቃራኒ ሕይወታችንን ይሖዋን በሙሉ ልብ ለማገልገል ከተጠቀምንበት የእሱን በረከት ስለምናገኝ እውነተኛ ብልጽግና ይኖረናል።—ምሳሌ 10:22ን አንብብ።

እውነተኛ እርካታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ሥራ ነው?

11. ቅዱሳን መጻሕፍት ሥራን በተመለከተ ምን ይላሉ?

11 ኢየሱስ፣ “አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 5:17) ይሖዋና ኢየሱስ በመሥራት እንደሚረኩ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በፍጥረት ሥራው እንደረካ ሲገልጽ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” ብሏል። (ዘፍ. 1:31) መላእክት አምላክ ያከናወነውን ሥራ ሲመለከቱ ‘እልል ብለዋል።’ (ኢዮብ 38:4-7) ሰሎሞንም በተመሳሳይ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት ያለውን ጠቀሜታ ተገንዝቦ ነበር።—መክ. 3:13

12, 13. (ሀ) አንዳንዶች ተግቶ መሥራት የሚያስገኘውን እርካታ የገለጹት እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ ጊዜ ሰብዓዊ ሥራ የሚያበሳጭ ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

12 ብዙዎች ተግቶ መሥራት እርካታ እንደሚያስገኝ ይገነዘባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሆሴ የተባለ የተዋጣለት ሠዓሊ “በአእምሮህ ያሰብከውን ሥዕል በሸራው ላይ ማስፈር ስትችል ረጅም ተራራ የወጣህ ያህል ይሰማሃል” ብሏል። በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ሚጌል * የተባለ ሰው ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “ሥራ፣ ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ስለሚያስችልህ እርካታ ያስገኝልሃል። እንዲሁም ጠቃሚ ተግባር እንዳከናወንክ እንዲሰማህ ያደርግሃል።”

13 በሌላ በኩል ግን በርካታ ሥራዎች አሰልቺ ከመሆናቸውም በላይ የፈጠራ ችሎታችንን ለማዳበር አጋጣሚ አይሰጡንም። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በሥራ ቦታቸው የሚያበሳጭ ሁኔታ ያጋጥማቸው አልፎ ተርፎም ፍትሐዊ ያልሆነ ነገር ይፈጸምባቸው ይሆናል። ሰሎሞን እንደገለጸው ሰነፍ ሰው፣ ምናልባትም በሥልጣን ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ባለው ትውውቅ በመጠቀም ትጉ ሠራተኛ የሆነው ሰው የሚገባውን ዋጋ ይወስድ ይሆናል። (መክ. 2:21) ሰዎች በሥራቸው ቅሬታ እንዲያድርባቸው ወይም እንዲያዝኑ የሚያደርጓቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። መጀመሪያ ላይ በጣም አትራፊ ይመስል የነበረ ንግድ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በማሽቆልቆሉ ወይም ያልተጠበቁ ሁኔታዎች በመከሰታቸው ምክንያት ኪሳራ ሊያስከትል ይችላል። ሰሎሞን እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “እኔም መለስ ብዬ ከፀሐይ በታች ያለውን ሁኔታ ተመለከትኩ፤ ሁልጊዜ ውድድር ለፈጣኖች፣ ውጊያ ለኃያላን፣ እንጀራ ለጥበበኞች፣ ሀብት ለአስተዋዮች፣ ሞገስ ለአዋቂዎች ይሆናል ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል።” (መክብብ 9:11 NW) ብዙውን ጊዜ፣ ስኬታማ ለመሆን ተግቶ የሚሠራው ሰው ‘የሚደክመው ለነፋስ እንደሆነ’ ሲገነዘብ ሊበሳጭና ምሬት ሊያድርበት ይችላል።—መክ. 5:16

14. ምንጊዜም ቢሆን እውነተኛ እርካታ የሚያስገኘው የትኛው ሥራ ነው?

14 ታዲያ ሐዘን የማያስከትል ሥራ ይኖር ይሆን? ቀደም ብሎ የተገለጸው ሆሴ የተባለ ሠዓሊ እንዲህ ብሏል:- “ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ የሥዕል ሥራዎች ሊጠፉ ወይም ሊበላሹ ይችላሉ። በአምላክ አገልግሎት በምናከናውነው ሥራ ረገድ ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አያጋጥምም። ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ይሖዋን በመታዘዜ፣ ሰዎች አምላክን የሚፈሩ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ በመርዳት ዘላቂ ጥቅም ያለው ተግባር ማከናወን ችያለሁ። ይህ ደግሞ በዋጋ ሊተመን የማይችል ነገር ነው!” (1 ቆሮ. 3:9-11) ሚጌልም በተመሳሳይ ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ በሰብዓዊ ሥራው ከሚያገኘው የላቀ እርካታ እንደሚያመጣለት ተናግሯል። “ለአንድ ሰው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነትን አካፍለኸው የነገርከው ነገር ልቡን እንደነካው ስታውቅ የሚሰማህ ደስታ ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር አይችልም” ብሏል።

“እንጀራህን በውሃ ላይ ጣል”

15. ሕይወትን ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?

15 ለማጠቃለል ያህል፣ ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው? በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለንን አጭር ሕይወት፣ መልካም ነገሮችን ለማድረግና ይሖዋን ለማስደሰት ከተጠቀምንበት እውነተኛ እርካታ እናገኛለን። ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና ልናዳብር እንችላለን፤ ለልጆቻችን መንፈሳዊ እሴቶችን ልናወርሳቸው እንችላለን፤ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ልንረዳቸው እንችላለን እንዲሁም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ልንመሠርት እንችላለን። (ገላ. 6:10) እነዚህ ሁሉ ተግባሮች ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኙ ከመሆኑም በላይ እነዚህ ግቦች ላይ መድረስ የቻሉ ሰዎች ይባረካሉ። ሰሎሞን መልካም ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም ለመግለጽ አስገራሚ የሆነ ንጽጽር በመጠቀም እንዲህ ብሏል:- “እንጀራህን በውሃ ላይ ጣል፤ ከብዙ ቀን በኋላ መልሰህ ታገኘዋለህና።” (መክ. 11:1) ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን “ስጡ፤ ይሰጣችኋል” በማለት አሳስቧቸዋል። (ሉቃስ 6:38) ከዚህ በላይ ይሖዋ ራሱ ለሌሎች መልካም የሚያደርጉ ሰዎችን እንደሚባርክ ቃል ገብቷል።—ምሳሌ 19:17፤ ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።

16. ሕይወታችንን እንዴት እንደምንጠቀምበት ለመወሰን ከሁሉ የተሻለው ጊዜ መቼ ነው?

16 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕይወታችንን እንዴት እንደምንጠቀምበት ገና ወጣት እያለን በጥበብ እንድንወስን ይመክረናል። እንዲህ ካደረግን፣ በኋላ ላይ የምንቆጭበት ምክንያት አይኖርም። (መክ. 12:1) ብዙ መሥራት የምንችልበትን የወጣትነት ዕድሜያችንን ዓለም የሚያቀርባቸውን መስህቦች በማሳደድ ካባከነው በኋላ እነዚህ ነገሮች እንደ ነፋስ የማይጨበጡ መሆናቸውን መገንዘብ እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል!

17. ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና ለመምረጥ እንድትችል ምን ሊረዳህ ይችላል?

17 እንደ ማንኛውም አፍቃሪ አባት ሁሉ ይሖዋም በሕይወትህ እንድትደሰትና መልካም ነገሮችን እንድታከናውን እንጂ አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ እንድትገባ አይፈልግም። (መክ. 11:9, 10) ይህን ለማድረግ ምን ሊረዳህ ይችላል? መንፈሳዊ ግቦችን አውጣ፤ እንዲሁም ያወጣሃቸው ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት አድርግ። ከ20 ዓመታት ገደማ በፊት ካቪየር፣ ጥሩ ደመወዝ በሚያስገኝ የሕክምና ሞያ ላይ በመሰማራትና የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን መካከል መምረጥ ነበረበት። ካቪየር እንዲህ ብሏል:- “የሕክምና ሥራ እርካታ የሚያስገኝ ሊሆን ቢችልም ብዙ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ በመርዳቴ ካገኘሁት ደስታ ጋር ሊወዳደር የሚችል ምንም ነገር የለም። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በሕይወቴ ሙሉ በሙሉ እንድደሰት አድርጎኛል። የሚቆጨኝ አንድ ነገር ቢኖር የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ቀደም ብዬ አለመጀመሬ ብቻ ነው።”

18. ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት ትርጉም ያለው ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

18 ታዲያ ጥረት ልናደርግለት የሚገባው ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ዋጋ ያለው ነገር ምንድን ነው? የመክብብ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል።” (መክ. 7:1) ይህን ጥቅስ ለመረዳት ከኢየሱስ ሕይወት የተሻለ ምሳሌ አናገኝም። ኢየሱስ በይሖዋ ዘንድ የላቀ ስም እንዳተረፈ ምንም ጥርጥር የለውም። ታማኝነቱን እንደጠበቀ ሲሞት፣ የአባቱን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ለእኛ መዳን መንገድ የከፈተውን ቤዛዊ መሥዋዕት አቅርቧል። (ማቴ. 20:28) ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው አጭር ሕይወት እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ምን ዓይነት እንደሆነ ግሩም ምሳሌ የተወልን ሲሆን እኛም እሱን ለመኮረጅ እንጥራለን።—1 ቆሮ. 11:1፤ 1 ጴጥ. 2:21

19. ሰሎሞን ምን ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል?

19 እኛም በአምላክ ዘንድ መልካም ስም ማትረፍ እንችላለን። በይሖዋ ፊት ጥሩ ስም ማትረፍ ከሀብት ይበልጥ ዋጋ ያለው ነገር ነው። (ማቴዎስ 6:19-21ን አንብብ።) በይሖዋ ፊት መልካም የሆኑና ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያስችሉ ነገሮችን ለማከናወን በየዕለቱ አጋጣሚ እናገኛለን። ለአብነት ያህል፣ ለሰዎች ምሥራቹን መስበክ እንዲሁም ትዳራችንንና የቤተሰብ ሕይወታችንን ማጠናከር አልፎ ተርፎም በግል ጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች መንፈሳዊነታችንን ማሻሻል እንችላለን። (መክ. 11:6፤ ዕብ. 13:16) አንተስ እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ትፈልጋለህ? ከሆነ “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና” የሚለውን የሰሎሞን ምክር ተከተል።—መክ. 12:13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 የሰሎሞን ዓመታዊ ገቢ 666 መክሊት (ከ22,000 ኪሎ ግራም በላይ) ወርቅ ነበር።—2 ዜና 9:13

^ አን.12 ስሙ ተለውጧል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በሕይወታችን ውስጥ ስለምናወጣቸው ግቦች በቁም ነገር እንድናስብ የሚገፋፋን የትኛው እውነታ ነው?

• ተድላንና ቁሳዊ ሀብትን ስለማሳደድ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

• ዘላቂ እርካታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ሥራ ነው?

• ጥረት ልናደርግለት የሚገባው ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ዋጋ ያለው ነገር ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መዝናኛ በሕይወታችን ውስጥ ምን ቦታ ሊኖረው ይገባል?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስብከቱ ሥራ እርካታ የሚያስገኝ እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?