በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሁሉም ነገሮች የአምላክን መመሪያ ፈልጉ

በሁሉም ነገሮች የአምላክን መመሪያ ፈልጉ

በሁሉም ነገሮች የአምላክን መመሪያ ፈልጉ

“ይህ አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችን ነውና፤ እስከ መጨረሻው የሚመራንም እርሱ ነው።”—መዝ. 48:14

1, 2. በራሳችን ጥበብ ከመታመን ይልቅ የይሖዋን መመሪያ መከተል የሚኖርብን ለምንድን ነው? የትኞቹ ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?

ከንቱ ወይም ጎጂ የሆኑ ነገሮችን ጠቃሚ እንደሆኑ በማሰብ ራሳችንን ማታለል ቀላል ነው። (ምሳሌ 12:11) ለክርስቲያኖች የማይገባ አንድ ነገር የማድረግ ከፍተኛ ምኞት ሲያድርብን ብዙውን ጊዜ ልባችን ያሰብነውን እንድናደርግ የሚገፋፉ አሳማኝ ምክንያቶች ያቀርብልናል። (ኤር. 17:5, 9) በመሆኑም መዝሙራዊው “ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ” ብሎ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ጥበበኛ መሆኑን አሳይቷል። (መዝ. 43:3) መዝሙራዊው ውስን በሆነው በራሱ ጥበብ ሳይሆን በይሖዋ ታምኗል፤ ደግሞም ከይሖዋ የተሻለ መመሪያ ሊሰጠው የሚችል ማንም የለም። እኛም እንደ መዝሙራዊው የአምላክን መመሪያ መፈለጋችን ጠቃሚ ነው።

2 ይሁን እንጂ ከማንም በላይ በይሖዋ መመሪያ የምንታመነው ለምንድን ነው? ይህንን መመሪያ መፈለግ ያለብን መቼ ነው? ከይሖዋ መመሪያ ለመጠቀም ምን ዓይነት አመለካከት ማዳበር አለብን? በዛሬው ጊዜ ይሖዋ መመሪያ የሚሰጠን እንዴት ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ ለእነዚህ አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።

በይሖዋ መመሪያ የምንታመነው ለምንድን ነው?

3-5. በይሖዋ መመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን የሚያደርጉን ምን ምክንያቶች አሉ?

3 ይሖዋ በሰማይ የሚኖር አባታችን ነው። (1 ቆሮ. 8:6) እያንዳንዳችንን በሚገባ የሚያውቀን ከመሆኑም በላይ ልባችንን ማንበብ ይችላል። (1 ሳሙ. 16:7፤ ምሳሌ 21:2) ንጉሥ ዳዊት አምላክን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “አንተ መቀመጤንና መነሣቴን ታውቃለህ፤ የልቤንም ሐሳብ ገና ከሩቁ ታስተውላለህ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ገና ቃል ከአንደበቴ ሳይወጣ፣ እነሆ፤ አንተ ሁሉንም ታውቃለህ።” (መዝ. 139:2, 4) ይሖዋ እኛን በደንብ የሚያውቀን በመሆኑ ለእኛ የተሻለ የሚሆነውን ነገርም እንደሚያውቅ ልንጠራጠር አይገባም። ከዚህም በላይ ይሖዋ በጥበቡ ተወዳዳሪ የለውም። እሱ ሁሉን ነገር የሚያይ ከመሆኑም በላይ ከማንኛውም ሰው ይበልጥ ውስጣችንን ይመለከታል፤ የነገሮችን መጨረሻ ከመጀመሪያው ያውቃል። (ኢሳ. 46:9-11፤ ሮሜ 11:33) “እርሱ ብቻ ጥበበኛ” የሆነ አምላክ ነው።—ሮሜ 16:27

4 ከዚህም በላይ ይሖዋ ይወደናል፤ እንዲሁም ሁልጊዜ የሚጠቅመንን ነገር እንድናገኝ ይፈልጋል። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐ. 4:8) አፍቃሪ አምላክ በመሆኑ ለጋስ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:17) አምላክ እንዲመራቸው የሚፈቅዱ ሁሉ ከልግስናው እጅግ ይጠቀማሉ።

5 በተጨማሪም ይሖዋ ሁሉን ቻይ ነው። በዚህ ረገድ መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ሥር ያድራል። እግዚአብሔርን፣ ‘መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ’ እለዋለሁ።” (መዝ. 91:1, 2) የይሖዋን መመሪያ ስንከተል ፈጽሞ የማያሳፍረንን አምላክ መጠጊያችን እያደረግነው ነው። ተቃውሞ ቢያጋጥመንም እንኳ ይሖዋ ይደግፈናል። እሱ በፍጹም አይተወንም። (መዝ. 71:4, 5፤ ምሳሌ 3:19-26ን አንብብ።) አዎን፣ ይሖዋ ለእኛ የተሻለው ምን እንደሆነ ያውቃል፤ የተሻለ የሆነውን ነገር እንድናገኝም ይፈልጋል፤ እንዲሁም ከሁሉ የተሻለውን ነገር ለእኛ የመስጠት ችሎታ አለው። መመሪያውን ችላ ብንል እንዴት ያለ ሞኝነት ይሆናል! ታዲያ መመሪያው የሚያስፈልገን መቼ ነው?

መመሪያ የሚያስፈልገን መቼ ነው?

6, 7. የይሖዋ መመሪያ የሚያስፈልገን መቼ ነው?

6 ከልጅነታችን ጀምሮ በሕይወታችን ሙሉ የአምላክ መመሪያ እንደሚያስፈልገን ጥርጥር የለውም። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “ይህ አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችን ነውና፤ እስከ መጨረሻው የሚመራንም እርሱ ነው።” (መዝ. 48:14) ልክ እንደ መዝሙራዊው ሁሉ ጥበበኛ ክርስቲያኖችም ምንጊዜም የአምላክን መመሪያ ከመፈለግ ወደኋላ አይሉም።

7 እርግጥ ነው፣ አፋጣኝ እርዳታ እንደሚያስፈልገን የሚሰማን ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ በስደት፣ በከባድ ሕመም ወይም ድንገት ሥራችንን በማጣታችን ምክንያት “ጭንቅ ውስጥ” እንገባ ይሆናል። (መዝ. 69:16, 17) በእነዚህ ጊዜያት ይሖዋ መጽናት እንድንችል እንደሚያጠናክረንና ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎች እንድናደርግ እንደሚመራን በመተማመን ወደ እሱ ዘወር ማለታችን ያጽናናናል። (መዝሙር 102:17ን አንብብ።) ይሁን እንጂ በሌሎች ጊዜያትም የእሱ እርዳታ ያስፈልገናል። ለአብነት ያህል፣ ለሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ስንሰብክ ውጤታማ ለመሆን የይሖዋ መመሪያ ያስፈልገናል። ከዚህም በላይ መዝናኛን፣ አለባበስንና አጋጌጥን፣ የጓደኛ ምርጫን፣ ሥራን፣ ትምህርትን ወይም ሌላ ማንኛውንም ነገር በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ በሚኖርብን ጊዜ የይሖዋን መመሪያ መከተል ጥበብ ያለበት አካሄድ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች የይሖዋ መመሪያ ያስፈልገናል።

የአምላክን መመሪያ አለመፈለግ የሚያስከትላቸው አደጋዎች

8. ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ መብላቷ ምን አንድምታ ነበረው?

8 የይሖዋን መመሪያ ለመከተል ግን እኛ ፈቃደኞች መሆን እንደሚያስፈልገን አስታውስ። እኛ የአምላክን መመሪያ ለመከተል ካልፈለግን እሱ እንዲህ እንድናደርግ አያስገድደንም። የይሖዋን መመሪያ ላለመከተል የመረጠችው የመጀመሪያዋ ሰብዓዊ ፍጡር ሔዋን ስትሆን የእሷም ምሳሌ መጥፎ ውሳኔ ማድረግ የሚያስከትለው መዘዝ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል። ሔዋን የወሰደችው እርምጃ ምን አንድምታ እንደነበረውም አስብ። ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ የበላችው “መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር [መሆን]” ስለፈለገች ነበር። (ዘፍ. 3:5) እንዲህ በማድረጓ የአምላክን ቦታ መውሰድ እንደምትፈልግ አሳይታለች፤ ይህም መልካምና ክፉ የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ የይሖዋን መመሪያ ከመከተል ይልቅ የራሷን ውሳኔ ለማድረግ እንደምትፈልግ የሚጠቁም ነበር። በዚህ መንገድ፣ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረኝ አለች። ሔዋን የራሷ ጌታ ለመሆን ፈልጋ ነበር። ባሏ አዳምም ተመሳሳይ የሆነ የዓመጽ ጎዳና ተከትሏል።—ሮሜ 5:12

9. የይሖዋን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ምን እንደማድረግ ይቆጠራል? ይህስ ፈጽሞ ከጥበብ የራቀ አካሄድ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

9 በዛሬው ጊዜም የይሖዋን መመሪያ የማንከተል ከሆነ ልክ እንደ ሔዋን እኛም ይሖዋ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር የመወሰን መብት እንዳለው አንቀበልም ማለታችን ነው። የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ያለውን ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ሰው የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከሆነ ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠውን መመሪያ ያውቃል። የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ነገሮችን በመመልከት መደሰት ይቅርና እንዲህ ዓይነት ርኩሰት ሊነሳ እንኳ አይገባውም። (ኤፌ. 5:3) እንዲህ የሚያደርግ ሰው የይሖዋን መመሪያ ችላ በማለት የእሱን ሉዓላዊነትም ሆነ የራስነት ሥልጣኑን እንደማይቀበል ያሳያል። (1 ቆሮ. 11:3) ይህ ደግሞ ፈጽሞ ከጥበብ የራቀ አካሄድ ነው፤ ምክንያቱም ኤርምያስ እንደተናገረው ሰው ‘አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ አይችልም።’—ኤር. 10:23

10. የመምረጥ ነፃነታችንን ኃላፊነት እንደሚሰማን በሚያሳይ መንገድ ልንጠቀምበት የሚገባው ለምንድን ነው?

10 አንዳንዶች በኤርምያስ ሐሳብ አይስማሙ ይሆናል፤ ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት እስከሰጠን ድረስ ይህን ነፃነታችንን በመጠቀማችን ሊነቅፈን እንደማይገባ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ የመምረጥ ነፃነት ስጦታ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ጭምር እንደሆነ መርሳት የለብንም። በመምረጥ ነፃነታችን ተጠቅመን ለምንናገረውና ለምናደርገው ነገር በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች ነን። (ሮሜ 14:10) ኢየሱስ “በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋል” ብሏል። እንዲሁም “ክፉ ሐሳብ፣ ነፍስ መግደል፣ ማመንዘር፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በሐሰት መመስከርና ስም ማጕደፍ ከልብ ይመነጫል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 12:34፤ 15:19) በመሆኑም የምንናገረውና የምናደርገው ነገር የልባችንን ሁኔታ ያሳያል። እውነተኛ ማንነታችንን በግልጽ ይጠቁማል። ጥበበኛ የሆነ ክርስቲያን በማንኛውም ጉዳይ ላይ የይሖዋን መመሪያ የሚሻው ለዚህ ነው። እንዲህ የሚያደርግ ከሆነ ይሖዋ ‘ልቡ ቀና’ እንደሆነ አድርጎ ስለሚመለከተው ‘መልካም ያደርግለታል።’—መዝ. 125:4

11. ከእስራኤላውያን ታሪክ ምን እንማራለን?

11 የእስራኤላውያንን ታሪክ አስታውስ። ሕዝቡ የይሖዋን መመሪያ በመታዘዝ ትክክለኛ ምርጫ ሲያደርጉ ይሖዋ ጥበቃ ያደርግላቸው ነበር። (ኢያሱ 24:15, 21, 31) አብዛኛውን ጊዜ ግን የመምረጥ ነፃነታቸውን አላግባብ ይጠቀሙበት ነበር። በኤርምያስ ዘመን ይሖዋ ስለ ሕዝቡ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብ ብለው ለማድመጥም አልፈለጉም፤ ይልቁን የክፉ ልባቸውን ሐሳብ በእልኸኝነት ተከተሉ፤ ወደ ፊት በመሄድ ፈንታም ወደ ኋላቸው ተመለሱ።” (ኤር. 7:24-26) ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው! እኛም በእልኸኝነት ወይም ለምኞቶቻችን በመሸነፍ የይሖዋን መመሪያ ችላ ብለን የራሳችንን ሐሳብ ላለመከተልና ‘ወደ ፊት በመሄድ ፈንታ ወደ ኋላ ላለመመለስ’ እንጠንቀቅ።

የአምላክን ምክር ለመከተል ምን ያስፈልጋል?

12, 13. (ሀ) የይሖዋን መመሪያ እንድንከተል የሚያነሳሳን የትኛው ባሕርይ ነው? (ለ) እምነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ለይሖዋ ያለን ፍቅር የእሱን መመሪያ እንድንከተል ያነሳሳናል። (1 ዮሐ. 5:3) ጳውሎስ “የምንኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም” ብሎ ሲናገር ሌላም የሚያስፈልገን ነገር እንዳለ ጠቁሟል። (2 ቆሮ. 5:6, 7) እምነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ “በጽድቅ መንገድ” የሚመራን ቢሆንም ይህ መንገድ በዚህ ዓለም ላይ ሀብት ወይም ክብር አያስገኝልንም። (መዝ. 23:3) በመሆኑም ይሖዋን ማገልገል ተወዳዳሪ የሌለው መንፈሳዊ በረከት እንደሚያስገኝ ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል። (2 ቆሮንቶስ 4:17, 18ን አንብብ።) እምነት፣ መሠረታዊ በሆኑ ቁሳዊ ነገሮች መርካት እንድንችልም ይረዳናል።—1 ጢሞ. 6:8

13 ኢየሱስ፣ እውነተኛ አምልኮ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን እንደሚጠይቅ ተናግሯል፤ ለዚህ ደግሞ እምነት ያስፈልጋል። (ሉቃስ 9:23, 24) አንዳንድ ታማኝ አገልጋዮች ድህነትን፣ ጭቆናን፣ መሠረተ ቢስ ጥላቻን እንዲሁም ከባድ ስደትን እንኳ ተቋቁመው በመጽናት ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። (2 ቆሮ. 11:23-27፤ ራእይ 3:8-10) እነዚህ ታማኝ አገልጋዮች የደረሱባቸውን ፈተናዎች ተቋቁመው በደስታ ለመጽናት የቻሉት ጠንካራ እምነት ስለነበራቸው ነው። (ያዕ. 1:2, 3) ጠንካራ እምነት ካለን የይሖዋን መመሪያ መከተል ምንጊዜም የተሻለ እንደሆነ እንተማመናለን። የይሖዋን መመሪያ መከተል ምንጊዜም ዘላቂ ጥቅም ያስገኝልናል። በታማኝነት የሚጸኑ ሰዎች ለጊዜው ከሚደርስባቸው ከማንኛውም መከራ የላቀ ዋጋ ወይም ሽልማት እንደሚያገኙ ፈጽሞ አንጠራጠርም።—ዕብ. 11:6

14. አጋር ትሕትና ማሳየት ያስፈለጋት ለምን ነበር?

14 የይሖዋን መመሪያ በመከተል ረገድ ትሕትና የሚኖረውን ድርሻም እንመልከት። የሣራ አገልጋይ የነበረችው አጋር ለዚህ ምሳሌ ትሆነናለች። ሣራ ልጅ መውለድ እንደማትችል ስትገነዘብ አጋርን ለአብርሃም ሰጠችው፤ አጋርም ከአብርሃም አረገዘች። ከዚያም አጋር መካን በነበረችው እመቤቷ ላይ ኮራች። በዚህም ምክንያት ሣራ አጋርን “ስላሠቃየቻት” አጋር ጥላት ኰበለለች። የይሖዋ መልአክ አጋርን ሲያገኛት “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለእርሷም ተገዥላት” አላት። (ዘፍ. 16:2, 6, 8, 9) አጋር በዚያ ወቅት ሌላ ዓይነት መመሪያ ቢሰጣት ትመርጥ ይሆናል። የመልአኩን መመሪያ ለመከተል የእብሪት ዝንባሌዋን ማስወገድ ነበረባት። ያም ሆኖ ግን አጋር መልአኩ ያላትን በትሕትና በመፈጸሟ ልጇ እስማኤል በአባቱ መኖሪያ ሊወለድ ችሏል።

15. በዛሬው ጊዜ የይሖዋን መመሪያ ለመከተል ትሕትና እንደሚያስፈልገን የሚያሳዩ አንዳንድ ሁኔታዎችን ጥቀስ።

15 የይሖዋን መመሪያ ለመከተል እኛም ራሳችንን ዝቅ ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል። አንዳንዶች እነሱ የሚወዱት ዓይነት መዝናኛ ይሖዋን እንደሚያሳዝነው መቀበል ይኖርባቸው ይሆናል። አንድ ክርስቲያን ሌሎችን በማስቀየሙ ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልገው ይሆናል። አሊያም ደግሞ ስህተት በመሥራቱ ጥፋቱን ማመን ይኖርበት ይሆናል። አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ሠርቶ ከሆነስ? ራሱን ዝቅ አድርጎ ኃጢአቱን ለሽማግሌዎች መናዘዝ ያስፈልገዋል። አንድ ግለሰብ ከጉባኤ ሊወገድም ይችላል። እንዲህ ያለው ሰው እንደገና በጉባኤው ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት በትሕትና ንስሐ መግባትና ከመጥፎ አካሄዱ መመለስ ይኖርበታል። በእነዚህና ከእነዚህ ጋር በሚመሳሰሉ ሁኔታዎች ውስጥ በምሳሌ 29:23 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ማጽናኛ ይሰጣል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤ ትሑት መንፈስ ያለው ግን ክብርን ይጐናጸፋል።”

ይሖዋ መመሪያ የሚሰጠን እንዴት ነው?

16, 17. የመለኮታዊ መመሪያ ምንጭ ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ የላቀ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ከሁሉም የሚበልጠው የመለኮታዊ መመሪያ ምንጭ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።) ከአምላክ ቃል የላቀ ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን ከቅዱሳን መጻሕፍት ምክር የምንሻው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስንገባ ብቻ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ እናዳብራለን። (መዝ. 1:1-3) በዚህ መንገድ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኙትን ሐሳቦች ማወቅ እንችላለን። አስተሳሰባችን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ተመሳሳይ ይሆናል፤ ያልጠበቅናቸው ችግሮች ቢያጋጥሙን እንኳ ለመቋቋም ዝግጁ እንሆናለን።

17 ከዚህም በተጨማሪ ከቅዱሳን መጻሕፍት ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰላችንና ካነበብነው ጋር በተያያዘ መጸለያችን አስፈላጊ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ስናሰላስል በአንዳንድ ሁኔታዎች እንዴት ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ እናስባለን። (መዝ. 77:12) አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ የሚያስፈልገንን መመሪያ እንዲሰጠን በመጠየቅ ወደ እሱ እንጸልያለን። የይሖዋ መንፈስ፣ ከአምላክ ቃል ወይም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ውስጥ ያነበብናቸውን ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድናስታውስ ይረዳናል።—መዝሙር 25:4, 5ን አንብብ።

18. ይሖዋ እኛን ለመምራት በክርስቲያናዊ የወንድማማች ኅብረት የሚጠቀመው እንዴት ነው?

18 ክርስቲያናዊ የወንድማማች ኅብረታችንም የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ይረዳናል። በበላይ አካሉ የሚወከለው “ታማኝና ልባም ባሪያ” በዚህ ኅብረት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያለው ሲሆን ይህ ባሪያ በጽሑፎች ብሎም በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ቋሚ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። (ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም፤ ከሐዋርያት ሥራ 15:6, 22-31 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ በክርስቲያናዊ የወንድማማች ኅብረታችን ውስጥ በግለሰብ ደረጃ ሊረዱንና ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሊሰጡን የሚችሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች በተለይም ሽማግሌዎች አሉ። (ኢሳ. 32:1) በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ደግሞ የይሖዋን መመሪያ ማግኘት የሚችሉበት ተጨማሪ መንገድ አለ። ወላጆቻቸው የሚያምኑ ከሆነ የአምላክን መመሪያ ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ አምላክ ሾሟቸዋል፤ ልጆቹም ይህንን መመሪያ መፈለግ ይኖርባቸዋል።—ኤፌ. 6:1-3

19. የይሖዋን መመሪያ አዘውትረን የምንፈልግ ከሆነ ምን በረከት እናገኛለን?

19 አዎን፣ ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች መመሪያ ይሰጠናል፤ እኛም ይህንን መመሪያ ሙሉ በሙሉ መከተላችን ጠቃሚ ነው። ንጉሥ ዳዊት፣ እስራኤላውያን ለአምላክ ታማኝ ስለነበሩበት ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “አባቶቻችን በአንተ ታመኑ፤ ተማመኑብህ፤ አንተም ታደግሃቸው። ወደ አንተ ጮኹ፤ ዳኑም፤ በአንተም ታመኑ፤ አላፈሩም።” (መዝ. 22:3-5) እኛም በይሖዋ ተማምነን መመሪያውን ከተከተልን ‘አናፍርም።’ ተስፋ ያደረግነው ነገር ሳይፈጸም ቀርቶ አናዝንም። በራሳችን ጥበብ ከመታመን ይልቅ ‘መንገዳችንን ለይሖዋ ዐደራ ከሰጠን’ ዛሬም ቢሆን በረከቱን አትረፍርፎ ያፈስልናል። (መዝ. 37:5) ይሖዋን ለእሱ ባለን ፍቅር ተገፋፍተን የምንታዘዘውና በታማኝነት የምንጸና ከሆነ ዘላለማዊ በረከት እናገኛለን። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኞቹንም አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤ . . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝ. 37:28, 29

ልታብራራ ትችላለህ?

• በይሖዋ መመሪያ የምንታመነው ለምንድን ነው?

• የይሖዋን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ምን አንድምታ አለው?

• አንድ ክርስቲያን ትሕትና ማሳየት የሚያስፈልገው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው?

• ይሖዋ በዛሬው ጊዜ መመሪያ የሚሰጠን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ትጥራለህ?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሔዋን፣ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረኝ ብላለች

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አጋር የመልአኩን መመሪያ ለመከተል የትኛው ባሕርይ ያስፈልጋት ነበር?