በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዚህ የመጨረሻ ዘመን ትዳርና ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት

በዚህ የመጨረሻ ዘመን ትዳርና ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት

በዚህ የመጨረሻ ዘመን ትዳርና ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት

“ዘመኑ አጭር ነው።”—1 ቆሮ. 7:29

1. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ካሉ ‘አስጨናቂ’ ሁኔታዎች መካከል የትኞቹ ነገሮች ይገኙበታል? (ለ) ከቤተሰብ ሕይወት ጋር በተያያዘ እየታዩ ያሉት ለውጦች የሚያሳስቡን ለምንድን ነው?

የአምላክ ቃል ጦርነት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ረሃብና ቸነፈር ‘የመጨረሻው ዘመን’ መለያ ምልክቶች እንደሚሆኑ ተንብዮአል። (ዳን. 8:17, 19፤ ሉቃስ 21:10, 11) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት ላይ ታላላቅ ማኅበራዊ ለውጦች እንደሚኖሩ ያስጠነቅቃል። ‘በመጨረሻው ዘመን’ ከሚከሰቱት ‘አስጨናቂ’ ነገሮች መካከል በቤተሰብ ውስጥ የሚነሱ ችግሮች ይገኙበታል። (2 ጢሞ. 3:1-4) እንዲህ ዓይነቶቹ ለውጦች እኛን የሚያሳስቡን ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህ ለውጦች በስፋት የሚታዩና ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ስለሆኑ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ስለ ትዳርና ወላጅ መሆን ስለሚያስከትለው ኃላፊነት ያላቸውን አመለካከት ሊያዛቡ ስለሚችሉ ነው። እነዚህ ለውጦች ተጽዕኖ የሚያሳድሩት በምን መንገድ ነው?

2. በዓለም ላይ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ትዳርና ስለ ፍቺ ምን አመለካከት አላቸው?

2 በዛሬው ጊዜ ፍቺ እንደ ቀላል ነገር ተደርጎ የሚታይ ከመሆኑም ሌላ እየተለመደ መጥቷል፤ በዚህም ምክንያት በበርካታ አገሮች ውስጥ የፍቺ ቁጥር በፍጥነት እያሻቀበ ነው። ይሁንና ይሖዋ አምላክ ስለ ትዳርና ስለ ፍቺ ያለው አመለካከት በዙሪያችን ካሉት ሰዎች ፈጽሞ የተለየ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። ታዲያ በዚህ ረገድ የይሖዋ አመለካከት ምንድን ነው?

3. ይሖዋና ኢየሱስ ለትዳር ምን አመለካከት አላቸው?

3 ይሖዋ አምላክ ያገቡ ሰዎች ለጋብቻ ቃል ኪዳናቸው ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ ይጠብቅባቸዋል። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በጋብቻ ሲያጣምራቸው “ሰው . . . ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” በማለት ገልጿል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንኑ ሐሳብ በድጋሚ የተናገረው ሲሆን አክሎም “ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው” ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ “በትዳሯ ላይ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል” ሲል ተናግሯል። (ዘፍ. 2:24፤ ማቴ. 19:3-6, 9) በመሆኑም ይሖዋና ኢየሱስ ጋብቻን አንዱ የትዳር ጓደኛ ሲሞት ብቻ የሚያበቃ የዕድሜ ልክ ጥምረት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። (1 ቆሮ. 7:39) ጋብቻ ቅዱስ ዝግጅት በመሆኑ ፍቺ እንደ ቀላል ነገር ተደርጎ መታየት የለበትም። እንዲያውም የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ በቅዱስ ጽሑፉ ላይ በቀረቡት ምክንያቶች ካልሆነ በቀር በማንኛውም መንገድ የሚፈጸምን ፍቺ እንደሚጠላ ይናገራል። *ሚልክያስ 2:13-16፤ 3:6ን አንብብ።

ትዳር የሚያስከትለው ኃላፊነት

4. አንዳንድ ወጣት ክርስቲያኖች ቸኩለው በማግባታቸው የሚቆጩት ለምንድን ነው?

4 ከአምላክ የራቀው ይህ ዓለም ለጾታ ግንኙነት የተጋነነ አመለካከት አለው። እንዲሁም የጾታ ፍላጎትን የሚያነሳሱ በርካታ ምስሎችን በየዕለቱ ያዥጎደጉድብናል። እነዚህ ነገሮች በእያንዳንዳችን ላይ በተለይም ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ባሉ ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ግልጽ ነው። ወጣት ክርስቲያኖች ሳይፈልጉ የጾታ ፍላጎታቸው እንዲቀሰቀስ የሚያደርገውን ይህን መጥፎ ተጽዕኖ መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ ወጣቶች ገና በልጅነት በማግባት ይህን ተጽዕኖ ለማሸነፍ ይሞክራሉ። እንዲህ ማድረግ የሥነ ምግባር ብልግና ከመፈጸም እንደሚጠብቃቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ አንዳንዶቹ ባደረጉት ውሳኔ መቆጨት ይጀምራሉ። ለምን? ምክንያቱም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የእነሱና የትዳር ጓደኛቸው ፍላጎት የማይጣጣም መሆኑን ይገነዘባሉ። ከዚህም የተነሳ እነዚህ የትዳር ጓደኛሞች ከባድ ችግር ያጋጥማቸዋል።

5. የትዳር ጓደኛሞች ለጋብቻ ቃል ኪዳናቸው ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ ምን ሊረዳቸው ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

5 ሌላው ቀርቶ ክርስቲያን የሆነን ሰው ብናገባም እንኳ የዚህ ሰው ባሕርይ እኛ ካሰብነው የተለየ ሆኖ ስናገኘው ሁኔታው አስቸጋሪ ሊሆንብን እንደሚችል ግልጽ ነው። (1 ቆሮ. 7:28) ይሁን እንጂ ሁኔታው ምንም ያህል ከባድ ቢሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ ምክንያት መፋታት ለችግሩ መፍትሔ እንደማይሆን ይገነዘባሉ። በመሆኑም ለጋብቻ ቃል ኪዳናቸው ታማኝ ለመሆን ሲሉ ትዳራቸው እንዳይፈርስ ከፍተኛ ጥረት ለሚያደርጉ ክርስቲያኖች ጉባኤው አክብሮት ሊያሳያቸውና ፍቅራዊ እርዳታ ሊያደርግላቸው ይገባል። *

6. ወጣት ክርስቲያኖች ለጋብቻ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

6 ገና ያላገባህ ወጣት ነህ? ከሆነ ስለ ጋብቻ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል? ከአንዲት ክርስቲያን ጋር የፍቅር ግንኙነት ከመመሥረትህ በፊት አንተ ራስህ በዕድሜ፣ በአስተሳሰብና በመንፈሳዊ እስክትጎለምስ ድረስ መቆየትህ ለሐዘን ከሚዳርጉ ችግሮች ይጠብቅሃል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው በየትኛው ዕድሜ ላይ ማግባት እንዳለበት አይናገርም። * ይሁንና የጾታ ፍላጎት የሚያይልበት ዕድሜ እስኪያልፍ ድረስ መጠበቅ እንደሚኖርብህ ይገልጻል። (1 ቆሮ. 7:36 NW) ለምን? ምክንያቱም ከፍተኛ የሆነ የጾታ ፍላጎት የማመዛዘን ችሎታህን ሊያዛባና የኋላ ኋላ ለሐዘን የሚዳርግ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ እንድታደርግ ተጽዕኖ ሊያሳድርብህ ይችላል። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጋብቻን አስመልክቶ ጥበብ ያለበት ምክር እንዲሰፍር ያደረገው ለአንተው ጥቅምና ደስታ ሲል መሆኑን አስታውስ።—ኢሳይያስ 48:17, 18ን አንብብ።

ወላጅ መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት

7. አንዳንድ ወጣት የትዳር ጓደኛሞች ምን ያጋጥማቸዋል? ይህስ በትዳር ውስጥ ውጥረትን ሊፈጥር የሚችለው እንዴት ነው?

7 በለጋ ዕድሜያቸው ትዳር የመሠረቱ አንዳንድ ወጣቶች ገና በልጅነታቸው ወላጆች ይሆናሉ። እርስ በርሳቸው በደንብ ለመተዋወቅ እንኳ ጊዜ ሳያገኙ ልጅ ይወልዳሉ፤ ልጅ ደግሞ የ24 ሰዓት እንክብካቤ ይሻል። ልጁን በዋነኝነት የምትንከባከበው እናትየው ስለሆነች ባልየው ቅናት ሊያድርበት ይችላል። ከዚህም በላይ ወላጆች ልጁን በመንከባከብ እንቅልፍ አጥተው ማደራቸው ጭንቀት ሊፈጥርባቸው ይችላል፤ ይህ ደግሞ በመካከላቸው ውጥረት እንዲነግሥ ያደርጋል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ነፃነታቸውን እንዳጡ ይገነዘባሉ። አሁን እንደበፊቱ የፈለጉበት ቦታ መሄድም ሆነ ያሻቸውን ማድረግ አይችሉም። ታዲያ እነዚህ ወላጆች እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ እንዴት ሊመለከቱት ይገባል?

8. የወላጅነት ኃላፊነት እንዴት መታየት ይኖርበታል? ለምንስ?

8 ጋብቻ በቁም ነገር መታየት እንደሚኖርበት ሁሉ ወላጅ መሆንም ከአምላክ እንደተሰጠ ኃላፊነትና መብት ተደርጎ መታየት ይኖርበታል። ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ልጅ መውለዳቸው በሕይወታቸው ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት ማስተካከያ ማድረግ ቢጠይቅባቸውም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ልጅ የመውለድ ችሎታን ለሰዎች የሰጠው ይሖዋ ስለሆነ ወላጆች ልጃቸውን ‘የይሖዋ ስጦታ’ እንደሆነ አድርገው መመልከት ይኖርባቸዋል። (መዝ. 127:3) ክርስቲያን ወላጆች፣ ኃላፊነታቸውን ‘ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ’ መወጣት ይኖርባቸዋል።—ኤፌ. 6:1 NW

9. (ሀ) ልጅ ማሳደግ ምን ነገሮችን ይጠይቃል? (ለ) አንድ ባል ባለቤቱ በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድትሆን ምን ማድረግ ይችላል?

9 ልጅ ማሳደግ ለበርካታ ዓመታት የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። ወላጆች ይህን ኃላፊነታቸውን መወጣት ብዙ ጊዜና ጉልበት ይጠይቅባቸዋል። አንድ ክርስቲያን ባል ልጅ ከተወለደ በኋላ ሚስቱ ለተወሰኑ ዓመታት በስብሰባዎች ላይ በትኩረት መከታተል እንደሚያዳግታት እንዲሁም የግል ጥናት ለማድረግና ለማሰላሰል ጊዜ እንደምታጣ መገንዘብ ይኖርበታል። ይህ ደግሞ መንፈሳዊነቷን ሊያዳክምባት ይችላል። ኃላፊነት የሚሰማው አንድ ባል ልጁን ለመንከባከብ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ባለቤቱ በስብሰባዎች ላይ ያመለጧትን ሐሳቦች ቤት ሲመለሱ ሊከልስላት ይችል ይሆናል። በተጨማሪም በስብከቱ ሥራ ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ እንድትችል ልጁን በመንከባከብ ሊረዳት ይችላል።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4ን አንብብ።

10, 11. (ሀ) ወላጆች ‘የይሖዋን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ’ ልጆቻቸውን ማሳደግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በርካታ ክርስቲያን ወላጆች ሊመሰገኑ የሚገባቸው ለምንድን ነው?

10 ኃላፊነት የሚሰማው ወላጅ ለልጁ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ከማቅረብ እንዲሁም ጤንነቱን ከመንከባከብ የበለጠ ነገር ያደርጋል። በተለይ አስቸጋሪ በሆነው በዚህ የመጨረሻ ዘመን ወጣቶች የሥነ ምግባር ሕግጋትን ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ መማር ይኖርባቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ” ማሳደግ ይኖርባቸዋል። (ኤፌ. 6:4 NW) ይህም ከሕፃንነታቸው አንስቶ አስቸጋሪ የሆነውን የጉርምስና ዕድሜ እስኪያልፉ ድረስ በልባቸው ውስጥ የይሖዋን አስተሳሰብ መትከልን ይጨምራል።—2 ጢሞ. 3:14, 15

11 ኢየሱስ፣ ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ በማለት ለተከታዮቹ ሲናገር ወላጆችም ልጆቻቸው ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት አለባቸው ማለቱ እንደነበር ግልጽ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ይህ ዓለም በወጣቶች ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ልጆች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ቀላል አይደለም። በመሆኑም ልጆቻቸው ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ በመርዳት ረገድ ስኬታማ የሆኑ ወላጆች ከጉባኤው ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። እነዚህ ወላጆች በእምነታቸውና ወላጅ መሆናቸው ያስከተለባቸውን ኃላፊነት በታማኝነት በመወጣት የዓለምን ተጽዕኖ ‘አሸንፈዋል።’—1 ዮሐ. 5:4

ክቡር ለሆነ ዓላማ ሳያገቡ ወይም ልጅ ሳይወልዱ መኖር

12. አንዳንድ ክርስቲያኖች ለተወሰኑ ዓመታት ሳያገቡ ለመቆየት የሚወስኑት ለምንድን ነው?

12 ‘ዘመኑ አጭር’ በመሆኑና ‘የዚህ ዓለም መልክ ስለሚያልፍ’ የአምላክ ቃል፣ ሳያገቡ መኖር ያለውን ጥቅም በቁም ነገር እንድናስብበት ያበረታታል። (1 ቆሮ. 7:29-31) በመሆኑም አንዳንድ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ሙሉ አሊያም ለተወሰኑ ዓመታት ሳያገቡ ለመኖር መርጠዋል። እነዚህ ያላገቡ ክርስቲያኖች ነፃነታቸውን የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደድ የማይጠቀሙበት መሆኑ የሚያስመሰግናቸው ነው። ብዙዎች ‘ልባቸው ሳይከፋፈል’ ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ ሳያገቡ ለመኖር ወስነዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:32-35ን አንብብ።) አንዳንድ ያላገቡ ክርስቲያኖች አቅኚ ወይም ቤቴላዊ ሆነው ያገለግላሉ። በርካቶች ደግሞ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል የሚያስችላቸውን ብቃት በማሟላት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግ ይጥራሉ። እንዲያውም ከማግባታቸው በፊት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተወሰኑ ዓመታት ያሳለፉ ክርስቲያኖች፣ በዚያ ወቅት ያገኙት ሥልጠና በትዳራቸው ውስጥ እንደጠቀማቸው ይገልጻሉ።

13. አንዳንድ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ልጅ ላለመውለድ የወሰኑት ለምንድን ነው?

13 በአንዳንድ አገሮች ደግሞ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ሌላ ዓይነት ለውጥ እየተከሰተ ነው። በርካታ ባልና ሚስቶች ልጅ ላለመውለድ ወስነዋል። አንዳንዶች እንዲህ ያደረጉት የኢኮኖሚ ችግር ስላለባቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ ብዙ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ነፃነት ለማግኘት ሲሉ ነው። አንዳንድ ክርስቲያን ባልና ሚስቶችም ልጅ ላለመውለድ ወስነዋል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ይህን የሚያደርጉት ይሖዋን በነፃነት ለማገልገል ስለሚያስችላቸው ነው። ይህ ሲባል ግን ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት የላቸውም ማለት አይደለም። ይሁንና እነዚህ ባልና ሚስቶች ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም ሲሉ ትዳር የሚያስገኛቸውን አንዳንድ በረከቶች ለመተው ፈቃደኞች ናቸው። (1 ቆሮ. 7:3-5) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በወረዳና በአውራጃ ሥራ ወይም ቤቴል ገብተው ያገለግላሉ። ሌሎች ደግሞ አቅኚዎች ወይም ሚስዮናውያን ናቸው። ይሖዋ ሥራቸውንና ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር አይረሳም።—ዕብ. 6:10

“በሥጋቸው ላይ መከራ” አለባቸው

14, 15. ክርስቲያን ወላጆች “በሥጋቸው ላይ መከራ” ሊያጋጥማቸው የሚችለው እንዴት ነው?

14 ሐዋርያው ጳውሎስ ያገቡ ክርስቲያኖች “በሥጋቸው ላይ መከራ” እንዳለባቸው ተናግሯል። (1 ቆሮ. 7:28 የ1954 ትርጉም) ይህም እነሱ ራሳቸው፣ ልጆቻቸው ወይም በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸው የሚያጋጥማቸውን የጤና ችግር ሊያመለክት ይችላል። ከዚህም ባሻገር ልጆችን ከማሳደግ ጋር የተያያዙ አስቸጋሪና አሳዛኝ ሁኔታዎችን ሊጨምር ይችላል። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻው ዘመን አስጨናቂ’ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። አስጨናቂ ከሆኑት ነገሮች መካከል ደግሞ ‘ልጆች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ’ መሆናቸው ይገኝበታል።—2 ጢሞ. 3:1-3

15 ለክርስቲያን ወላጆች ልጆችን ማሳደግ ተፈታታኝ ሥራ ነው። ይህ ‘አስጨናቂ ጊዜ’ ከሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ ማምለጥ አንችልም። በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች ይህ ‘ዓለም’ በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድረውን ጎጂ ተጽዕኖ ለመመከት የማያቋርጥ ትግል ማድረግ አለባቸው። (ኤፌ. 2:2, 3) አንዳንድ ጊዜ ግን በትግሉ ሊሸነፉ ይችላሉ! በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያለ አንድ ልጅ ይሖዋን ማገልገሉን ካቆመ እሱን በእውነት መንገድ ለማሳደግ ሲጥሩ ለነበሩት ወላጆቹ “መከራ” ይሆንባቸዋል።—ምሳሌ 17:25

“ታላቅ መከራ ይሆናል”

16. ኢየሱስ ስለ የትኛው “መከራ” ትንቢት ተናግሯል?

16 በቅርቡ የሚመጣው ታላቅ መከራ ከትዳርም ሆነ ልጆችን ከማሳደግ ጋር በተያያዘ ከሚያጋጥም ከየትኛውም “መከራ” በእጅጉ ይበልጣል። ኢየሱስ መገኘቱንና የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚያም በኋላ የሚስተካከለው የሌለ፣ ታላቅ መከራ ይሆናል” ብሏል። (ማቴ. 24:3, 21) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ እጅግ ብዙ ሕዝብ ከዚህ “ታላቅ መከራ” እንደሚተርፍ ገልጿል። ይሁንና የሰይጣን ዓለም ሰላማዊ በሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥቃት ይሰነዝርባቸዋል። አዋቂዎችም ሆንን ልጆች፣ ይህ ወቅት ለሁላችንም አስቸጋሪ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

17. (ሀ) የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት መጠበቅ የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ስለ ትዳርና ወላጅ ስለመሆን ባለን አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ምንድን ነው?

17 የሆነ ሆኖ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ መጨነቅ የለብንም። ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ወላጆች እነሱም ሆኑ ሕፃናት ልጆቻቸው ጥበቃ እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረግ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 26:20, 21ን አንብብ፤ ሶፎ. 2:2, 3፤ 1 ቆሮ. 7:14) የምንኖረው በአስጨናቂ ጊዜ ውስጥ መሆኑን መገንዘባችን በዚህ የመጨረሻ ዘመን ስለ ትዳርና ወላጅ ስለመሆን ባለን አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይኖርበታል። (2 ጴጥ. 3:10-13) እንዲህ ስናደርግ ያገባንም ሆንን ያላገባን፣ ልጆች ያሉንም እንሁን የሌሉን ሁላችንም ሕይወታችን ለይሖዋም ሆነ ለጉባኤው ክብርና ውዳሴ ያመጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የይሖዋ ቀን ከሐሳባችሁ አይጥፋ በሚለው መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 125 ላይ የሚገኘውን “ፍቺን ይጠላል” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት።

^ አን.5 በትዳር ውስጥ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች በመስከረም 15, 2003 መጠበቂያ ግንብ እና በጥር 2001 ንቁ! መጽሔቶች ላይ እንዳሉት ያሉ ሐሳቦችን በማንበብ ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ።

^ አን.6 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 30 ላይ የሚገኘውን “ለማግባት ደርሻለሁን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ለክለሳ ያህል

• ወጣት ክርስቲያኖች ለማግባት መቸኮል የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?

• ልጅን ማሳደግ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

• በርካታ ክርስቲያኖች ላለማግባት፣ ያገቡ ከሆኑ ደግሞ ልጅ ላለመውለድ የወሰኑት ለምንድን ነው?

• ክርስቲያን ወላጆች ምን ዓይነት “መከራ” ሊያጋጥማቸው ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣት ክርስቲያኖች ለማግባት መቸኮል የሌለባቸው ለምንድን ነው?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ባል ባለቤቱ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንድታደርግ ሊረዳት ይችላል

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ልጅ ላለመውለድ የወሰኑት ለምንድን ነው?