ታስታውሳለህ?
ታስታውሳለህ?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-
• ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን የጠየቁት መቼ ነበር?
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እትም እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል:- “ኮከብ ቆጣሪዎቹ ኢየሱስን የጠየቁት እረኞቹ እንዳደረጉት በተወለደበት ምሽት በግርግም ውስጥ ሳለ አልነበረም። የመጡት ከተወሰኑ ወራት በኋላ ነበር።” እነሱ በመጡበት ወቅት ኢየሱስ ‘ከፍ ያለ ልጅ’ ሲሆን ያገኙትም ቤት ውስጥ ነበር። (ማቴ. 2:7-11) ደግሞስ ኢየሱስ በተወለደበት ምሽት ወርቅና ሌሎች ውድ ስጦታዎች ተሰጥተውት ቢሆን ኖሮ ማርያም ከ40 ቀናት በኋላ በቤተ መቅደስ ሁለት ዋኖሶችን ብቻ ታቀርብ ነበር?—1/1 ገጽ 31
• ብዙዎች ሕይወታቸው ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?
አንድ ሰው ‘ሁኔታዎቼን ማስተካከልና አኗኗሬን ቀላል ማድረግ እችላለሁ?’ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ኤሚ ያደረገችውም ይህንኑ ነበር። ኤሚ ሀብታም ብትሆንም ደስተኛ አልነበረችም። በዚህ ዓለም ውስጥ ሰብዓዊ ሥራን ስታሳድድ የእምነትን መንገድ ስታ ልትሄድ ምንም እንዳልቀራት ተገነዘበች። በመሆኑም በሕይወቷ ውስጥ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም የወሰነች ሲሆን ለተወሰነ ጊዜም በአቅኚነት ማገልገል ችላለች። ኤሚ “በአሁኑ ወቅት፣ አብዛኛውን ጊዜዬን ለዓለም በመሥራት ሳጠፋ አግኝቼው የማላውቀው ከፍተኛ ደስታ አለኝ” ብላለች።—1/15 ገጽ 19
• አንዳንድ እናቶች በሕይወታቸው እርካታ እንዲያገኙ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
በርካታ እናቶች በሥራው ዓለም ላይ ተሰማርተዋል። አንዳንዶች ይህን የሚያደርጉት የቤተሰባቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ነው፤ ሌሎች ደግሞ በሥራው ዓለም የሚሠማሩት እንደፈለጉ የሚያወጡት ገንዘብ ለማግኘት ወይም የቅንጦት ሕይወት ለመምራት ሲሉ ነው። ሌሎች በሥራቸው የተዋጣላቸው ስለሆኑ ሥራቸውን ይወዱታል። ክርስቲያን እናቶች በተለይም ልጃቸው ሕፃን እያለ በቤት ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው። አንዳንዶች ለቤተሰባቸው የበለጠ ትኩረት ለመስጠት ሲሉ ከቤት ውጭ በመሥራት የሚያሳልፉትን ሰዓት ለመቀነስ አሊያም ሥራቸውን ለማቆም የመረጡ ሲሆን እንዲህ በማድረጋቸውም እርካታ አግኝተዋል።—2/1 ገጽ 28-31
• ኢየሱስ በማቴዎስ 24:34 ላይ የተናገረው ስለ የትኛው “ትውልድ” ነበር?
ኢየሱስ በአብዛኛው “ትውልድ” የሚለውን ቃል አሉታዊ ትርጉም በሚያስተላልፍ መንገድ የተጠቀመበት ክፉ ሰዎችን ለማመልከት ነበር። በማቴዎስ 24:34 ላይ ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ለሚቀቡት ደቀ መዛሙርቱ ሲናገር ይህን ቃል በአሉታዊ መንገድ አልተጠቀመበትም። በማቴዎስ 24:32, 33 የተገለጸው ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚችሉት እነሱ ናቸው። ከዚህ በመነሳት ኢየሱስ ትውልድ ሲል በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ በዘመናችን የሚገኙትን ቅቡዓን ተከታዮቹን ማመልከቱ ነበር ብለን መደምደም እንችላለን።—2/15 ገጽ 23-24
• በገላትያ 3:24 ላይ በተገለጸው መሠረት ሕጉ ሞግዚት የነበረው በምን መንገድ ነበር?
በጥንት ዘመን፣ አብዛኛውን ጊዜ ለሞግዚትነት የሚመረጥ ሰው ታማኝ አገልጋይ መሆን የነበረበት ሲሆን የልጁን ደኅንነት የመጠበቅ እንዲሁም ልጁ አባትየው በሚፈልገው መንገድ መያዙን የመከታተል ኃላፊነት ነበረበት። በተመሳሳይም ሕጉ እስራኤላውያንን ከመጥፎ ተጽዕኖዎች ጠብቋቸዋል፤ ለምሳሌ ያህል ሕጉ ከሌሎች አሕዛብ ጋር በጋብቻ መተሳሰርን ይከለክል ነበር። ሆኖም እንደ ልጁ ሞግዚት ሁሉ ሕጉ የሚሰጠው አገልግሎት ጊዜያዊ ሲሆን የሚያስፈልገውም ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ብቻ ነበር።—3/1 ገጽ 18-21
• በያዕቆብ 3:17 መሠረት የትኞቹን ባሕርያት ልናሳይ ይገባል?
ንጹሕ ሆነን ለመገኘት ከክፉ ነገሮች ለመራቅ ፈጣን መሆን ይኖርብናል። (ዘፍ. 39:7-9) ከዚህም በተጨማሪ ንዴትን በማስወገድ እንዲሁም ሰላም የሚያደፈርሱ ድርጊቶችን ከመፈጸም በመቆጠብ ሰላማዊ መሆን አለብን። በመሆኑም እያንዳንዳችን እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል:- ‘የምታወቀው ሰላም ፈጣሪ በመሆን ነው ወይስ ችግር ፈጣሪ? ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ጋር እጋጫለሁ? በቀላሉ የምቀየም ወይም ሌሎችን የማስከፋ ነኝ? ይቅር ለማለት ፈጣን ነኝ? ሌሎች የእኔን አቋም እንዲቀበሉ ከመጫን እርቃለሁ?’—3/15 ገጽ 24-25
• ኢየሱስ ማየት የተሳነውን ሰው በአንድ ጊዜ ያልፈወሰው ለምን ነበር? (ማርቆስ 8:22-26)
መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ግልጽ የሆነ መልስ አይሰጠንም። ይሁን እንጂ በዚህ አጋጣሚ ኢየሱስ፣ የሰውየው የማየት ችሎታ ቀስ በቀስ እንዲመለስለት ያደረገው ሰውየው በአካባቢው ከሚያየው ነገር ጋር እንዲላመድ ጊዜ ለመስጠት ብሎ ይሆናል። ይህም ኢየሱስ ማየት ለተሳነው ሰው ፍቅር እንዳለውና እንደሚያስብለት የሚያሳይ ነበር።—4/1 ገጽ 30